ከ7500 በላይ አልባሳት ተሰበሰበ

በፈትለወርቅ ደስታ
«ሁለት ልብሶች ያሉት…..» በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የቀጠለ ሲሆን የመጀመሪያውን ቀን ጨምሮ እስከ እሁድ ጥር 29 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት ከ7500 በላይ አልባሳት፣ ከ10 በላይ ጣቃ የተለያዩ ብትን ጨርቆችና ለመነኮሳት የሚሆኑ አልባሳት እንደተሰበሰበ ታውቋል፡፡

በዚህ መርሐ ግብር አልባሳቱ ከአዲስ አበባ፣ ከአዲስ ዓለምና ከኳታር እንደተሰበሰቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአልባሳት መደገፍ ያልቻሉ በርካታ ምዕመናንም መርሐ ግብሩን በገንዘብ በመደገፍ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡

አንዳንድ ምዕመናን ይዘውት ከመጡት አልባሳት በተጨማሪ ደርበው የመጡትን ጃኬትና ሸሚዝ እስከመስጠት ደርሰዋል፡፡ «ዓላማው በጣም ደስ ብሎኛል በረከትና ረድኤት አገኝበታለሁ ብዬ ነው የማደርገው፤ እኛ ለእኛ እንበቃ ነበር ነገር ግን ሁላችንም አነሳሽና መሪ እንፈለጋለን» በማለት ስሙን መግለጽ ያልፈለገ ወጣት ገልጾልናል፡፡

 

ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ ምዕመናን መርሐ ግብሩ የሚከናወንባቸው ቀናት አጭር በመሆኑ መሳተፍ አለመቻላቸውን በስልክና በኢሜይል በመግለጻቸው እስከ የካቲት 6 ቀን 2003 ዓ.ም እንደተራዘመ አስተባባሪ ክፍሉ አሳውቋል፡፡

በእስከ አሁኑ መርሐ ግብር ከ800 በላይ የሆኑ ምዕመናን ተሣትፈዋል፡፡ መርሐ ግብሩ ዘወትር ከጠዋት 2፡30 እስከ ምሽቱ 2፡30 ድረስ ይካሄዳል፡፡

‹‹በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡›› ፊልጵስዩስ 2፡6

                                                   በማሞ አየነው
 
እነሆ የጨለማው ዘመን አለፈ፡፡ በጨለማ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦችም ብርሃን አዩ፡፡ መላእክትና ኖሎት /እረኞች/ በአንድነት እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ እርቅ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ተደረገ፡፡ የሰው ምኞትም ተፈፀመ፡፡ ሰላም፣ ፍቅር፣ ተስፋ በምድር ሰፈነ፡፡ እነዚህ ሁሉ በክርስቶስ የልደት ገፀ በረከት የተገኙ ናቸው፡፡ ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በቀቢጸ ተስፋ፣ ሰላም በማጣት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሆነው ለብዙ ሺህ ዓመታት ኖረዋል፡፡ የነቢያት ጾም ጸሎት፣ የካህናት መሥዋዕት ምድርን ከኃጢአት ሊያነጻ አልቻለም፡፡ ምድርን ከኃጢአት የሚያነጻት ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በመሆኑ እነሆ አምላክ ሰው ሆነ፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› ዮሐ 1፡29  በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በፍፁም ትህትና የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ ሰው መሆንን የመረጠው፡፡

 በጌታችን ልደት ያገኘናቸውን በረከት እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

             1.ልጅነትን አግኝተናል፡፡

የሰው ልጅ የተፈጠረው በአርአያ እግዚአብሔር ሲሆን የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስሙን ይቀድስ ክብሩን ይወርስ ዘንድ ነው፡፡ ነገር ግን የምኞት ፈረስ ከልጅነት ይልቅ አምላክነት እንዲመርጥ ገፋፋው፡፡ ስለዚህም ልጅነቱን በፈቃዱ አጣ፡፡ ምንም አንኳን የሰው ልጆች ልጅነታቸውን ቢጥሉ እግዚአብሔር አምላክ ግን አባትነቱን አልተወም፡፡ በነቢያት እያደረ መምህራንን እያስነሳ ዳግመኛ ልጆቹ እንዲሆኑ መክሯል፣ አስመክሯል፣ ‹‹እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ እኔም አጽናናችኋለሁ›› ኢሳ 66:13 በማለት አባትነቱን ተናግሯል፡፡ ይህን ያጣነውን ልጅነት ሊያስመልስልን ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው ሆነ፡፡ ባርነታችን ወደ ልጅነት፣ ባዕድነታችን ወደ ወራሽነት ተለወጠ፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንደ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ›› ገላ 4፡7 በማለት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በልደቱ እንዳገኘን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ገልጧል፡፡ በክርስቶስ ልደት ማመን ከልደቱም በረከት መካፈል ልጅነትን የሚያሰጥ ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ መጽሐፍም ‹‹የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው›› ዮሐ 1፡11 በማለት ልጅነታችንን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ልጆቹም ስለሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮህ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ›› ገላ 4:6 በማለት ልጅነታችንን እንዳገኘን ያረጋግጣል፡፡

        2.   ነጻነታችን አግኝተናል፡፡

ሰው ነጻ መሆኑ የሚታወቀው ፈቅዶ በመረጠው ነገር ያለምንም ከልካይ መኖር ሲችል ነው፡፡ ከውድቀቱ በኋላ የሰው ልጅ ያጣው ታላቅ ነገር ቢኖር ነጻ ፈቃዱን ነበር፡፡ ጽድቅን መርጦ በጽድቅ መንገድ ቢጓዝ እንኳ መንግሥቱን ለመውረስ አይችልም ነበር፡፡ ነቢያትም አምርረው ሲያለቅሱ የነበረው ‹‹ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ›› በማለት ነበር፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ይህን ነጻነታችንን አስመልሶልናል፡፡ ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን›› ገላ 5፡1 እንዳለ፡፡ የጌታን ልደት መላእክቱ ለኖሎቱ ሲያበስሩም እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ›› ሉቃ 2፡14፡፡ ከእስር የተለቀቀ ሰው ነጻ እንደሆነ ሁሉ የሰው ልጅም ለሺህ ዘመናት በዲያብሎስ ግዞት ይኖር ስለነበር በልደቱ ከዚህ እስር በመላቀቁ ነጻነቱን አግኝቷል፡፡

      3.    ሰላማችን ተመልሷል ተስፋችን ተሳክቷል፡፡

በቀደመው ዘመን ከልደተ ክርስቶስ በፊት ሰው ሰላሙን አጥቶ ይኖር ነበር፡፡ ‹‹ የሰላምን መንገድ አያውቁም… መንገዳቸውን አጣመዋል፤ የሚሄዱባትም ሁሉ ሰላምን አያውቁም›› ኢሳ 59፡7 በማለት ሰላም አንዳልነበረ አስረድቷል፡፡ ልደት እውነተኛ ሰላማችንን ያገኘንባት፣ ተስፋችንም የተረጋገጠበት ልዩ ቀን ናት፡፡ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በመውጣት ያጣነው ሰላም በልደቱ ተመልሷል፡፡ ሰላምን የሚያድል እርሱ ስለሆነም ‹‹ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› ብሏል፡፡ ለብዙ ዘመናት ሰላምን ብንነፈግም እውነተኛ ሰላምን ያገኘነው በክርስቶስ ልደት ነው፡፡ ‹‹ሰላም በምድር ሆነ›› ብለው መላእክት የዘመሩትም በልደቱ ነው፡፡በልደት ካገኘናቸው ገጸ በረከቶች በተጨማሪ ሌሎች ለሕይወታችን ጠቃሚ የሆኑ መልእክቶችንም አግኝተናል፡፡ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ምሳሌ የሆነ ዐቢይ ቁም ነገሮችንም በልደቱ ገብይተናል፡፡

             ሀ. ትህትና

እግዚአብሔር አምላክ ‹‹እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ›› በማለት ትህትና የባህርይ ገንዘቡ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ በልደቱም ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማመን በሚከብድ ፍፁም ትህትና ራሱን ዝቅ አድርጎ ለሰዎች ተገልጧል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዕቆብ ‹‹በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም›› ዘፍ 40:9 የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጻሚ እንዲሆን ከይሁዳ ወገን ቢወለድም ቅሉ ከይሁዳ ግዛትም ታናሽ በሆነችው ቤተልሔም እንደተወለደ መጻሕፍት ይነግረናል፡፡ ‹‹አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ ከይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ›› ሚክ 5:2፣ ሉቃ 1:5 ማቴ 1:1 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከታናሿ ቤተልሔም ለመወለድ የመረጠው በበረት ግርግም ውስጥ ነው፡፡ ሁሉ የእርሱ የሆነ አምላክ ምንም እንደሌለው የሆነው የትህትናን ልዕልና ሊገልጽልን ፈልጎ ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ትህትና መገለጫው ያለንን ነገር እንደሌለን መቁጠርና  መተው ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ ባለፀጋ ሳለ ደሀ ሆነ ፤ ሁሉ የሞላለት ሳለ ማደሪያ ስፍራ አጥቶ በበረት (ግርግም)ተወለደ፡፡ ይህንን ትህትናውን በጥምቀቱ ገልጿል፤ ወደ ፈጠረው ዮሐንስ ሄደ ‹‹እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል›› በማለት ጽድቅ ለፍፁም ትህትና የሚደረግ ሕይወት እደሆነ አስረድቶናል፤ ማቴ 3:14፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ትህትና እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹የባሪያውን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ›› ፊሊ 2:6  ‹‹ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አነሰ›› ዕብ 2፡9 ‹‹ስለዚህ የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተሰረይ….በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው›› ዕብ 2፡17 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጀመሪያው እስከ ፍጻሜው ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በትህትና የተደረጉ ናቸው፡፡ ወደ ምድር ሲመጣ ፍፁም ትህትና ባላት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አድሮ መጣ፡፡ ሲወለድ በቤተልሔም በበረት ግርግም፣ ሲጠመቅ ባገልጋዩ በዮሐንስ እጅ፣ ወደ መስቀል ሲወጣም በፈጠራቸው ፍጡራን እጅ መሆንን ስንመለከት እውነትም እግዚአብሔር የትህትና ባለቤትና የትሁታን ወዳድ መሆኑን እንረዳለን፡፡

            ለ. ፍቅር

እግዚአብሔር ሰውን ለምን ወደደው; ብለን ብንጠይቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን መልስ ቀላልና ግልፅ ነው፡፡ ‹‹…እንዲሁ…›› ዮሐ 3:16፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለመውደድ /ለማፍቀር/ ምክንያት የለውም፡፡ ኃጢአተኛና ጻድቅ፣ ንጹሕና ቆሻሻ፣ ምሁርና ያልተማረ፣ የሚል መመዘኛም በአምላክ ዘንድ የለም፡፡ እግዚአብሔር እንዲወደን ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከማፍቀሩ የተነሳ ዓለምን እንዲያድን አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከው፡፡ በልደትም የምናየው ይህን የአምላካችንን ልዩ ፍቅር ነው፡፡ ቀድሞ በነቢያት ‹‹በዘላለም ፍቅር ወድጃችኋለሁ›› ኤር 31:3 በማለት ፍቅሩን ገልጦ ነበር፡፡  ይህን ፍቅሩን ደግሞ በልደቱ በይበልጥ ገለጠው፡፡ ሰውን ለመውደድ ምክንያት የምናበዛ ሰዎች ስንቶች ነን? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ ያሳየንን ግሩም ፍቅር ለእህት ለወንድሞቻችን በማሳየት ክርስቶስን በግብር ልንመስለው ይገባል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ወርዶ በበረት ግርግም የተወለደው እስከ መስቀል ሞትም የደረሰው ለሰው ልጅ ባለው ፍፁም ፍቅር መሆኑን መገንዘብ ያደረገውን የትህትና ስራ መመልከት የልደትን መንፈሳዊ ምስጢር እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ ካለዚያ ልደትን ለመታሠቢያነት ብቻ ከማክበር የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረ ሰውን ፍፁም በሆነ ፍቅር መውደድ ከባድ ቢሆንም እንኳ የማይቻል ነገር ግን አይደለም! ሰውን መውደድ ቀስ በቀስ እየዳበረ እስከ ፍጽምና የሚያደርስ መንፈሳዊ ሀብት ነው፡፡ በፍቅር ላይ ያልተመሠረተ መንፈሳዊ ሱታፌ፤ መንፈሳዊ ሕይወት መጨረሻው አያምርም፡፡ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሕይወት ‹‹በሁሉ ይጸናል›› 1ኛ ቆሮ 13:7 የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደትም የፍቅር የመጨረሻው ማሳያ መሆኑን መገንዘብ ሕይወታችንን በዚህ መነጸርነት እንድናይ ያግዘናል፡፡

                  ሐ. ተስፋን መፈጸም፡-

እስራኤል ዘሥጋ የመሲሑን መምጣት በተስፋ ሲጠብቁ ቢቆዩም የክርስቶስን ሰው ሆኖ መምጣት ለመቀበል ዳተኞች ነበሩ፡፡ መጽሐፍም ‹‹የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም›› ዮሐ 1:7 ይላል፡፡ ነቢያት በሙሉ እግዚአብሔር የሰው ዘር ማዳኑን በተስፋ ሲጠብቁ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ተስፋውን ሊፈጽም አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከ፡፡ ተስፋችንም ተፈጸመ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ›› ገላ 4:4 ይላል፡፡ ነቢያት ይህን ቀን በተስፋ ሲጠብቁ እንደነበር በትንቢታቸው ገልጸዋል፡፡ ኢሳ 7:14 ፣ ኢሳ 9:6 ፡፡ አምላካችን ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ የሰጠን ነገር ቢኖር ተስፋን ነው ‹‹እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፡፡›› ዘፍ 3:22 በማለት ሰው ሆኖ ወደ ምድር እንደሚመጣ ተስፋን ሰጠን፡፡ ይህንም ተስፋ ይዘን ለሺህ ዘመናት በጉጉት ጠበቅን ነቢዩ አንደተናገረው አምላክ ጻሕቀ ልቡናችን ፈጸመልን፡፡ ‹‹ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች›› ኢሳ 40:80 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው የገባውን ቃል አስታውሶ ወደ ምድር እንደመጣ ሁሉ በእርሱ ስም የሚጠሩ ክርስቲያኖችም የገቡትን ቃል፣ የሰጡትን ተስፋ በመፈጸም አምላካቸውን መምሰል ይገባቸዋል፡፡ የተሰጣቸውን ሥራ በጊዜ የማይጨርሱ፣ ጉባኤ የሚያስተጓጉሉ፣ ሰው ቀጥረው ሲያረፍዱ እንኳ ቅንጣት የማይሰማቸው ክርስቲያኖች ካሉ በእውነትም በልደት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንን ቀጠሮ የማክበር ቃልን የመጠበቅ አሰረ ፍኖት የዘነጉ መሆናቸውን መረዳት አለባቸው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚያስተላልፈው ዐቢይ መልእክትም ይህን  ነው፡፡ ‹‹ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም›› እንደተባለ በቃላችን የምንገኝ፣ ባልነው የምንጸና ተአማኒ መሆን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡

ባጠቃላይ በልደቱ ያገኘናቸውን ሀብታት በመጠበቅ፣ የተማርናቸውን ትምህርቶች በመፈጸም እውነተኛ የልደት በዓል ተካፋዮች መሆን ይገባናል፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሰማያውያን መላእክት ከምድራውያን እረኞች ጋር በአንድ ላይ እንዳመሰገኑ እኛም በዝማሬና በምስጋና በፍፁም ደስታ ልናመሰግን ይገባል፡፡

                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ከታሪክ አንድ ገጽ

እንደዚህ ሆነ፡፡
በአንዲት መንደር ውስጥ አንድ ሰው ነበረ፡፡ አንደበቱ ከጸሎት እጁ ከምጽዋት ልቡ ከጠዋሐት ተለይቶ የማያውቅ፤ ሰው ተጣላ ማን ያስታርቅ፣ ልጅ አገባ ማን ይመርቅ ቢባል በመጀመሪያ የሚጠራው እርሱ ነው፡፡

ለሽማግሌዎች መኩሪያ ለታዳጊዎች አርአያ መሆንን የሚያነሣ የለም፡፡ ኃጢአትን ሊሠራት ቀርቶ ስሟን ያውቃታል ብሎ የሚገምት የመንደሩ ነዋሪ ከማግኘት አንድ ቀን ሰይጣን ሊመለስ ይችላል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ማግኘት ይቀላል፡፡
ለብዙዎች መለወጥ፣ ለብዙዎች ለጽድቅ መመረጥ፣ ለብዙዎች ከዓለም መመለስ፣ ለብዙዎች ዓለምን ጥሎ መመንኮስ አንድም መሪ ያለያም አበረታች መካሪ እርሱ ነው፡፡
የተናገረው ከልቡና ያስተማረው ከኅሊና ጠብ ሲል ልብ ያደርሳል ኩላሊት ያድሳል፡፡
ያለ ሠርክ ሰዓት እህል የማይቀምስ ያለ ተርታ ነገር ነጠቅ መንጠቅ ያለ የማይለብስ መሆኑን በአካባቢው ሐይቅ ስለሌለ የባሕር ዓሦች ካልሆኑ በቀር የማይመሰክር ፍጥረት አለ ማለቱ ይቸግራል፡፡

ትዳሩን አክባሪ ባለቤቱን አፍቃሪ በመሆኑ ከአብርሃምና ከሣራ ቀጥሎ ለሰርግ ምርቃት እርሱና ባለቤቱ ሳይጠሩ አይውሉም፡፡ አንድ ቀን ከቤተክርስቲያን መልስ ወደ ቤቱ በማምራት ላይ እያለ ዓይኑን ዓይኑ አንድ የማይወራውን ነገር ተመለከተ፡፡ አንድ አገር ያስቸገር መናፍቅ ከርሱ ቤት ግቢ ወጣ፡፡ ለምን?

 
ባለቤቱን አግኝቶ እስኪጠይቃት ነፍሱ የቸኮለችውን ያህል የመኪና እሽቅድድም ተወዳዳሪዎች ቸኩለው አያውቅም፡፡ ገባ፤
‹‹ ይኸ ሰውየ እንዴት መጣ?››
‹‹ ረጋ በልና አስረዳሃለሁ፡፡››
‹‹ ለመናፍቅ ምን እርጋታ ያስፈልገዋል››
‹‹ እኮ ረጋ በል››
‹‹ ለምን ታረሳሽኛለሽ?››
‹‹ ምኑን?›› የሆነ ነገር ብልጭ አለበት፡፡ ሰይጣን እሳት ጫረና ቤንዚን ለቀቀበት፡፡
‹‹ምን ሊሰራ መጣ?››
‹‹ለምን ትቆጣለህ?›› ሰይጣን እሳቱን እፍ በማለት ላይ ነው፡፡
እርስዋ ራስዋ ሰይጣን መስላ ታየችው፡፡ ደክሞታል፡፡ ተናዷል፡፡ ዝሏል፡፡ አእምሮው ዕረፍትን ብቻ ነበር የሚሻው፡፡ ውሳኔ ለመስጠት፤ ነገር ለማመዛዘን ዐቅሙም አልነበረውም፤ ብቻ ሳይሆን ዐቅሙ እንደሌለውም አላወቀም፡፡ አደርጎት የማያውቀውን ዓይኑን አጉረጠረጠና ገፈተራት፡፡ ወደ ኋላ ተንደረደረችና አንገትዋ ኮመዲኖው ጠርዝ ላይ አረፈ፡፡ በስተመጨረሻም መሬት ላይ ተኛች፡፡ ላንዴም ለመጨረሻም፡፡
ነቃ፣ ነቃና አያት፤ ያደረገውን ለማስታወስ ሞከረ፡፡ እርሱ ወይስ ሌላ ሰው? ምንድን ነው የፈጸመው? ሚስቱን ገደላት ማለት ነው? ገዳይ-ወንጀለኛ-ጨዋ-ሰላማዊ-አርአያ-ምሁር- መምህር-ገዳይ-ወንጀለኛ፡፡
ጮኸ – ከማለት ይልቅ የጩኸቱ ደምጽ ፈነዳ ማለቱ ይቀላል፡፡ አካባቢው በሰው ተጥለቀለቀ፡፡
 
እርሱ ያለቅሳል፡፡ ሰውም ያለቅሳል፡፡ አለቃቀሳቸው ግን ለየቅል ነበር፡፡ አንዱ ‹‹ክፉ ተናግራው መልአክ ቀስፏት ነው፡፡ ይላል፡፡ አንዱ ደግሞ ‹‹ የጻድቅ ሰው ዕንባ፡፡ ድሮም የማይናገር ሰው ዕንባው ሰይፉ ነው፡፡›› ሌላው ‹‹ አሁንኮ ወይ እማታለሁ ወይም እገላለሁ ብላ ይሆናል፡፡ ይቺ ሰው መሳይ በሸንጎ የርሱ ደግነት ክፋቷን ሸፍኖላት ዛሬ እግዜር አጋለጣት፡፡›› እርሱ ይገላል ቀርቶ ዝንብ ያባርራል ብሎ የጠረጠረ የለም፡፡ ወንጀሉ ሁሉ የርስዋ ሆነ፡፡
እርሱ ግን የደም ዕንባ አለቀሰ፡፡ የሰዎችን ንግግር በሰማ ቁጥር ዕንባው ይጨምር ነበር፡፡ ‹‹እኔ ነኝ እኔ ነኝ እኔ ነኝ›› አለ ድምፁን ከፍ አድርጎ፡፡
‹‹አይ የዋህ ሰው፡፡ ከባቴ አበሳ አይደል፡፡ ስሟ በክፉ እንዳይነሳ ብሎእኮ ነው›› ይላል አንዱ፡፡
‹‹ስላዘንኩባት ነው ማለቱኮነው›› ቀጠለ ሌላው፡፡ ሊያምነው ቀርቶ ሊሰማው የወደደ የለም፡፡ ሰው የሚናገርለት እና እርሱ የሆነው እየተጋጨበት ኅሊናው ዞረ፡፡ ማን ይመነው፡፡
ለያዥ ለገራዥ ቢያስቸግርም በሽማግሌ ጥረት ሊቀመጥ ቻለ፡፡ ‹‹አይዞህ አንተ አልገደልካት እግዜር መታት እንጂ›› ይሉታል ሽማሎች ሰብሰብ ብሎው፡፡ ያ ለርሱ መርፌ ነው ልብ የሚወጋ፡፡
‹‹እንዲያው እግዚአብሔርን ማመስገን አለብህ፡፡ ፊትህ ላይ ተአምሩን ሲያሳህ›› ሲሉት ደግሞ የተወጋው ልቡ መድማት ጀመረ፡፡
‹‹እኔ አይደለሁም እንዴ አለና መጠራጠር ያዘ፡፡›› አሰበው /ድርጊቱን ሁሉ አሰበው/ ነው እርሱ ነው እኔ ነኝ፡፡ እኔ ነኝ ገዳይዋ- ተንሰቀሰቀ፡፡
‹‹ወይ ግሩም ጻድቃን የወንድማቸው ኃጢአት ከሚገለጥ የራሳቸው ኃጢአት ቢገለጥ የተባለው ደረሰ።›› አሉ አንዲት ወይዘሮ፡፡
‹‹የነ አባ እንጦንስ ታሪክ ሲደገም በዓይናችን አየንኮ›› ሌላዋ ተቀበሉ፡፡
ማን ይመነው፡፡ የልቡን ማን ይወቅ፡፡ እሳት እየከመሩበት መሆኑን ማን ይረዳ፡፡
ጊዜያት ነጎዱ፡፡ ሰው ሁሉ ሊረሳው ጀመረ ጉዳዩን፡፡ እርሱ ግን የሚንተገተግ እሳት ሆኖበታል፡፡
በመጨረሻ እንዲህ ወሰነ፡፡ ለአንድ ለሚወደው ጓደኛው ሊነግረው፡፡ ሐሳብ ቢከፍልልኝ ምክር ቢለግሰኝ ብሎ፡፡
ያደረገውን፡፡ የሆነውን ሁሉ ነገረው፡፡ እየማለ እየተገዘተ የጓደኛው ፊት ሲለዋወጥ ታየው ነጣ- ከዚያ ቀላ መጨረሻ ላይ ጠቆረ፡፡ ‹‹ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ….ለካ አንድ ሰው የለም ባገሩ፡፡ አንተ ስናምንህ ስናከብርህ- ለካ አውሬ ኑረሃል…›› ሰቀጠጠው፡፡ እናም ሸሸው ‹‹ ለኔም ፈራሁህ ››
‹‹እኔኮ የነገርኩህ… ›› አላስጨረሰውም ‹‹ዝም በል!››
ልቡ  ሌላ ነገር ፀነሰ፡፡ የነገርኩት እንዲቀልድብኝ አይደለምኮ አለና ‹‹ባይሆን ነገሩን በልብህ ያዘው›› ሲል ለመነው፡፡
‹‹ገና በአደባባይ ትሰቀላለህ›› ሲል መለሰለት፡፡
ብልጭ አለበት- ሰይጣን እሳት ጫረ፡፡ ዓይኑ ዘወር ዘወር አለ ክትክታ አነሣና ሠነዘረ፡፡ ተጥመልምሎ ወደቀ፡፡ ትኩር  ብሎ ሲያየው ነፍሱ ሸሽታዋለች፡፡ እያለቀሰ፡ ደረቱን እየደቃ ወጣ፡፡ ከቤቱ ብቻ ሳይሆን ከመንደሩ ወጣ፡፡ ወደ በረሃው ሰው ወደ ሌለበት ዘለቀ፡፡ ልክ መንገዱን ሲጨርስ አንድ ሽማግሌ አገኘ፡፡
‹‹ እንደምን ዋሉ አባቴ ››
‹‹እግዚአብሔር ይመስገን ይኼ ደም ምንድነው ልጄ››ልብሱን አሳዩት ደነገጠ፡፡
‹‹እይውልዎት›› አለና ታሪኩን መናገር ሲጀምር ደነገጡና አፈገፈጉ፡፡
‹‹ ዘወር በል አንተ ሰይጣን፡፡!››
‹‹ ይምከሩኝ አባቴ ምን ላድርግ እባክዎ አያውግዙኝ››
‹‹ ዘወር በል ዲያብሎስ እኔንም እንዳትጨምረኝ››
‹‹እኔ እኮ ከቁስሌ ትፈውሰኝ ብዬ እንጂ በቁስሌ ላይ እንጨት የሚሰሰድማ መች አጣሁ፡፡›› አለና ክትክታውን አነሣ እኒያ ሽማግሌ ወደቁ፡፡
ሰው ሁሉ አውሬ መሰለው፡፡ ልቡ እየደነደነ መጣ፡፡ ‹‹ታዲያ ምን ይሁን›› አለው ሰይጤ ‹‹አንተ የመጀመሪያው አይደለህ ››
‹‹ ካሁን በኋላ ማንም ቁስሌን ሊነካ አይችልም ›› አለና በፍጥነት በረሃውን ማቋረጥ ጀመረ፡፡ ማዶ ማዶ ነው አንድ አረጋዊ ካህን ደበሏቸውን ለብሰው ዛፍ ሥር ተቀምጠው ጸሎት ያደርሳሉ፡፡
‹‹ለመጨረሻ ጊዜ›› አለ ‹‹ለርሳቸው ነግሬ መፍትሔ ካልሰጡኝ፤ በቁስሌ ላይ ዘይት መጨመር ትተው ኮምጣጤ ከደፉብኝ የሰው ልጅ ሁሉ ጠላቴ ነው ማለት ነው።›› ወሰነ፡፡
ቀና ብለው አዩት፡፡ ያስፈራል ፡፡ ልብሱ ደም ነክቶታል፡፡
‹‹ ምን ሆንክ ልጄ?›› አሉና ከመቀመጫቸው ተነሡ፡፡ ሠይጣን አንድ ርምጃ አፈገፈገ፡፡
‹‹ ተቀመጥ ደክሞሃል›› ድንጋዩን ለቀቁለት፡፡ ሰይጣን ተናደደ፡፡
‹‹ ምን ሆነሃል?››
በዕንባ ጀምሮ በዕንባ ጨረሰው፡፡
‹‹በተሰቀለው ክርስቶስ ዛሬ ጓደኛ አገኘሁ፡፡›› ዕልል አሉ፡፡
ሰይጣን ፈረጠጠና ዛፍ ሥር ተሸጉጦ ማየት ቀጠለ።
በመገረም ተመለከታቸው፡፡ ‹‹ይገርምሀል፡፡ ሚስቴን ገድዬ፤ ልጆቼን አርጄ፣ የሰው ሀብት ዘርፌ፣ ስንት ልጃገረዶች አባልጌ፣ ሰው መቀመጫ ሲነሳኝ ጻድቅ መስዬ እዚህ ተቀምጫለሁ፡፡ ያንተማ ምን አላት፡፡ በኔ አይነትኮ ያንተ በጥቂት ቀኖና ትሻራለች፡፡››
የፊቱ ጥቁረት ቀነሰ
ክትክታው ከእጁ ወደቀ፡፡
‹‹ በል አሁን ካንድ ሁለት ይሻላል፡፡ ሰው እንደሆነ ቂመኛ ነው ይቅር አይለንም፡፡ እግዚአብሔር ግን መሐሪ ነው፡፡ በዚህ ከቀጠልን እኛ ራሳችን ከሰይጣን መብለጣችን ነው፡፡ ስለዚህ ገደል እንቆፍርና እዚያ ውስጥ ገብተን ንስሐ እንግባ፡፡›› አሉት፡፡ ፈነደቀ፡፡ ዘሎ ተነሣና ዐቀፋቸው፡፡ እናም በዚያው ክትክታ መቆፈር ጀመረ፡፡ እጅግ አድካሚ ሥራ ነው፡፡ አባ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ይደግማሉ፡፡ ቀና ብሎ አየና እርሱም ጸሎቱን ቀጠለ፡፡
ቀን-ሳምንት-ወር-ሁለት- ሦስት- ወር ፈጀ ቁፋሮው፡፡
ቅጠል ይበላሉ፡፡ አብረው ስለጥንቱ እያወሩ፡፡ ከዚያ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መሐሪነት ያስተምሩታል ዐረፍ ሲሉ፡፡ ይቆዩና ደግሞ ይቆፍራሉ፡፡
በሰው ቁመት ልክ ገደሉ ተቆፈረ፡፡
እንዴት እንግባ፡፡
‹‹አንተ እዚያው ቆየኝ ዕቃውን ሰብስቤ ምግባችንን ይዤ እኔ መጣሁ፡፡›› ተስማማ፡፡
በገመዱ ተንጠልጥለው አባ ወጡ፡፡እላይ ከደረሱ በኋላ ገመዱን ሳቡት፡፡ ደነገጠና ቀና ብሎ አያቸው፡፡
‹‹ ልጄ አሉት አባ›› የነገርኩህ ታሪክ ውሸት ነው፡፡ ‹‹ አንተ እንዳይሰማህ ብዬ ነው ከአሁን በኋላ ምግብህን አመጣልሃለሁ እየሰገድህ፣ እየጾምክ ጸልይ፡፡ እግዚአብሔር ይምራል››  አሉት፡፡ ተናደደ ክትክታው አጠገቡ የለም፡፡ ከግራ ገደል ከቀኝ ገደል አለቀሰ፡፡ አነባ፡፡
‹‹ዕንባ የኃጢአት ክምር ትንዳለች ›› አሉ አባ፡፡
ምንም አማራጭ የለም፡፡ ጸሎቱን ጀመረ፡፡
አባም በዘጠኝ ሰዓት ምግቡን አስበው ያመጡ ነበር፡፡
ከሰባት ዓመት በኋላ አባ ምግቡን ሊያደርሱለት ሲሄዱ ክንፍ አውጥቶ ሲበር አዩት፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፦  ሐመር 7ኛ ዓመት ቁጥር 3 ሰኔ/ሐምሌ 1991 ዓ.ም.