የዘወረደ ወንጌል (ዮሐ.3÷10-24)

ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን አንዴት ይህን አታውቅም?” አለው፡፡

እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም፡፡ በምድር ያለውን ስነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁን ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ አንጂ ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፡፡ ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ ነው እንጂ በዓለም አንዲፈርድ እግዚአአብሔር ልጁን ወደዚህ ዓለም አልላከውምና፡፡ በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን ፈጽሞ ተፈርዶበታል፤ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም አላመነምና፡፡ ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጥቶአልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጦአልና፡፡ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደብርሃን አይመጣም፡፡ አውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ አብሮአቸው ተቀመጠ፡፡ ዮሐንስም በዮርዳኖስ ማዶ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ያጠምቅ ነበር፤ በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ እየመጡ ያጠምቃቸው ነበር፡፡ ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልገባም ነበርና፡፡

የዘወረደ ምንባብ 3 (ሐዋ.25÷13-ፍጻ. )

ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡

ተገናኙት፡፡በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው÷ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ፡፡ በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ፡፡ አኔም፡- ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም÷ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ÷ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ፡፡ የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ÷ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው÷ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤ ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም  ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት፡፡” አግሪጳም ፊስጦስን÷ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወደለሁ” አለው፤ ፊስጦስም÷ “እንግደያስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው፡፡

በማግሥቱም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጡ፤ ከመሳፍንቱና ከከተማው ታላላቅ ሰዎች ጋርም ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ፊስጦስም እንዲህ አለ÷ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ÷ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ወንድሞቻችን ሁላችሁ÷ ስሙ፤ አይሁድ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው በኢየሩሳሌምም ሆነ በዚህ እየጮሁ የለመኑኝ ይህ የምታዩት ሰው እነሆ፡፡ እኔ ግን ለሞት የሚያደርሰው በደል እንዳልሠራ እጅግ መርምሬ÷ እርሱም ራሱ ወደ ቄሣር ይግባኝ ማለትን ስለወደደ እንግዲህ ልልከው ቈርጫለሁ፡፡ ለገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የታወቀ ነገር የለኝም፡፡ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን አገኝ ዘንድ ወደ እናንተ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ ወደ አንተ አመጣሁት፡፡ የበደሉ ደብዳበቤ ሳይኖር እስረኛን ወደ ንጉሥ መላክ አይገባምና፤ ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል፡፡”

የዘወረደ ምንባብ 2 (ያዕ.4÷6-ፍጻ. )

ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡

እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡

የዘወረደ ምንባብ 1 (ዕብ.13÷7-17)

የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም የሚኖር እርሱ ነውና፡፡ ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና፡፡ ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤ ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ፡፡ አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን÷ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ፡፡ በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም የምትመጣውን እንሻለን እንጂ፡፡ በውኑ እንግዲህ በሰሙ አናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡
የዘወረደ መዝሙርና ምንባባቱ በዜማ

ዘወረደ(የዐቢይ ጾም አንደኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ ባኡ ቅድሜሁ በተጋንዮ ወውስተ አ|ዕፃዲሁ በስብሐት አምንዎ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ወንትፋቀር በበይናቲነ  እስመ ለዓለም ምሕረቱ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ እስመ ሰንበትሰ በእንተ ሰብእ ተፈጥረት እስመ ለዓለም ምሕረቱ ምሕረተ ወፍትሐ አሐሊ ለከ እዜምር ወእሌቡ ፍኖተ ንጽሕ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ አባግዓ መርዔቱ።

ትርጉም፦ እግዚአብሔርን በመፍራት ተገዙለት ለእርሱ መገዛትም ደስ ያሰኛችሁ። እግዚአብሔር ቸር ምሕረቱም ለዘላለም፣ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነው ። እኛስ ሕዝቡ የመሰማሪያው በጎች ነን፡፤ ወደ ደጁ በመገዛት፣ ወደ አደባባዮችም በምስጋና ግቡ፤ ጾምን እንጹም፤ጓደኞቻችንን እናፍቅር፤እርስ በርሳችንም እንፋቀር ። ሰንበት ስለሰው ተሠርታለችና ሰንበትን እናክብር። እውነትንም እንሥራ፤ አቤቱ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ፤ እዘምራለሁ፤ንጹሕ መንገድንም አስተውላለሁ።

ምንባባት
መልዕክታት
ዕብ.13÷7-17የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)

ያዕ.4÷6-ፍጻ. ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)
ግብረ ሐዋርያት
ሐዋ.25÷13-ፍጻ. ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)

ምስባክ
መዝ. 2፡11 ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ።አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐፅ እግዚአብሔር።

ትርጉም፦ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።ጥበብን አጽኑአት ፤ እግዚአብሔር እንዳይቆጣ።

ወንጌል
• ዮሐ.3÷10-24 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን አንዴት ይህን አታውቅም?” አለው፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
ቅዳሴ
ዘእግዚእነ

የዘወረደ መዝሙርና ምንባባቱ በዜማ

መዝሙሩንና ምንባባቱ በዜማ ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

akebabele.jpg

ከ400 በላይ የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት ተጠመቁ።

በሪሁን ተፈራ ከባህር ዳር ማዕከል
በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወንበርማ ወረዳ የሚገኙ ከ400 በላይ የሚሆኑ የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት በጎመር ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስቲያን እሑድ  የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ በርናባስ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በሀገረ ስብከቱ ቆሞሳትና ካህናት መጠመቃቸውን የማኅበረ ቅዱሳን ባህር ዳር ማዕከል ገለጸ፡፡

 
ብፁዕ አቡነ በርናባስ የካቲት 12ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ በ10፡40 ሰዓት ጎመር ሲደርሱ  የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ሠራተኞች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ባሕር ዳር ማዕከል፣ የሽንዲ ወረዳ ማዕከል አባላት፣ የአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምእመናን እና የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት፣ በመዝሙርና በእልልታ የታጀበ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
akebabele.jpg

ከዚህ በተጨማሪም በዕለቱ የማኅበረ ቅዱሳን ሽንዲ ወረዳ ማዕከል አባላት፣ የኮሊ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መዘምራን፣ የሸንዲ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መዘምራን፣ ጎመር ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች መዝሙርና ሥነ ጽሑፍ በኦሮምኛ በአማርኛ ቋንቋ ለምእመናን አቅርበዋል፡፡

Abune Bernabas Siatemku.jpgሥርዓተ ጥምቀቱ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት የተጀመረ ሲሆን የተጠመቁት ምእመናን በሥርዓተ ቅዳሴው ተሳትፈው ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ በሊቀ ማዕምራን ሀዲስ ጤናው የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ እና በመጋቤ ምሥጢር ኃይለማርያም ታዬ ትምህርት ተሰጥቶ ሀገረ ስብከቱ ለተጠማቂያን የብሔረሰቡ አባላት 600 የአንገት መስቀል አበርክቷል፡፡

ተጠማቂ  ምእመናኑ አባይ በረሃን ከሚያዋስኑ ከወንበርማ ወረዳ ሦስት ቀበሌዎች የመጡ ሲሆኑ በአካባቢው ከአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት ጀምሮ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት አልፎ አልፎ ያሉና የተጠመቁ የብሔረሰቡ ምእመናን ቢኖሩም ለዚህ በርካታ  የብሔረሰቡ አባላት መጠመቅ ምክንያት የሆኑት አቶ አያና የተባሉ የቻግኒ ወረዳ ማዕከል አባል ወደ ቦታው ለሥራ በመጡና አሁን የተዛወሩት ግለሰብ እና መምህርት መድኃኒት ሞላ የሽንዴ ወረዳ ማዕከል አባል አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሽንዲ ወረዳ ማዕከል በ1994 ዓ.ም ሁለት ህፃናትን ከአካባቢው በመውሰድና የአብነት ትምህርት ቤትYewerwda Maekelu Meketel sebsabi Betemeherte laye.jpg ለማስገባት የጀመረው ሙከራ ልጆቹ ሊለምዱ ስላልቻሉ ቢቋረጥም ለዚህ እንቅስቃሴ መጠናከር በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወንበርማ ወረዳ ቤተክህነት እና ከአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጋር በመሆን 2000 ዓ.ም ግንቦት 16 ቀን ወደ የማቤል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በወረዳ ማዕከሉ አስተባባሪነት የተደረገ የእግር ጉዞና ከአካባቢው የጎሳ አካላት ጋር የተደረገው ትምህርትና ውይይት ትልቅ በር እንደከፈተና ከዚያም በኋላ በወረዳ ቤተክህነቱ እና ወረዳ ማዕከሉ የሚደረጉ ትምህርተ ወንጌል ይበልጥ ግንኙነታቸውን እንዳጠናከረው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባህርዳር ማዕከል እና ሽንዲ ወረዳ ማዕከል በሽንዲ ከተማ የእራት ግብዣ በማዘጋጀትና ከበጎ አድራጊዎች 4000 ብር አስባስቦ ቆርቆሮ እና እንጨት ገዝቶ በማጓጓዣ፤ ግንቦት 2002 ዓ.ም ጉባኤ በማካሄድና ከ460 በላይ የብሔረሰቡ አባላት ጋር ውይይት አድርጎ በቀበሌው ባሉት በመምህርት መድኃኒት ሞላና አንድ ሌላ መምህር አስተባባሪነት ተጨማሪ እንጨት እንዲያዋጡ በማድረግ ቤተክርስቲያን በጎመር ቀበሌ ሊሠራ ችሏል፡፡

ብፁዕ አቡነ በርናባስ ከአሁን በፊት የተጠመቁትንና አዲስ ተጠማቂያንን እንዲበረቱ መክረው በበዓሉ ለተገኙ ምዕመናን እንዳሉት “የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ወገኖቻችን ወደዚህች ሃይማኖት ሊመጡ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በደስታ ልንቀበላቸው፣ ልንከባከባቸውና ልንደግፋቸው ይገባል”፡፡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የብሔረሰቡ አባላት በበኩላቸው ከ 2፡00-4፡00 ሰዓት የሚፈጅ የእግር ጉዞ ተጉዘው  እንደተጠመቁ በመግለጽ ለሰሩት ቤተክርስቲያን ጽላት እንዲገባላቸው፣ በቅርብ ቦታ ተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናት እንደሰሩላቸውና ካህናት እንዲመደቡላቸው ጠይቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ በርናባስም ከወረዳ ቤተክህነት ጋር በመሆን የተቻላቸውን እንደሚፈጽሙና ምዕመናን ከጎናቸው በመሆን ለቤተክርስቲያን ሥራ እንዲተጉ ጠይቀዋል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

 ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።

 

ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የተውጣጡ ሰልጣኞች ተመረቁ፡፡

 በፈትለወርቅ ደስታ

የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ባዘጋጀው ስልጠና  ከተለያዩት ቦታዎች የመጡ 27 ሰልጣኞች ለሁለት ሳምንት የቆየ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ተመረቁ፡፡

የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አስተባባሪ ቀሲስ ታደሰ ጌታሁን እንደገለፁት ይህ ሥልጠና ለ13ኛ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን ከዚህ በፊት በተካሄዱት 12 ዙር ስልጠናዎች 219 ሰልጣኞች ስልጠናውን ተከታትለዋል፡፡ ስልጠናውን ከወሰዱት በጠረፋማ ቦታዎች ከሚኖሩት ብሔረሰቦች ውስጥ ከጋምቤላ፣ ከአፋር፣ ከኦሮሚያ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከደቡብ ኦሞ፣ ከጂንካ፣ ከሰመራ፣ ከአላባ፣ ከጠምባሮ፣ ከስልጤና ከጉራጌ ዞኖች የተውጣጡ  እንደነበሩ አስታውሰው በአሁኑ መርሐ ግብር ስልጠናውን የወሰዱት ከሱማሌ፣ ከቦረና፣ ከጉጂና ሊበን ዞኖች የመጡ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስልጠና ስለ ስነ ፍጥረት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ክርስትያናዊ ሥነ ምግባር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የስብከት ዘዴ በሚሉ ርእሶች ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪ ሰልጣኞቹ ታሪካዊ ቦታዎችንና ሙዚየሞችን በቆይታቸው ወቅት ጎብኝተዋል፡፡

የሰልጣኞቹ ተወካዮች እንደገለጹት “በሚኖሩበት ጠረፋማ አካባቢ ያሉ ምእመናን በመናፍቃንና በአሕዛብ የተከበቡ ሲሆን መናፍቃን በገንዘብና በስልጣናቸው በመጠቀም የተለያዩ ስልጠናዎችን እያዘጋጁ አብዛኛውን ምእመን በቋንቋቸው እያስተማሩ ወደ መናፍቅነት እየለወጧቸው እንደነበርና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ምንም አይነት ቤተክርስቲያን ባለመኖሩ ሕብረተሰቡ በባእድ አምልኮ ውስጥ እንደሆነ ገልጸው፤ የአካባቢው ምዕመናን መጠመቅ እንደሚፈልጉና ቤተክርስቲያንም ተሠርቶላቸው ቅዳሴ የሚያስቀድሱበት፣ ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት፣ ጸሎት የሚያደርሱበት፣ ወንጌልን የሚማሩበት በአጠቃላይ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጽሙበት ቤተክርስቲያን እንዲሰራላቸው ለቤተክርስቲያን ልጆች ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በስልጠናው በቆዩበት ወቅት ለምግብ፣ አልባሳትና ለመጓጓዣ 50.000.00 ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህ ገንዘብ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሁም በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ክፍልና አውሮፓ ባሉ በጎ አድራጊ ምእመናን የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቀሲስ ታደሰ በሰጡት አስተያየት የአሁኑን ጨምሮ በአጠቃላይ 246 ሰልጣኞች እንደተመረቁ ገልጸው ሰልጣኞቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ መጻሕፍት፣ አልባሳት፣ ትራንስፖርት በተደጋጋሚ ስልጠናና ድጋፍ እንደሚያስፈለጋቸው፣ ወደ ተለያዩ ከፍተኛ መንፈሳዊ ተቋማት እየመጡ የሚሰለጥኑበትና ሃይማኖታቸውን የሚያጸኑበት መንገድ ለመፈለግ የብዙ ምእመናን ድጋፍና ርብርብ አስፈላጊ በመሆኑ እውቀት ያለው በእውቀቱ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ እንዲሁም በጸሎት ቤተክርስቲያንን መደገፍና የተሰጠውን ኃላፊነት  እያንዳንዱ ምዕመን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀትና ለወደፊት እውቀታቸውን ለማዳበርና ለአገልግሎት የሚረዳቸውን መጽሐፍ ቅዱስንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት የተዘጋጁ የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ትውፊትና የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚያስረዱ መጽሐፍትና ሌሎች አጋዥ ጽሑፎች ተሰጥቷቸዋል፡፡

የማኅበሩ ዋና ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ለሰልጣኛቹ ባስተላለፉት መልእክት ማኅበሩ ወደ ፊት በእያንዳንዱ ብሔረሰብ ቋንቋ ስልጠና እንደሚሰጥና አሁን ግን ሠልጣኞቹ የሰለጠኑትን ለወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ በቋንቋቸው እየተረጎሙ ማስተማር እንዳለባቸውና በጾምና በጸሎት በሕይወት በመተርጎም የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባቸውና ማኅበሩም በየጊዜው የማሻሻያ ስልጠና  እንደሚሰጣቸው ገልጸው መርሃ ግብሩን በጸሎት ዘግተው ፍጻሜ ሆኗል፡፡

 

ነፍስና ሥጋ የውል ስምምነት ተፈራረሙ

በመ/ርት ጸደቀወርቅ አሥራት
ነፍስና ሥጋ እንደከዚህ በፊቱ ለሚጠብቃቸው ከባድ የሥራ ኃላፊነትና አለመግባባት የውል ስምምነት ተፈራረሙ። የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት በቀጣዩ ሣምንት የሚገባውን የዐቢይ ፆም ምክንያት በማድረግ ነው።
 
በውሉ ሥነ ሥርዐት ላይ ነፍስ እንደገለጸችው ከዚህ በፊት በአጽዋማት ጊዜ በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ውሉ ጠቃሚነቱ የጎላ ነው።

ባለፉት ዓመታት ሥጋ የአጽዋማትን ወቅት ጠብቆ ነፍስ ተገቢውን ድርሻ እንዳትወጣ እንቅፋት እየሆነ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸው ስምምነቱ በመካከላችው ሰላም እንዲሰፍን ምክንያት ይሆናል ያሉን በስምምነቱ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት የነፍስ አባት ናቸው።

ከፊርማው ሥነ ሥርዐት በኋላ ባነጋገርነው ወቅት ስምምነቱን ተቀብሎ የነፍስን ሥራ ሳይቃወም ሊገዛላት መዘጋጀቱን ሥጋም ቢሆን አልሸሸገም።

በሥነ ሥርዐቱ ላይ የተገኙት ሌሎች ምዕመናንም ሥጋን በቃልህ ያጽናህ እያሉ ከስብሰባው አዳራሽ ሲወጡ እንደተሰሙ “ሪፖርተራችን” ዘግቦልናል።

KidaneMihret

ኪዳነ ምሕረት

ዲ/ን ኅብረት የሺጥላ

KidaneMihret

‘ኪዳን’ የሚባለው ቃል “ቃል” ከሚለው ጋር እየተቀናጀ በብሉይ ኪዳን ለ280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከ33 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ “ኪዳን” ቃሉ “ተካየደ” ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡

 

“ምሕረት” የሚለው ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡

“ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደርጋለሁ” ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ ወደ ፊትም ያደርጋል፡፡ /መዝ. 88÷3/ ቃል ኪዳኑም የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡ በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት/እናቶች/ ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸዋል፤ የምሕረት ቃል ኪዳንም ይሰጣቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዙሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡት አፈርና ለተጋደሉበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡

ለቅዱሳን ከሞት አስቀድሞ የእግዚአብሔር መገለጥ ወይም የሚሞቱበትን ጊዜና የአሟሟታቸውን መንገድ ገልጦ መንገር በቅዱሳት መጻሕፍት የተለመደ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዴት ባለ አሟማት እንደሚሞት ነግሮታል፡፡ /ዮሐ.21÷39፤ 2ኛ ጴጥ.1÷14/ ለቅዱስ ጳዉሎስ ስለሚሞትበት ጊዜ ተነግሮታል፡፡ /የሐዋ.20÷25 ፣ 21÷10-13/ “ከሞቱ አስቀድሜ እገለጥለታለሁ” እንዲል፡፡ /ሰኔ ጎልጎታ/፡፡

 

እግዚአብሔር ከሞታቸው አስቀድሞ በመገለጥ ለቅዱሳን የምሕረት ቃል ኪዳን የሚሰጣቸው በእነርሱ በጎ ሥራ ከእነርሱ በኋላ ያሉ የሰው ልጆችን ለመጥቀም ፈልጎ ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው ናቸው እንዳይባል ወደ ሞት አፋፍ የተጠጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለቃል ኪዳን የበቁት የሚጠቀሙበት በጎ ሥራ በመሥራታቸው ነው፡፡ የሰው ልጆች ያለፉ ቅዱሳንን በመዘከር የቃል ኪዳናቸው ተጠቃሚ ሲሆኑ ቅዱሳኑ ግን ከመታሰብ በቀር በሰው በኩል የሚጨመርላቸው የለም፡፡ ቅዱሳን የምሕረት ቃል ኪዳን ሲቀበሉ ለወገናቸው መትረፋቸውን እንረዳለን፡፡

የምሕረት ቃል ኪዳን ለምን ያስፈልጋል ቢባል ሕግ መተላለፍ ካለ ሁልጊዜ ተጠያቂነት ወይም ቅጣት ይኖራል፡፡ ይህም በአዳም ይታወቃል፡፡ የሰው ልጆች ደግሞ ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ አኗኗር ይዘው አይገኙም፡፡ በዚህ ምክንያት ቅጣት እንዳያገኛቸው የሚድኑበትን በርካታ መንገዶች እግዚአብሔር አዘጋጀ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡

የምሕረት ቃል ኪዳን ሁሉ በጎ እንድንሠራ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህም ዘወትር ከቃል ኪዳኑ ጋር ተያይዘው በሚቀመጡ ግዴታዎች ይታወቃል፡፡ ለበጎ ሥራ ምክንያት የማይሆን ባዶ የምሕረት ቃል  ኪዳን የለም፡፡ “ስምሸን /ስምህን/ የጠራውን፣ ዝክር ያዘከረውን፣ የተራበ ያበላውን፣ የተጠማ ያጠጣውን፣ የታረዘ ያለበሰውን፣ እንግዳ በስምህ /በስምሽ/ የተቀበለውን፣ ገድልህን ያነበበውን፣ የሰማውን፣ የተረጎመውን ወዘተ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ፣ እምረዋለሁ” የሚሉ ቃል ኪዳናት በሙሉ ከባዱን መልካም ሥራ መፈጸም ባይቻለን እንኳን ቀላሉን መሥራት እንዳለብን ግዴታ የሚጥሉ ናቸው እንጂ አንዳንዶች እንደሚያስቡት መልካም እንዳንሠራ የሚያሳንፉ አይደሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ለበጎ ሥራ የሚያነሣሡና የታዘዙትን መሥራት ያልተቻላቸውን ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ እስከ መጨረሻው ሰዓት የሚድኑበት መንገድ እንዳለ አውቀው የተቻላቸውን እንዲያደርጉ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ይህም ሰዎች በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ በሚያነሡት ጥያቄ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ በየዜና ገድላቸው እንደምናነበው እግዚአብሔር ለብዙ ቅዱሳን “እስከ አሥር፣ ሠላሳ፣ ሃምሳ አምስት ወዘተ ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ” እያለ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን በማንበብ እምነት የጎደላቸው አንዳንዶች “ይህ እንዴት ይሆናል?” እያሉ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ብቻ በራሱ የፈጣሪ ቸርነት ከሕሊና በላይ መሆኑን አያስረዳምን ?

ፈጣሪ ስለ ፈራጅነቱና ስለ መሐሪነቱ ሲናገር “በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወዱኝ ትእዛዜን ለሚጠብቁ እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ” ይላል፡፡ /ዘጸ.20÷2-6/ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ የሚደርስ የእግዚአብሔርን ምሕረት መናገሩ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያለው የሠላሳና የሃምሳ ትውልድን ምሕረት የሚያወሳው ኃይለ ቃል ሊስተባበል አለመቻሉን ያሳያል፡፡ ያን   ማክፋፋት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደመቃወም ይቆጠራል፡፡

ዓለም ከተፈጠረች ሰባት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት ገደማ ሊሆናት ነው፡፡ የሰው ልጅን አማካይ እድሜ እጅግ አሳንሰን በመቁጠር የአንድ ትውልድ ዘመን ሠላሳ ዓመት ነው ብንል እንኳን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለው ትውልድ ከሁለት መቶ ሃምሳ አይበልጥም፡፡ ነገር ግን ፈጣሪ የሚወደውና ትእዛዙን የሚጠብቅ እውነተኛ ሰው ከተገኘ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ያን ያህል ትውልድ እስከዓለም ፍፃሜ የሚኖር ከሆነም “እስከ ሺሕ ትውል” ድረስ እንኳን ይቅር ሊል ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው የእግዚአብሔርን የቸርነት ስፋት ነው፡፡ ሺሕ ትውልድ ባይኖር እንኳን ሺሕ ትውልድ ስለሌለ እግዚአብሔር ሺሕ ትውልድ ሊምር አይችልም አይባልም፡፡ ስለዚህ የፈጣሪን ቃል ኪዳን ከመሐሪነቱ አንጻር እንጂ ከዓመታቱ መብዛት አንጻር ሊመለከቱት አይገባም፡፡

ፈጣሪ ለቅዱሳኑ በየዕለቱ ብዙ ነፍሳትን ከሲዖል እንዲያወጡ የምሕረት ቃል ኪዳን ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ የተሰጣቸውም ቅዱሳን አሉ፡፡ ነገር ግን ተፈጻሚነቱን ስንመለከት በቀን የተባለውን ያህል ነፍሳት ከሲዖል ሊወጡ ወይም አንድም ነፍስ ከሲዖል ላትወጣ ትችላለች፡፡ ይህ ግን በተገባላቸው ቃል ኪዳን ላይ ምንም ዓይነት አሉታ የለውም፡፡ ምክንያቱም ለቅዱሳኑ ይህ ቃል ኪዳን ሲሰጥ ሲዖል ካለችው ነፍስ ደግሞ የሚጠበቅ ነገር ይኖራልና፡፡ ያን የምታሟላ ነፍስ ካልተገኘች ኪዳኑ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ይህም በመሆኑ ቃል ኪዳኑ ከንቱ ነው አይባልም፡፡ ከላይ እንዳየነው ተፈጻሚ ሊሆን ባለመቻሉ ብቻ ለሺሕ ትውልድ የተገባው ቃል ኪዳን ከንቱ ነው ሊባል አይቻልምና፡፡

ስለዚህ ምእመናን ቅዱሳን የተገባላቸው ቃል ኪዳን ለሰው ልጆች የተሰጠ የመዳን ጸጋ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል፡፡ በኃጢአት ወድቀን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ፍርድ ፊት የሚያፍር ነፍስ እንዳለን ስንረዳ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ለወዳጆቹ ስለገባው ቃልኪዳን ብሎ እንዲምረን መማጸን ይገባል፡፡«ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደርጋለሁ» ባለው መሠረት ጌታ ከእመቤታችን ጋር ብዙ ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ እርሷ የተመረጠች ብቻ ሳትሆን ከተመረጡትም ሁሉ የተመረጠች ናትና፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ እመቤታችን ድንግል ማርያም በሁሉም ረገድ ስለምትበልጥ ከተሰጣቸውም የምሕረት ቃል ኪዳን ለሷ የተሰጣት ኪዳን ኪዳነ ምሕረት ተብሎ ተለይቶ ይታወቃል፤ ማለትም ትጠራበታለች፤ ኪዳነ ምሕረት ትባላለች፡፡ ስለዚህ የኃጥአን ሁሉ ዓይን የእርሷን የምሕረት ቃል ኪዳን ተስፋ ያደርጋል፡፡ የሚገባቸውን ሁሉ አድርገው ላወቁትና ላላወቁት ጉድለቶቻቸው ሁሉ ስሟን ለሚጠሩ ቃል ኪዳንን ለመቀበል ያበቃትን ለሰው ልጆች ነጻነት ልጇ ለሰጠው ፍፁም መድኃኒት ምክንያት የሆነችበት ጸጋዋ ሁሉ በሥላሴ ፊት ይታሰብላቸዋል፡፡

                                           ቅድስት ድንግል ማርያም በቃል  ኪዳኗ አትለየን! 

Jesus.JPG

ዐቢይ ጾም፤ ወደ ትንሣኤ የሚደረግ ጉዞ

 

በዲ/ን ዘላለም ቻላቸው

 

አንድ ሰው ለጉዞ ሲነሣ ወዴት እንደሚሄድ ማወቅ አለበት፡፡ በዐቢይ ጾምም እንዲሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ዐቢይ Jesus.JPGጾም መንፈሳዊ ጉዞ ነው፤ መድረሻውም ትንሣኤ ነው፡፡ ለእውነተኛው መገለጥ ለፋሲካ መሟላት የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ የሆነና ስለ ክርስትና እምነታችንና ሕይወታችን በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ስለሚገልጥልን ይህን በዐቢይ ጾም እና በትንሣኤ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት በመሞከር መጀመር አለብን፡፡

 

የትንሣኤ በዓል ከበዓላት አንዱ ከመሆን እና የአንድ ያለፈ ክስተት መታሰቢያ ከመሆን በላይ ሊታሰብ ያስፈልገዋል፡፡ አንድ ጊዜም ብቻ እንኳን ቢሆን የትንሣኤን በዓል በሚገባው መልኩ አክብሮ በዚያም ከቀን ይልቅ በሚያበራው ሌሊት የተሳተፈና ያንን ልዩ ደስታ የቀመሰ ማንም ሰው ያውቀዋል፡፡ ያ ደስታ ግን ስለ ምንድን ነው? በትንሣኤ በዓል ዕለት እንደምናደርገው «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሀጺባ በደመ ክርስቶስ»፤ «ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ»፣ «ዛሬ ሁሉም ነገር፣ ሰማይም፣ ምድርም፣ ከምድር በታች ያሉ ነገሮችም በብርሃን ተሞሉ» እያልን መዘመር የምንችለው ለምንድነው? «የሞት መሞት፤ የሲኦል መበዝበዝ፣ የአዲስና የዘለዓለማዊ ሕይወት መጀመሪያ…» እያልን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?

 

ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ ይህ ነው፡፡ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ከመቃብር ወጥቶ ያበራው አዲስ ሕይወት በክርስቶስ ለምናምን ለሁላችንም ተሰጥቶናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ «በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን» /ሮሜ.6:4/ እንዳለው ይህ አዲስ ሕይወት እና ብርሃን ለእኛ የተሰጠን በጥምቀታችን ዕለት ነው፡፡

 

ስለዚህ የትንሣኤን በዓል ስናከብር፣ የክርስቶስን ትንሣኤ በእኛ ላይ እንደ ተደረገ እና አሁንም እንደሚደረግ አድርገን እናከብራለን፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዳችን የዚያን የአዲስ ሕይወት ስጦታ እና ያንን የምንቀበልበት እና በእርሱም የምንኖርበትን ኃይል ተቀብለናል፡፡ ይህ ስጦታ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር ሁሉ ስለ ሞትም ጭምር ያለንን አመለካከት የሚቀይር ነው፡፡ በደስታ «ሞት የለም» ብለን በእርግጠኝነትም መናገር እንድንችል የሚያደርገን ነው፡፡

 

ኦ! ሞት ግን አሁንም አለ፤ በእርግጠኝነት እንጋፈጠዋለን፤ አንድ ቀንም መጥቶ ይወስደናል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በራሱ ሞት፣ የሞትን ባሕርይ /ምንነት/ እንደቀየረው ይህ ሙሉ እምነታችን ነው፤ ሞትን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ፣ ማለፊያ፣ ፋሲካ አድርጎታል፤ ከአሳዛኝ ነገሮች ሁሉ የበለጠ አሳዛኝ የነበ ረውን ሞት ወደ ፍጹም ድልነት ቀይሮታል፡፡ «ሞትን በሞቱ ደምስሶ» የትንሣኤው ተካፋዮች አድርጎናል፡፡ ለዚህም ነው «ክርስቶስ ተነሥቷል፣ ሕይወትም ሆኗል፤ ማንም በመቃብር አይቀርም» የምንለው፡፡

 

ቁጥር በሌላቸው በቅዱሳኖቿ የተረጋገጠውና ግልጽ የተደረገው የቤተክርስቲያን እምነት ይህ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እምነት በእኛ ውስጥ ሁልጊዜ አለመኖሩ [ይህንን ሁል ጊዜ አለማሰባችን]፤ እንዲሁም እንደ ስጦታ የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት ሁልጊዜ መጣላችንና መካዳችን እንዲሁም ክርስቶስ ከሞት እንዳልተነሣ ሆነን የመኖራችን ነገር እና ያ ልዩ ክስተት ለእኛ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለው መሆኑ የዕለት ተዕለት ተሞክሮአችን አይደለምን?

ይህ ሁሉ የሆነው በድካማችን ምክንያት ነው፡፡ ማለትም ጌታ «አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ፈልጉ» ባለን ጊዜ በወሰነልን ደረጃ «በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር» መኖር ለእኛ የማይቻለን በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ በቀላሉ እንረሳዋለን፤ ምክንያቱም ሁልጊዜም በተለያዩ ሥራዎች የተጠመድን እና በዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን የተዋጥን ነን፤ ስለ ምንረሳም እንወድቃለን፤ በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት እና ብርሃንም እንጠራለን፡፡

 

በዚህ በመርሳት፣ በመውደቅ እና ኃጢአት በመሥራት በኩልም ሕይወታችን በድጋሜ «አሮጌ» ይሆናል፤ ጥቅም /ረብ/ የሌለው፤ ጨለማ እና ትርጉም አልባ፤ ትርጉም የሌለው ጉዞ፤ ትርጉም ወደሌለው ፍጻሜ ይሆናል፡፡

ሞትን እንኳን ሳይቀር ረስተነው ከቆየን በኋላ በድንገት «ደስታ በሞላበት ሕይወታችን» መሐል አስፈሪ፣ ሊያመልጡት የማይችሉት እና አስጨናቂ ሆኖ ወደ እኛ ይመጣል፡፡

በየጊዜው ኃጢአታችንን ልንናዘዝ እንችላለን፤ ነገር ግን ሕይወታችንን ከዚያ ክርስቶስ ለእኛ ከገለጠውና ከሰጠው ከአዲሱ ሕይወት ጋር ማዛመድና ሕይወታችንን በዚያ ላይ መመሥረት እናቆማለን፡፡ ትልቁና እውነተኛው ኃጢአት፣ የኃጢአቶች ሁሉ ኃጢአት፣ የስም ብቻ የሆነው ክርስትናችን በጣም አሳዛኝ ገጽታ ይህ ነው፡፡ የሕይወታችንን ትርጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ አለመመሥረት፡፡

 

ይህንን ልብ ካልን፣ የትንሣኤ በዓል ምን እንደሆነና ዐቢይ ጾም ለምን ከእርሱ በፊት እንዲኖር እንዳስፈለገ እንረዳለን፡፡

በዐቢይ ጾም በቤተክርስቲያን የሚደረገው ሥርዓተ አምልኮ ዓላማም በቀላሉ የምንጥለውንና የምንወስደውን የዚያን የአዲስ ሕይወት ርእይ እና ጣዕም በውስጣችን እንድናድሰው ለመርዳት እና ተጸጽተን ወደ እርሱ እንድንመለስ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የማናውቀውን ነገር እንዴት ልንወድና ልንፈልግ እንችላለን? አይተነው እና አጣጥመነው የማናውቀውን ነገር እንዴት በሕይወታችን ካሉ ነገሮች ሁሉ በላይ ልናደርገው እንችላለን? በአጭሩ ስለ እርሱ ምንም አሳብ የሌለንን መንግሥት እንዴት ልንፈልግ እንችላለን? አንችልም፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን በእነዚህ ሥርዓተ አምልኮዎች ይህን እንድናደርግ ትረዳናለች፡፡

 

በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ወዳለው ሕይወት መግቢያችን፤ ከዚያም ጋር ያለን ኅብረት መሠረት በቤተክርስቲያን ያለው አምልኮ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን «ጆሮ ያልሰማውን፣ ዓይንም ያላየውን በሰው ልብም ያልታሰበውን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት ያዘጋጀውን» ከዚያ ነገር ጥቂቱን ለእኛ የም ትገልጥልን በአምልኮ ሕይወቷ አማካኝነት /through her liturgical life/ ነው፡፡ በዚያ በአምልኮ ሕይወት መሐል ላይ ደግሞ፣ እንደ  ጠቅላላው የአምልኮ ሥርዓት ልብ እና ከፍታ፣ እንዲሁም ጨረሮቿ ሁሉም ቦታ እንደሚደርሰው ፀሐይ ሆኖ የትንሣኤ በዓል ይቆማል፡፡

የትንሣኤ በዓል በየዓመቱ ወደ ክርስቶስ መንግሥት ግርማ እና ውበት ለማሳየት የሚከፈት በር ነው፡፡ የሚጠብቀን ዘለዓለማዊ ደስታ ቅምሻ ነው፡፡ ምንም እንኳን በስውር ቢሆንም ፍጥረትን ሁሉ የሞላው፣ «ሞት የለም!» የሚለው የዚያ ድል ክብር መገለጫ ነው፡፡

 

አጠቃላይ የቤተክርስቲያን የአምልኮ ሕይወት ዓመታዊው የአምልኮ መርኀ ግብር /liturgical year/ የተደራጀው በትንሣኤ ዙሪያ ነው፤ ማለትም በዓመቱ በተከታታይ የሚመጡት ወቅቶች እና በዓላት ወደ ፋሲካ፣ ወደ ፍጻሜው የሚደረጉ ጉዞዎች ይሆናሉ፡፡ ፋሲካ ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ጅማሬም ነው፤ «አሮጌ» የሆነው ነገር ሁሉ ፍጻሜ እና የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ፤ ከዚህ ዓለም በክርስቶስ ወደ ተገለጠው መንግሥት መሸጋገሪያ ነው፡፡

 

ይሁን እንጂ የኃጢአት እና የማይረቡ ነገሮች መንገድ የሆነው «አሮጌው» ሕይወት ግን በቀላሉ የሚሸነፍ እና የሚቀየር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ አሁን ባለበት ሁኔታ ሊፈጽመው የማይችለውን ነገር የወንጌል ሕግ ትጠብቅበታለች፡፡ ከአቅማችን እና ከምንችለው እጅግ በጣም በሚበልጥ ርእይ፣ ግብ እና የሕይወት መንገድ እንፈተናለን ምክንያቱም ሐዋርያት እንኳን ሳይቀሩ የጌታን ትምህርት ሲሰሙ ተስፋ በመቁረጥ «ይህ እንዴት ይቻላል?» ብለው ጠይቀውታል፡፡ በእርግጥም በየዕለቱ በሚያስፈልጉን ነገሮች በመጨነቅ፣ ቀላል ነገሮችን፣ ዋስትናን እና ደስታን በመፈለግ የተሞላን የማይረባ የሕይወት እሳቤ ትቶ «ሰማያዊ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ» የተባለለትንና ከፍጽምና በቀር ሌላ ምንም ግቡ ያልሆነውን የሕይወት እሳቤ መያዝ ቀላል አይደለም፡፡

 

ዓለም በመገናኛ ብዙኃኖቿ በሙሉ «ተደሰቱ፣ ቀለል አድርጋችሁ እዩት /take it easy/፣ ሰፊውን መንገድ ተከተሉ» ትለናለች፡፡ ክርስቶስ ደግሞ በወንጌል «ጠባቡን መንገድ ምረጡ፣ ተዋጉና መከራን ተቀበሉ፤ ይህ ወደ እውነተኛው ደስታ የሚያደርስ ብቸኛው መንገድ ነውና» ይለናል፡፡ ቤተክርስቲያን ካልረዳችን ካልደገፈችን እንዴት ያንን አስጨናቂ ምርጫ መምረጥ እንችላልን? እንዴትስ መጸጸት /ንስሐ መግባት/ እና በየዓመቱ በትንሣኤ በዓል ዕለት ወደሚሰጠው የከበረ ቃል ኪዳን መመለስ እንችላለን? የዐቢይ ጾም አስፈላጊነቱ እዚህ ላይ ነው ይህ በቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀልን ዕርዳታ፣ የትንሣኤ በዓልን የመብላት የመጠጣት እና የመዝናናት ፈቃድ የሚገኝበት ዕለት ነው ብለን ሳይሆን፣ በውስጣችን ያለው የአሮጌው መጨረሻ እና የእኛ ወደ አዲሱ መግቢያ አድርገን እንድንቀበለው የሚያስችለን የንስሐ ትምህርት ቤት ነው፡፡

 

በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾም ዋና ዓላማ ንኡሰ ክርስቲያንን ማለትም አዳዲስ አማንያንን በዚያን ጊዜ በትንሣኤ ዕለት ለሚፈጸመው ጥምቀት ማዘጋጀት ነበር፡፡ ነገር ግን /ክርስትና ከተስፋፋና/ የሚጠመቁ ሰዎች ቁጥር ከቀነሰ በኋላም ግን ቢሆን የዐቢይ ጾም መሠረታዊ ትርጉም በዚያው ጸንቷል፡፡ ስለዚህም ትንሣኤ በየዓመቱ ወደ ጥምቀታችን መመለሻ ሲሆን ዐቢይ ጾም ደግሞ ለመመለስ መዘጋጃችን ነው፤ በክርስቶስ ወደሆነው አዲስ ሕይወት ለመተላለፍ የምናደርገው ትጋትና ጥረታችን ነው፡፡

 

ዐቢይ ጾም ጉዞ ነው፤ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ ገና ስንጀምረው፣ በዐቢይ ጾም ብሩህ ሐዘን /bright sadness/ ውስጥ የመጀመሪያውን እርምጃ ስንራመድ ከር. . . ቀት ፍጻሜውን /መጨረሻውን/ እናያለን፡፡ ይህም የትንሣኤ በዓል ደስታ ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ክብር መግባት ነው፡፡ የዐቢይ ጾምን ሐዘን ብሩህ የሚያደርገውና በወቅቱ የምናደርገውን ጥረት «መንፈሳዊ ምንጭ» የሚያደርገውም ይህ የትንሣኤ በዓል ቅምሻ የሆነው ብሩህ ርእይ ነው፡፡

ሌሊቱ ጨለማ እና ረጅም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በመንገዱ ሁሉ ምስጢራዊ የሆነ ብሩህ ወገግታ በአድማሱ ላይ ያንፀባርቃል፡፡«ሰውን ወዳጅ /መፍቀሬ ሰብእ/ ሆይ! አቤቱ ተስፋ ያደረግነውን ነገር አታስቀርብን» አሜን፡፡

 

ምንጭ፡- [The Lent, Father Alexander Schemaman, St. vladmir’s Seminary Press,].

ሐመር መጋቢት 2002