ፍቅር ግን እርሱ ነው!

መንበረ ዓባይነህ

ኅዳር ፳፮፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ፍቅርህ ይለያል…
በሰው ልጅ አእምሮስ እንዴት ይታሰባል?

ፍቅር ግን ምንድነው? ብዬ ስጠይቀው
ሁሉም ሊያብራራልኝ ሊገልጸው አቃተው!
ፍቅር ግን እርሱ ነው
ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወሰብእ የሆነው
ራሱን በመስቀል ለእኛ ሲል የሰዋው!

እንዴት ያለ ፍቅር!
እንዴት ያለ መውደድ!
ለሞት ተዘጋጅቶ የአምላክ መወለድ።

መንክር ብል ይደንቃል!
ዕፁብ ብል ይገርማል!
የአምላካችን ፍቅር እጅግ ያስደምማል!

እንዲህ ያለ ፍቅር
እንዲህ ያለ መውደድ
ምነው ቢገባው የዚህ ዘመን ትውልድ!

ሲዘልፉት ዝም ነው
ሲገድሉትም እንዲያው
ሲጠሉት ይወድዳል
ግን እኮ አምላክ ነው ሁሉን ማድረግ ይችላል
እንዲህ ዓይነት አምላክ ከወዴት ይገኛል!

አስተውል ወዳጄ! ያስተውል ልቡናህ!
ይሄ ሁሉ ዋጋ የተከፈለልህ
በመስቀል ተሰቅሎ ፍቅሩን የሰዋልህ
ለአንተው ነፃነት ነው ስለ አንተ የሞተልህ!
በመስቀል ተሰቅሎ ሕይወት የሰጠህ!