‹‹የእግዚአብሔር ሰው›› (፩ኛሳሙ.፱፥፮)

ክፍል ሦስት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ኅዳር ፳፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ሐሰተኞች ነቢያት በየዘመናቱ ነበሩ፡፡ በራሳቸው በነቢያት ዘመንም፣ በሐዋርያት ዘመንም ዛሬም በዘመናችን ሐሰተኞች ነቢያት አሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን በርካቶች ዐውቀው ለገንዘብ ብለው የሐሰት ትንቢት ይናገሩ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ተሳስተው፥ ከራሳቸው ከልባቸው አንቅተው ከራሳቸው የልብ አሳብ ይናገሩ ነበር፡፡ በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ‹‹ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡-ፈጽሞ ሳያዩ ከገዛ ልባቸው አንቅተው ትንቢት ለሚናገሩ ወዮላቸው›› የሚል ቃል አለ፡፡ (ሕዝ.፲፫፥፪)

ሌሎቹ ደግሞ በክፉ መንፈስ ተመርተው ትንቢት የሚናገሩ ናቸው፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ነቢዩ ሚክያስ ከእግዚአብሔር የተነገረውን የትንቢት ቃል ለንጉሡ ለአክዓብ ሁልጊዜ ይነግረውና ያስጠነቅቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን የነቢዩን ትንቢት እውነት በመሆኑ ለመቀበልም ስለሚያዳግተው እርሱ የሚፈልገውን በጎ ነገር ብቻ በትንቢት መልክ እንዲነግረው ይሻ ነበር፡፡

አንድ ቀን የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከጦር መሪዎቻቸው ጋር በአደባባይ ተቀምጠው ሳለ ነቢያቱ ሁሉ የሐሰት ትንቢት ይናገሩ ነበር፡፡ እነዚያ የንጉሥ አሸርጋጅ የሐሰት ነቢያት ንጉሡን የሚመክሩት ወደ ሬማት ዘገልአድ እንዲዘምት ሶርያውያንንም እንዲወጋቸው፣ እግዚአብሔርም እንደሚረዳው፣ የሶርያውያንንም ንጉሥ እግዚአብሔር አሳልፎ በእጁ እንደሚሰጠው ወዘተ ንጉሡ የሚሻውን በትንቢት መልክ በጎ በጎውን ይናገሩ ነበር፡፡ ንጉሡም የእግዚአብሔር ነቢይ ሚክያስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ለማወቅ እንዲጠሩት ሰው ላከበት፡፡

መልእክተኛውም ሚክያስን ‹‹እነሆ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካሙን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ›› ይለዋል፡፡ (፩ኛ ነገ.፳፪፥፲፫) ነቢዩ ግን ‹‹ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ›› አለው፡፡ ሚክያስም ለንጉሡ መራራውን እውነት ነገረው፡፡ ሶርያውያንንም እንደማያሸንፍ፥ ይልቁንስ እስራኤላውያን ጠባቂ እንደሌላቸው በተራራ ሲበተኑ ማየቱን፣ እርሱም እንደሚሞት ጭምር ነገረው፡፡ በዘመናችንም ያሉ ነቢያት ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› (ለውጥ) አየን የሚሉ፣ መሪዎችን በሐሰተኛ ትንቢት ጦርነት ታሸንፋለህ የሚሉ፣ መራራውን እውነት ሳይሆን የመሪዎችን የልብ ትርታ በትንቢት መልክ የሚናገሩ፣ እግዚአብሔርን ሳይሆን ሥርዓትን የሚያገለግሉ ለመሆናቸው ሚድያውን የተቆጣጠሩትን ነቢያት ነን ባዮች ቃል በመስማት ለመረዳት አይከብድም፡፡

አክዓብ ግን ኢእዮሣፍጥ ምን አለ? ‹‹ክፉ እንጂ ደግ እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን?›› አለው፡፡ ሚክያስ እንደ ክፉ ተናጋሪ ተቆጥሯል፡፡ ምክንያቱም ንጉሡ የፈለገውን ሳይሆን እግዚአብሔር የነገረውን ተናግሯልና፡፡ ዛሬም በሀገራችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን ጭምር እንደ ሚክያስ እውነቱን ሊመጣ ያለውን ጉዳት፣ እግዚአብሔር ያልወደደውን ሥራ የሚናገሩ እንደ ክፉ ተናጋሪ፣ እንደ ሟርተኛ፣ በጎ በጎ እንደማይታያቸው ጨለምተኞች ይታያሉ፡፡ ነቢዩ ሚክያስ ግን ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የሰማሁት እኔ አይደለሁምን?….በሬማት ዘገልአድ ወጥቶ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው?›› አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ክፉ መንፈስ ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊትም ቆሞ ‹‹እኔ አስተዋለሁ›› አለ፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም በምን ታስተዋለህ?›› ቢለው እርሱም ‹‹ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ›› አለ፡፡

ሚክያስ ግን በንጉሡ ትእዛዝ በጥፊ ተመታ፤ በግዞትም እንዲቀመጥ ተወሰነበት፤ የመከራ እንጀራም መገቡት፤ የመከራ ውኃም እንዲጠጣ ተደረገ፡፡ በዘመናችን ክፉ መንፈስ ወጥቶ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ ሆኗል፡፡ እውነት የሚናገሩ ግን በጥፊም፣ በሰይፍም ይመታሉ፤ በግዞትም ይጣላሉ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ናቸው፤ እውነትን ይናገራሉና፡፡

ነቢይ ሐሰተኛ ነው የሚባለው ምን ሲሆን ነው? ለሚለው በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጡ ምክንያቶች ጥቂቶቹን ለማንሣት እንሞክር፡፡

ንደኛ ቃሉ ሳይፈጸም ሲቀር ነው፡፡ ቀደም ሲል በጠቀሰነው በአክዓብና በነቢዩ ሚክያስ ታሪክ ውስጥ ነቢያተ ሐሰት አክዓብን ዝመት ሶርያውያንን ታሸንፋለህ፤ ንጉሡንም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል ወዘተ የሚል ትንቢት ነግረውት ነበር፡፡ ነገር ግን ሐሰተኛ የቤተ መንግሥት ቅልብ ነቢያት ያሉትን ትንቢት ሰምቶ ሚክያስን ወደ ግዞት ልኮ ለጦርነት የሄደው አክዓብ በሳንባውና በደረቱ መካከል በጦር ተወግቶ፣ ደሙም በከንቱ ፈሶ ሞተ፡፡ (፩ኛ ነገ.፳፪፥፴፬፤ ፪ኛዜ.መ ፲፰፥፳፰-፴፬) እግዚአብሔር ለነቢዩ ሙሴ ‹‹ያ ነቢይ በእግዚአብሔር ስም ከተናገረው ባይደርስ፣ እንደተናገረውም ባይሆን እግዚአብሔር ያን ቃል አልተናገረውም፤ ነቢዩ በሐሰት ተናግሮታልና አትስማው›› ብሎታል፡፡ (ዘዳ.፲፰፥፳፪)

ሁለተኛ ባዕድ አምልኮትን ሲከተል ነው፡፡ በባዕድ አምልኮ የሚኖሩ ነገር ግን “ትንቢት እንናገራለን፤ ራእይ እናያለን፤ ተአምራት እናደርጋለን” የሚሉ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት በየዘመናቱ አሉ፡፡ ምልክትም ተአምራትም ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተአምራት ቢፈጽሙም እንኳን ለፈተና በመሆኑ ከእግዚአብሔር ቃል እንዳንወጣ፣ በአምልኮአቸውም እንዳንከተላቸው የዚያን ሕልም አላሚ ወይም ነቢይ ቃል እንዳንሰማ በሙሴ አማካኝነት ተነግሮናል፡፡ (ዘዳ.፲፫፥፩-፬)

ሦስተኛ አካሄዱ ክፉ ሲሆን ነው፡፡ ስለ እነዚህ የሐሰት ነቢያት ደግሞ ኤርምያስ ሲናገር ‹‹ስለ ነቢያት ልቤ በውስጤ ተሰብሯል፤ አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ከጌትነቱም ክብር የተነሣ እኔም በመከራ እንደተቀጠቀጠ ሰው፣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈውም እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ፡፡ ዝሙታቸው ምድርን ሞልቷልና፤….ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋል፤ በቤቴ ውስጥ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ ይላል እግዚአብሔር›› ይላል፡፡ (ኤር.፳፫፥፱) በእውነቱ ይህ ቃለ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በእኛ ዘመን አስኪመስል ድረስ ያስደንቀናል፡፡ በተአምራት ስም፣ በትንቢት መናገር ሰበብ፣ በፈውስና በራእይ ሽፋን እንዴት ምድራችን በክፉ ሥራ እንደ ተሞላች ያስረዳናል፡፡ በርካቶች ተአምራትና ፈውስ ፍለጋ፣ ያልደከሙበትን ሀብት ለማግኘት ሲሉ በአምልኮ ስም በዝሙት ረክሰዋል፤ አካሄዳቸው ክፉ በሆኑ ነቢያተ ሐሰት፣ ካህናተ ሐሰት ሕይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡ ከዚህ የተነሣ የእውነተኞችን ልብ የሚሰብር ርኩሰት በየቀኑ እንሰማለን፡፡

አራተኛ ኀጢአት በበዛ ጊዜ ስለ ፍርድ ሳይሆን ስለ ሰላም ሲተነብይ ነው፡፡ ይህንንም ሐሳብ በትንቢተ ኤርምያስ የትንቢት ቃል እንመለከተዋለን፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ በምድር ላይ ኀጢአት ሞልቶ ሲፈስ፣ ስለ መለኮታዊ ፍርድ መናገር ሲገባቸው፣ ስለ ንስሓ መስበክ ትተው፣ በከንቱ ሰላም ሳይሆን ሰላምን የሚሰብኩትን ሐሰተኞች ነቢያት ቃላቸውን እንዳንሰማ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ትንቢት የተናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሯችኋል፡፡ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣን ራእይ ይናገራሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ለሚያቃልሉ ሰላም ይሆንላችኋል፤ በፍላጎታቸውና በልቡናቸው ክፋት ለሚሄዱም ሁሉ ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ›› በማለት ይነግረናል፡፡ (ኤር፳፫፥፲፮) ትልቁ የትውልዳችን ፈተና ይህ ነው፡፡ ሰላም ሳይኖር ሰላም ነው የሚሉ፣ ሰው ራሱን እንዳያይ፣ በንስሓ እንዳይመለስ፣ ኀጢአቱን እየዘከረ እንዳይጸጸት፣ የአምላኩን ዳግም መምጣት፣ የእርሱን ለፍርድ መቅረብ እንዳያስብ፣ አስቦም እንዳይዘጋጅ ድነሃል፤ ዋጋ ተከፍሎልሃል፤ ፍርድ የለብህም እያለ ኀጢአትን የሚያደፋፍር የንስሓን ዋጋ ያቃለለ፣ ክፉ ትምህርት ምድሪቱን ሞልቷታል፡፡

እንደ ሀገርና እንደ ቤተ ክርስቲያንም ችግሩ ሰፊ ነው፡፡ በእነዚህ ሐሰተኛ ነቢያት ትንቢት ልምምድ ውስጥ እንድንኖር አድርጎናል፡፡ ሰላም ሳይሆን ሰላም ነው እንላለን፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ማንሳት ጊዜ ይገድበናል፡፡ በተጨማሪም በትንቢት ስም፣ በራእይ ስም ትውልዱ ተዘክሮተ ሞትን እንዴት እንደዘነጋ ለብዙዎቻችን የተሰወረ አይደለምና፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ግን አስቀድማ ታስጠነቅቀናለች፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት እንደሚነሡ፣ ብዙዎችንም እንደሚያስቱ ከአምላኳ የተነገራትን የወንጌል ቃል ነግራናለች፡፡ የሐሰተኞች ነቢያትን ሥራ የሚሠሩ አሁን በቤተ ክርስቲያናችንም ውስጥ አሉ፡፡ ብዙዎችንም ከእውነት ፈቀቅ እንዲሉ ከወንጌል ቃል ይልቅ አጋንንታዊ ትምህርታቸውን እንዲሰሙ፣ ከጌታ ይልቅ እነርሱን እንዲከተሉ ያደረጉ፣ ከእውነተኛው አምልኮ ወደ አጋንንታዊ አምልኮ የወሰዱ፣ ባሕታዊ ነኝ፤ አጥማቂ ነኝ፤ መምህር ነኝ፤ አዋቂ ነኝ የሚሉ ብዙ ክፉና ሐሰተኞች በመካከላችን አሉና እንጠንቀቅ፡፡

በመጨረሻም እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አድሮ ‹‹የሐሰት ነቢያቶቻችሁንና ሟርተኞቻችሁን፣ሕልም አላሚዎቻችሁንና ባለ ራእዮቻችሁን መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤ ከምድራችሁ እንዳያርቋችሁ፤ እኔም እንዳላሳድዳችሁ እናንተም እንዳትጠፉ›› ሲል ባስጠነቀቀን ቃል እንጨርስ፡፡(ኤር.፳፯፥፱)

ከምድራችን፣ ከርስታችን ከቤተ እግዚአብሔር እንድም ከሰማያዊቷ ርስታችን እንዳያርቁን፣ እርሱም እንዳያሳድደን፣ እኛም እንዳንጠፋ ከሐሰተኞች ነቢያት እንጠበቅ፡፡ እርሱም ይጠብቀን፤ አሜን!!!