ፈቃደ እግዚአብሔር

የካቲት ፳፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በሰዎች ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔር ክቡር ፍቃድ አለ፤ እነዚህም ሁለት ፍቃዳት ናቸው፡፡ አንደኛው ግልጽ ፈቃድ ሲባል ሁለተኛው ደግሞ ስውር ፈቃድ ይባላል፡፡ ግልጽ ፍቃዳት የሚባሉት በመጽሐፍ ተጽፈው የምናነባቸው ናቸው፤ በሕግ መልክ በብሉይ እና በሐዲስ ኪዳን የተቀመጡልን ትእዛዛቱ እንድንሰማቸው፣ እንድንማራቸው፣ እንድንኖራቸው የተሰጡትን ነው፡፡ መጽናናትን፣መረጋጋትን ገንዘብ የምንዳርባቸው፣ ተግሣጽንና ምክርን የምንሸምትባቸው ገባያችን ናቸው፡፡

በነቢያትና የሐዋርያት የገለጻቸው፣ በሊቃውንት የገለጣቸው፣ ተነበው የተተረጎሙና የተመሰጠሩ፣ ተዘጋጅተው ዕለት ዕለት ለእኛ የሚቀርቡ መርሖችም እንዲሁም በዓለም ላይ የምንኖረውንና የሚመጣውን ነገር ሁሉ መለኪዎያቻችንና መመዘኛዎቻችን ናቸው፡፡ ምክንያቱም ያለ እነዚያ መለኪያ ሕይወታችን ሙሉ አይሆንም፡፡

ሕግጋተ እግዚአብሔር

፩. ሕገ ልቦና (የኅሊና ሕግ)

፪. ዐሠርቱ ቃላት፣ ዐሠርቱ ትእዛዛት፣ ዐሠርቱ ሕግጋት፣ ሕገ መጽሐፍ (ሕገ ኦሪት)

፫. ስድስቱ ሕግጋት፣ ስድስቱ ትእዛዘት፣ ስድስቱ ቃላተ ወንጌል:-

፬. ዐሥሩ አንቀጸ ብፁዓን

እግዚአብሔር አምላክ ፈጣሪ እንደመሆኑ ፈቃዱ የማይለወጥ ቀዋሚ ስለሆነ ጊዜያዊና ቅጽበታዊ ፍጥረት አልፈጠረም። ፈጥሮም ያለዓላማ። ያለሕግ ያለሥርዓት አልተወም።

በዓለሙ ሙሉ የሆነ እግዚአብሔር ሕግጋቱም ሁሉን የሚመለከትና ለዓለሙ ሁሉ ቀዋሚ የሆኑ ሕግጋት ናቸው። እነዚህም:- ሕገ ልቦና (የኅሊና ሕግ) ዐሠርቱ ቃላትና ስድስቱ ቃላተ ወንጌል ናቸው።

፩. ሕገ ልቦና (የኅሊና ሕግ):-

በሰው ልቦና አንድ ጊዜ ከተጻፈ ሳያረጅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የሚኖር ሕግ ነው። ሕገ ልቦና በሰው ሁሉ ልብ የሚገኝ እያንዳንዱን ሰው ማንም ሳያስተምረው ክፉውንና ደጉን ለይቶ ሳይነግሩት እንዲያውቅ የሚያደርገው ነው። እውነተኛ ሰው ምንም ባይማር በዚህ በሕገ ልቦና ወይም በሕገ ተፈጥሮ መሠረት እውነትን ከሐሰት ጽድቅን ከኃጢአት ደጉን ከክፉ ለይቶ ያውቃል። ከዚህም የተነሣ እውነቱን ይናገራል፤ ይሠራል፤ ከክፉም ይርቃል።

ስለ ሕገ ተፈጥሮ (ሕገ ልቦና) ቅዱሳት መጽሐፍት በተለያየ መንገድ ይመሠክራሉ።

ስለዚህም ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ:- እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና። ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል። በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና።

ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና እነርሱም ኅሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ። (ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕ. ፪÷፲፩-፲፭)

ሕገ ልቦና የተባለው ያን ጊዜ በተፈጥሮ እንደተሰጠ ያለ የጸናም ሕግ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በሕገ ልቦና ብቻ ሊጠበቅ ባለመቻሉ በግድ የጹሑፍ ሕግ አስፈለገ። ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ በእጁ ጽፎ ሌላ ሕግን በሙሴ አማካይነት ለጊዜው ለእሥራኤል ወገን ፍጻሜው ግን ለሰው ልጅ ሁሉ ሰጥቷል። ቀጥሎም የጌታ ደቀ መዛሙርት ሐዲሱን የኪዳን ሕግ (ስድስቱን ቃላት ወንጌል) በጹሑፍ አበርክተዋል።

፪. ዐሠርቱ ቃላት፣ ዐሠርቱ ትእዛዛት፣ ዐሠርቱ ሕግጋትሕገ መጽሐፍ (ሕገ ኦሪት):-

እግዚአብሔር አምላክ ግንኙነቱን ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በማድረግ መገናኛ ይሆኑ ዘንድ የሠራቸውና የደነገጋቸው ሲሆኑ በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፉ ዐሠርቱ ቃላት እየተባሉ የሚጠሩ ናቸው። እነዚህም እግዚአብሔር በሁለት ሠሌዳ ጽፎ ለእስራኤል ያስተላለፈው ሕግ ነው።

ሁለቱ የሕግ ጽላት የዐሥርቱ ቃላት ማደሪያ ሠሌዳ ሁነው የተሰጡ ናቸው። እንደ ሊቃውንቱ አስተያየት በአንደኛው ጽላት ሦስት ቃላት እግዚአብሔር ወይም እግዚአብሔር አምላክን የሚመለከቱ ለእርሱ ልናደርግና ልንፈጽመው የሚገባንን የሚገልጡ ናቸው። በሁለተኛው ጽላት ደግሞ ሰባት አንቀጾች ተጽፈውበታል: ይኸውም ሰውን የሚመለከቱ ማለት ነው። ሰው አንዱ ለሌላው ሊያደርገውና ሊፈጽመው የሚገባውን የሚያሳዩ ዐሠርቱ ቃላት በመጀመሪያ ለሰው መመሪያ እንዲሆኑ በጽሑፍ የተላለፉ ሕግጋት ናቸው።

ምክንያቱም የሰው ልጅ በመጀመሪያ በሕገ ልቦና እንዲሁም በሕገ ኅሊና በሕግ ሊጸና ለእግዚአብሔርም ሊታዘዝ ተፈጥሮ ነበር። ይህ ግን ባለመቻሉ በጧትና በማታ እያነበበ እያየም ሰው የሆነ ሁሉ እንዲጠብቀውና እንዲፈጽመው እግዚአብሔር አምላክ ስለፈቀደ ሕጉን በጽሑፍ ሰጠው እነዚህ በጽሑፍ የተላለፉ የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ለክርስቲያኑ ሕዝብ አሁንም አስፈላጊዎች ናቸው።

ከዐሠርቱ ቃላት ዘጠኙ ተጠብቀው አንደኛው እንኳን ከፈረሠ ዐሠርቱ ሕግጋት ሁሉ እንደፈረሱ ይገመታል እንጂ የዘጠኙ መጠበቅ ምንም ዋጋ የለውም። ለምሳሌ ዐሥር በር ያለው ቤት ቢኖር ዘጠኙ በሮች ቢዘጉና አንዱ ክፍቱን ቢያድር ሌባ ክፍት በሆነው በአንደኛው በር ገብቶ ንብረቱን ሁሉ ከወሰደው የዘጠኙ በሮች መዘጋት ምንም ጥቅም አላስገኘም ማለት ነው።

የአንደኛው መከፈት ለንብረቱ መጥፋት ምክንያት ሆኗልና። ዐሠርቱ ቃላትም በትክክል ካልተጠበቁ ዋጋ የማያሰጡ መሆናቸውን ሐዋርያው ያዕቆብ እንዲህ ሲል ያስረዳል፤ ‹‹ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ አትግደል ብሎአልና፡፡›› (የያዕቆብ መልእክት ፪፥፲)

ዐሥርቱ ትእዛዛት እነማን ናቸው?

አንቀጽ አንድ

‹‹ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።›› (ኦሪት ዘፀአት ፳፥፫)

አንቀጽ ሁለት

‹‹የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።›› (ኦሪት ዘፀአት ፳፥፯)

አንቀጽ ሦስት

‹‹የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።›› (ኦሪት ዘፀአት ፳፥፰)

አንቀጽ ዐራት

‹‹አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።›› (ኦሪት ዘፀአት ፳፥፲፪)

አንቀጽ አምስት

‹‹አትግደል!›› (ኦሪት ዘፀአት ምዕ. ፳፥፲፫)

አንቀጽ ስድስት

‹‹አታመንዝር!›› (ኦሪት ዘፀአት ምዕ. ፳፥፲፬)

አንቀጽ ሰባት

‹‹አትስረቅ!››  (ኦሪት ዘፀአት ምዕ. ፳፥፲፭)

አንቀጽ ስምንት

‹‹በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር!›› (ኦሪት ዘፀአት ምዕ. 20:16)

አንቀጽ ዘጠኝ

‹‹የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።›› (ኦሪት ዘጸአት ምዕ. ፳፥፲፯)

አንቀጽ ዐሥር

‹‹ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ›› (ኦሪት ዘሌዋውያን ፲፱፥፲፰)

፫….ስድስቱ ሕግጋት (ትእዛዘተ) ወንጌል:-

በብሉይ ኪዳን እምነት ሥርዓት ሕግን እንደፈጸመ የሚቆጠረው ፍጹምም አይሁዳዊ ነው የሚባለው ዐሠርቱ ቃላተ ኦሪትን የጠበቀው ነበር። በሐዲስ ኪዳንም ዐሠርቱ ቃላት ኦሪት ምንም ሳይነኩ እንደተጠበቁ ሆነው በተጨማሪ ሌሎችም አዲሶች ሕጎች አስፈለጉ። ዐሠርቱ ቃላተ ኦሪት መጠበቃቸውንና እንዳሉም መጽናታቸውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። (የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. ፭፥፲፯-፲፰) ሲል ግልጽ አድርጎ ተናግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ ግን እነዚህኑ ዐሠርቱ ቃላትን በስድስቱ አንቀጽ አጠቃሎና አሳጥሮ ቃላተ ወንጌል ወይም ትእዛዛተ ወንጌል ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ግን እላችኋለሁ እያለ አጥብቆ አጽንቶና ወስኖ ተናግሮ ይገኛል።

አሁንም የሐዲስ ኪዳንን ሕግጋት ስናቀርብ እነዚህ የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ለሐዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ሆነው አጥረውና ተጠቃልለው በስድስት ቃላት ይቅረቡ እንጂ አሁንም መሠረቶቹ ዐሠርቱ ቃላት ናቸው።

ሆኖም አጥረው ተጠቃለው ከበድም ብለው ለሐዲስ ኪዳን መታወቂያ መለያም ሕግ ሆነው የቀረቡ ሲሆን እነዚህን ሕግጋት ለይቶ ጠንቅቆ ማወቅና መጠቀም በጣም አስፈላጊ በመሆኑ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል:-

አንቀጽ አንድ

አትግደል ላለው ‹‹ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል።››

‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።›› (የማቴዎስ ወንጌል ፭፥፳፩÷፳፪)

አንቀጽ ሁለት

አታመንዝር ላለው

‹‹አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል።››

‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።››(የማቴዎስ ወንጌል ፭፥፳፯÷፳፰)

አንቀጽ ሦስት

መፍታት እንደማይገባ

‹‹ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።›› (የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. ፭፥፴፩÷፴፪)

አንቀጽ ዐራት

‹‹ፈጽመህ አትማል ላለው ደግሞ ለቀደሙት። በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ። ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው።›› (የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. ፭፥፴፫-፴፯)

አንቀጽ አምስት

‹‹ክፉውን በክፉ አትቃወሙዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፡፡›› (የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. ፭፥፴፰-፴፱)

አንቀጽ ስድስት

ጠላትህን ስለመውደድ

‹‹ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።
፤የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።››
(የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. ፭፥፵፫-፵፰)

፬. ሥሩ አንቀጸ ብፁዓን

ስድስቱ ቃላተ ወንጌል የዐሥርቱ ቃላት ኦሪት መጠበቂያና ማጠረያ እንደሆኑ አንድም ዐሠርቱ ቃላት በስድስት ቃላተ ወንጌል እንደጸኑ ስድስቱ ቃላተ ወንጌል ደግሞ ዐሥሩ አንቀጸ ብፁዓን ይታጠራሉ፤ ይጸናሉ፤ ፍጹምነታቸው እንዲታወቅ ይሆናል።

እነዚህ ዐሥሩ አንቀጸ ብፁዓን የሕግ ፈጻሚነት ምልክትና የፍጹምነት መታወቂያ ትሩፋት ናቸው እንጂ ሕግጋት አይደሉም። እነዚህ የፍጹምነት የብፅዕናና የቅድስና መታወቂያ አንቀጾች ጌታ የተናገራቸው ሲሆኑ የፍጹምነት ማዕረግ የሚሰጡ ናቸው።

ሙሴ ዘጠኙን ሕግጋት በኦሪት ዘፀአት ፳፥፲፯ ተናግሮ ዐሥረኛውን በኦሪት ዘሌዋውያን ፲፱፥፲፰ እንዳመጣው ጌታም የተናገረውን ዐሥሩን አንቀጸ ብፁዓን ዘጠኙን በማቴዎስ ወንጌል ተናግሮ ዐሥረኛውን በዮሐንስ ወንጌል ያመጣዋል። ይህም የመጨረሻው የብፅዕና አንቀጽ ትሕትና ነው።

ሁለተኛው ስውር የእግዚአብሔር ፍቃዳት ደግሞ ሲከናውኑና የምንመለከታቸው ቀደም ሲል ይልተጻፉ፣ ያልተመለከትናቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ፍቃዳት በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚሰጡ የእግዚአብሔር ስጦታዎች እና በቅዱሳን ጻድቃን እንዲሁም ሰማዕታት ተጋድሎ ውስጥ የሚገለጡ ገቢረ ተአምራት ናቸው፡፡ ለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረባቸው ፴፫ (ሠላሳ ሦስት ዓመታት) በእምነታቸው ኃይልና በሃይማኖታቸው ጽናት ለሰዎች ያደረገው ሲሆኑ እንዲሁም ደግሞ ነገረ ድኅነትን ፈጽሞ ካረገ በኋላ በሐዋርያት፣ በጻድቃን በሰማዕታት እና በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባሉ ሁሉ ያደረገው ፈቃድ ናቸው፡፡ ለዚህም ምሳሌ የሚደረጉ ታሪኮች በቀዳሚነት የተመዘገቡት በመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በሌሎች ቅዱሳት መጽሐፍት እንደ መጽሐፈ ስንክሳር፣ ገድላት እና የዝክረ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተመዝግበው እናገኛቸዋለን፡፡ ስለዚህም ከእነዚህ ታሪኮች የእግዙአብሔርን ፈቃድ ተረድተን በእርሱም ትእዛዛቱ ልንኖር ይገባል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራቸው ሕግጋት እንድንፈጽም ይርዳን! የእናቱ ምልጃ የመላእክትና የቅዱሳን ሰዎች ፈጣን ተራዳይነት ከኛ ከወዳጆቻቸው ጋር ፀንቶ ይኑር። ለዘላለሙ አሜን!

(ምንጭነገረ ምጽአት በአባ ወልደ ዮሐንስ ልደ ኢየሱስ) ከሚል መጽሐፍ በከፊል የተወሰደና ፹፩ አሐዱ መጽሐፍት የተወሰደ)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር፤ አሜን!