የዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

 

የተከበራችሁ አንባብያን በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታና በየአካባቢው እና በየክልሉ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ክፍል አንድና ሁለትን  ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወቃል፡ ፡ከፍል ሦስት እነሆ ብለናል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የተነሡ አካላት ለጥፋታቸው የሚጠቅሱትን የፈጠራ ታሪክ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ልደት እስከ አሁን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በመጠኑ አሳይተናል፡፡ የገጠማትን ፈተና፣ ሊወጓት የመጡትን ያለዘበችበትን መንፈሳዊ ጥበብ ባለፈው ዝግጅት አቅርበናል፡፡ በተለይ ከ፲፱፻፹፫ ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋትና የመንግሥት አካላትን ምላሽ ፍርድ ቤትን ጨምሮ ማቅረብ ጀምረናል፡፡ ባለፈው የጀመርነውን ቤተ ክርስቲያንን የማቃጠል ጥፋት መረጃዎችን በመጨመር ወደ ቀጣዩ እናልፋለን፡፡

በየቦታው ቤተ ክርስቲያን ትቃጠላለች፡፡ መቃጠሉ በዓላማ መሆኑ የሚታወቀው አሻራው እንዳይገኝ ወዲያውኑ የሌላ ዕምነት ቤት፣ የሌላ ዕምነት ቤት አዳራሽና ሌላም እንዲሠራበት መደረጉ ነው፡፡ «በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያኖች ተቃጥለው ወደ መስጊድነት የተቀየሩ መሆናቸውን የአካባቢው ምዕመናን ይህ እኮ ቤተ ክርስቲያን የነበረበት ነው» እያሉ ቦታውን የሚያመለክቱት በቁጭት ነው፡፡ የሚፈጸመው ጥፋት የራስን ዓላማ ለማሳካት የሌላውን መብት መጋፋት ትክክለኛ ተደርጐ ሲፈጸም እየታየ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ዓላማን ማሳካት አንድ ነገር ነው፡፡ የሌላውን መብት እየተጋፉ ዓላማን ማሳካት ግን ተገቢነት የሌለው ነው፡፡ የሌላውን ተደራጅቶ ማጥፋት በጥንታዊት ማሌ፣ በሴኔጋል፣ በጥንታዊት ግብፅና ሜርዋ፣ በርበሮችና አክራሪዎች ነባር የሥልጣኔ አሻራዎችን ማጥፋታቸውን አስታውሰን ነቅተን እንድንጠብቅ ያደርገናል፡፡ ነባሮቹና ተረጋግተው በመኖር ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች በዕምነታቸው ስም ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን የሚፈፅሙ ወገኖቻቸውን ማስታገስ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥትም ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጐ ሳይመለከት ሌሎችን የሚያስተምር ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡

በዚህ ሀገር እስላሙም፣ ክርስቲያኑም፣ ፕሮቴስታንቱም የመኖር መብት አለው፡፡ አንዱ ገፊ ሌላው ተገፊ፣ አንዱ ባለ አገር ሌላው አገር የሌለው መምሰል የለበትም፡፡ ይህ ሃይማኖት የእነ እገሌ ነው ያንተ ሃይማኖት ይህ ነው ማለትም ፖለቲካ እንጂ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ሃይማኖት የሚሰበከው የሃይማኖት ትምህርት ባላቸው ወገኖች እንጂ፣ የፖለቲካ ዓላማ ባላቸው  የጥፋት ኃይሎች አይደለም፡፡ የምናመልከውን በሚመርጡልን ወገኖች ሃይማኖተኛ መሆን የለብንም፡፡ ሰሞኑን በሊሙ ኮሳ በዕምነታቸው ሽፋን አክራሪነትን የሚያራምዱ ሰዎችና ቡድኖች ክርስቲያኖችን ከማጥፋት አልፈው ‹‹ክርስትና የአማራ ነው የኦሮሞ ክርስቲያን የለውም›› በማለት ይቀሰቅሱ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ የኦሮሞ ክርስቲያን እንዳይኖር ከክርስትና ውጪ ሌሎች የኦሮሞ ሃይማኖት እንዲኖር የፈቀደው ማን ነው? አክራሪነት ሥሩ የት ሆኖ ነው የኦሮሞ ሃይማኖት መስሎ የሚሰበከው፡፡ ይህ አብረን እንዳንኖር የሚያደርግ ተባብሮ ለማጥፋት የተደረገ ሴራ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ የሚያምነው ሃይማኖት መምረጥ ያለበት ራሱ ምእመኑ እንጂ በኋላቸው ፖለቲካ አንግበው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ወገኖች መሆን የለባቸውም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ይህን የሚለው ሰላም የሚገኘው ሰላማውያንን በመግፋት ባለመሆኑ የበለጠ ጥፋት እንዳይፈጠር ነው፡፡ ይህ የእኔ ነው አትድረሱብኝ ማለትና ነባር ገዳማት ያለባቸውን ሁሉ ይጥፉ ማለት ሰላም አያመጣም፡፡

በጀጁ ወረዳ አቦምሳ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ፣ አቡሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አብሸራ መድኃኔዓለም በጉና ወረዳ አንድሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ተራም ቅዱስ ገብርኤልና መሶ ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ በእሳት ሲወድሙ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ፈርሰው፣ ጽላቱን ጨምሮ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸው ከዓመታት በፊት ተዘግቧል፡፡ ይህን የምናቀርበው መንግሥት ባለበት ሀገር እንዲህ ዓይነት ጥፋት መፈጸሙን በማሳሰብ ዳግም እንዳይፈጸም እንዲከላከል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተመሠረተች ዘለዓለማዊት እንደሆነች ብናምንም በጥፋታችን እግዚአብሔር እንዳይቀጣን፣ ከኃጢዓት እንድንርቅ፣ እንደ ዘመነ ሰማዕታት አጥፊዎችን የሚማርክ ክርስትና የሚነበብ ክርስትና እንዲኖረን ጭምር ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን በሰማይ አለች፣ በምድርም ትኖራለች፣ በገሀድ የሚኖሩትና የተሰወሩት አንደነት መሆኗን እየመሰከርን እኛ ግን በስንፍናችን እንዳንቀጣ መንቃት ይኖርብናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደማትጠፋ መረዳትና በእምነት መጽናት ይኖርብናል፡፡ ዲያብሎስ ዓላማየን ያሳኩልኛል ያላቸውን አካላት ጦር እያስመዘዘ፣ ገጀራ እያስጨበጠ፣ እሳት እያስለኮሰ፣ ቃታ እያሳበ ጥፋታቸውን ጽድቅ አስመስሎ እያሳያቸው በማጥፋት ለመርካት ቢፈልጉም ደስታን እንደማያገኟት መረዳት ይገባል፡፡ ከአጥፊዎች ወገንም የዲያብሎስን ሽንገላ አልፈው የእግዚአብሔር ጥሪ ደርሷቸው የሚመጡ እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ «ሰውን ብትታገለው ያሸንፍሀል ወይም ታሸንፈዋለህ፤ ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች፤ ተሸንፋ ግን አታውቅም፡፡ ዲያብሎስ ቤተ ክርስቲያንን ለመውጋት ዝናሩን አራገፈ፤ ቀስቱንም ጨረሰ፤ ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጐዳትም» በማለት ያስተማረውን ክርስቲያኖች በተግባር ተፈጽሞ፣ ያዩት ነው፡፡ ይህንን እያመንንም ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠልና ምእመናን ቦታችሁ አይደለም ተብለው ሀብት ያፈሩበትን፣ ወልደው ከብደው የኖሩበትን ቦታ ሲለቁ ችግሩ እየተባባሰ ሔዶ ልንቋቋመው ከማንችልበት ደረጃ እንዳይደርስ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች በመሆን ማሰብ አለብን፡፡ የግል ፍላጐታቸውንና ዓላማቸውን ለማስፈጸም ሀገራችንን በተፅዕኖአቸው ሥር ማድረግ የሚናፍቁ ወገኖች እርስ በርስ ስንፋጅ ዓላማቸውን እንዳያስፈጽሙብን፣ መሬታችንን እንጂ እኛን ስለማይፈልጉ የሩቅ ተመልካች ሆነው ሰንጫረስ ቆመው አይተው ሀገራችንን እንዳይወሰዱብን ጭምር ነው፡፡

በሥልጣኔ ሰበብ፣ በሉላዊነት ስም እየተፈጸመ ያለውን ድሀ ሀገሮችን የማዳከምና በጠንካራው የመዋጥ መጥፎ አካሔድ እንዳይደርስብን ዘመኑን የሚዋጅ ተግባር መፈጸም ግድ ይላል፡፡ በጦርነት አልሳካ ያላቸውን በማዘናጋትና በተናጥል በሚፈጽሙት ጥፋት ከእስከ አሁኑ የበለጠ እንዳንጐዳ እየተፈጸመ ያለውን እኩይ ተግባር መረዳት ይገባል፡፡ በሌሎች ሀገራት ከተፈጸሙ የሀገርን ቅርስ አጥፍቶ በአዲስ የመተካት ድርጊት ልንማርበት ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃጥሉ፣ ምእመናንን የሚያሳድዱ፣ ይዞታዋን የሚቀሙ ወገኖች በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንንና ሀገራቸውን የሚያስጠላ ትምህርት ሲጋቱ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህም የምዕራባውያን አድናቂዎች፣ የራሳቸውን ግን አናናቂዎች ሆነዋል፡፡ የጻፏቸውን የጥላቻ መጻሕፍት እየጠቀሱ ቤተ ክርስቲያንን ሲያብጠለጥሏት ኖረዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ሥልጣን ሲይዙም ቤተ ክርስቲያንን ለሀገሪቱ ኋላ መቅረት አስተዋጽኦ ያደረገች አስመስለው ከመሳል አልፈው በክርስቲያኖች ላይም ጥላቻና ጥርጣሬ አሳድረዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ዮሐንስ አድገህ የተባሉ ተመሪማሪ «ከዚያ በኋላ (ከንጉሡ ቀጠሎ) የመጣው መንግሥትም ዓላማዊነት (secularism) በሚል ከንቱ ፍልስፍና ተጀቡኖ ለሃይማኖት ቦታ የማይሰጥ፣ ይልቁንም ቤተ ክርስቲያኒቱን የነገሥታት መጨቆኛ መሣሪያ እንደነበረች አድርጐ በመሳል በሕዝብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት ለመቀነስ ይሞክር ነበር» ብለዋል፡፡

ይቆየን

ምንጭ ፤ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከሰኔ!  ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም