ጥንተ ስደት

ግንቦት ፳፫ ቀን፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት እናቱ እመቤታችን ድንግል ማርያም፣ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደደበት ዕለት ግንቦት ፳፬ በቅድስት ቤተ ክርስተያናችን ይከበራል፡፡ ጌታችንም በአረጋዊ ዮሴፍ በትር ብዙ አስደናቂ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ዳግመኛም እመቤታችንና የተወደደ ልጇን መድኃኒዓለምን በእጆቹ ሥራ ይመግባቸው የነበረና እነርሱንም ከኄሮድስ ለማዳን ብዙ ሰማዕትንት የተቀበለ ጻድቁና የ፹፫ ዓመቱ አረጋዊ ዮሴፍ ግብፅ የገባበትና ቅዳሴ ቤቱ የከበረበት ዕለት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ ገና ከሕፃንንቱ ጀምሮ ከእናቱ ጋር ስደትንና መከራን ተቀብሏል፡፡ እርሱ የሁለት ዓመት ነበረበትም ጊዜ እመቤታችን እሳትን አዝላ በብርድ ተንገላታለች፤ ለእኛ የሕይወት እንጀራን ተሸክማ እርሷ ተርባለች፤ የሕይወትን ውኃ ተሸክማ እርሷ ተጠምታለች፤ የሕይወት ልብስን ተሸክማ ሳለ እርሷ ተራቁታለች፤ የሕይወት ሐሴት ደስታ ተሸክማ እርሷ አዝናለች፡፡  እመ አምላክ ስለ ልጇ ብላ ተርባ፤ ተጠምታ፤ ታርዛለች፤ ደክማና አዝና አልቅሳለች፡፡

ምድረ ግብፅ በደረሰ ጊዜ ጌታችን የግብፅ ጣዖታት ከመሠረታቸው ተነዋውጠው ምድር አፏን ከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በግብፅ ኤሌዎጶሊዎስ ሀገር ሲገቡ ዮሴፍ ማረፊያ ሠራ፡፡ በዚያም ባለች ተራራ ሥር ጌታችን ውኃን አፈለቀ፡፡ ይህችውም በእኛና በቅብጥ ሰዎች ዘንድ ሰኔ ስምንት ቀን የምትታሰበው ዕለት ናት፡፡ ኄሮድስ ሚስቱን ማርያናንም ከገደላት በኋላ ይበቀሉኛል በማለት ከእርሷ የወለዳቸውን የገዛ ልጆቹንም ገደላቸው፡፡ በሥጋውም በጽኑ መከራ ተያዘ፤ እግዚአብሔርም የደዌውን ዘመን አስረዘመ፡፡ አብዝቶ ቢበላም የማይጠግብ ሆነ፤  ረኃብና ጥም በዛበት፤ አንጀቱም ተቋጠረ፤ ሰውነቱም ተልቶ ሰው ሁሉ ሊልቀርበው አልቻለም ነበር፡፡ እጅጉን ከማቀቀ በኋላ በመጨረሻ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ ዮሴፍን ኄሮድስ ስለሞተ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል እንዲመለስ ነገረው፡፡

ከተመልሰሱም በኋላ በፍልስጤም አልፈው ድልማጥያ ወደምትባል አንዲት ሀገር ሲደርሱ በበረሃ ውስጥ ተቀመጡ፡፡ እመቤታችንም ከነልጇ ረኃቡ ቢጠናባት ትዕማን ወደምትባል አንዲት ከበርቴ ባለሀብት ቤት ሄዳ ቁራሽ እንጀራንና ለልጇም ጥቂት ወተትን ለመነቻት፡፡ ያቺ ክፉ ሴት ግን ልብን በኅዘን የሚሰብር ክፉ ንግግርን ተነጋረቻት፡፡ ጻድቅ ዮሴፍም ‹‹እንግዳን ካለ ይሰጡታል ከሌለ በሰላም ይሸኙታል እንጂ ለምን ክፉ ንግግርን ትናገሪያታለሽ?›› በማለት ሲጠይቃት አሽከሯ ኮቲባ የእመቤቷን ቁጣ ሰምታ መጥታ ጌታችንን ከመሬት ላይ ጣለችው፡፡ እመቤታችንም ደንግጣ እያለቀሰች ልታነሣው ስትል ዮሴፍ ‹‹ተይው አታንሽው፤ ኃይሉን ይግለጥ›› አላት፡፡ ያንጊዜም ምድር አፏን ከፍታ ዋጠቻት፤ ገረዷ ኮቲባም በለምጽ ተመታች፡፡ በቤታቸውም ውስጥ በሕይወት የቀረ የለምና ቤተሰቦቿ ጦጣ ሆነው ከተራራ ወደ ተራራ ሸሹ፡፡

እመቤታችን፣ ዮሴፍና ሰሎሜም በትዕማን ቤት ስድስት ወር ከተቀመጡ በኋላ መልአኩ ተገልጦ ከዚያ እንዲወጡ አዘዟቸው ወጡ፡፡ አርዲስ ወደምትባል ሀገርም ደርሰው የሀገሪቱ ሰዎች በሰላም ተቀብለው አስተናገዷቸው፡፡ እመቤታችንም ከሀገረ ገዥው ሆድ ውስጥ በጸሎቷ እባብ ስላወጣችለትና ከሕመሙ ስላዳነችው በጣም አከበሯቸው፡፡ ዕውሮችን፣ አንካሶችን፣ ለምፃሞችንና አጋንንት ያደሩባቸውን ሁሉ እያመጡላት የልጇን እጆች ይዛ ከሩቅ እያማተበች ፈወሰቻቸው፡፡ ኄሮድስም እንደሚያፈላልጋቸው መልአኩ በሲነገራቸው ጊዜ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር እየተዘዋወሩ ታችኛው ግብፅ ንሂሳ ድረስ ደረሱ፡፡ እመቤታችንም በዚያ ያሉ ሕመምተኞችን ፈወሰችላቸው፡፡

ከዚህም በኋላ አሁንም መልአኩ በተነጋገራቸው መሠረት ደመና መጥታ ነጥቃ ወሰደቻቸው፤ የ፴፰ቱን ወራት መንገድንም በአንድ ጊዜ አደረሰቻቸው፡፡ በዚያም ትንሽ ከቆዩ በኋላ ወደ ቤጎር ቆላ ደረሱ፡፡ ግብፃውያንም እንደ ሕጋቸው ለአማልክቶቻቸው ላሞችን አርደው ሠውላቸው፡፡ በጎሽ፣ በአውራሪስ፣ በነጭ ዝንጀሮ የሚመሰሉ አጋንንትም መጡ፡፡ እመቤታችንም ከሩቅ ሆና ተመልክታቸው እነዚያን አጋንንት በጸሎቷ እንደጢስ በተነቻቸው፡፡ ግብፃውያንም ፈርተው እየጮኹ ሸሹ፡፡ በዚያም ወራት ‹‹ረዳት አማልክቶቻችንን ጠፉብን›› ብለው እያዘኑ ሳለ ዮሴፍን ሲጸልይ አግኝተውት አስረው በምድር ላይ አስተኝተው ፵ ግርፋት ገረፉት፡፡ እርሱም በዚህ ጊዜ ‹‹እመቤቴ ሆይ ስለ አንቺና ስለ ልጅሽ ይህ መከራ አግኝቶኛልና እርጂኝ›› ብሎ
በኃይል ጮኸ፡፡ እመቤታችንም ድምጹን ስትሰማ የኄሮድስ ጭፍሮች የመጡ መስሏት እጅግ ደነገጠች፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ተገልጦ ካረጋጋት በኋላ ዮሴፍን በኃይል ይደበድቡ የነበሩትን በእሳት ሰይፉ ጨረሳቸው፡፡ ዮሴፍንም በእጆቹ ዳሰሰውና ፈወሰው፡፡ እመቤታችንም ዮሴፍን ባየችው ጊዜ ‹‹ይህ ሁሉ መከራ ያገኘህ በእኔና በልጄ ምክንያት ነው›› ብላው አንገት ለአንገት ተቀቅፈው ተላቀሱ፡፡ መልአኩም ‹‹ይሄ ኀዘናችሁ በደስታችሁ ጊዜ ይረሳል…›› እያለ አረጋጋቸውና ዐረገ፡፡

የሀገሩ ሰዎችም እነርሱን ለመውጋት ወጥተው ክፉ ውሾችን ለቀቁባቸው፡፡ ነገር ግን ውሾቹ በሰው አንደበት እመቤታችንን እያነገሯት ሰግደውና የእግሯን ትቢያ ልሰው በመመለስ ባለቤቶቻቸውን መልሰው መናከስ ጀመሩ፤ ብዙዎቹንም ገደሏቸው፡፡ ዮሴፍም ‹‹እመቤቴ ሆይ በዚህ ሀገር ከምንኖርስ በዱር በበረሃ ብንኖር ይሻለናል›› አሏት፤ የሰላም ሀገር ወደሆነች ዲርዲስ ሀገር ደረሱ፡፡ ሰዎቹም ‹‹ይህችስ የነገሥታት ወገን ትመስላለች፤ በላያችን ላይ ትነግሥብናለች›› ብለው በክፉ ሲነሱባቸው በማግሥቱ ደመና ነጥቃ ወስዳ ኤልሳቤጥ በሞት ካረፈችበት በረሃ አደረሰቻቸው፡፡ ዮሐንስ በእናቱ በድን ላይ ሆኖ እያለቀሰ ሳለ ዮሴፍንና ሰሎሜን ባያቸው ጊዜ ደነገጠ፤ ጌታችንም አረጋጋው፡፡ እመቤታችንም ስለ ኤልሳቤጥ ሞት እጅግ መሪር የሆነ ልቅሶን ስታለቅስ አረጋጋት፡፡ እመቤታችንም ‹‹እናቱ ስለሞተችበት በዚህም በረሃ ማንም ስለሌው ዮሐንስን ከእኛ ጋር እንውሰደው›› አለችው፤ ጌታችን ‹‹ዕድሉ በዚህ በረሃ ነው›› ብሎ አረጋጋት፡፡

ከዚህም በኋላ ደመና ነጥቃ ወስዳ ወደ ጋዛ ምድር አደረሰቻቸው፤ በዚያም አተር የሚያበራዩ ሰዎችን አግኝታ እመቤታችን ‹‹ለልጄ አተር ስጡኝ›› አለቻቸው፡፡ እነርሱም ክፉዎች ነበሩና ‹‹ይህ አተር ሳይሆን ድንጋይ ነው›› አሏት፡፡ ሕፃኑ ልጇም ‹‹እናቴ ሆይ እንደቃላቸው ይሁንላቸው ተያቸው›› አላት፡፡ ያንጊዜም አተሩ ድንጋይ ሆነ፤ ይህም እስከዛሬም ድረስ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ እመቤታችን ወደ ተወለደችበት ሀገር ወደ ሊባኖስ ተራራ ሄደው በዚያ ያሉ ሰዎችም በሰላም ተቀበሏቸው፤ እመቤታችንም ብዙ ተአምራት አደረገችላቸው፡፡ ገዥው ደማትያኖስም ኄሮድስን ሊወጋው ጦሩን አዘጋጅቶ ሳለ፤ ነገር ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ከለከለችው፡፡ መልአክም ተገልጦለት በእርሱ ምክንያት ብዙ ሰማዕታት ይሰየፉ ዘንድ አላቸውና ጊዜው ገና መሆኑን አስረድቶት ኄሮድስን በጦር እንዳይገድለው ከለከለው፡፡ ደማትያኖስም ኃይሉና ጦሩ እጅግ የበረታ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊጋርም በዚህ ወቅት ስለ እመቤታችንና ስለልጇ ሰማዕት ሆነ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ለእመቤታችን ተገልጦ ወደ ግብፅ እንድትሄድ ነገራት፡፡ ዳግመኛም መልአኩ ለገዥው ለደማትያኖስ ተገልጦለት ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ እንዲያሰናብታት ነገረው፡፡ እርሱም አስቀድሞ ‹‹በዙፋኔ ተቀመጪ እኔና ሚስቴ አገልጋይሽ እንሁን እንጂ ከዚህስ አትሄጂም›› ብሎ ግድ ብሏት ነበርና፡፡

ከዚህም በኋላ የአንድ ቀን መንገድ ሸኝቷት እንዲህ አላት፤ ‹‹እመቤቴ ሆይ ኄሮድስ ቢፈልግሽ ወደኔ መልእክት ላኪብኝ፤ ፈጥኜ እመጣለሁ፡፡ የእስራኤል አምላክ ቢፈቅድልኝ ከዛብሎን፣ ከንፍታሌምና ከሐሴቦን ጀምሮ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ሁሉ አጠፋቸዋለሁ፡፡ ሰውን ብቻ የምገድል አይደለሁ፤ ዛፎቻቸውም ቆመው እንዲታዩ አልፈቅድም፡፡ ሀገሪቱንም ፍርስራሽ አደርጋታለሁ›› አላት፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ አስረድታው መርቃ አሰናበተችውና በበነጋታው ተለያዩ፡፡ ወደ ቤተልሔምም ከደረሱ በኋላ አሁንም መልአኩ አዘዛቸው፤ በሌሊት ተነሥተውም ወደ ግብፅ ተጓዙ፡፡ ኄሮድስም ሀገሪቱን መጥቶ ከበባት፡፡ እነርሱንም ቢያጣ በዚያ ያገኘውን ሁሉ ሰየፈ፡፡ ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ ሕፃናትን ሁሉ ሰብስበው እንዲያመጡአቸው አዘዘ፤ ፻፵፬ (መቶ ዐርባ) ሽህ የቤተልሔም ሕፃናትን ከእናቶቻቸው ላይ እየቀማ ሰየፋቸው፡፡ መላእክትም እጅግ ደንግጠው ይህ ለምን እንዲሆን ፈቀድክ? ብለውም አምላካቸውን ጠየቁ፡፡ እንዲህ የሚል ቃልም ከዙፋኑ ወጣ፤ ‹‹ኢየሩሳሌም በሰው ደም እንደምትታጠብ በነቢያት እንዲሁ ተጽፏልና እነዚህ ሕፃናት ለመንግሥተ ሰማያት ቀድመው የተዘጋጁ ናቸው፡፡››

እመቤታችንና እነ ዮሴፍም ግብፅ ደርሰው በዚያ ተቀመጡ፤ ነገርን ግብፅ አልተመቸቻውም፤ ሕዝቡም በሰላም አልተቀበላቸውም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ግን ሁሉ በሰላም ተቀበላቸው፡፡ ከመንገዱና ከረኃብ ጥሙ ጽናት የተነሣ እጅግ ደክማለችና የኢትዮጵያ ሰዎች እመቤታችንን አይተው እጅግ አዘኑላት፡፡ ‹‹ይህችስ የነገሥታት ዘር ትመሥላለች፤ ነገር ግን አንዳች ችግር አጋጥሟት ተሰዳ ወደ ሀገራችን መጥታለች..›› ብለው እንክብካቤን አደረጉላት፡፡ እግራቸውን አጥበው በክብር ማረፊያዎች ላይ አሳረፏቸው፡፡ መልካም መስተንግዶም አደረጉላቸው፡፡ እመቤታችንም ከድካሟ ካረፈች በኋላ ሀገሪቱን በእጅጉ ወደደቻትና የተወደደ ልጇን ‹‹ይህን ሀገርና ሕዝቧን በመላ ስለወደድኳቸው በዚህ እስከ መጨረሻው እንኑር›› አለችው፡፡ ጌታችንም ክብርት እናቱን ‹‹ይህች ቅድስት ሀገር ናት፤ በኋለኛው ዘመን የቅዱሳን መነኰሳት ቦታ ትሆናለች፡፡ በውስጧም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እመሰገንባታለሁ፤ የአንቺም ስም ሳይጠራ አይውልባትም›› አላት፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ደመና ጠቅሶ በእርሷ ላይ ተቀመጡ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤልም መጣና እየመራቸው መላ ኢትዮጵያን ጎበኟት፡፡ እመቤታችንም ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን ስለወደደችና ደስም ስለተሰኘችባቸው ጌታችን ለክብርት እናቱ ‹‹ይህችን ቅድስት ሀገር ዐሥራት አድርጌ ሰጠሁሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም እጅግ ተደስታ ‹‹ልጄ አምላኬ›› ብላ አመሰገነችው፡፡ ከዚህም በኋላ ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ እየተዘዋወሩ መላዋ ኢትዮጵያን በኪደተ እግራቸው ባረኳት፡፡ ጌታችንም በሀገራችን ስለሚታነጹ ቤተ ክርስቲያናት እና  ስለሚነሡ ቅዱሳን ብዙ ምሥጢራትን ለእናቱ ነገራት፡፡

የስደቱ ዘመን ሲያልፍም ኄሮድስ በመጨረሻ ክፉ አሟሟትን ሲሞት መልአኩ ወደ ገሊላ አውራጃ እንዲመለሱ ነገራቸው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ከዚህች ሀገርስ ባንሄድ እመርጣለሁ›› አለችው፡፡ የተወደደ ልጇም ‹‹እናቴ ሆይ ጽድቅንና ፈቃድን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› ብሎ አጽናናትና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡

ምንጭ፡- ገድለ አረጋዊ ዮሴፍ