በዓለ ደብረ ምጥማቅ

ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፲፻፬ ዓ.ም

የክርስተያን ወገን ሁሉ አምላክን የወለደች እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ ስለመታየቱ ታላቅ በዓልን ያደርጋሉ፡፡

እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያም ብርሃን ተጎናጽፋ በተገለጠችበት ጊዜ በዙሪያዋ የመላእክት ሠራዊት የመላእክት አለቆችም በየማዕረጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው ይቆሙ ነበር፤ ይጋርዷታልም፡፡ ሱራፌል ማዕጠንታቸውን ይዘው ለንግሥትዋ ገናናነት ሰገዱ፤ በየስግደታቸውም እንዲህ እያሉም አመሰገኗት፤ ‹‹አብ በሰማይ ሁኖ ተመለከተ፤ እንዳንቺ ያለ አላገኘም፤ አንድ ልጁንም ልኮ ከአንቺ ሰው ሆነ፡፡›› (መጽሐፈ ስንክሳር ግንቦት ፳፩ ገጽ. ፫፻፲፰)

ሰማዕታትም በየማዕረጋቸው ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው ወደ እርሷ ቀርቡ፤ በመጀመሪያ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምባላይ ፈረሱ ወርዶ ሰገደላት፡፡ እንዲሁም ባልንጀሮቹ ሰማዕታት መጥተው ሰገዱላት፤ ለእርሱ በኋላ የመጣው በዱሪ ፈረስ የተቀመጠው ቅዱስ መርቆሬዮስ ነው፡፡

ከዚህም በኋላ ሰማዕታት ሁሉ በመከታተል መጥተው ሰገዱላት፤ ምስጋናም አቀረቡላት፤ ጻድቃን በአንድነት መጥተው በፊቷ ሰግደው ተመለሱ፤ ቀጥሎም ሄሮድስ የገደላቸው ሕፃናት መጥተውም ሰገዱ፤ በፊቷም እየዘለሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየዘለለ በመተቃቀፍ ተጫወቱ፡፡ በዚያ የተሰበሰቡትም በአዩ ጊዜ ደስታ ሞልቶባቸው በሰማይም ያሉ ይመስላቸው ነበር፡፡

እናትና አባቱም የሞቱበት ቢኖር ወይም ለዘመዶቹ ወይም ባልንጀራው ‹‹ቅድስት ድንግል እመቤቴ ሆይ ዕገሌን አሳይኝ›› ብሎ በሚለምናት ጊዜ ቀድሞ በነበረበት መልኩ ያን ጊዜ ታመጣዋለች፡፡ ደግሞ መሀረባቸውን ወደ ላይ ይወረውሩላታል፤ የወደደችውንም በእጅዋ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች፤ ለበረከትም በየጥቂቱ ይካፈሉታል፡፡ እንዲህም አምስት ቀን ሁሉ ክርስቲያንም፣ እስላሞችም፣ አረማውያንም ያይዋታል፡፡ ወደ ቤታቸውም ለመሄድ ሲሹ በፊቷ ሰግደው ይሰናበቷታል፤ እርሷም ትባርካቸዋልና ይመለሳሉ፡፡

የእመቤታችንም የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅ ተራዳኢነት ከእኛ ጋር ይሁን፤አሜን!

ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት