ጥምቀተ ክርስቶስ 

አንኳን አደረሰን! 

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ከዘጠኙ ታላላቅ በዓላት አንዱ ነው፤ ለእኛ አርአያና አብነት ለመሆን በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ የባሕርይ ልጅነቱንና አምላክነቱን ከአብ እና ከመንፈሰ ቅዱስ አስመሰከረ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው ሕግና የሠራው ሥርዓት ቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን በኋላም በነቢያት ያናገረውን ትንቢትና ምሳሌ፣ ያስቈጠረውን የዘመን ሱባዔ፣ ለአዳም የሰጠውን የመዳን ተስፋ ለመፈጸም ነው፡፡ የተነገረውን ትንቢት፣ የተመሰለውን ምሳሌም እንደሚከተለው መጻሕፍት ያስተምሩናል፤ወአሜሃ መጽአ እግዚአ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ፤ ይጠመቀ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፤›› (ማቴ.፫፥፲፫፤ ማር.፩፥፱፤ ሉቃ.፫፥፳፩፤ ዮሐ.፩፥፴፪)፡፡ ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን? ብሎ አይሆንም አለው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ዓይነ ከርም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በመጣች ጊዜ የዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታዬ እናቱ እኔ ወደ አንቺ እመጣለሁ እንጂ ወደኔ ትመጭ ዘንድ ይገባኛልን?›› ብላ ነበርና ከዚያ አያይዞ ተናግሮታል፡፡ ጌታም መልሶ ‹‹ይህ ለኛ ተድላ ድስታችን ነው፤ አንተ መጥመቀ መለኮት ተብለህ ክብርህ ሲነገር፤ እኔም በአገልጋዩ እጅ ተጠመቁ ተብዬ ትሕትናየ ሲነገር ይኖራል፡፡ ትንቢት ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናልና አንድ ጊዜስ ተው››  አለው፤ አንድ ጊዜ ቢጠመቅ ሁለተኛ፤ በፈቃድ ቢጠመቅ በግድ፤ ሰውነቱ ቢጠመቅ በአምላክነቱ መጠመቁ አያሻውምና፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ጌታም በዮሐንስ እጅ እንዲጠመቅ በነቢያት ትንቢት ተነግሯልና ጌታችን ‹‹ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናል›› አለ፡፡ ዳግመኛም ይህ ለምእመናን ተድላ ነውና ‹‹እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል›› ለማለት፤ እንደዚሁም ይህ ለባሕርይ አባቴ ለአብ፣ ለባሕርይ ልጁ ለእኔ፣ ለባሕርይ ሕይወቴ ለመንፈስ ቅዱስ ተድላ ደስታችን ነውና ማለቱ ነው፡፡ አንዱ አካል ወልድ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፤ እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር፤ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ ብሎ ሲመሠክር፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ተገልጧልና፡፡ ጌታችን ዮሐንስን ‹‹የጀመርነውንም የቸርነት ሥራ ልንፈጽም ይገባናል፤ አንድ ጊዜስ ተው›› ካለው በኋላም ተወው (ለማጥመቅ ፈቃደኛ ሆነ)፡፡

ዮሐንስም ‹‹አብ በአንተ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡ አንተም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአንተና በአብ ህልው ነው፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለው አንተን በማን ስም ላጥምቅህ?›› ቢለው ‹‹ወልዱ ለብሩክ ከሣቴ ብርሃነ ተሣሃለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ፤ እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ነህ፤ ብርሃንን የምትገልጽ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለን›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ባሕር ወርደዋለወ፡፡ ‹‹ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ሶቤሃ ወፅአ እማይ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኃው ወጣ፡፡›› (ዮሐ.፫፥፲፮)

ቃለ ወንጌል ‹‹ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ፤ ሰማይ ተከፈተለት›› ይላል፡፡ ይህን ሲልም በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም፡፡ የተዘጋ በር በተከፈተ ጊዜ በውስጡ ያለው ዕቃ በግልጽ እንዲታይ ጌታን ሲጠመቅ ከዚህ በፊት ያልተገለጸ ምሥጢር ታየ ሲል ነው፤ ይኸውም የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ነው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሔዶ መጠመቁ ለምንድን ነው? ምነው አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን? አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋይ እጅ ይጠመቃልን?›› የሚልጥያቄ ከተነሣ ጌታችን መምጣቱ ለትሕትና እንጂ ለልዕልና አይደለምና ነው፡፡ ዳግመኛም ለአብነት ነው፤ ጌታችን ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ››  ብሎት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ነገሥታት፣ መኳንንት ካህናትን ‹‹ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን›› ባሉ ነበርና፡፡ ካህናት ካሉበት ከቤተ ክርስቲያን ሒዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመሆን ራሱ ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሔዶ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን መጠመቁም ለእርሱ ክብር የሚጨመርለት ሆኖ አይደለም፤ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅፀን እንድትሆን ለማድረግ፤ እኛ ምእመናንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግም ተወልደን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ ለማድረግ፤ እንደዚሁም ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመሆን ነው፡፡ ‹‹ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ዳግመኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኀፀነ ዮርዳኖስ ያልተወለደ ማለተም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኀን ወዘሰ ኢአምነ ወኢተጠምቀ ይደየን፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል›› ተብሎ ተጽፏልና (ዮሐ. ፫፥፫፤ ማር.፲፮፥፲፮)፡፡ ያውስ ቢሆን ጥምቀቱን በዮርዳኖሰ ያደረገው ስለምን ነው? ቢሉ ትንቢቱን፤ ምሳሌውን ለመፈፀም ነው፡፡ ትንቢቱ ‹‹ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ፤ ባሕሩ አይታ ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፡፡ ርእዩከ ማየት እግዚኦ ርእዩከ ማየት ወፈርኁ፤ አቤቱ ውኆች አንተን አይተው ሽሹ ተብሎ ተነግሯል፡፡ (መዝ. ፸፮፥፲፮፤ ፻፲፫፥፫)

ምሳሌው፤ ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ (ምንጩ) አንድ ነው፤ ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል፤ ከታች ወርዶ ይገናኛል፡፡ ዮርዳኖስ ከላይ (ነቁ) ምንጩ አንድ መሆኑ የሰውም መገኛው (ምንጩ) አንድ አዳም ለመሆኑ፤ ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት መከፈሉ እስራኤል በግዝረት፣ አሕዛብ በቍልፈት ለመለያየታቸው፤ ዮርዳኖስ ከታች በወደብ መገናኘቱ በክርስቶስ ጥምቀት ሕዝብና አሕዛብ አንድ ወግን ለመሆናቸው ምሳሌ ነው፡፡

ዳግመኛም አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ደስ ቢለው በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከ ወሚመ ታርዕየኒሁ ኪያሃ ዕለተ፤ በዘመኔ ቃልህን (እግዚአብሔር ወልድን) ትልከዋለህን? ወይስ ያቺን የማዳንህን ቀን በዓይኔ ታሳየኝ ይሆን፤›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ ‹‹ምሳሌውን ታያለህና ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድ፤›› ብሎታል፡፡ አብርሃምም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሔድ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ አኮቴት፣ ጽዋዓ በረከት ይዞ ተቀብሎታል፡፡ ይኸውም አብርሃም የምእመን፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት፤ መልከ ጼዴቅ የካህናት፤ ኅብስተ አኰቴት፣ ጽዋዓ በረከት የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነው (ዘፍ. ፲፬፥፲፫-፳፬)፡፡

ኢዮብና ንዕማን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀው ከደዌያቸው ድነዋል (፪ኛነገ.፭፥፰-፲፱)፡፡ ኢዮብና ንዕማን የአዳምና የልጆቹ፤ ደዌ የመርገመ ሥጋ፣ የመርገመ ነፍስ፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ኢዮብ፣ ንዕማን፣ ጌታ የተጠመቁበት ዮርዳኖስ ወደቡ አንድ ነው፡፡ እንደዚሁም እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ በኢያሱ ጊዜ ወደ ምድረ ርስት ሲሔዱ ከዮርዳኖስ ወንዝ ደረሱ፡፡ ታቦቱን የተሸከሙና ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ሌዋውያን ካህናት በፊት በፊት ሲጓዙ ታቦቱን የሚያጅቡ ሕዝበ እስራኤል ከታቦቱና ከሌዋውያን ካህናት ሁለት ሺሕ ክንድ ርቀው ዮርዳኖስ ከላይና ከታች ተከፍሎላቸው በየብስ ተሻግረው ኢየሩሳሌም ገብተዋል፡፡ ምእመናንም በማየ ገቦ ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡

ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፡፡ የኤልያስ ደቀ መዝሙር ኤልሳዕ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዮርዳኖስ ዳር እንጨት ሲቈርጡ መጥረቢያው ከውኀው ውስጥ ወደቀ፡፡ ኤልሳዕ የእንጨት ቅርፊት በትእምርተ መስቀል አዘጋጅቶ ምሳሩ ከወደቀበት ላይ ቢጥልበት የማይዘግጠው ቅርፊት ዘግጦ የዘገጠውን ብረት አንሳፎ አውጥቶታል፡፡ እንደዚሁም ዅሉ በባሕርዩ ሕማም ሞት የሌለበት አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ በቀራንዮ በዕፀ መስቀል ተሰቀሎ፣ ከጎኑ ጥሩ ውኀና ትኩስ ደም አፍስሶ በሲኦል የወደቀው አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው (፪ኛነገ. ፮፥፩-፯)፡፡ ይህንን ሁሉ ምሳሌ ለመፈጸም ጌታችን በዮርዳኖስ ተጠምቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምሥጢር ምንድን ነው? ቢሉ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ አገዛዝ ስቃይ አጸናባቸው፡፡ ከዚያም ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሐዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ፤ አዳም የዲያብሎስ ተገዥ፤ ሔዋንም የዲያብሎስ ተገዥ አገልጋዮች ነን›› ብላችሁ ስመ ግብርናታችሁን (የተገዥነታችሁን ስም)ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራውን አቀልላችሁ ነበር›› አላችሁ፡፡ እነርሱም መከራው የሚቀልላቸው መስሏቸው‹‹አዳምገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ›› ብሎ  በማይጠፋ በሁለት ዕንበነ ሩካም (ዕብነ በረድ) ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ፤ አንዱን በሲኦል ጥሎት ይኖር ነበር፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ አጥፍቶልናል፡፡ በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ሲያወጣ አጥፍቶልናል፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት አንደኛው ምሥጢርም ይህ ነው፡፡

ጌታችን ጥምቀቱን በውኀ ያደረገው በሌላ ያላደረገው ስለምንድን ነው ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው ሊፈጸም፤ ትንቢት፤ ‹‹ወእነዝኃክሙ በማይ ወትነጽሑ፤ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ፤›› ተብሎ ተነግሯል (ሕዝ.፳፮፥፳፭)፡፡ ምሳሌ፤ ውኀ ለሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ውኀ መኖር የሚችል የለም፡፡ ጥምቀትም ለሁሉም የሚገባ ሥርዓት ነው፡፡ ያለ ጥምቀት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልምና፡፡ ውኀ መልክ ያሳያል፤ መልክ ያለመልማል (ያጠራል)፡፡ ጥምቀትም መልክዐ ነፍስን ያሳያል፤ መልክዐ ነፍስን ያለመልማልና (ያጠራልና)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት አየ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱም ምሥጢር አለው፡፡ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና፡፡ ርግብ በኖኅ ጊዜ ‹‹ሐጸ ማየ አይኅ ነትገ ማየ አይኅ፤ የጥፋት ውኀ ጎደለ›› ስትል ቆጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ተገኝታለች፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተስፋ መስቀልን ያበሥራልና፡፡ ጥምቀቱን በቀን ያላደረገው በሌሊት ያደረገው ስለ ምን ነው ቢሉ በቀን አድርጎት ቢሆን መንፈስ ቅዱስ በቁሙ ርግብ ነው በተባለ ነበርና፤ አሁንስ ርግብ አለመኾኑ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ጌታ የተጠመቀው ከሌሊቱ በዐሥረኛው ሰዓት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ተሐዋስያን ወፎች (ርግቦች) ከየቦታቸው አይወጡምና መንፈስ ቅዱስ መኾኑ በዚህ ይታወቃል፡፡

መንፈስ ቅዱስም መውረዱ ከውኀው ከወጣ፣ ከዮሐንስ ከተለየ በኋላ ነው፡፡ ከውኀው ውስጥ ሳለ ወርዶ ቢሆን ለቀድሶተ ማያት ነው የወረደው ባሉት ነበርና፡፡ ከዮሐንስ ጋርም ሳለ ወርዶ ቢሆን ለክብረ ዮሐንስ ወረደ ባሉት ነበርና፡፡ ረቦ ወርዷል ያሉ እንደ ኾነ አብ ምሉዕ ነው፤ አንተም ምሉዕ ነህ፤ እኔም ምሉዕ ነኝ ሲል፡፡ አሰይፎ ወርዷል ያሉ እንደ ሆነ የብሉየ መዋዕል የአብ ሕይወት ነኝ፤ የአንተም ሕይወት ነኝ፤ እኔም ብሉየ መዋዕል ነኝ ሲል፡፡ ወርዶ ራሱን ቆንጠጥ አድርጎ ይዞታል ቢሉ አብ አኃዜ ዓለም ነው፤ አንተም አኃዜ ዓለም ነህ፤ እኔም አኃዜ ዓለም ነኝ ሲል፡፡ ምሥጢሩም እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፣ አብነት ለመሆን ነው፡፡

‹‹ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቀር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ ፤ተዋሕዶ የመረጥኩት በእርሱ ህልው ሆኔ ልገለጥበት የወደድኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው፤››የሚል ቃል ከወደ ሰማይ ተሰማ፡፡ ይህም አብ የተናገረበት ቃል ያው የሚጠመቀው አካላዊ ቃል ነው እንጂ ሌላ ቃል አይደለም፡፡ የሥላሴ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አንድ ነውና፡፡ አብ ልብ፤ ወልድ ቃል፤ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በመሆን አንድ አምላክ ነውና፡፡ ‹‹አብኒ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ ወመንፈስ ቅዱስኒ እስትንፋሶሙ ለአብ ወለወልድ፤ አብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልቡናቸው ነው፡፡ ወልድም ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለአብ ለወልድ ሕይወታቸው ነው፤›› በማለት ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት እንደ ተናገረው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀውም በሠላሳ ዓመቱ ነው (ሉቃ. ፫፥፳፫)፡፡ በሠላሳ ዓመቱ የተጠመቀበት ምሥጢርም አዳም የሠላሳ ዓመት፤ ሔዋን የዐሥራ አምስት ዓመት ሰው ሆነው ተፈጥረው አዳም በዐርባ ቀን፣ ሔዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ የተቀበሉትን ልጅነት በምክረ ከይሲ ዕፀ በለስን በልተው አስወስደው ነበረና በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቆ መልሶላቸዋል፡፡ በሠላሳ ዓመት የመጠመቁ ምሥጢር ይህ ሲኾን እኛ ዛሬ ወንዶች በዐርባ ቀን፣ ሴቶች በሰማንያ ቀን በዕለተ ዓርብ ከቀኝ ጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ የምንወለድበት ምክንያትም አዳም በዐርባ ቀኑ፣ ሔዋን በሰማንያ ቀኗ ከሥላሴ ያገኙትን ልጅነት መሠረት በማድረግ ነው (ኩፋ. ፬፥፱)፡፡ የምንጠመቀውም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ‹‹ወእንዘ ታጠምቅመው በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ስታጠምቋቸውም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው፤››ንዲል (ማቴ. ፳፰፥፲፱)፡፡

ዛሬም ታቦታቱን ወደ ጥምቀተ ባሕር በማውረድ በዓለ ጥምቀቱን ለሚያከብሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ከታቦታቱ ሁለት ሺሕ ክንድ ርቀው መከተል እንዲገባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎተገልጿል፤ ‹‹ሕዝቡን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት፡፡ በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ይሁን፡፡ በዚህ መንገድ በፊት አልሔዳችሁበትና፤ የምትሔዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አርቅረቡ፡፡›› (ኢያ.፫፥፩-፲፯)

ይህ ኃይለ ቃል ዛሬ ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው ለማደራቸው መነሻ ትምህርት ነው፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀትም ጌታችን ከተጠመቀበት ከ፴ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሲከበር ይኖራል፡፡ ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት፣ በረከት ይክፈለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር