ዘመነ አስተርእዩ
                                                                    ርእሰ ደብር ብርሃኑ አካል

አስተርእዮ መታየት ወይም መገለጥ የሚል ትርጓሜ ያለው የግእዝ ቃል ነው፡፡በግሪክ ‹‹ኤጲፋኒ›› የሚል ስያሜ አለው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ይህን ቃል  በመጠቀም ኤጲፋኒያ እያሉ በዜማ መጻሕፍቶቻቸው ይጠሩታል፡፡

አስተርእዮ የሚለው ቃል አስተርአየ የተባለው ግሥ ራሱን ችሎ ሳይለወጥ በአምስቱ አዕማድ የሚፈታ ብቸኛ ግሥ ነው፡፡ ይህም ማለት፤ አስተርአየ፤ ታየ፤ ተያየ፤ አሳየ፤ አስተያየ፤ አየ ተብሎ ይፈታል ማለት ነው፡፡ ዘመነ አስተርእዮ ሲያጥር ከጥር ፲፩ ቀን እስከ ጥር ፴፤ ሲረዝም ደግሞ ከጥር ፲፩ ቀን እስከ መጋቢት ፫ ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ቀናቱ ሲያጥር ፳፤ ሲረዝም ፶፫ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ጌታችን ኢየሱስ ለሐዋርያት ሕፅበተ እግር ያደረገበት ቀንም (ከጸሎተ ሐሙስ) እስከ ጰራቅሊጦስ ቢቆጠር ፶፫ ቀናት ስለሚሆኑ የእነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስ በጥምቀት ዕለት ለልዕልና (ጌታ ሰውን ምን ያህል እንዳከበረው) ለማሳየት እጁን ከጌታ ራስ በላይ ከፍ እንዳደረገ፤ ጌታንንም ለትሕትና እጁን ከሐዋርያት እግር በታች ዝቅ አድርጎ እግራቸውን አጥቧቸዋልና ነው፡፡ ጥምቀት የሕጽበት አምሳል ሲሆን፤ ሕጽበት (መታጠብ) ደግሞ በንባብ አንድ ሆኖ ሁለት ምሥጢራት አሉት፡፡

የመጀመሪያው ምእመናን የእንግዳ እግር እንዲያጥቡ ትምህርት ማስተማሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለሐዋርያት ጥምቀታው መሆኑ ነው፡፡ ሐዋርያት በጸሎተ ሐሙስ ቢጠመቁም መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት የጰራቅሊጦስ ዕለት ነውና፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለ ቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያን እንደ ጠየቀውና ጥምቀታቸው ሕጽበተ እግር መሆኑን እንደ መለሰለት፡፡

በሌላ በኩል ከዘመነ ልደት እስከ ጥምቀት ተወልደ፤ ተሠገወ (ሰው ሆነ)ይባላል እንጂ ተገለጠ አይባልም፡፡ ከጥምቀት በኋላ ግን አብሮ፣ ተባብሮ ተጠምቀ፤ ተወለደ፤ ተሠገወ፤ አስተርአየ ይባላል፡፡ ከጥምቀት በፊት አስተርእዮ ለመባሉ በሦስት ነገሮች ነው፡፡

የመጀመሪያው የማይታየው ረቂቅ አምላክ በበረት ተወልዶ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ ቢታይ፤ እንደ ሕፃን ሲያለቅስ ቢሰማም ሰው ሁሉ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ሙሉ ሰው ይሆናል እንደሚባለው፣ አምላክ ነኝብሎ በአንድ ቀን ሳያድግ በጥቂቱ ማደጉንና ስደት እንደ ውርደት ሆኖ እንዳይቆጠር ለሰዎች ስደትን ባርኮ ለመስጠት፤ ሄሮድስም ሊገድለው ይፈልገው ስለነበር ወቅቱ የሚሰደድበት እንጂ የሚታይበት ስላልነበረ ነው፡፡

ሁለተኛው፤ ሰው በተፈጥሮም ሆነ በትምህርት አዋቂ ቢሆን ለሚመለከተው ሥራና ደረጃ እስከ ተወሰነ ጊዜ ይህ ሕፃን ለእንዲህ ያለ ማዕረግ ይሆናል አይባልም፤ ተንከባክባችሁ አሳድጉት ይባላል እንጂ ሕፃኑ አዋቂ ነው አይባልም፤ ያውቃል ተብሎም ለትልቅ ደረጃ አይበቃም፡፡ በየትኛውም ኃላፊነት ላይ አይሰጥም፤ ራሱን በመግዛት ይጠበቃል እንጂ፡፡ እንዲሁም ጌታ የመንፈሳዊ እና የሥጋዊ ባለሥልጣን ቢሆንም ፍፁም ሰው ሆኗልና የሰውን ሥርዓት ከኃጢአት በቀር ለመፈጸም በበሕቀ ልሕቀ፤ በየጥቂቱ ዐደገ ይላል፡፡ አምላክ ነኝና ሁሉን በዕለቱ ልፈጽም ሳይል በየጥቂቱ ማደጉን እናያለን፡፡ በዚህም የተነሣ ሰው ሁሉ ፴ ዓመት ሲሆነው ሕግጋትን እንዲወክል እንዲወስን እስከ ፴ ዓመት መታገሡ ስለዚሁ ነው፡፡ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን ሰው ቢመቸው ይወፍራል፤ ቢከፋው ይከሳል እንጂ ቁመት አይጨምርም፤ አይቀንስም፡፡ ስለዚህ ጌታ ሙሉ ሰው የ፴ ዓመት አዕምሮው የተስተካከለለት ሰው (ጎልማሳ) ሆኖ በመታየቱ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

ሦስተኛው፤ በ፴ ዓመት እሱ ሊጠመቅበት ሳይሆን የመጀመሪያ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት መሠረት የሆኑ ጥምቀትንና ጾምን ሠርቶ በማሳየትና መመሪያ አድርጎ በመስጠት እሱ ሙሉ ሰው ሆኖ ተገልጾ የቃሉን ትምህርት ለመስማት፤ የእጁን ተአምራት ለማየት ይከተለው ለነበረው አምስት ገበያ ያህል ሕዝብ  ትምህርት፣ ተአምራት ያደረገበት፤ ሥራዬ ብሎ የመጣበት መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት የፈጸመበት ዘመን በመሆኑ ነው፡፡  የታየውም ብቻ አይደለም፤ አብ ‹‹ይህ የምወደው ልጄ ነው፤›› ሲል መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ረቂቁ የታየበት የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠበት ስለሆነ ‹‹ዘመነ አስተርእዮ›› ተብሏል፡፡

በአስተርእዮ ሌሎች በዓሎችም ይጠሩበታል፡፡ ለምሳሌ ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይቶ በደመና ተነጥቃ ወደ ገነት በመግባት ለጻድቃን ሰዎችና ለመላእክት በሰማይና በምድር የተሰጣት ጸጋና ክብር የተገለጸበት ዕለት ስለሆነ በዓሉ ‹‹አስተርእዮ ማርያም›› ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ አምላክ በሥጋ ከድንግል መወለዱን በዚህ አካለ መጠን ለዓለም መገለጡን አስተርእዮ ብሎ ሲናገር፤ አባ ጽጌ ብርሃን ደግሞ በማኅሌተ ጽጌ እግዚአብሔር ጽጌ ትንቢት ለቢሶ ሥጋኪ ሥጋ ዚአነ፤ አመ አስተርአየ በምድር ወተአምረ ለነ፤ ንዌድሰኪ እንዘ ንብል ምክሐ ዘመድነ፤ ዮም በፍሥሓ ለማርያም እምነ፤ አስተርእዮ በሰማይ ኮነ፤ የትንቢት አበባ እግዚአብሔር እኛን ሥጋ የሆነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንዲታወቅ ድንግል ሆይ የወገናችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለቅድስት ማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግናለን›› ብሏል፡፡ ዳዊትም እንዲህ አለ ‹‹በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ፤ እንደ ሰማን እንዲሁ አየን››፡፡ (መዝ. ፵፯፥፰) በነቢያት ይወለዳል ሲባል የሰማነው በበረት ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው እንዲሁም በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አየነው፡፡