ገብር ኄር

መምህር ሶምሶን ወርቁ

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር የተሰየመው በቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ለሰው ሁሉ የማገልገያ ጸጋ መሰጠቱን፣ ሰጪው እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን፣ ቅን አገልጋዮች ስለሚቀበሉት ዋጋ ፣ ሰነፍ አገልጋዮች ስለሚጠብቃቸው ፍርድ ይሰበካል፡፡ «ገብር ኄር ወገብር ምእመን ዘአሥመሮ ለእግዚኡ፤ ጌታውን ያስደሰተው አገልጋይ ታማኝና ቸር አገልጋይ ነው፤መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ቸር አገልጋይ ማን ነው?» እያሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይዘምራሉ፤ በቅዳሴው ደግሞ የማቴዎስ ወንጌል ፳፭፤፲፬-፴ ይነበባል።

. የምሳሌው ትርጉም

የመክሊቱ ባለቤት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ባለ አምስት፤ ባለ ሁለትና ባለ አንድ መክሊት የተቀበሉት በጥምቀት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ፤ተምረው የሚያስተምሩ መምህራን ናቸው፡፡ የስጦታው መለያየት መበላለጥን ለማሳየት ሳይሆን የአንዱ ጸጋ ከሌላው እንደሚለይ የሚያጠይቅ ነው፤ «መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ   ልዩ ነው፡፡ ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ» ፩ቆሮ ፲፪፥ ፬፡፡

ባለ አምስትና ባለ ሁለት መክሊት የተባሉት አገልጋዮች ቃለ እግዚአብሔርን ከተማሩ በኋላ መክረው አስተምረውና ራሳቸውን አስመስለው ያወጡ ናቸው፡፡ ባለ አንድ መክሊት የተባለው ዐላውያን ነገሥታት፤ ዐላውያን መኳንንት እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ፣መናፍቃን ተከራክረው ቢረቱኝ፣ ምላሽ ቢያሳጡኝ፣ ሃይማኖቴን ቢያስቱኝ ብሎ ከማገልገል ይልቅ ሃይማኖቱን የማያስተምርና የማይመሰክር ነው፡፡  «ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ» ብሏል፤ ማቴ ፲፤፴፪ ፡፡ ስለዚህ በተሰጠን መክሊት በተባለ ጸጋ በሰው ሁሉ ፊት በማገልገል ልንመሰክር ይገባል፡፡

አምስትና ሁለት መክሊት የተቀበሉ አገልጋዮች ጠባይ

እነዚህ አገልጋዮች ለጌታቸው ታማኝ የነበሩ፤ በተቀበሉት መክሊት ወጥተው፤ ወርደውና አትርፈው የተገኙ ናቸው፡፡ መክሊታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በእምነት ሊሰማሩ ወጡ እንጂ በሥጋት እጅና እግራቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፡፡ እነርሱም በተሰጣቸው መክሊት መጠን በእምነት በማገልገላቸው ሁለቱም ገብር ኄር (ቸር አገልጋይ) የሚል የክብር ስም ተሰጣቸው፤ «ወደ ጌታህ ደስታ ግባ» የሚለውን የምሥራች ቃል ሰሙ፡፡

. አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ጠባይ

እምነት የጎደለው ተጠራጣሪ ነበረና ማትረፉን ሳይሆን መክሰሩን፣ ማግኘቱን ሳይሆን መድከሙን፣ ብቻ አሰበ፡፡ በተቀበለው መክሊት ባለማትረፉ ራሱን ከመውቀስ ይልቅ ሰጪውን ጌታ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው ብሎ የጽርፈት ንግግርን ተናገረ፡፡ ጌታው አስቀድሞ መክሊቱን ሲሰጠው አልቀበልም ሳይል ምን ሠራህና ምን አተረፍህ ሲባል ጌታውን ከሰሰ፡፡ ልቡ የደነደነ፣ጥፋቱን ለማመን የማይፈቅድ፣ለመመለስ የዘገየ ነበረና ወደ ውጭ ልቅሶ፤ ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት አውጡት የሚለውን የፍርድ ቃል ሰማ፡፡ ዛሬ መልካም ሥራ ላለመሥራታቸው ምክንያት የሚያበዙ፣ ሃይማኖታቸውን ለመመስከር የሚያፍሩ፣ የሚፈሩና ኀጢአት ለመሥራት ግን የሚደፍሩ ሰዎች ባለ አንድ መክሊቱን አገልጋይ ይመስላሉ፡፡ እንግዲህ «በጎ ነገር ማድረግን የሚያውቅ፤ የማይሠራትም ኀጢአት ትሆንበታለች» ተብሏልና፤ያዕ ፬፥፲፯፡፡

ለአገልግሎት ተፈጥረናል

እግዚአብሔር ሰውን በአርአያው ፈጥሮ፤ በልጅነት ጸጋ አክብሮ፤ ሁሉን አዘጋጅቶ ለአዳም አንድ ልጁን ለመስቀል ሞት ያዘዘው በዓላማ ነው፡፡ ይኸውም «እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ላዘጋጀው በጎ ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ  የፈጠረን ፍጥረቱ ነንና» ኤፌ ፪፥፲፡፡ ለመልካሙ ሥራ ሁሉም ሰው ተጠርቷል፤ በጥምቀት ዳግም የወለደንና በመስቀሉ ያዳነን በመልካም ሥራ እንድናገለግል ነው፡፡

እኛ በመክሊታችን ምን አተረፍን?

ጸጋችንን እናውቃለን? ለማወቅስ እንሻለን? በተሰጠን ጸጋ አትርፈናልን? ካላተረፍን ለምን? በእርግጥ አለማትረፋችን ግድ ይለናል? ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋ ያልተቀበለ የለም፤ ሰው ጸጋውን አለማወቁ አልተቀበለም፤ ጸጋ የለውም አያሰኝም፡፡ ከሁሉ አስቀድመን ጸጋ እንደ ተሰጠን ማመን ይጠበቅብናል፡፡ የተሰጠንን ጸጋ ለማወቅ ለሕይወታችን በሚጠቅም አገልግሎት  ራሳችንን መፈተን መሞከር ይጠበቅብናል፤ ሳንሰማራና ራሳችንን ሳንፈትን ጸጋችንን ማወቅም ሆነ ማትረፍ አይቻልም፡፡ ጸጋ እንደተሰጠን አምነን ስንረዳና ራሳችንን ለአገልግሎት ስናዘጋጅ ማትረፊያ አገልግሎቱን መመልከት እንችላለን፡፡ በምን ማገልገል እዳለብን አለማወቅ አገልግሎትን ውስን አድርጎ መመልከት፣ለአገልግሎት መዘግየትና እንዴት ማገልገል እንዳለብን አለመረዳት ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ፡-

ሀ) በምን እናገልግል?

አንዳንዶች ምን ጸጋ ኖሮኝ ነው የማገለግለው? ሲሉ ይሰማሉ፤ ነገር ግን ከጸጋ እግዚአብሔር የጎደለ ሰው የለም፡፡ «መንፈስ ግን አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው፤ ጌታም አንድ ሲሆን  ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የጥበብ ቃል የሚሰጠው አለ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም የዕውቀት ቃል የሚሰጠው አለ፡፡ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፤ ለአንዱም ተኣምራትን ማድረግ፤ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፤ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፤ለአንዱም በልዩ አይነት ልሳን መናገር፤ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል» ይላል፤፩ቆሮ ፲፪፥፬–፲፡፡ ስለዚህ በአለን ጸጋ ማገልገል ይገባናል፡፡

ለ) አገልግሎት ውስን ነውን?

አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን፤ በበዓላትና በአጽዋማት ብቻ የሚመስላቸው፣ ካልቀደሱና ካላወደሱ፣ ካልዘመሩና ካላስተማሩ አገልግሎት የሌለ የሚመስላቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ነገር ግን አገልግሎት በጊዜና በቦታ፤ በሁኔታም ሆነ በዓይነት አይወሰንም፡፡ «ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ፤ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ፤ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» ፩ጴጥ ፪፥፭፡፡ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ስንሆን ሕዋሳቶቻችን እግዚአብሔርን የምናገለግልባቸው ንዋየ ቅድሳት ናቸው፡፡ በዐይናችን ቅዱሳት መጻሕፍትን ስናነብ፣ በጆሮአችን የተገፉትንና የተቸገሩትን ሰዎች ጩኸት ስንሰማ፣አፋችንን ለጸሎት ለምስጋና ስንክፈት፣ እጆቻችን ለአሥራት በኩራት ለምጽዋት ሲዘረጉ፣እግሮቻችን ማልደው ወደ ቤተክርስትያን ለጸሎት ሲገሰግሱ፣መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እየሠራን እያገለገልን ነው፡፡ በጊዜያችን የታመሙትንና የታሰሩትን ብንጠይቅ፣ በጉልበታችን ደካሞችን ብንረዳ፣ በዕውቀታችን ያላወቁትን ብናሳውቅ ፣ በገንዘባችን የተቸገሩትን ብንጎበኝ፤ በጸጋ ላይ ጸጋና በበረከት ላይ በረከት እናተርፋለን፡፡ ወደ ጌታ ደስታ ግቡ የሚለውን የምስራች ቃል እንሰማለን፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንሆናለን፡፡

ሐ) ለአገልግሎት ብንዘገይስ?

አንዳንድ ሰዎች ማገልገል እንዳለባቸው ቢያውቁም ለውሳኔ ይዘገያሉ፡፡ «ዛሬ ወይም ነገ ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን ፤ በዚያችም ዓመት እንኖራለን፤ እንነግዳለንም፤ እናተርፋለንም፤ የምትሉ እናንተ ተመልከቱ፤ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና» ያዕ ፬፥፲፫-፲፬፡፡ ዛሬ እንኑር ነገ ስለማናውቅ የኛ የሆነውን ተረድተን ልናገለግል ይገባል፡፡ «ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች» ዮሐ፤፱፥፬፡፡ ሌሊት የተባለው ዕለተ ሞትና ዕለተ ምጽአት  ነው፤ በሞት ከተጠራን በኋላ ልማር ላስተምር፣ ልወድስ ልቀድስ፣ ላጉርስ ላልብስ ማለት የለምና ለአገልግሎት ልንፈጥን ይገባል፡፡

መ) እንዴት እናገልግል?

ማገልገል አንድ ነገር ሆኖ ሳለ እንዴት ማገልገል እዳለብን ካልተረዳን አገልግሎታችን ያለእምነት የተሟላ አይሆንም፡፡ «ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም» ዕብ ፲፩፥፮፡፡ ሰማያዊ ዋጋን እያሰብን እናገልግል፤ «ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን?» ሮሜ.፰፥፴፭፡፡ ሰማያዊውን ዋጋ ስናስብ በፈተና በመከራ እንጸናለን፤ በትሕትና  ሆነን እናገልግል «ከእኔ ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና» ብሏል፤ ማቴ ፲፩፡፳፱፡፡

እንግዲህ መክሊት የተቀበሉትን አገልጋዮች ስናስብ፤ አምስትና ሁለት መክሊት የተቀበሉ፤ ለጌታቸው ታማኝ የነበሩ፤ በተቀበሉት መክሊትም መከራን ታግሰውና በእምነት በማገልገላቸው ሁለቱም ገብር ኄር (ቸር አገልጋይ) ተባሉ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ እምነት የጎደለው ተጠራጣሪ ነበረና ማትረፉን ሳይሆን መክሰሩን ብቻ የሚያስብ ደካማ፤ የተፈጠረበትን  ዓላማና የተሰጠውን ተልእኮውን ያልተረዳ ሰው ነበር። እኛም በጥምቀት ዳግም የተወለድነውና በመስቀሉም የዳንነው ተልእ£ችንን ተረድተን በመልካም ሥራና በታማኝነት እንድናገለግል ነው፡፡ ቀደምት ቅዱሳን አባቶቻችንን አርአያ በማድረግ ለምን፤ በምንና እንዴት ማገልገል እዳለብን ልንረዳ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወወላዲቱ ድንግል፤ ወመስቀሉ ክቡር!