‹‹ሰላም ለኒቆዲሞስ ለወልደ ማርያም ዘአምኖ››

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዚያ 5/2011 ዓ.ም.
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት፣ ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል ሰባተኛው ሳምንት በኒቆዲሞስ ተሰይሟል፡፡ ሳምንቱ በስሙ ከመጠራቱም ባሻገር በቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው ትምህርትም ኒቆዲሞስ ከጌታ የተማረዉን ምሥጢረ ጥምቀት መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ እንደሚገባው ያትታትል፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ ምዕራፍ ፲፮ ቍጥር ፲፮ ላይ ‹‹ያመነ፣ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ፣ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፤›› በማለት ያስተማረው ትምህርትም ከዚህ መልእክት ጋር የሚስማማ ነው፡፡

ወደ ርእሰ ጉዳያችን ስንመለስ ኒቆዲሞስ፣ ከፈሪሳውያን ወገን የተገኘ የአይሁድ መምህር የነበረ ሰው ነው (ዮሐ. ፫፥፩)፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ ላይ እንደ ተጻፈው ሌሊት ወደ ጌታችን እየመጣ ቃለ እግዚአብሔር ይማር ነበር፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ ላይ እንደ ተገለጸው፣ ጌታችንን ያልተቀበሉ የአይሁድን ምክር ንቆ፣ ዐመፃቸዉንም ርቆ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን አምኖ ይከተለው ነበር፡፡ ከከሃድያንና ከመናፍቃን ማኅበር ተለይቶ እግዚአብሔርን ማምለክ እንሚቻል ኒቆዲሞስ ያስተምረናል፡፡ ይህ መምህር፣ ቀን ቀን አይሁድን ሲያስተምር፣ ሲመክር፣ ሲገሥፅና ሲያወያይ እየዋለ፤ ማታ ማታ ደግሞ ከአይሁድ ተደብቆ ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየሔደ እግዚአብሔርን ያመልክ፤ ቃለ ወንጌልንም ይማር ነበር፡፡ ወንጌልን በትጋት ከመማሩም ባሻገር ትምህርቱን ተቀብሎ በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምኗል፤ አምኖም ለሌሎች መስክሯል፡፡ ክርስትና ማወቅና ማመን ብቻ ሳይሆን አምኖ መመስከርና ያላመኑትንም ማሳመን መሆኑን ከኒቆዲሞስ ሕይወት እንማር፡፡

ኒቆዲሞስ ቀን ቀን ከአይሁድ ጋር እየዋለ ማታ ማታ ደግሞ ከጌታችን ወንጌልን መማሩ ለእኛ ብዙ ትምህርት የሚሰጥ ምሥጢር አለው፡፡ በአካባቢያችን ወይም በምንሠራበት መሥሪያ ቤት አብረዉን የሚኖሩ (የሚሠሩ) ሰዎች በሃይማኖት ወይም በአመለካከት ላይመስሉን ይችላሉ፡፡ በምናልመከው በእግዚአብሔር የማያምኑ፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የሚኰንኑ፣ የሚነቅፉ፣ የሚቃወሙ እንዳውም ለማጥፋት የሚተጉ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ብንከተላቸው የሚሔዱበት መንገድ አያዋጣም፡፡ ብንቃወማቸው ወይም ብንገሥፃቸው ደግሞ ለሕይወታችን አሥጊ ፈተና ይገጥመናል፡፡ ምን ማድረግ ይቻለናል? መፍትሔዉን ከኒቆዲሞስ እናገኘዋለን፡፡

እርሱ ክርስቶስን ከሚቃወሙት ከፈሪሳውያን ወገን የተገኘ ነው፡፡ በሥራው ደግሞ ክርስቶስን ለመግደል የሚመክሩ ካህናተ አይሁድ መምህር ወይም አለቃ ነው፡፡ ዳሩ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ተገልጦለት በአምላክነቱ አምኗል፤ በትምህርቱም ተማርኳል፡፡ በዚህ ውሳኔው ከዘመዶቹም ከባልንጀሮቹም ጋር መስማማትም መኖርም አይችልም፡፡ ኒቆዲሞስ ምን ማድረግ እንዳለበት ከሕሊናው ጋር መከረ፤ መክሮም አንድ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ቀን ቀን እነርሱን መስሎ እየዋለ ማታ ማታ ደግሞ ወንጌልን እየተማረ ለፈጣሪው ሲሰግድ ያድር ነበር፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ ኒቆዲሞስ በኑሯችን እግዚአብሔርን አጥብቀን መያዝ ይገባናል፡፡ ከዚህም ሌላ ሥርዓተ አምልኮን፣ በጎ ምግባርን ለመፈጸም ወይም ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር ‹‹እዩኝ እዩኝ፤ ዕወቁልኝ ዕወቁልኝ›› ማለትን ትተን ጽድቅን በስውር መፈጸም እንደሚገባን ከኒቆዲሞስ ሕይወት መማር አለብን፡፡

የሚደንቀው ነገር ኒቆዲሞስ ከጌታችን ወንጌልን ለመማር ብቻ ሳይሆን በዕለተ ሞቱ ተገኝቶ ለመገነዝም በቅቷል (ዮሐ. ፲፱፥፴፱)፡፡ የኒቆዲሞስ በዓለ ዕረፍቱ በሚዘከርበት በነሐሴ ፩ ቀን ስንክሳር እንደ ተገለጸው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ችንካሮቹን ነቅለው፣ ቅዱስ ሥጋዉን ከመስቀል ላይ አውርደው፣ በትከሻቸው ተሸክመው ክብር ይግባውና የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋ በሚገንዙበት ጊዜ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት …›› የሚለዉን ጸሎተ ኪዳን ከጌታችን ክቡር ሥጋ ሰምተዋል፡፡ ይህ ጸሎተ ኪዳን ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን በነግህም፣ በቀትርም፣ በሠርክ የሚቀርብ ልዩ ጸሎት ነው፡፡ ስለዚህ ኒቆዲሞስ ከጌታችን ከመማሩና ቅዱስ ሥጋዉን ገንዞ ከመቅበሩ ባሻገር ልዩ የሆነ የሕይወት ቃልን ከእግዚአብሔር ለመስማትም ታድሏል፡፡ እግዚአብሔርን መከተል የሕይወት ቃልን ለመስማት ያበቃልና፡፡

በነሐሴ ፩ ቀን አርኬ፡- ‹‹ሰላም ለኒቆዲሞስ ለወልደ ማርያም ዘአምኖ፡፡ ከመ እምኀበ አብ መጽአ ለምሕረት ወለአድኅኖ፡፡ በዕለተ ተሰቅለሂ እንዘ ይከድን ዕርቃኖ፡፡ ለዮሴፍ ቢጾ ወሱታፌሁ ከዊኖ፡፡ ምስለ አፈዋት ገነዘ ወቀበረ በድኖ፡፡›› ተብሎ የኒቆዲሞስ ጸጋ ተመሥጥሯል፡፡ የአርኬው ትርጉምም ኒቆዲሞስ፣ ወልደ አብ ወልደ ማርያም የተባለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን እንደ መጣ ማመኑን፣ በመስቀል ላይ በፈቃዱ በሞተ ጊዜም ከዮሴፍ ጋር ሆኖ በድኑን ለመገነዝና ለመቅበር መታደሉን፤ እንደዚሁም ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ ለተከተለ፣ በሞቱ ጊዜም ገንዞ ለመቅበር ለተመረጠ ለኒቆዲሞስ ሰላምታ ማቅረብ ተገቢ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ እኛም ከልጅነት ጀምሮ ለእግዚአብሔር መገዛት ከሞት በኋላም ቃለ ሕይወትን ለመስማት፣ መንግሥቱን ለመውረስ እንደሚያበቃ ተገንዝበን እንደ ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው እግዚአብሔርን እንከተል፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን በጨለማ ወይም በኀጢአት የሚኖር ሰው ብርሃንን ማለት ጽድቅን ይጠላል፤ ይሸሻል፡፡ ሥራው እንዳይገለጥበትም ይደበቃል፡፡ ኒቆዲሞስ ግን በስውር ይሠራ የነበረው ኀጢአትን ሳይሆን ሃይማኖታዊ የጽድቅ ምግባርን ነው፡፡ እኛ ደግሞ ተደብቀን የምንሠራው ኀጢአትን ነው፡፡ ሰው ሲያየን ጻድቅ የምንመስል በስውር ግን የምንበድል አስመሳዮች ጥቂት አይደለንም፡፡ አንዳንዶቻችን ነጠላ ለብሰን እንጓዛለን፤ በንጽሕና ግን አንኖርም፡፡ መኖርም አንፈልግም፡፡ ጽድቅ ደግሞ ካልፈለጓት አትገኝም፡፡ ትልቅ መስቀል አንገታችን ላይ አንጠልጥለን እንታያለን፤ በመስቀሉ ቃል ግን አንኖርም፡፡ የሚገርመው ነገር መስቀል ያለበትን ማተብ በአንገታችን አስረን የምንታይ በግብራችን ግን ጨለማን ተገን አድርገን በየመጠጥ ቤቱ የምናድርና የምንሰክር፣ ከዚህ ባለፈም በዝሙት የምንኖር ምእመናንም በየቦታው አለን፡፡ እግዚአብሔር እንደ ኒቆዲሞስ ልቡናችንን ወደ እርሱ ይመልስልን እንጂ!

ሰዎችን የምናሳድድ፣ ባልንጀሮቻችንን የምናስለቅስ፣ ቤተሰቦቻችንን የምንበድል ነገር ግን ጻድቃን ነን ወይም ክርስቲያኖች ነን የምንል ሰዎች አለን፡፡ በአጠቃላይ ክፉ ሥራችንን እንደ በጎነት የምንቆጥር ሰዎች ብዙዎች ነን፡፡ ኀጢአት ልቡናን ያጨልማልና፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ እንዲህ በማለት ያስተማረን፤ ‹‹በብርሃን ውስጥ አለሁ የሚል ወንድሙን የሚጠላ ገና እስካሁን በጨለማ ውስጥ አለ፡፡ ወንድሙን የሚወድ ግን በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱ ዘንድም መሰናክል የለበትም፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ግን እርሱ በጨለማ አለ፤ በጨለማም ይመላለሳል፤ የሚሔድበትን አያውቅም፤ ጨለማው ዐይኑን አሳውሮታልና፤›› (፩ኛ ዮሐ. ፪፥፱-፲፩)፡፡

በስውር በሚፈጸም ኀጢአት የምንኖር ሁሉ ኀጢአተኛ መስሎ በጽድቅ ሥራ መኖርን ከኒቆዲሞስ ሕይወት እንማር፡፡ ኀጢአትን በመሥራት የጨለማ ሕይወት የምንኖር ሁሉ፣ እንደ ኒቆዲሞስ የብርሃኑን ጌታ በስውር ጽድቅ ወይም በሱባኤ እንፈልገው፡፡ ያን ጊዜ ከማስመሰል የኀጢአትና የጨለማ ሕይወት ወጥተን በክርስቶስ ብርሃንነት መመላለስ እንችላለን፡፡ ብርሃን እግዚአብሔርን፣ ብርሃን ክርስትናን፣ ብርሃን ምግባረ ጽድቅን ይዘን በኀጢአት ምክንያት ከሚመጣ ጨለማ ወጥተን በሕይወት እንኑር ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡ ‹‹… ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፡፡ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንደሚሔድ አያውቅም …፤›› ተብሎ ተጽፏልና (ዮሐ. ፲፪፥፴፮ )፡፡ ርቱዐ ሃይማኖትም ሰዉን መውደድና እግዚአብሔርን መፍራት ከኒቆዲሞስ የምንማራቸው ቁም ነገሮች መሆናቸዉን በኒቆዲሞስ ሳምንት በሚነበበው ድርሳኑ አስፍሯል፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከተገለጠላቸው ከሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች አንዱ ኒቆዲሞስ እንደ ነበረ ያስተምራሉ (ትርጓሜ ወንጌል፣ ሉቃ. ፳፬፥፲፫)፡፡ በእውነት ይኼ ሰው እግዚአብሔርን ለማየት የታደለ ደግ መምህር ነበር፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ሰላም ለኒቆዲሞስ ለወልደ ማርያም ዘአምኖ …፤ የቅድስት ድንግል ማርያምን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ላመነው ለኒቆዲሞስ ሰላምታ ይገባል፤›› እያለች ስሙን በማክበር የምትጠራው፡፡ በሃይማኖት፣ በበጎ ምግባር መኖር በጎ ስም ያስገኛልና፡፡ እንደ ኒቆዲሞስ በሃይማኖትና በበጎ ምግባር ጸንተን እግዚአብሔርን ለማየት፣ መንግሥቱንም ለመውረስ ያብቃን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡