የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የዋጀ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለዓመታዊው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

‹‹ወይእዜኒ ረዐዩ ዘሀለዉ ኀቤክሙ መርዔቶ ለክርስቶስ፤አሁንም በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ (፩ኛ ጴጥ. ፪፥፮)

እግዚአብሔር አምላካችን የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ፣ ጠባቂ፣ መጋቢ፣ አስተናባሪና አስተዳዳሪ ነው፤በሰማይና በምድር ያለው የሚታየውና የማይታየው ፍጥረታት በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ጥበቃና አስተዳደር ሥር ነው፤

ፍጡራን ከእርሱ በተገኘ የአእምሮ ነጻነት በሚፈጽሙት ተግባር የራሳቸው ድርሻና ኃላፊነት እንዳላቸው ቢታወቅም ያለ እርሱ ዕውቅና የሚደረግ እንደሌለ ግን ከቅዱስ መጽሐፍ እንማራለን፡፡

እንግዲህ እርሱ የጠባቂዎች ጠባቂ ሆኖ ሳለ ከፍጡራን ወገን ደግሞ በልዩ ምርጫው እየሾመ መንጋውን ወይም ፍጥረቱን ያስጠብቃል፤ ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የእግዚአብሔር አሠራር እንደሆነ ቅዱስ ያሬድ ሲገልጽ ‹‹ኢኃደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት አንሥቶ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ምድርን ያለ ካህናት እና ያለ ዲያቆናት አልተዋትም›› በማለት ያደረጋግጣል፡፡

ይህ የሚያመለክተን እግዚአብሔር ዓለምን ያለ ጠባቂ የተወበት ዘመን ካለመኖሩም ሌላ ጠባቂዎቹ ካህናትና ዲያቆናት መሆናቸው ነው፤ካህናት የሚለው ስያሜ የወል ስም ሆኖ ከቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ያለው ውሉደ ክህነት በሙሉ እንደሚያጠቃልል ይታወቃል፡፡

ከዚህ አኳያ ኰኵሐ ሃይማኖት ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን በተሰጠው የጥበቃ ኃላፊነት መሠረት እርሱም በክህነት ለወለዳቸው ልጆቹ በፈንታው ‹‹መንጋውን ጠብቁ›› እያለ ምእመናንን ሲያስጠብቅ እናያለን፡፡ ትልቁ የእግዚአብሔር ትእዛዝና የቤተ ክርስቲያን ተልእኮም ይህ የጥበቃ ተግባር ነው፡፡

እግዚአብሔር እኛ ካህናትን በኃላፊነት የሾመበት ዋና ዓላማ መንጋውን እንድንጠብቅለት ነው፤ ይህ መንጋ ተብሎ የተገለጸው ወገን የተለየ ሕዝብና ጎሳ ሳይሆን ለትዝምደ ሰብእ ወይም የሰው ዘርን በሙሉ ነው፡፡ በራሱ እምቢተኝነት ከሚቀርበት በስተቀር የጌታችን ጥሪ ለትዝምደ ሰብእ በሙሉ እንደሆነ ‹‹ሑሩ ወስብኩ ወንጌለ ለኵሉ ፍጥረት፤ ሒዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ›› በማለት አሳውቆናል፡፡

እንዲሁም ከሆነ ጠብቁ ተብለን የታዘዝነው ያመኑት ወይም የተጠመቁትን ብቻ ሳይሆን ያለመኑትንም፣ ያልተጠመቁትንም በአጠቃላይ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡

ከዚህ አንጻር መንጋችንን ስንጠብቅ ያመኑትን በነፍሳቸውም በሥጋቸውም ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የተሟላ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ፣ ያላመኑትንም በፍቅር በማቅረብና ዘመድ ዘመድ በማለት፣ ውሳጣዊና መንፈሳዊ ስሜታቸውን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በማነቃቃትና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በማምጣት እንደሆነ ለሁላችን ግልጽ ነው፡፡

ሆኖም ይህን የጥበቃ ሥራ በአግባቡ ለማሳካት ትልቁ ትጥቃችን ቅዱስ ወንጌል እንደሆነ ምንጊዜም መዘንጋት የለብንም፡፡ ቃለ ቅዱስ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ የተለያዩ ዘዴዎችና አቀራረባችን፣ ሥልጠናዎችንና አስተምህሮቶችን መጠቀምና በዚህ የባዘነውን በግ ወደ መንጋው የምንመልስበት ታሪካዊና ወቅታዊ ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ የሚባክንኑ እና በተኩላ የሚነጠቁ በጎች በእጅግ እየተበራከቱ ነው፤ ዛሬ ሁሉን ነገር መልካም ነው ብለን የምንዘናጋበት ጊዜ ሳይሆን የጎደለውን ለመሙላትቃል የምንገባበት ያኑንም በተግባር ፈጽመን በጎቻችንን የምንሰበስብበት ጊዜ ነው፡፡

በዚህ አኳኋን በንቃትና በትጋት በኃላፊነትና በቁጭት ከሠራን ከባዘኑት በጎች መካከል ብዙዎችን ወደ መንጋው መመለስ እንደምንችል፣ ያሉትንም ባሉበት ጸንተው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

የጥበቃ ተግባራችን ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ከውስጥ ጥቅመኞች የተነሣ ተደጋጋሚ እንቅፋት በበዛበት በአሁኑ ጊዜ ‹‹በእንቅርት ላይ …›› እንደሚባለው በሀገራችን በተፈጠረው ያለመረጋጋት ክስተት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ካህናትና ምእመናን ተገድለዋል፤ አሁንም ስጋቱ እንዳለ፣ ከቀረበልን የአህጉረ ስብከት ሪፖርት ሰምተናል፤በዓይናችንም አይተናል፤ ነባር የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታዎች ሥልጣንን መከታ ባደረጉ ወገኖች እየተነጠቁ ነው፤ምእመናን በሚደርስባቸው የማያባራ ተጽእኖና አድሎ ከቀያቸው እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ነው፡፡

ለመሆኑም እንዲህ ዓይነቱ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው? ይህ ድርጊት እንዲቆም እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕት መሆን ከዚህ ጉባኤ አባላት ይጠበቃል፡፡ ይህ ጉባኤ የኃያሉ የእግዚአብሔር ጉባኤ ነው፤ ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብቻ ከሰባ ሚሊዮን ያላነሰ ሠራዊት ያለው ጉባኤ እንጂ ብቻውን አይደለም፤ ይህ ጉባኤ በሙሉ አቅሙ ሥራውን ከሠራና ድምጹን ካነሣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ሰሚው ብዙ ነው፡፡

ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በታችኛውም የመንግሥት መዋቅር እየደረሰብን ያለውን የማንታገሰው ግፍ መንግሥት እንዲያስተካክልን ደጋግመን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እኛም በጸሎት አምላካችንን ከመማጸን ጋር ሁሌም በተጎጂው ሕዝባችን መካከል እየተገኘን በልዩ ልዩ ግፍ ልባችን የተሰበረውን የልጆቻችን ኃዘን መቅረፍ ይኖርብናል፡፡ ችግራቸውንም ማጋራት ይጠበቅብናል፤ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያትን እንደገና መገንባት አለብን፤ መንግሥትም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሃይማኖት ክብር ነፃነትና እኩልነትን በሚሸረሽሩ የታችኛው መዋቅር ባለ ሥልጣናት ላይ የማያዳግም የእርምጃ ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥብቅ ክትትል ማድረግ አለብን፡፡

የመንጋ ጥበቃችን ሥራ እየተሰነካከለ የሚገኘው ከውጭ ሆነው በገንዘብ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ እርስ በእርሳችን በመከፋፈል በሚተነኩሱን ኃይሎች ብቻ አይደለም፤ በውስጣችን ያለው ያልዘመነ አሠራርም የምእመናንን ልቡና እያቆሰለ የሚገኝ ሌላው የጥበቃችን እንቅፋት ነው፤ በመሠረቱ ይህንን ችግር ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማጽዳት ማስተካከል ካልቻልን ችግራችን በወሳኝ መልኩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡

በመሆኑም ቀደም ሲል የተጠኑትን የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ችግር መፍትሔና የመሪ ዕቅድ ጥናቶች ይህ ዐቢይ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአስቸኳይ ይተገብር ዘንድ ጠበቅ ያለ መመሪያ ሊያስተላልፍ ይገባል፡፡ ከእንግዲህ
ወዲህ በብልሹ አሠራር አዙሪት የሚታመስ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ሊኖር አይገባም፤ በዚህ ዓመት አሠራራችንን ሁሉ አስተካክለን ወደ
መንጋ ጥበቃና ወደ ልማት ሥራችን በፍጥነት መሸጋገር አለብን፡፡

በመጨረሻም፡-

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ዙሪያ መለስ ጥቃት ለመመከትና ለመከላከል ብሎም ለማስቆም አንድ የጥቃት መከላከል ግብረ ኃይል እንዲሁም በየአካባቢው የሚሰነዘሩት ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ ተጽእኖዎችና አድሎአዊ አሠራሮችን እየተከታተልን ትክክለኛ ኢንፎርሜሽንን የሚያቀርብ የኮሙኒኬሽን ግብረ ኃይል በአሁኑ ጉባኤያችን አቋቁመን ቤተ ክርስቲያናችንንና መንጋችንን ከመከራ እንድንታደግ የሀገራችን ሰላምና የሕዝባችንን አንድነትን በጽኑ እንድናስጠብቅ አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን፣ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ