‹‹ተገሐሥ እምዕኲይ ወግበር ሠናየ፤ ከክፉ ነገር ራቅ ሰላምን ፈልጋት›› (መዝ. ፴፫፥፲፪)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሥራቿ አምላኳ የሰላም አባትና አለቃ የሆነው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደመሆኑ በጸሎቷና በአገልግሎቷ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ሕዝቦቿ ስለ መላው ዓለም ሰላም ዘወትር ወደ አምላኳ ስታማጽንና ስትማልድ የኖረች ያለችና ወደፊትም የምትኖር የሀገር ባላውለታና የሁሉም እናት መሆኗ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች የአማራና የቅማንት፣ የሱማሌና የአፋር፣ የአማራና የትግራይ፣ የኦሮሞና የአማራ፣ የጉምዝና የአማራ፣ የሲዳሞና የወላይታ በሚል ብሔርና ሃይማኖት እንዲሁም ቋንቋን መሠረት ያደረገ በኢትዮጵያ ሀገራችን እንኳንስ ሊደረጉ ይቅርና ሊታሰቡ የማይገባቸው መጠነ ሰፊ ግጭቶች በመከሰታቸው የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ በርካታ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ከቀያቸው አለአግባብ እየተፈናቀሉ ለከፋ እንግልትና እርዛት ተዳርገዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በግጭቶች እየደረሱ ካሉት የሰው ሕይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ልንማር ባለመቻላችን በያዝነው ሳምንት ችግሩ ቀጥሎ በአዲስ አበባ፣ በኦሮምያ ክልልና በሌሎችም ክልሎች እየተከሰተ ያለው ግጭት እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ ጊዜ የማይሰጥና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንንድነትና በሕብረት ችግሩን ካልቀረፍነው መጠነ ሰፊ ጉዳትን የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ በሀገራችን ያሉ ጅምር የልማትና የእድገት ጉዞዎችን በመግታት ሀገሪቱን ለከፍተኛ ጥፋትና ድኅነት የሚዳርግ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ዓመታዊ ስብሰባውን በማካሔድ ላይ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስለ ሀገር ሰላም ቅድሚያ በመስጠትና ከሌሎች የመወያያ አጅንዳዎች በማስቀደም በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያየን በኋላ ተከታዩን አስቸኳይ የአቋም መግለጫና የሰላም ጥሪ አስተላልፏል፡፡

  1. ማንኛውም የተለየ ሐሳብና አመለካከት ያለው ወገን ቢኖር ሐሳቡን በሰለጠነና በሰከነ መንገድ ሀገራዊ አንድነትን ማእከል ባደረገ ሁኔታ በክብ ጠረጴዛ በመወያየት ችግሮቹ እንዲፈቱና የአሠራር ግድፈቶች ካሉም እንዲታረሙ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፣
  2. የሀገር ተረካቢ የሆናችሁ መላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ከዛሬ ይልቅ ነገ በእናንተ ተተኪነትና በምታከናውኑት የማይተካ የላቀ አስተዋጽኦ ወደላቀ የእድገት ደረጃ ደርሳ እናንተም ሆናችሁ መላው ወገናችሁ ተጠቃሚ የሚሆንባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና እውን ለማድረግ የሀገሪቱን ሙሉ ተስፋ በእናንተ በወጣት ልጆቻችን ትከሻ ላይ የተጣለ መሆኑ ይታወቃል፤ በመሆኑም በወቅታዊና ሚዛናዊ ባልሆነ አንዳንድ ከሕግ ማዕቀፍ የወጡ አካሔዶችን በሰከነ አእምሮ ትኩረት በመመልከት ሀገራችን ኢትዮጵያን ከጥፋትና ካልተገባ ግጭት ትታደጓት ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከአደራ ጋር በአጽንኦት ለእናንተ ለልጆቿ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡
  3. በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተከትሎ ለሀገራችሁ የሚሆን ልዩ ልዩ አማራጭ ሐሳቦችን በማመንጨት ሕጋዊ ዕውቅና አግኝታችሁ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኙ ሁላችሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ፖሊሲ ቀርጻችሁና ያመናችሁበትና ርዕዮተ ዓለም አቅዳችሁ የምትንቀሳቀሱት ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ወደተሻለ የእድገት ደረጃ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ ለመወጣ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከዚህ አንጻር በየጊዜው ዘር፣ ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ከጅምሩ በአንድነት ማስቆም ካልተቻለ ነገ የምትረከቧትና የምታስተዳድሯት ሀገር ልትኖር ስለማትችል በቅድሚያ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገድባችሁ ለሀገር ሰላምና አንድነት በሕብረት ዘብ በመቆም የበኩላችሁን ኃላፊነት ትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪን ያስተላልፋል፡፡
  4. ለመንግሥታችሁና ለሕዝባችሁ ሙያዊ ትንታኔን መሠረት ያደረገ አማራጭ ሐሳቦችን በግብዓትነት በማበርከት የሀገራችንን እድገትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለማበርከት በማሰብ ልዩ ልዩ ጽሑፎችንና ዘገባዎችን በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያ የምታቀርቡና የምታስተላልፉ የፖለቲካ ተንታኞችና አክቲቪስቶች ከስሜት፣ ከብሔር፣ ከቋንቋና ከሃይማኖት ልዩነት በጸዳ ሁኔታ እናት ሀገራችሁን ማእከል በማድረግ ለተሻለ ሰላምና አንድነት የበኩላችሁን ድርሻ ከማበርከት ባለፈ ሕዝብን ከሕዝብ የሚጋጩና አንዳንድ ያልተገቡ ትርክቶችን አላግባብ ከማሰራጨት በመቆጠብ ሀገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን፤
  5. የመንግሥትም ሆነ የግል የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ከተቋቋማችሁበት መሠረታዊ ተልዕኮና ዓላማ አንጻር በተቻለ አቅም ዘርን፣ ቀለምን፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላቶች በመራቅና ሚዛናዊ የሆኑ መረጃዎችን ለሕዛባችን በማድረስ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የበኩላችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ አደራ እንላለን፤
  6. የማኅበራዊ ሚዲያ መሠረታዊ ዓላማው ዜጎች በእውነት ላይ የተመሠረቱ ወቅታዊ መረጃዎችን በተሻለ ፍጥነት እንዲያገኙ ታስቦ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው እውነታ ከዚህ በተለየ መልኩ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር፣ ጎሳን ከጎሳ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩና ከእውነት የራቁ ግጭት ቀስቃሽ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሠራጨት ሀገራችን ኢትዮጵያ የቆየ የአብሮነትና የአንድነት ባሕሏን በሚያጎድፍ መልኩ ላልተገባ ዓላማ እየዋለ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፤ ከዚህ አንጻር ዛሬ በሌሎች ላይ የሚደርሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ነገ በየአንዳንዱ ቤት ሲያንኳኳ ሁሉም የጉዳቱ ሰለባ እንደሚሆን በመረዳት በተቻለ አቅም የማኅበራዊ ሚዲያውን ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት በመጠቀም ሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ሕዝባችን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እንጠይቃለን፤
  7. ሀገር በዕውቀት እና በተሻለ ሐሳብ የምታድግና የምትመራ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር የሀገራችን ምሁራን ያላቸው ድርሻ በቀላሉ ሊገመት የማይችል ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን አንዳንድ ምሁራን የሚያስተላልፏቸው የኢትዮጵያ ታሪክ መሠረት ያላደረጉ ትርክቶች ለሀገራችን የግጭትና ያለመግባባት መንስኤ ሲሆኑ ይስተዋላሉ፡፡ በመሆኑም የሀገራችን ምሁራን በተቻለ አቅም ከልዩነትና ከግጭት ይልቅ ለሀገራዊ አንድነት እና ሰላም ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
  8. በየደረጃው ያላችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መላው ሕዝባችን ትመሩትና ታስተዳድሩት ዘንድ የሰጣችሁን ይሁንታና ሀገራዊ ኃላፊነት ከግምት ውስጥ ባስገባና በታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ስሜት በተቻለ መጠን ግጭቶችና አለመግባባቶች ከመከሰታቸው በፊት ልዩ ልዩ የውይይት መድረኮችን ለመላው ሕዝባችሁ በማዘጋጀት እና በውይይት መድረኩ የሚገኙትን ግብአት የእቅዳችሁ አካል አድርጋችሁ በመተግበር ኃላፊነታችሁን ከቀድሞው በተሻለና በላቀ ሁኔታ በመፈጸም ለሀገራችን ሰላምና አንድነት እድገትና ብልጽና የድርሻችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤
  9. በየደረጃው ያላችሁ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ሁሉ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶችና አለመግባባቶች ከመከሰታቸው በፊት ቅድመ መከላከል መሠረት ያደረገ የፀጥታ ሥራን በመተግበር እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችንና የሰው ሕይወት መጥፋትን እንዲሁም የንብረት ውድመትን በመከላከል የተጣለባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ እናሳስባለን፤
  10. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ሰላም በማይወዱ አካላት የሚከሰቱ ልዩ ልዩ አፍራሽና ግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን ወደ ጎን በመተውና በአርቆ አሳቢነትና በሀገር ባለቤትነት መጠነ ሰፊ ትዕግሥት የተሞላበት ሀገራዊ አንድነትና ሕብረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ላበረከታችሁት የማይተካ ሚናና ታሪክ የማይረሳው ውለታ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እያመሰገነ እንደ አሁን ቀደሙ ሁሉ ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ዘር፣ ብሔርና ሃይማኖት ሳይለያያችሁ እጅ ለእጅ በመያያዝ የበኩላችሁን የማይተካ ድርሻ እንድትወጡ የአደራ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
  11. በሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኙ የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሃይማኖት ብዝሃነትና ተቻችሎና ተከባብሮ በመኖር አስደናቂ ባሕሏ ሌሎች ሀገራት የሚቀኑባትና በአርአያነትም የሚጠቅሷት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይህን አኩሪና አርአያ የሆነ ታሪኳን በሚያደበዝዝ ሁኔታ ሃይማኖትና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እየተበራከቱ በመሆናቸው ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅና ተጽእኖ እምነታቸውን ለማምለክና ለማስመለክ የማይችሉበት የስጋት አደጋ እየተጋረጠ ከመሆኑ አንጻር ሁሉም ቤተ እምነቶች ለሀገራዊ አንድነትና ለእምነት ነጻነት በአንድነትና በሕብረት ለመላው ሕዝባችን የሰላም ጥሪ በማስተላለፍ ዘወትር በየአስተምህሮአችን ለሕዝባችን የሰላም ጥሪ ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
  12. በመጨረሻም ያለ ሀገር ሰላምና አንድነት እንዲሁም ፍቅርና እድገት መኖር ስለማይቻል መላው ሕዝባችንን እንደየእምነቱና ሃይማኖቱ ሥርዓት ከዛሬ ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀን ያህል በጾም፣ በጸሎትና በሐዘን ስለ ሀገር ሰላም በአንድነት ጥሪውን ለፈጣሪውና ለአምላኩ ያቀርብ ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጸሎትና ምሕላ እንዲደረግ በቤተ ክርሰቲያኒቱ ስም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ መንፈሳዊ አዋጁንም አውጇል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ