‹‹ጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን›› (ሐዋ.፳፩፥፲፬)

በኃጢአት ተፀንሼ በዓመፃ ተወልጄ

ከቃልህ ሕግ ወጥቼ በዝንጉዎች ምክር ሄጄ

በኃጢአተኞች መንገድ ቆሜ በዋዘኞች ወንበር ተቀምጬ

በውኃ ማዕበል ሰጥሜ የሞት ጽዋን ጨልጬ

ጥርሴ ጦር ፍላፃ ቁጣዬ እንደ እባብ መርዝ አንደበቴ ምላጭ ሾተል

ልቤ በክፋት ቀንቅኖ ውስጤ በበደል ነቅዞ ሰውነቴ ሁሉ ጎብጧል

  • በሰውነቴ መደርጀት በቀስቴ ታምኛለሁ

ለእግሮቼ ወጥመድን ለፊቴ ጉድጓድን ቆፍሬያለሁ

እንደ ሰገነት ላይ ሣር ሳይነቀል እንደሚደርቅ እቅፍ እንደማይሞላ

ኃጢአቴ ሚዛን ደፍቶ በምግባሬ ቀልያለሁ ስለወጣሁ ከጥበቃህ ከለላ

በወይን ጠጄ ላይ ውኃን ደባልቄ ወርቅ እና ብሬን አዝጌ

ከኃጢአቴ የተነሣ አንገቴን የብረት ጅማት ግንባሬን ናስ አድርጌ

በጭንጫ መሬት ላይ ዘርህን ዘርቼ

የሠርግ ልብሴን ሳልለብስ ከሠርግህ ቤት ገብቼ

የሰጠኸኝን አንድ መክሊት በመሬት ውስጥ ቀብሬ

የጽድቅ እና የዕውቀት መክፈቻን በጨለማ ውስጥ ሠውሬ

የነቢያትን መቃብር ስሠራ የጻድቃንን መቃብር ሳስጌጥ

ትንኝን ሳጠራ ግመልን እንዳለ ስውጥ

በምኩራብ ፊተኛ ወንበር በማዕድ በክብር ስፍራ ስቀመጥ

ከአዝሙድ እና ከእንስላል ዐሥራትህን ሳወጣ

መምህር ሆይ! እየተባልኩ ወደ ገበያ ስወጣ

የሙታንን አጥንት ተሞልቶ እንደ ተለሰነ መቃብር

ውስጤ ዓመፅ እና ቅሚያ አቤት ውጭዬ ግን ሲያምር

ወዮልኝ! ወዮልኝ!

ብመለስ  ነበር ለእኔስ የሚሻለኝ

በሥራዬ ተቆጥቶ ከመንበረ ሥልጣኑ ወርዶ እረኛዬ ይጠራኛል

አዳም ሆይ ወዴት አለህ ከትእዛዜ ወጥተህ ከበለሷ ቀጥፈሃል

በኃጢአት ውስጥ ተሸሽገህ የበደልን ቅጠል አገልድመሃል

ፍሬን ፈልጌ ስመጣ እሾህን አብቅለሃል ኩርንችትን አፍርተሃል

ወደ ዕረፍት ውኃ መርቼ በለመለመ መስክ ባሰማራህ እረኝነቴን ንቀሃል

በዓለም ፍቅር ተነድፈህ ቀራንዮን ረስተሃል ከመንጋው ወጥተህ ሄደሃል

ጸሐፍትን እና ፈሪሳውያንን መስለህ እንደ ይሁዳ ከድተኸኝ በሥራቸው ተባብረሃል

ስለዚህ ና ወደ እኔ ከበረቱ ተቀላቀል ከመንጋው ጋር ይሻልሃል

እያለ እረኛዬ ይጠራኛል ወዮልኝ…! ወዮልኝ…!

እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ብመለስ ነበር ለእኔስ የሚሻለኝ

የራስህ ላይ አክሊል ወድቆ ሕጌ ከልቡናህ ከስሎ ደርቆ

ስምህ ከሕይወት መጽሐፍ ተደምስሶ ከመዝገቤ ተፍቆ

የደሜ ማኅተም ከውስጥህ ጠፍቶ የገሃነም እሳት እንዳይበላህ

ሁልጊዜ ተዘጋጅተህ ኑር ዕቃ ጦሬን ለብሰህ

ና ወደ መንጋው! ና ወደ እኔ! እያለ ይጠራኛል ለካስ ይወደኛል

ዘጠና ዘጠኙን በዱር ትቶ አዳም ሆይ ወዴት አለህ እያለ ደጋግሞ ይጠራኛል

ከእንቅልፌ እንድነቃ ልጄ ሆይ ክፈትልኝ እያለ ደጄን ከውጭ ቆሞ ይመታል

ወዮልኝ…! ወዮልኝ…! ወዮልኝ…!

እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ብመለስ ነበር ለእኔስ የሚሻለኝ

ብሎ ተረበሸ እምነት ጎድሎት በፍርሃት ሲማጸን

ሊቀበል እንቢ ብሎ ተግሣጽ እና ምክርን

ስለእርሱ ጥፋት እኛም አዝነን ያገኝ ዘንድ ምሕረትን

ሐዋርያት እንዳሉት ‹‹የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን››