‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?›› (ዮሐ. ፳፩፥፲፭)

በእንድርያስ ስንታየሁ  

የዮና ልጅ ስምዖን በቤተ ሳይዳ ዓሣ አጥማጅ የነበረ ሰው ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ዕለት ማግሥት ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ አድርጎ መረጠው፤ ስሙም ጴጥሮስ ተባለ፡፡ ወንጌልን ይሰብክ እና ምእመናንም ይፈውስ ዘንድ ሥልጣንና ኃይልን የተሰጠው ቅዱስም ሆነ፡፡ የአስቆርቱ ይሁዳ ጌታን ለአይሁድ አሳልፎ እስኪሰጠው ድረስም ከእርሱ ጋር ኖሯል፡፡ ፍጹም ሃይማኖት፣ ለጌታውም ቅንዓት እና ፍቅርም ነበረው፡፡ (ስንክሳር ሐምሌ ፭)

ሆኖም አይሁድ በምቀኝነት ተነሣስተውና ተረባርበው፤ ሰይፍና ገመድ ይዘው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እያንገላቱ በሚወስዱት ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከእርሱ ሸሸ፡፡ እንግልት እና ስቅለትንም ፈርቶ ተሸሸገ፤ በዚያን ጊዜ በአካባቢው እሳት የሚሞቁ ሰዎች ስለነበሩ ወደ እነርሱ ጠጋ ብሎ ቆመ፡፡ ከዚያም በረኛይቱ አገልጋይም፥ አንተም ከዚያ ሰው ደቀ መዝሙርት አንዱ ነህ? አለችው፡፡ እርሱም አይደለሁም ብሎ በሰዎች ፊት በአፉ ካደ፤ ተሰብስበው የቆሙት ሰዎች እሳት አንድደው ይሞቁ ነበርና ጴጥሮስ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር፡፡ ሲያዩትም አንተስ ከእርሱ ደቀ መዝሙር ወገን አይደለህምን? ብለው ጠየቁት፤ እርሱም አይደለሁም ብሎ ካደ፡፡ ቀደም ብሎ ጴጥሮስ ጌታችን ሊይዙት ከመጡት ሰዎች ውስጥ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ወገን የሆነ ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮችም አንዱ፥ እኔ በአትክልት ቦታ ውስጥ ከእርሱ ጋር አይቼህ አልበነረምን? አለው፡፡ ጴጥሮስም ደግሞ ካደ፤ በዚያች ቅጽበት አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው እርሱ እንዲህ ከካደ በኋላ ዶሮ ጮኸ፡፡ ጴጥሮስም ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለውን የጌታችን የኢየሱስን ቃል አሰበ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶን አለቀሰ፡፡ (ዮሐ.፲፰፥፲፯-፳፯፣ ማቴ.፳፮፥፸፭)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ የሰው ልጆችን በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሥጋውን ቆርሶ፣ ደሙን አፍሶ፣ ሞቶ ተቀብሮ፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ፣ ከትንሣኤው በኋላ ለሐዋርያት ተገልጦ ባስተማራቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፤ ‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?›› እርሱም፥ ‹‹አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ›› ብሎ መለሰ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም፥ ‹‹በጎቼን ጠብቅ›› አለው፡፡ ዳግመኛም፥ አሁንም ‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?›› አለው፤ እርሱም አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥  እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው፤ ጠቦቶቼን አሰማራ አለው፡፡ ሦስተኛም ‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?›› አለው፡፡ ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን ስላለው አዘነ፤ ‹‹ጌታዬ ሆይ፥  አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔም እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ›› አለው፡፡ እንኪያስ ግልገሎቼን ጠብቅ አለው፡፡» እንዲህም ብሎ በምእመናን ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ ጠባቂም አደረገው፡፡

እግዚአብሔር አምላችንን በፍጹም ልባችን መውደድ እንዳለብን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንረዳለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ወንጌልን በሰበከበት በዘመነ ሥጋዌ ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን ተሰብስበው ወደ እርሱ ሄዱ፡፡ ከመካከላቸውም አንድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈትነው እንዲህ ብሎ ጠየቀው፤ ‹‹መምህር ከኦሪት ማንኛይቱ ትእዛዝ ትበልጣለች? ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ አምላካህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደደው፡፡ ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት፡፡ የምትመስላት ሁለተኛይቱ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትለው ናት፡፡ ኦሪትና ነቢያት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ጸንተዋል›› ብሎ መለሰለት፡፡ (ማቴ. ፳፪፥፴፭)

ይህም ሰው ራሱን እንደሚወደው ሁሉ አባቱን እና እናቱን፣ ወንድሙን እና እኅቱን፣ ዘመዶቹን እና ባልንጀራውን እንደራሱ መውደድ እንዳለበት የሚያመልክት ነው፡፡ ለራሳችን ያደረግነውንም በጎ ነገር ለእነርሱ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አምላካችንን መውደዳችን በዚህ ይገለጣልና ነው፤ በወንጌልም «እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ ካመኑ ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁትን ሁሉ ለእኔ አደረጋችሁት» ብሎ በምጽአት ዕለት ጻድቃንን ወደ ዘለዓለም ሕይወት እንደሚወስዳቸው ተናግሯል። (ማቴ. ፳፭፥፴፱)

የሰው ልጅ ፈጣሪውን መወደዱ ይገለጽ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ በብዙ ሊፈትነው ይችላል፤ በምድር ላይ እጅግ በጣም የሚወደውን ሰው በሕመም በሕይወቱ ውስጥ ማጣት የማይፈልገውን ነገርም በመውሰድ ይፈትነዋል፡፡ ይህም አምላክ ለእርሱ ያለውን ፍቅር ለማወቅ እንጂ ተስፋ ለማስቆረጥ ስላልሆነ ፈተናችን ለበጎ መሆኑን ማመወቅና ማመን አለብን፡፡ ማማረር ወይንም አምላክነቱን መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ በአሁኑ ጊዜም እምነታችንና ሃይማኖታችን  እየተፈተነ ነውና ጸንተን ችግርና መከራውን ልንቋቋም ይገባል፡፡ ሃይማኖት ያለ ምግባር ዋጋ ስለሌለው በአንደበታችን መጸለይ፣ መጾምን እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን መመላለስ ብቻ ሳይሆን ልባችን አንጽተን መማጸን፣ መጾም እና ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን በሚገባ መፈጸም ያስፈልጋል፡፡  ይህንንም እንድናደርግ አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤አሜን፡፡

ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ