‹‹የገሃነም ደጆችም አይችሏትም›› (ማቴ.፲፮፥፲፰)

መምህር ኃይለሚካኤል ብርሃነ

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድረ እስራኤል በኪደተ እግሩ እየተመላለሰ ሲያስተምር የፊልጶስ ግዛት በምትሆን በቂሳርያ ሳለ ቅድስት ቤተ ክርስትያንን በዐለት ላይ እንደሚሠራትና የገሃነም ደጆችም እንደማይችሏት አስተማረ፡፡

‹‹ጌታችን ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ ሀገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል? ብሎ ጠየቃቸው እነርሱም መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉ አሉ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም  ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት እርሱም እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ? አላቸው ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ÷ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልሃለሁ÷ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚያች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ÷ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም…››(ማቴ.፲፮፥፲፫—፳)

ቅዱሳን ሐዋርያት ለቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲመልስ ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ (ሰው የሆነ አምላክ) መሆኑን መሰከረ፡፡ እግዚአብሔር የገለጠለትን ምስክርነት ሲሰጥ ይህንን ምሥጢር ምድራዊ መምህር፣ ምድራዊ ጥበብ፣ ሥጋዊ ኃይል የገለጠለት ሳይሆን የሰማይ አባቱ እንደገለጠለት ጌታችን ክርስቶስ ጠቅሶ አንተ ብፁዕ ነህ አለው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የመሰከረለት ማለትም ‹‹ሰው የሆነ አምላክ›› በዚህ እምነት ላይ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚሠራት ቅዱስ ጴጥሮስም የምእመናን አባት እንደሚሆን የሰጠው ምስክርነትም የማናወጥ ጽኑዕ የማያልፍ ለዘለዓለም የሚኖር ስለሆነ አንተ ዐለት ነህ ተብሏል፡፡

ይህች በቅዱስ ጴጥሮስ እምነት ማለትም ክርስቶስን ‹‹ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፤የሕያው እግዚአብሔር ልጅ›› ብላ በማመን የምትመሰክር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዕለተ ዓርብ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በመስቀል ላይ ተመሠረተች፡፡ እርሷም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነገረን የገሃነም ደጆችም አይችሏትም፡፡ የገሃነም ደጆች የተባሉትም የሞት ጎዳናዎች፣ የጥፋት መንገዶች፣ የኃጥኣን ክፉ ሥራዎች እነዚህና መሰሎች የዲያብሎስ የግብር ልጆች የሚሠሯቸው ሲሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ይዋጓታል ግን አያሸንፏትም፣ ጦራቸውን ይመዙባትል ግን አያጠፏትም፣ ይታገሏታል ግን አይችሏትም ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች ተሸንፋ ግን አታውቅም ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱንም ጨረሰ ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጎዳትም›› በማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን ድል አድራጊነት ያስተማረውን ትምህርት ማስተዋል ይገባል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትፈተናለች እንጂ ወድቃ አታውቅም አትወድቅምም በማይናወጥ ጽኑዕ ዐለት ላይ ተመሥርታለችና፡፡ መገለጫዋም በተጋድሎ ውስጥ ማለፍና በክርስቶስ ኃይል ዓለምንና ፈቃዱን ድል አድርጋ የድል አክሊል (ሽልማት) መቀበል ነው፡፡ ከድል በኋላ እንደ መላእክት በምስጋና ላይ ምስጋናን እያቀረበች መኖር ዓላማዋ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በመከራ ውስጥ ሆና መከራውን ታግሣ በማሸነፍ በድል አድራጊነት ተልእኮዋን ጨርሳ   በክብር ላይ ክብር ተጨምሮላት ከቅዱሳን መላእክት ጋር በምስጋና ጸንታ የምትኖር ሰማያዊት ናት፡፡

በመከራ ውስጥ ያለች ቤተ ክርስቲያን

በመከራ ውስጥ ያለች ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ገና በጉዞና በተጋድሎ ላይ ያሉት የምእመናን አንድነት ናት፡፡ ለዚህም ጌታችን በወንጌል ‹‹በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ ነገር ግን ጽኑ እኔ ዓለምን ድል ነሥቼዋለሁና›› (ዮሐ.፲፮፥፴፫) በማለት በዓለም ያሉ ምእመናን መከራ እንዳለባቸውና መከራውን ተሰቀው ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ ፈጣሪያቸውን እንዳይክዱ በሃይማኖት ጸንተው ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን እያገለገሉ ሊኖሩ እንደሚገባ አስተምሯል፡፡

ምእመናን በዓለም እየኖሩ ሰማያዊ ዜግነት ያላቸው ናቸውና ዓለምንና በውስጧ ያሉትን  ነገሮች ኃላፊ ጠፊ መሆናቸውን ስለሚያምኑ ናፍቆታቸው ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም ነው፡፡ ዓለም ደግሞ የራሷ ባልሆኑት ለእግዚአብሔር በተለዩት ምእመናን ላይ መከራ ታደርስባቸዋለች፡፡ ምክንያቱም ዓለም የራሷ የሆኑትን በምድራዊ አሳብና በሥጋዊ ፈቃድ ብቻ የሚኖሩትን ትወዳለች፣ ትሾማቸዋለች፣ ትሸልማቸዋለች የራሷ ያልሆኑትን ማለትም ዓለምንና ፈቃዷን ንቀው በመንፈሳዊ ሕይወት የሚመላለሱትን ስለምትጠላቸው መከራ ታደርስባቸዋለች፡፡

ጌታችን እንዳስተማረን ‹‹ዓለም ቢጠላችሁ አስቀድሞ እኔን እንደጠላኝ ዕወቁ እናንተስ ከዓለም ብትሆኑ ዓለም በወደዳችሁ ነበር፤ ዓለም ወገኖቹን ይወዳልና፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ ከዓለም አይደላችሁምና ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል፤ እኔ  ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም ያልኋችሁን ቃሌን አስቡ እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ቢሆንስ  ቃላችሁንም በጠበቁ ነበር፡፡ ነገር ግን ስለ ስሜ ይህን ሁሉ ያደርጉባችኋል፤ የላከኝን አያውቁትምና፤ ባልመጣሁና ባልነገርኋቸውስ ኖሮ፤ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም፡፡ እኔን የሚጠላ አባቴን ይጠላል፤ ሌላ ያልሠራውን ሥራ በመካከላቸው ባልሠራ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፡፡ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፤ ጠልተውማል›› (ዮሐ.፲፭፥፲፰) በማለት የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ በዚህ ዓለም ሲኖሩ መከራ እንዳለባቸውና ምንም እንኳ በፈቃዱ ቢሆንም ዓለም ግን በጥላቻ ስለታወረች በመስቀል ሰቅላ የገደለችው ስለ ሆነች የእርሱ የሆኑትንም እንዲሁ ትጠላቸዋለች፤ መከራም ታደርስባቸዋለች፡፡ይሁን እንጂ እርሱ ዓለምን እንዳሸነፈ የእርሱ የሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም መከራውን በትዕግሥት፣ በጽናት ተቋቁማ በድል ታጠናቅቃለች፡፡

ስለዚህ ዓለም በተደጋጋሚ ቀስቷን በቤተክርስቲያን ላይ ብትወረውርም ጌታችን ቀድሞ ስላስተማረን ምንም አይደንቀንም፡፡ ይልቁንም ከዓለም የሚሰነዘሩባትን ሰይፎችና መከራዎች ሁሉ በአሸናፊነት አጠናቃ፣ የድል አክሊል ለመቀበል ሁል ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በተጋድሎ ላይ ናት፡፡ በውስጧም ሐሰተኞችና ክፍዎች ተደባልቀው ይኖሩባታል፡፡ ይህም ማለት ይሁዳ ከጌታ ደቀ መዛሙርት ከሐዋርያት ጋር እንደነበረ፣ ከሐዋርያነ አበው ጋር ቢጽ ሐሳውያን እንደነበሩ፣ በየዘመናቱ ቤተ ክርስቲያን ከምታፈራቸው ከሊቃውንቱ ጋር መናፍቃን እንደ ነበሩ ማለት ነው፡፡ ይህም ይሆን ዘንድ ግድ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸው ‹‹ከእናንተ የተመረጡት ወንድሞች ተለይተው እንዲታወቁ ትለያዩ ዘንድ ግድ ነው››(፩ኛቆሮ.፲፩፥፲፱) ይላልና፡፡

በገድል ላይ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስንዴው ከገለባው በሚለይበት ቀን አብረዋቸው የማይገኙ ነገር ግን በዚህ ዓለም አብረው የሚኖሩ ብዙዎች አሉ፡፡ ጌታችንም ይህንን ሲያስረዳ በምሳሌ አስተምሯል፡፡ ‹‹…ተዉአቸው እስከ መከር ድረስ አብረው ይደጉ በመከርም ጊዜ አጫጆችን አስቀድማችሁ እንክርዳዱን ልቀሙ፤ በየነዶውም አስራችሁ በእሳት አቃጥሉት፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ሰብስቡት እላቸዋለሁ አለ›› (ማቴ.፲፫፥፴)፡፡

በዚህ ዓለም በመከራ ውስጥ እያለፈች ጌታዋን የምታከብር ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳ በምድር ያለች ብትሆንም ፍጹም መንፈሳዊትና ቅድስት ናት፡፡ ከዓለማውያን ሰዎችና ከዲያብሎስ የሚወረወሩባት ፍላጻዎች ቢኖሩም መልካሙ እረኛዋ አይለያትምና ምንም ሳይጎድልባት ተልእኮዋን በድል ታጠናቅቃለች፡፡ በዓለም እስካለች ድረስ በአወቃቀሯ፤ በአሠራሯና በአባላቶቿ ‹‹ምድራዊ›› በሆኑ ነገሮች ትፈተናለች፡፡ ቢሆንም ግን ሁሉን እየቀደሰች ለክብር ታበቃለች፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን በዓለም እስካለች ድረስ ሙሉ በሙሉ ከፈተና ነጻ ልትሆን አትችልም፤ ነገር ግን ከማንኛውም ፈተናና መከራ ነጻ የምትሆነው ገድሏን ካጠናቀቀች በኋላ ነው፡፡

አሸናፊዋ ቤተ ክርስቲያን

አሸናፊዋ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ያለውን መልካሙን የሃይማኖት ገድል (መንፈሳዊውን ሩጫ) ጨርሰው ዓለምንና ፈቃዷን ድል በማድረግ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም ወደ ሰማያዊው ዓለም የሄዱት የቅዱሳን አበው የጻድቃን የሰማእታት አንድነት (ጉባዔ) ናት፡፡

ይህችን ጉባኤ በመናፈቅና ተስፋ በማድረግ በዚህ ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን ገድሏን ትፈጽማለች፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሃይማኖት ለወለደው ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት መልእክቱ ‹‹በወንጌል እንደምሰብከው ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ከዳዊት ዘር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስበው ስለ እርሱም እንደ ወንጀለኛ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም፡፡ ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ሕይወትና የዘለዓለም ክብር በሰማያት ያገኙ ዘንድ ስለ ተመረጡት ሰዎች በሁሉ ነገር እታገሣለሁ፡፡ ነገሩ እውነት ነው፤ ከእርሱ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ ብንታገሥም ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው ግን እርሱም ይክደናል፤ ባናምነውም እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን መካድ አይቻለውምና›› (፪ኛ ጢሞ. ፪፥፰) ይላል፡፡

አሸናፊዋ (ድል አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለው አይነት መውጣት መውረድ ሳይኖርባት በጽንዐት በጸጋ ላይ ጸጋ እግዚአብሔር እየጨመረላት ከክብር ወደ ክብር የምትሸጋገር ሰማያዊት ናት፡፡ አኗኗሯም እንደ መላእክት ነው፡፡ ከቅዱሳን መላእክት ጋር በአንድ ጉባኤ ጌታዋን የምታመሰግን ሕያዊት ናት፡፡ ዓለምንና ፈቃዷን ድል አድርጋ የድል አክሊል ስለተጎናጸፈች ‹‹ምድራዊ›› ከሆኑ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነች የቅዱሳን አንድነት ናት፡፡

ወደዚህች ጉባዔ በመግባት የሚታደሙትም ምእመናን በዚህ ዓለም እያሉ ሃይማኖታቸውን የጠበቁ፣ መልካም ሥራን በመሥራት የኖሩ፣ ስለ እግዚአብሔር ሲሉ መከራ የተቀበሉ፣ በስሙ የታሰሩ የተገረፉ፣ የተሰደቡ፣ ሃይማኖታችንን አንለውጥም፤ ፈጣሪያችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አንክድም ያሉና የሃይማኖታችን መገለጫ የሆነውን የልጅነት ማዕተባችንን አንበጥስም ብለው አንገታቸውን ለሰይፍ ሰውነታቸውን ለግርፋት አጥንታቸውን ለመከስከስ አሳልፈው የሰጡ ርኅራኄ በሌላቸው በዲያብሎስ የግብር ልጆች የተገደሉ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ‹‹እኔ ፈጽሜ ግዳጄን ጨርሻለሁ የማርፍበት ዕድሜዬም ደርሷል መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄአለሁ፤ እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም›› (፪ኛጢሞ.፬፥፮) እንዲል፡፡

ሐዋርያው እንደገለጸው የክርስትና ሃይማኖት በብዙ ፈተናና መከራ ውስጥ የሚያልፉበት የሕይወት ጎዳና ነው፡፡ ለዚህም ነው በባሕርይዋ ቅድስት የሆነች ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ ስትፈተን መከራውን ስደቱን በእሳት መቃጠሉን እያስተናገደች ከጉዞዋ ሳትገደብ ተልእኮዋን የምትፈጽመው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዕለተ ዓርብ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መስቀል ከተመሠረተች ጊዜ ጀምሮ በብዙ በመከራና ስቃይ ውስጥ አልፋ ነው ዛሬ ላይ የደረሰችው፡፡ ይህም የሰማእታቱ ደም፣ የጻድቃን ገድል፣ የንጹሓን ዕንባ፣ የእናቶች ልቅሶ፣ የሕፃናቱ ዋይታ ለዛሬዋ ቤተ ክርስቶያን ጥንካሬ መሠረት እየጣለ እንደመጣው ዝክረ ቅዱሳን ለነገዋ ቤተ ክርስቲያንም የዛሬው መከራ የክርስቲያኖች ዕንባና በግፍ መገደል፣ በሰይፍ መቆረጥ፣ በድንጋይ መወገር፣ በእሳት መቃጠል፣ በቢላ መታረድ የራሱን ጥንካሬንና ጽናትን አድሎ ያልፋል፡፡

ይህም እየተገደሉ መብዛትን፣ እየተገፉ መጠንከርን፣ እየተናቁ መክበርን፣ እየተነጠቁ መበልጸግን የተማርንበት ክርስቲያንና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል የተባለውን በተግባር የምናይበት ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ወርቅነቱ እንዲረጋገጥ ሁሉ ክርስቲያን መሆንም በመከራ ውስጥ ማለፍ እንደሆነ ሁልጊዜ ላፍታም እንኳ እንዳንዘነጋው ያደርገናል፡፡

የክርስትና ሃይማኖት በዚህ ሁሉ መከራ የሚያልፉበት ቢሆንም ፍጻሜው ግን ከሁሉ ይልቅ እጅግ የከበረና ማንም ባላየው ደስታና ክብር የሚኖሩበት ዘለዓለማዊ ዕረፍትና እውነተኛ ሰላም የምናገኝበት የእውነት መንገድ ነው፡፡ ይኸውም ተከብረው የማይዋረዱበት፣ አግኝተው የማያጡበት፣ ተደስተው የማያዝኑበት፣ የማይራቡበት፣ የማይጠሙበት፣ የማይራቆቱበት ዘለዓለማዊ ሕይወት ነው፡፡

ክርስቲያኖች በብዙ መከራ ውስጥ አልፈው የሚወርሱትን ሰማያዊ ርስት ባለ ራእዩ ቅዱስ ዮሐንስም በፍጥሞ ደሴት ተግዞ ሳለ ቅዱስ ጳውሎስ የመሰከረላትን ሰማያዊቷን ጉባኤ ተመልክቷታል፡፡ ይህንንም ሲገልጥ ‹‹ከዚህም በኋላ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን አየሁ፤ የፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ባሕርም ወደፊት የለችም፤ ቅድስቲቱም ከተማ አዲስቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ ለባልዋ እንደ አጌጠች  ሙሽራም  ተዘጋጅታ ነበር›› (ራዕ.፳፩፥፩) በማለት ቤተ ክርስቲያን የዚህን ዓለም ፈተናና መከራ በድል አጠናቅቃ በክብር የምትኖር መሆኗን መስክሯል፡፡

በመሆኑም አብን ወላዲ ወልድን ተወላዲ መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ብለን አምነን ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን የእግዚአብሔርነ ልጅነትን ያገኘንና በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኝን  ኦርቶዶክሳውያን ስለ ሃይማኖታችን የሚገጥመንን መከራ በጽናት ሆነን በትዕግሥት አሳልፈን ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንወርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅንት አይለየን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት ኅዳር ፳፻፲፪ ..