‹‹ለራስህ እና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ›› (ኛ ጢሞ. ፬ ፲፮)

መምህር ሶምሶን ወርቁ

አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ሐዋርያትን የምሥራቹን ቃል ሊሰብኩ ወደ ዓለም ላካቸው ‹‹እንግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ›› (ማቴ ፳፰፤፲፱) ሲል
ሐዋርያቱን አዟቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መስበክ ማስተማር እንደየዘመኑ ለሐዋርያት፣ ለሐዋርያውያን አበው፣ ለሊቃውንት፣ በየዘመኑ ለተነሱ የሐዋርያትን ትምህርት ለያዙ በሐዋርያት እግር ለሚተኩ መምህራን የተሰጠ ኃላፊነት ነው፡፡ ሐዋርያ በጎቹን በለመለመ መስክ እንደሚያሰማራ በጎቹ በተኩላ እንዳይነጠቁ እንደሚጠብቅ መልካም እረኛ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፡፲) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚገባው የመንፈስ ልጁን ጢሞቴዎስን ሲመክር ‹‹ለራስህ እና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ›› ብሏል፡፡ (፩ኛ ጢሞ. ፬ ፥፲፮)

ይሁን እንጂ ጠላት ዲያብሎስ ጥንትም ዛሬም ከንጹሕ የእግዚአብሔር ቃል ጋር እንክርዳድ ቀላቅሎ ይዘራል፡፡ (ማቴ. ፲፫፥፳፯) ቅድስት ቤተክርስቲያን በየዘመኑ እግዚአብሔር ባስነሳቸው ቅዱሳን አበው  በጉባኤያት እንክርዳድ የተባለ  የሐሰት ትምህርት ለቅማ፣ ለይታ፣ ንጹሕ  ቃለ እግዚአብሔርን እየዘራች ኖራለች፡፡ ዛሬም ቢሆን ጠላት እንክርዳድ ለመዝራት እየሞከረ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ  የዕቅበተ እምነት መጻሕፍት መበራከታቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ የሚታዩትን ከንጹሕ የእግዚአብሔር ቃል ጋር ቀላቅለው እንክርዳድ ለመዝራት የሚሞክሩ መጻሕፍትን በዚህ አጭር ጽሑፍ ለመግለጽ እና መፍትሔ ለመስጠት መሞከር የችግሩን ጥልቀትና ስፋትን በሚገባ አለመረዳት ነው፡፡  ችግሩን በሚገባ ለመረዳትና መፍትሔ ለመጠቆም በመረጃና በማስረጃ  ላይ የተመሠረተ ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ባለፈ የጥናትና ምርምሩን ውጤት ለመግለጽ የቤተክርስቲያን ዕውቅናና ይሁንታ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ዛሬ ላይ በቤተክርስቲያናችን የሚጻፉ ቤተክርስቲያንን ይወክላሉ ተብለው የሚታሰቡ ‹‹መንፈሳዊ›› ሆኑ የቤተክርስቲያን ‹‹የታሪክ›› መጻሕፍት የሚጽፉትን ጸሐፍትን፣ መጻሕፍትን ከአንዱ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ የሚተረጉሙትን መተርጉማንን፣ አሳታሚዎችን ለመገሠጽ ወይም ለመተቸት ሳይሆን በመጻሕፍት ላይ እየታዩ ባሉ ግድፈቶች ያለበቂ ግምገማና እርማት መታተም ችግር ነባራዊ ሁኔታ ላይ የውይይት ርእስ ለማንሳት እንዲሁም ነገ ቤተክርስቲያንን ለሚረከበው ትውልድ ንጹሕ እንክርዳድ ያልተቀላቀለበት ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተላለፍ ምን ብናደርግ ይሻላል ብለን እንድንመካከር መሆኑን ተረድተን ጽሑፉን እንብበን ልንነረዳ ያስፈልጋል፡፡

የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ በዋነኝነት በመንፈስ እግዚአብሔር የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት እናት የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በየዘመኑ ያስነሳቸውና የመረጣቸው ቅዱሳን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጽፈውታል፡፡ በዘመኑ ለነበረው ትውልድና ለሚነሳው ትውልድ ሁሉ በቅብብሎሽ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬ ካለንበት ዘመን ደርሷል፡፡ ይህ ሲባል መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ፈተና እና ያለ ችግር ከዘመናችን የደረሰ ሳይሆን ገና ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ክርስትና እንዳይስፋፋ ወንጌል እንዳይሰበክ በጠላትነት ተነስተው ከነበሩት አይሁድ ብዙ ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡  አይሁድ ወንጌልን ለመበረዝ የቶማስ ወንጌል፣ የፊሊጶስ ወንጌል፣ የይሁዳ ወንጌል ተብለው በተጻፉ እንክርዳድ የሐሰት ትምህርቶች ከንጹሕ ወንጌል ጋር ቀላቅለው ተቀባይ ለማሳጣት በብዙ ደክማዋል፡፡ ለዚህም ነበር በጊዜው የጥርጥር ትምህርት እየበዛ መጥቶ የምእመናንን ሕይወት ማናጋት ሲጀምር ቤተክርስቲያን፣ ሊቃውንትን በጉባኤ ጠርታ፣ የሐሰት ትምህርቶችን ከማውገዝና ከመለየት ባሻገር የጥርጥር ምንጭ የሆኑትን የሐሰት መጻሕፍት  ተመርምረው እንዲለዩ ቀኖና ሠርታ፣ እውነተኛ መጻሕፍትን ከሐሰተኛ ለይታና አስተምህሮዋን በእውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዲጸና አድርጋ ቅዱሳት መጻሕፍትን ዛሬ ካለንበት ዘመን አድርሳለች፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል›› (፪ኛ ጢሞ. ፫፥፲፮) እንዲል የመጽሐፍ ቅዱስ ልጆች የሆኑት አዋልድ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ተአምራት፣ ገድላትና ድርሳናት መጽሐፍ ቅዱስን ዐምድ በማድረግ የተጻፉት በየዘመኑ የማይቋረጠውን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥራ ሲመሰክሩ ኑረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሁለት ሺህ ዘመን አስተምህሮዋ ሳይበረዝና ሳይከለስ ካለንበት ዘመን የደረሰው በምድራዊ ሐሳብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ባሳለፈችው ሁለት ሺህ ዘመን በዋነኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ከተጻፈበት ጥንተ ቋንቋ ወደ ግእዝ እና ወደ ሌሎች በሀገራችን የሚነገሩ ቋንቋዎች ሲተረጒሙ፤ ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ከግሪክ፣ ከሱርስትና ከዐረብኛ ወደ ግእዝ ተተርጉመዋል፤ አልፎ ተርፎ በቤተክርስቲያናችን በየዘመኑ የተነሱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተአምራት፣ ገድላትና ድርሳናትን ሲጽፉና ሲተረጉሙ ኖረዋል፡፡ በተለይ ቤተክርስቲያናችን ከተጓዘችባቸው ረጅም ዘመናት  ከ፲፪ኛ-፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለቤተክርስቲያን ወርቃማ ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በእነዚህ ምዕት ዓመታት ስብከተ ወንጌል በመላው ኢትዮጵያ በመስፋፋቱ፣ ገዳማዊ ሕይወት በማበቡ፣ በዋነኝነት የቤተክርስቲያን ሥነ ጽሑፍ በእጅጉ በማደጉ ዘመኑ  ወርቃማ ዘመን ተብሏል፡፡ ለአብነት ያህል  ዜና መዋዕል፣ ክብረ ነገሥት፣ መጽሐፈ ሰዓታት፣ ስንክሳር፣ ገድላት፣ ድርሳናትና ተአምራትን በመተርጎም መጻፋቸው ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ዛሬ ያለንበት ዘመን በከፊልም ቢሆን የቤተክርስቲያንን መጻሕፍት መበራከታቸው ወርቃማ ዘመንን ይዘክራል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነን ከጥቂት ዐሥርት ዓመታት በፊት ለማግኘት ይቸግሩ የነበሩ የጸሎት፣ የአገልግሎት፣ የዜማና የአንድምታ ቅዱሳት መጻሕፍት ዛሬ ለኅትመት በቅተው በቀላሉ ማግኘት ተችሏል፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማግኘት ችለዋል፤ ምእመናን ሊረዱት በሚችሉት ደረጃ ተብራርተው የተጻፉ የዕቅበተ እምነት መጻሕፍት እንዲሁም የቤተክርስቲያንን አምልኮ ሥርዓትን የሚያስተምሩ መጻሕፍት እንዲሁም የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት ሕይወታቸውና ትምህርታቸው በብዛት ተጽፈዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ ያለንበት ዘመን በከፊልም ቢሆን የቤተክርስቲያንን ወርቃማ ዘመንን ያስታውሰናል፡፡

ከዚህ በተለየ ግን ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደመጻፋቸውና እንደመተርጎማቸው ነገር ሁሉ የሠመረና እንከን የለሽ ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአንድም በሌላ አንዳንድ የይዘት፣ የትርጉም፣ የፍቺ ግድፈቶች ከዛ የባሰም የዶግማ ችግር ያለባቸው ለቤተክርስቲያን ትምህርት ስጋት የሆኑ ከስንዴ መሐል የተቀላቀሉ ጥቂት እንክርዳድ የተቀላቀለባቸው መጻሕፍት በቤተ ክርስቲያን ስም እየወጡ ነው፡፡ ስለዚህ እንክርዳዱን ከስንዴው ለቅሞ መለየትና ማረም ያስፈልጋል፡፡ ማረም ግን  ልዩ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ተግባር በመሆኑ ለሃይማኖቴ ‹‹ቀናተኛ›› ነኝ በማለት ብቻ አራሚ መሆን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ማረም ከስሜታዊነትና ከፈራጅነት ነጻ መሆንን፤ ሥራውን በአግባብ፣ በሥርዓትና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ለመሥራት የሚያስችል አቅምን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሃይማኖታችንን ከተሳሳቱ አስተምህሮዎች የመጠበቅ (ዕቅበተ እምነት) ዓላማዎች ምእመናን ከተሳሳተ ትምህርት መጠበቅ ተቀዳሚ ዓላማው ሲሆን በተሳሳተ ትምህርት የጠፉትን ለማዳን እውነትን በፍቅር መግለጥ ደግሞ ይከተላል፡፡ ዕቅበተ እምነት ትኩረቱን ያደረገው ሐሰት እንክርዳድን መንቀል ላይ ብቻ ሳይሆን እንክርዳዱን ስንነቅል ለጥሩ ዘር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግንም ያገናዘበ ነው፡፡ ‹‹እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን  ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም››፡፡ (ማቴ፲፫፥፳፱) ምክንያቱም ጸሐፍትና መተርጉማን የሚሳሳቱት ባለማወቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ እየተመለከትናቸው ያሉት በቤተክርስቲያናችን ስም እየታተሙ ያሉ አንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ እየታዩ ያሉት ስሕተቶች ብዙ መነሻ ምክንያት ቢኖራቸውም ዋና ዋናዎቹ ግን የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ) በቤተክርስቲያናችን ስም እየታተሙ ባሉ አንዳንድ መጽሐፍት እየታዩ ላሉት ስሕተቶች መነሻ ምክንያቶች

ያለበቂ ዕውቀት መጻፍ

ዕውቀትን ለማስተማር አስቀድሞ መማር ይቀድማል፡፡ ስለዚህ አንድ ጸሓፊ ከመጻፉ በፊት
አስቀድሞ በቤተክርስቲያናችን ባሉ የአብነት ወይም መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት ገብቶ መማርና የተማረውን ትምህርት ማደላደል ይገባዋል፡፡ ‹‹ሕዝቤ ዕውቀትን ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› (ሆሴ. ፬ ፥፮) ብዙውን ጊዜ ነቀፋ የሚገኝባቸው ጽሑፎች አንዳንዶች ከጉባኤ ሳይውሉ በጆሮ ጠገብነት ብቻ ተነሳስተው የተጻፉ ለመሆናቸው ዋቢ አያስፈልግም፡፡ የጸሓፊው ደግነት በመጽሐፉ ደግነት ይታወቃል እንዲሉ አበው ጸሓፊው ከጥሩ ምንጭ የተማረ ሲሆን መጽሐፉ እውነተኛ ይሆናል፤ እርሱም አይጠፋም፤ ሌሎችንም አያጠፋም
ነበር፡፡ ስለዚህ ከማድመጥ ለመናገር፣ ከማንበብ ለመጻፍ፣ ከማወቅ ለማሳወቅ መቸኮል የብዙ ጸሐፍትና መተርጉማን የስሕተት ምክንያት ነው፡፡

መጻሕፍትን በግብታዊነት መተርጎም

መጻሕፍትን ለመተርጎም መጽሐፉ የተጻፈበትም ሆነ ሊተረጎም የሚታሰበውን ሀገር ቋንቋ፣ ባሕል፣ ታሪክና ሥነ ልቡና በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ላይ እየተመለከትን ያለነው እንግሊዘኛ ቋንቋ አንብቦ መረዳት የሚችል ሁሉ እየተነሳ መንፈሳዊ ነው ብሎ የሚያስበውን መጽሐፍ ሲተረጉም እንመለከታለን፡፡  ‹‹ቅዱስ›› ይሁን አይሁን የማይታወቅ ‹‹ገድል›› ይሁን ግለ-ታሪክ የማይለይን ‹‹አባት›› ‹‹ቅዱስ›› ‹‹መነኮስ›› እየተባለ ይተረጎማል፡፡ ጥያቄው በእርግጥ ቤተክርስቲያን እነዚህን  ‹‹አባት››‹‹ቅዱስ››‹‹መነኮስ›› ተብለው ታሪካቸው የሚጻፍላቸውን ባለታሪኮች ታውቃቸዋለችን? በእርግጥ መጻሕፍቱ የመተርጎማቸው ዓላማ በግልጽ ይታወቃልን? መጻሕፍቱ ተመዝነው ለምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ይጠቅማሉን? የመጻሕፍቱ የዶግማ ይዘት በሚገባ የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ ያገናዘበ ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች ያስነሳሉ፡፡ ስለዚህ መጻሕፍትን በግብታዊነት መተርጎም ሌላው የስሕተት ምክንያት ነው፡፡

ሆን ተብሎ በአፅራረ ቤተክርስቲያን በሚደረግ የጥፋት ተግባር

ዛሬ ላይ ለቤተክርስቲያን እና ለሃይማኖታችን ‹‹ቀናተኛ›› ነን የሚሉ የቤተክርስቲያንን ታሪክ በማዛባት ላይ ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያንን የአንዱ ወገን ብቻ አድርጎ በማስመሰል እየቀረበ ያለው የፈጠራ ታሪክን መጻፍ፤ ትናንት አፅራረ ቤተክርስቲያን መናፍቃን ጀምረውት ያልተሳካላቸው፤ ቤተክርስቲያንን የመከፋፈል የማፍረስ ድርጊት ቀጣይ ተልእኮ ነው፡፡ ምእመናን የአገልጋይ ካህናት አባቶችን ምክርና ተግሣጽ እንዳይቀበሉ የግለሰቦችን ጉድለት እንደቤተክርስቲያን ጉድለት አድርጎ በማቅረብ ምእመናንን ከጠባቂ እረኞች አባቶች ጋር ለመለየት የሚደረጉ በሥርዋጽ በመንፈሳዊ መጽሐፍ ስም የሚታተሙ የአፅራረ ቤተክርስቲያንን ተልእኮ የሚያስፈጽሙ መጻሕፍት መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ሆን ተብሎ በአፅራረ ቤተክርስቲያን ምእመናንን ለማደናገር እየተጻፉ ያሉ መጽሕፍት እንዳሉም መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የተደራጀ የመጻሕፍት ማረሚያ ተቋም አለመኖር

በቤተክርስቲያናችን የመጻሕፍት እርማት ሥራ የሚሠራ አደረጃጀት የሊቃውንት ጉባኤ እንዳላት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በጣት የሚቆጠሩ ሊቃውንት በየቀኑ በቤተክርስቲያን ስም የሚወጡ የድምጽ፣ የምስል፣ የጽሑፍ ሥራዎችን መርምሮ ትክክለኛውን እርማት በተገቢው ጊዜ ይስጡ ማለት ውቅያኖስን በጭልፋ እንደማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ጸሐፍትና መተርጉማን ሥራዎቻቸውን ለማሳረም ቢፈልጉም አርታዒ ከማጣት የተነሳ ጽሑፎቻቸውን ከነስሕተቱ ለማሳተም ይገደዳሉ፡፡ ስለዚህ የተደራጀ የመጻሕፍት ማረሚያ ተቋም አለመኖር የችግሩ ሁሉ መነሻ ምክንያት ነው፡፡

ለ) በመጻሕፍት ዙሪያ እየታዩ ያሉት ችግሮችን ለመፍታት ምን ቢደረግ ይሻላል?

የሊቃውንት ጉባኤ አደረጃጀትን ማስፋት

ቤተክርስቲያን  የሚመክሩ፣ የሚገሥጹና የሚያርሙ መምህራንንና ሊቃውንትን ሳታጣ የመጻሕፍት እርማት ሥራ በአግባቡ መሥራት አለመቻል ቤተክርስቲያን ያላትን የዕውቀት ሀብት በአግባቡ አለመጠቀም ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የሊቃውንትን ጉባኤ በማእከል ብቻ መወሰን ስለሆነ አደረጃጀቱን እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን እንደ የአግባቡ ማውረድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ በአንዳንድ የቤተክርስቲያን መዋቅራት ላይ በጥቂቱም ቢሆን ይስተዋላል፤ ጅምሩ መልካም ቢሆንም የአርትዖት ሥራው ዕውቀቱ እና ፍላጎቱ ባላቸው መምህራን መደራጀት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ነባሩን የሊቃውንት ጉባኤ ከማጠናከር ባሻገር ከችግሩ ስፋት አንጻር የቤተክርስቲያን መዋቅርን ጠብቆ የሊቃውንት ጉባኤን በሀገረ ስብከት፣ በክፍለ ከተማ፣ በወረዳና አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ ማደራጃት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡

ምእመናንን በመንፈሳዊ መጻሕፍት ዙሪያ እየታዩ ባሉት ችግሮች ግንዛቤ ማስጨበጥ

ምንም እንኳን ምእመናን የችግሩ ግንባር ቀደም ተጎጂ ቢሆኑም የመፍትሔውም አካል መሆን ይችላሉ፡፡ በየጊዜው ለምእመናን የግንዛቤ ትምህርት መስጠት ችግሩን ለመቅረፍ አንዱና መሠረታዊ ችግሩን የምንከላከልበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ በቀላሉ ምእመናን የሚያነቡዋቸውን መንፈሳውያን መጻሕፍት ለመምረጥ በገዛ ስሜታቸው ከመመራት ይልቅ በምክረ መምህራን መጻሕፍትን ቢያነቡና ያልተረዱትን ቢጠይቁ ራሳቸውን ከስሕተት በመጠበቅ የድርሻቸውን ሊወጡ ይቻላሉ፡፡

አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በቅጽራቸውና በዙሪያቸው የሚሸጡትን መንፈሳዊ መጻሕፍትን በመለየት ለምእመናን ማሳወቅ

አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በቅጽራቸውና በዙሪያቸው የሚሸጡትን መጻሕፍት ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር ሐሰተኛ መጻሕፍትን ቢለዩ፤ ለምእመናን ተገቢ ግንዛቤ ቢያስጨብጡና የአጥቢያቸውን ምእመናን ከስሕተት ከጥርጥር ጠብቀው በቀላሉ የሐሰት መጻሕፍትን ስርጭት መቆጣጠር ይቻላል፡፡

፬ አሳታሚዎች  የሚያትሙትን በቤተክርስቲያን ስም የተጻፈ መጽሐፍ ሕጋዊነትን እንዲጠይቁ ማድረግ

አሳታሚዎች በተቋም ወይም በድርጅት ስም ለሚያትሙት ማንኛውም ሥራ ሕጋዊነትን እንደሚጠይቁት ሁሉ በቤተክርስቲያን ስም የተጻፈ መጽሐፍ ሕጋዊነትን ከሚመለከተው የቤተክርስቲያን አካል ፈቃድ ተገቢነት ጠይቀው መጻሕፍትን በኃላፊነት ቢያሳትሙ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ይቻላል፡፡

በሕጋዊ መንገድ ቤተክርስቲያን መብቷን ማስከበር

ቤተክርስቲያን ለዘመናት የሀገርን፣ ባሕል፣ ታሪክ፣ ቅርስና ሀብት ጠብቃና አስጠብቃ የኖረች የሀገር ባለውለታ ብትሆንም ወርቅ ላበደረ ጠጠር ሆነና ከቅርብ ዐሥርት ዓመታት ወዲህ ህልውናዋን የሚገዳደሩ ፈተናዎች እያጋጠሟት ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች መካከል  ጠላት ዲያብሎስ ባነሳሳቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በድፍረት ሆን ተብሎ የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ ለመበረዝ፣ ምእመናንን ለማደናገር፣ ለማሳትና ለመለያየት ተብለው የሚሰራጩ የሐሰት መጻሕፍት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህን ችግር መከላከል የጉዳዩ ባለቤት የሆነችው ቤተክርስቲያን ብትሆንም ከቤተክርስቲያን ዐውድ ውጭ ለሚደረጉ በቤተክርስቲያን ላይ ያነጣጠረ የጥፋት ተልእኮ  መንግሥት በሕግ የመፍታት ኃላፊነት አለበት፡፡ የቤተክርስቲያናችንን ልዕልና የሚነኩ፣ የካህናት አባቶችን ስም የሚያጠፉ፣ የምእመናንን ክብር የሚያሳንሱ መጻሕፍት በአፅራረ ቤተክርስቲያን ተጽፈው መመልከት ተለምዷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለምአቀፋዊቷን ቤተክርስቲያን የጥቂት ቋንቋ ተናጋሪ የሆነች በማስመሰል፣ ያልነበሩበትን ዘመን ታሪክ በመጻፍ፣ ቤተክርስቲያንን የመከፋፈል ዓላማ ይዘው የሚጻፉ መጻሕፍት የችግሩን መጠን አስፍቶት ከሃይማኖታዊነት ወደ የግጭት መንስኤ እስከመሆን እያደረሱት ይገኛል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሆን ተብለው በሕዝቦች መካከል መለያየትን ለመፍጠር የሚጻፉ የፈጠራ ታሪክ መጻሕፍት  በሀገራችን ሕግ መሠረት ጉዳዩን በአግባብ እየተከታተልን የቤተክርስቲያንችንን መብቷን ልናስጠብቅ ያስፈልጋል፡፡

በሕገ መንግሥት የሃይማኖት ነጻነትን በተመለከተ በአንቀጽ ፳፯ ‹‹የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት›› በሚል የተደነገገ ሲሆን ንዑስ አንቀጽ ፳፯/፭ ደግሞ ገደብ ያስቀምጣል፡፡ ‹‹ሃይማኖትና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች፣ ነጻነቶች እና መንግሥት ከሃይማኖት ነጻ መሆኑን ለማረጋረገጥ በሚወጡ ሕጐች ይሆናል››፡፡ ስለዚህ በሃይማኖት ነጻነት ስም ማንም እየተነሳ በቤተክርስቲያን ላይ አንደበቱን ሊያላቅቅ እጁን በስድብ ብዕር ሊያነሳ አይችልም፡፡ በተጨማሪ አንቀጽ  ፳፱ የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ  ፳፱/፮  ገደብ ሊጣልባቸው የሚችልባቸውን ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ ‹‹እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሐሳብና መረጃ የማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ሕጐች ብቻ ይሆናል፡፡ የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በእነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ›› በማለት ገደቡን አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ በሐሳብ ነጻነት ስም የካህናት አባቶቻችንን ስም ማጥፋት የምእመናን ክብር መንካት አይቻልም፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር ፭፻፺/፳፻ የተገለጸው የፕሬስ ነፃነትም በተለያዩ ምክንያቶች ሊገደብ ይችላል። የፕሬስ ነፃነት የሰው ክብርንና መልካም ስምን ለመጠበቅ እንዲሁም ብሔራዊ ደኅንነትንና ማኅበራዊ ጤንነትን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ሲባል በፕሬስ ነፃነት ላይ እገዳ ሊጣል እንደሚችል ያስቀምጣል፤ ስለዚህ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በዝርዝር ሕጎች የተጠቀሱትን አንቀጾች መሠረት አድርጎ የቤተክርስቲያን መብቷን ማስከበር ይገባል፡፡

በመጨረሻ በቤተክርስቲያን ስም በማወቅና ባለማወቅ እየታተሙ የሚወጡትን የሐሰትና የስሕተት መጻሕፍትን ኅትመት ስርጭት ለመቆጣጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ቢሆንም በዋነኝነት ግን ኃላፊነቱ የቤተ ክርስቲያናችን ነው፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያ ያልተቆራረጠ የዕቅበተ እምነት ትምህርት ለምእመናን በመስጠት የእነርሱን ግንዛቤ ማሳደግ፣ በየጊዜው ከሚደረጉ የዘመቻ ሥራዎች ተላቆ ዘለቄታ ያለው ሥራ መሥራት፣ በግል ጥቅምና በወገንተኝነት ላይ ከተመሠረተ ‹‹የሃይማኖት ጥብቅና›› መላቀቅ ፣ለእውነት ቃለ እግዚአብሔር ብቻ ወገንተኝነት ያለው ጠንካራ ተቋማዊ መሠረት ያለው እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የሊቃውንት ጉባኤ ማደራጀት ጊዜ የማይሰጠውና አማራጭ የሌለው ተግባር ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ለራስህ እና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ›› እንዳለ ጸሐፍትና መተርጉማን ለራሳችን ብንጠነቀቅ አንባቢ ምእመናንን ማዳን ብቻ ሳይሆን  የአፅራረ ቤተክርስቲያንንም የሐሰት መጻሕፍትን በማጋለጥና ምላሽ በመስጠት ማሳፈር ይቻላል፡፡ ዛሬ ችግሩን በጊዜ ለመፍታት ጥረት ካላደረግን ነገ ቤተክርስቲያንን የሚረከበው ትውልድ ልምዱ ከግንድ ከብዶበት እውነቱን ከሐሰት፤ እምነቱን ከክሕደት ለመለየት ይቸገራል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር