‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል›› (መዝ. ፴፬፥፯)

ከምንባባት ዐውድ

ሐምሌ ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ከመከራና ሥቃይ ለመታደግና በችግር ጊዜም ለመርዳት ሥልጣን ከተሰጣቸው ጊዜ አንሥቶ በእግዚአብሔር አምላክ አምነውና ታምነው የኖሩ ጻድቃንን ሲራዱ ኖረዋል፡፡ እንደየተልእኳቸውም በአምላካቸው ትእዛዝ ከጠላት እጅ በማዳን ከእቶን እሳትና ከፈላ ውኃ አውጥተዋል፤ በማዕበል ከመስጠም አድነዋል፤ አንዲሁም በአራዊት አፍ ከመበላት ታድገዋል፡፡

ኃያሉ ሊቀ መላእክ ቅዱስ ገብርኤልም በሐምሌ ፲፱ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ከእሳት አድኗቸዋል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመዘገበውም ታሪኩን ይዘንላልችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ!

ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖትና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ናት፡፡ ቂርቆስ የሚባል ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት ሀገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፣ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡

በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አስነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡

ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ የፈላ ውኀ ያድነናል›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ውኀም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡

ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ‹‹ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በመልአኩም ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ምእመናንም ድነዋል፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ስም በሚጠራባቸውና በሚዘከርበት ገዳማትና አድባራት መልአኩ የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን ለሞት እንደሚታደጉና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡ (ሮሜ ፰፥፴፰-፴፱)

ሰዎች በሃይማኖታቸው ጸንተው በሕይወታቸው ዘመናቸው መከራ ባጋጠማቸው ጊዜ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ሁሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል በመተዛዘንና በመደጋገፍ የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይጠበቅብናል፡፡

ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን ‹‹በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወሌሊተ፤ በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን›› እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ መልአኩ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል›› እንዲል። (መዝ.፴፬፥፯)

የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው አይለየን፤ አሜን!

ምንጭ፤ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሐምሌ፣ ድርሳነ ገብርኤል፣ ገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!