‹‹የመባርቅት ምሥጢሮች ሁሉ ተገለጡልኝ›› (ሄኖክ ፲፭፥፵፬)

ሐምሌ ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ሰማይ በደመና ተሸፍኖ ዝናብ በሚዘንብበት በዘመነ ክረምት መብረቅ በነጎድጓዳማ ድምጽ በብልጭታ በሰማይ ይፈጠራል፤ የእሳት ሰይፍ፣ የእሳት ፍላፃ፣ በዝናም ጊዜ ከደመና አፍ የሚመዘዝ የሚወረወርና ውኃው በደመና አይበት ተቋጥሮ በነፋስ ወደል ጋዝ ተጭኖ ሲመጣ፣ ደመናና ደመና በተጋጨ ጊዜ መብረቅ እንደሚፈጠር መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል፡፡ይህም በደመና ውስጥ የሚፈጠር  ሲሆን ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ የሚከሠትና በሰማይ የሚታይ ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የመብረቅ ትርጓሜ ከሥርወ ቃሉ እንደተገኘ ሲያስረዱ ‹በረቀ፣ ብልጭ አለ› ማለት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (ራእ. ፬፥፭፣ ኤር ፲፥፲፫፣ ኢዮ. ፴፯፥፬፣ መጽሐፈ ስዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፪፻፹፱)

ነቢዩ ሄኖክ ደግሞ ‹‹ከዚህም በኋላ የብርሃናትና የመባርቅት ምሥጢሮች ሁሉ ተገለጡልኝ›› በማለት እንደተናገረው መብረቅ በተለያየ መልኩ ይከሠታል፡፡ በሁለት ደመናዎች መካከልም ይከሠታል፤ መብረቅ ደመናትን የሚሞላበት ሁኔታም አለ፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜም ብልጭታ በሰማይ ከታየ በኋላ መብረቁ ከደመና እስከ ደመና ይደሳል፡፡ (ሄኖ. ፲፭፥፵፬፣ ማኅቶት ዘመን ገጽ ፪፻፲፪-፪፻፲፫)

ሰዎች ስለ መብረቅ የተለያየ አመለካከት አላቸው፤ መብረቅ የዝናብ ውጤት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ የእግዚአብሔር የቁጣ መግለጫ እንደሆነ ያምናሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ መብረቅን የፈጠረው ለሰዎች ጥቅም ነው፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ እንደተናገረው እግዚአብሔር ‹‹በላይ በሰማይ ውኅችን ይሰበስባል፤ ከምድርም ዳርቻ ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፡፡›› (ኤር. ፲፥፲፫)ነቢዩ ሄኖክ ደግሞ ‹‹ለበረከትና ለጥጋብም ያበራሉ›› በማለት እንደተናገረው በመብረቅ ብልጭታ ዕፅዋት ያብባሉ፤ ያፈራሉም፤ እነርሱንም በመመገብ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳትም ጭምር ናቸው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ነጎድጓድ መብረቅ ከወረደ በኋላ የሚሰማ ድምፅም እንደሆነ ገልጾ ነገር ግን ለማስደንገጥ ወይም ለመዓት ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን አዝርዕትና አትክልት እንዲበቅሉ፤ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚያደርግ ጭምር መሆኑን ይነግረናል፡፡ ከመብረቅ የሚፈጠረው ድምጽ ነጎድጓድ ማሕፀነ ምድርን በመክፈት ውኃው ሠርፆ እንዲገባና አዝርዕትና አትክልት እንዲበቅሉ፤ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚያደርግ ጭምር ነው፡፡ (መዝ.፳፰፥፫፣ ኢዮ.፵፥፬፣ ማኅቶት ዘመን ገጽ ፪፻፲፪-፪፻፲፫)

ነገር ግን መብረቅ ለመርገምም ቢሆን በመናፍስት ቃል እንደሆነ ነቢዩ ሄኖክ እንደተናገረው ‹‹በእነዚያም ወራቶች የመባርቅትንና የብርሃናትን ምሥጢራት፥ ፍርዳቸውንም አዩ፤ የመናፍስት ጌታም እንደ ወደደ ለበረከትና ለመርገም ያበራሉ፡፡›› መብረቅ ለሰው ልጆች ጥቅም ቢፈጠርም በሚከሠትበት ወቅት በብልጭታውና በነጎድጓዳማው ድምጹ ሊጎዳ ይችላልና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም መብረቅ ሲከሠት የነጎድጓዱ ድምጽ አስፈሪና አስደንጋጭ በመሆኑ በአቅራቢያው ሰዎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር ሊገድል ይችላል፡፡ ሰዎች መብረቅ በሚከሠትበት ጊዜ በሰማይ ስንመለከት ገዳይ፣ አውዳሚ፣ አጥፊ እንደሆነም የምናስበው ለዚህ ነው፡፡ (ሄኖክ. ፲፭፥፴፱-፵)

መብረቅ በሚከሰትበት ጊዜ ሰዎች በአካባቢው ካሉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፤ ወደ ቤታቸው ሮጠው መግባት አለባቸው፡፡ መብረቅ በሚከሠትበት ጊዜ ዛፍ ሥር መቆምም የለብንም፤ ብልጭታው የስበት ኃይል ስላለው መሬቱም ሆነ በአካባቢው ያሉ ነገሮችን ይስባል፤ ሲወድቅ ደግሞ ኃይሉ በእጥፍ ይሆናል፤ ስለዚህም መጠንቀቅና መብረቅ ከሚፈጠርበት ሥፍራ መራቅ ያስፈልጋል፡፡ በሜዳ ላይ ደግሞ በሚከሰትበት ጊዜ ሰውነታችን መሬት እንዳይነካ መጠንቀቅ አለብን፡፡

ከዚህ በሻገር ግን መብረቅ እግዚአብሔር አምላክ ለመግቦት ለፈጠራቸው ድንቅ ሥራዎቹ መካከል በመሆኑ ፈጣሪያችንን ማመስገን አለብን፡፡ በተለይም በዚህ ወር የተዘራ እህል የሚበቅልበትና ታጭዶ ለመብል የሚደርስበት በመሆኑ ሁሉም ወቅቱን ጠብቆ መከሠቱ የአግዚአብሔር ቸርነት መገለጫው ነው፡፡ እርሱ ዝናብን አዝንቦና መባርቅትን በደመና እንዲፈጠሩ ባያደርግልን መኖር አንችልም፤ ኑሮአችንም በችግርና በመከራ የተጋለጠ ይሆን ነበር፡፡

ስለዚህም በዘመነ ክረምት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መብረቅንና ነጎድጓድን እንዲሁም ዝናብን የሚመነው መዝሙራት ይዘመራሉ፤ ምንባባት ይነበባሉ፤ ስብከት ይሰበካል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በነጎድጓድና በመብረቅ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን፤ የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡ ምንባባትም ከቅዱስ ወንጌልና ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት እንዲሁም ከሐዋርያት ሥራ ክረምቱን በተመለከተ የተዘጋጁት ይነበባሉ፡፡

ቅዱስ ያሬድም ይህን ወቅት አስመልክቶ በድጓው ላይ ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን፤ ይጸግቡ ርኁባን ምድርኒ ርእየቶ ወአእኰተቶ ባሕርኒ ሰገደት ሎቱ፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናብም በዘነመ ጊዜ ድሆች ደስ ይሰኛሉ፤ ረኃብተኞችም ይጠግባሉ፤ ምድር አየችው፤ አመሰገነችውም፤ ባሕርም ሰገደችለት›› የሚለው ዜማ ይዜማል፡፡ (ድጓ ዘክረምት)

ቅዱስ ዳዊት ደግሞ በመዝሙሩ ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፤ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፡፡ ‹‹ሰማይን በደመና የሚሸፍን፤ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ ልምላሜውንም ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል›› በማለት ዘምሯል፡፡ (መዝ.፻፵፮፥፰፤መዝ.፻፴፬፥፮-፯፤መዝ.፸፮፥፲፰፤ መዝ.፷፬፥፱)

እግዚአብሔር አምላክ ቸርነቱን ያብዛልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር