dsc03541

የአሰቦት ገዳም የመንገድ ችግር በመቀረፍ ላይ ነው

ኅዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ

•    በሁለት በጎ አድራጊ ወጣቶች የ6 ኪሎ ሜትር የተራራው አስቸጋሪ መንገድ ተሠራ
•    የ12 ኪሎ ሜትሩ መንገድ በመሠራት ላይ ነው

dsc03541የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድሥት ሥላሴና አቡነ ሳሙኤል ገዳም 6 ኪሎ ሜትር የተራራው መውጫ መንገድ በሁለት በጎ አድራጊ ወጣቶች ሙሉ ወጪውን በመሸፈን የጥርጊያ መንገዱን ሥራ ከመስከረም 7 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ  በ17 ቀናት ውስጥ በመሥራት ተጠናቀቀ፡፡

የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ማርያም ተክለ ፃድቅ ስለ መንገድ ሥራው ሲገልጹ “እግዚአብሔር አነሣሥቷቸው ይህ ቅዱስ ገዳም ያለበትን የመንገድ ችግር ተገንዝበው ሙሉ ወጪውን በመሸፈንና መንገዱ ተሠርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ እዚሁ ከእኛው ጋር በመሆን ሥራውን እየተቆጣጠሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ የመንገዱ መሠራት ገዳሙን ከእሳት ቃጠሎ፤ በተለይም የደን ጭፍጨፋ ከሚያካሂዱ አካላትና ከተለያዩ አደጋዎች ይታደገዋል፡፡ ምእመናንም ከዚህ ቅዱስ ሥፍራ በመገኘት በረከት እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል፡፡ ለኛ ለገዳማውያንም መውጣት መውረዱን ያቀልልናል፡፡ ሁለቱ ወጣቶች ያከናወኑት በጎ ተግባር ሌሎችም አርአያነታቸውን ሊከተሉ ይገባል  ” ብለዋል፡፡

 

ቴዎድሮስ ሰሎሞን ይባላል፡፡ የ”ዴታና ቢዝነስ ሓላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር” ባለቤት ነው፡፡ የ6 ኪሎ ሜትር የተራራውን ጥርጊያ መንገድ ከጓደኛው ጋር በመሆን  ሙሉ ወጪውን በመሸፈን ለመሥራት በቅቷል፡፡ ምን እንዳነሣሣው ጠይቀነው ሲመልስ “አሰቦት ገዳም ላለፉት 10 ዓመታት በዓመታዊ ንግሥ በዓል ላይ በረከት ለማግኘት ተመላልሻለሁ፡፡ ዋነኛ ችግር ነው ብዬ የተመለከትኩትም ምእመናን ተራራውን ለመውጣት የሚያደርጉትን አድካሚ ጉዞ ነበር፡፡ አረጋውያን መውጣት ተስኗቸው በየመንገዱ እያረፉ ሲጨነቁና ሲጠበቡ እመለከታለሁ፡፡ ይህንን መንገድ መች ነው የምሠራው እያልኩ ሳስብ ቆይቻለሁ፡፡ አሰበ ተፈሪ የሚገኙ ወንድሞችን አማክሬያቸው ለኦሮሚያ ግብርና ጉዳዩን በማሳወቅና መንገዱን ለመቀየስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚወገዱ ዛፎችን ጉዳይ በመነጋገርና ፈቃድ በመውስድ የጥርጊያ መንገዱን ሥራ ከጓደኛዬ ጋር ተመካክረን የምሠራበትን ዶዘር ቦታው ድረስ በመውሰድ እግዚአብሔር የፈቀደልንን ያህል አባቶች በጸሎት እየተራዱን መንገዱን በማስፋትና በመጥረግ ለመኪናም ሆነ ለሰው በቀላሉ መውጣት እንዲያስችል ተደርጓል፡፡” ብሏል፡፡

“ከዚህ በፊት ወደ ገዳሙ ሄጄ አላውቅም፡፡ ጓደኛዬ  ወደዚህ ገዳም ይመላለስ ስለነበር የገዳሙን ችግር ይነግረኝ ነበር፡፡ አብረን ለመሥራት ተነጋግረን የራሴን ግሬደር በማምጣት በመቀየስና ተለዋጭ መንገድ በማዘጋጀት መንገዱን አስተካክለን ለገዳሙ አስረክበናል፡፡ ከዚህ በረከት ልሳተፍ በመቻሌ ተደስቻለሁ” በማለት የገለጸው ደግሞ የ”ዳክ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ኪራይ አገልግሎት” ድርጅት ባለቤት ወጣት ክብሮም ተክሌ ነው፡፡

dsc03547ሥራውን ለመሥራት በገዳሙ በቆዩባቸው ጊዜያት ያስተዋሉትን ሲገልጹም “የገዳማውያኑ ስሜት ልዩ ነው፡፡ የገዳማውያን አባቶችና እናቶች ደስታ ተመልክተናል፡፤ እንኳን እነሱ ለዘመናት የተቸገሩት ቀርቶ እኛም የተሰማን ስሜት መግለጽ ከምንችለው በላይ ነው፡፡ ደስታቸው አስደስቶናል፡፡ ሰዎች ለእግዚአብሔር በሰጡ ቁጥር የሚጎድልባቸው የሚመስላቸው አሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የተሻለ ነገር እንደሚሰጣቸው ማመን አለባቸው፡፡ ለእግዚአብሔር መስጠት አያጎድልም ይጨምራል እንጂ፡፡ የእኛን ደስታ ሌሎችም እንዲጋሩት እንፈልጋለን፡፡ ያደረግነው ነገር ትንሽ ቢሆንም ከእግዚአብሔር ጋር ከሆንክ ትረካለህ፡፡ ወደፊትም አቅማችን እያዳበርን ሌሎች ገዳማትን የመርዳት እቅድ አለን፡፡” በማለት ሁለቱ በጎ አድራጊ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡

ማኅበረ መነኮሳቱ ስለተከናወነው የመንገድ ሥራ  ሲገልጹ “ብርሃን አየን፡፡ ለዘመናት የተቸገርንበትና ከአቅማችን በላይ የሆነውን ነገር እግዚአብሔር ደብቆ ያስቀመጣቸው ልጆቹን በመላክ አስወገደልን” ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ከአሰቦት ከተማ መገንጠያ እስከ ተራራው መውጫ ሥር ድረስ 12 ኪሎ ሜትር የሚፈጅ ሲሆን ገዳሙ ያለበትን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከተው ከክልሉ መንገዶች ባለስልጣን መሥሪያ ቤት ጋር  በመወያየት እንዲሁም አዲስ አበባ ከሚገኙ ምእመናን ጋር በመነጋገር  የመንገድ ሥራውን የሚቆጣጠርና የሚመራ አንድ ኮሚቴ አዋቅሮ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን ሁሉን አቀፍ ተደራሽነት ያለው የገጠር መንገድ ፕሮግራም (Universal Rural Road Access Program) – URRAP መንገዱን ለመሥራት ባጠናው ጥናት መሠረት እሰከ 6 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅና 1 ሚሊዮን ብር ገዳሙ ከቻለ ቀሪውን ወጪ በመንግሥት እንደሚሸፈን በመግለጹ ስምምነት ላይ በመድረስ ሥራው ሊጀመር ችሏል፡፡

 

“ገዳሙም ባቋቋመው ኮሚቴ መሠረት ገንዘብ ከምእመናን በማሰባሰብ ላይ የሚገኝ ሲሆን የመንገዱ ሥራም የመጀመሪያውን ዙር በማጠናቀቅ ወደ ሁለተኛው ክፍል ተሸጋግሯል፡፡ ሥራውንም በቅርበት በመከታተል ላይ እንገኛለን፡፡ ገዳሙ ገንዘብ ለማሰባበሰብ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን ከምእመናን  የታቀደውን ያህል ለማሰባበሰብ ባይቻልም በተገባው ቃል መሠረት የመጀመሪያ ዙር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ቀጣዩንም ሥራ ለማከናወን የገንዘብ ማሰባሰቡ ይቀጥላል“ በማለት የኮሚቴው የቴክኒክ ክፍል ሓላፊ የሆኑት ኢንጂነር ዮሐንስ ዘውዴ  ገልጸዋል፡፡

 

በተጨማሪም ማኅበረ ቅዱሳን ገዳሙ ያለበትን የውኃ ችግር ለመቅረፍ በቅርቡ የባለሙያዎች ቡድን በመላክ አጥንቶ መመለሱን ከቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተገደመው የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድሥት ሥላሴና አቡነ ሳሙኤል ገዳም በተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎ ያጋጠመው ሲሆን እሳቱን ለመጥፋት በተደረገው ጥረት ውስጥ የተራራው አስቸጋሪነት ትልቁ ፈተና እንደነበር ይታወሳል፡፡