ledet04

የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር

ኅዳር 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ሰሎሞን መኩሪያ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ledet04በቤተ እስራኤል ስም ጠባይን፣ ግብርን፣ ሁኔታን እንደሚገልጥ ሁኖ ይሰየማል፡፡ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ማርያም” የሚለውን ስያሜ ከማየታችን በፊት ስለ ድንግል ማርያም አባቶቻችን በነገረ ማርያም ያሉትን ጥቂት እንመለከታለን፡፡ “ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ በም.1፥9 ላይ እንደተናገረ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር፡፡” እንዳለ በኦ.ዘፍ.ም.19፥1 ጀምሮ እንደተጻፈ የሰዶምና የገሞራ ሰዎች በበደላቸው ምክንያት እንደተደመሰሱ /እንደጠፉ/ እናነባለን፡፡ አዳምና ልጆቹ በሲዖል ባህር ሰጥመን እንዳንቀር እግዚአብሔር በቸርነቱ ንጽህት የሆነች ዘር መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እያማለደች የምታሰጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባያስቀርልን ከእርሷም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ በሞቱ ሞታችንን ባይደመስስ ወደ ሕይወት ባይመልሰን ኖሮ መኖሪያችን ሲዖል ነበር፡፡

 

ለፍጥረት ሁሉ መዳን ምክንያት ያደረጋት ንጽሕት ዘር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትውልዷ በአባቷ በኩል ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፡፡ በእናቷ በኩል ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን ነው፡፡ የአባቷ ስም ቅዱስ ኢያቄም የእናቷ ስም ቅድስት ሐና  ይባላል፡፡ ሁለቱም በሕግ በሆነ ቅዱስ ጋብቻ ሲኖሩ ለብዙ ዘመን ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጠናል በማለት ተስፋ እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት ደጅ እየጸኑ ኖሩ እንጂ፡፡ በዘመኑ ልጅ ያልወለደ ኀጢአተኛ፣ እግዚአብሔር የተጣላው ተደርጎ ይወሰድ ስለነበረ ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚያመጡትን መብዓ አይቀበሏቸውም፤ ይሰድቧቸው፣ ያሽሟጥጧቸውም ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ታግሰው ሲኖሩ እግዚአብሔር ትእግሥታቸውን ተመልክቶ የሚወልዷትን የድንግል ማርያምን ነገር በህልም ገለጸላቸው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሲጠብቁ እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተፀንሳለች፡፡ በተፀነሰች ጊዜ ብዙ ተአምራት ተደርጓል፡፡ የሃናን ማሕፀን እየዳሰሱ፡- ብዙ እውራን አይተዋል፣ ድውያን ተፈውሰዋል፣ ምውታን ተነሥተዋል፡፡ ይህንን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ ኢያቄምን እና ቅድስት ሐናን በድንጋይ ወግረው በእሳት አቃጥለው ሊገድሏቸው በጠላትነት ሲነሡ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሊባኖስ ወደ ሚባል ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሳሉ በግንቦት 1 ቀን ከፀሐይ 7 እጅ የምታበራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመኀልይ በም.4፥8 ላይ እንደተናገረ “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ነይ…. ከአንበሶች ጉድጓድ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች፡፡” እንዳለ ይህ ትንቢት ተፈጸመ በተወለደች በ8ኛው ቀን ስሟን “ማርያም” ብለው አወጡላት ለመሆኑ ማርያም ማለት ምን ማለት ነው?

 

ሀ. ማርያም ማለት ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝ.126፥3 ላይ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፡፡” ብሎ እንደተናገረ አባቷ ቅዱስ ኢያቄም እናቷ ቅድስት ሐና ከእግዚአብሔር የተሰጠችን ስጦታችን፣ ሀብታችን ናት ብለው “ማርያም” አሏት፡፡ ለጊዜው ለእናት እና ለአባቷ ስጦታ ሁና ትሰጥ እንጂ ለፍፃሜው ለፍጥረት ሁሉ እናት አማላጅ ሆና ከእግዚአብሔር የተሰጠች ናት በተለይ ለክርስቲያኖች በእምነት እናትነቷን እና አማላጅነቷን ለሚቀበሉ በዮሐንስ ወንጌላዊ አማካኝነት እናት ሁና የተሰጠች ልዩ ስጦታ ናት አምላካችን ክርስቶስ በቀራኒዮ አደባባይ በመስቀል ተሰቅሎ ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍስሶ ለድኅነታችን እንደሰጠን ሁሉ እናቱንም እናት ትሁናችሁ ብሎ ሰጥቶናል፡፡” ዮሐንስ ወንጌላዊ ወደ ቤቱ እንደወሰዳት እኛም ወደ ቤተ ልቦናችን ልናስገባት ጣዕሟን በአንደበታችን ፍቅሯን በልቦናችን ልናሳድረው ያስፈልጋል፡፡ ዮሐ.19፥26 የድንግል ማርያም ጣዕሟ በአንደበታችን ፍቅሯ በልቦናችን ይደር፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ከእግዚአብሔር ተልኮ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መጥቶ እያመሰገናት እየተሳለማት የነገራት ነገር ቢኖር እርሷ “ምልዕተ ጸጋ ወክብር” እንደሆነች ነው፡፡ ሉቃ.1፥28 እንግዲህ መልአኩ ከእግዚአብሔር አግኝቶ የእመቤታችንን ነገር እንደነገረን የጐደለባት ጸጋ የሌለ እመቤት ናት እና እኛ ደግሞ ብዙ ነገር ጐድሎብናልና ከተትረፈረፈ ጸጋዋ እንድታድለን ምልዕተ ጸጋ ምልዕተ ውዳሴ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልንማፀናት ይገባል፡፡ እመቤታችን ጸጋ በረከት ታድለን፡፡

 

ለ. ማርያም ማለት ፍፅምት ማለት ነው፡ “ፍፅምት” ማለት እንከንና ጉድለት የሌለባት ማለት ነው፡፡ እመቤታችን ለጊዜው መልክ ከደምግባት ጋር አስተባብራ በመገኘቷ ፍፅምት ተብላለች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በባሕርይው ቅዱስ ነው፡፡ ዘሌ.19፥2 ቅዱስ እና ንፁሐ ባሕርይ የሆነ እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን በወደደ ጊዜ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንደተናገረ “እግዚአብሔር በሰማይ ሁኖ ምሥራቁን እና ምዕራቡን ሰሜኑን እና ደቡቡን ዳርቻዎችን ሁሉ ተመለከተ እንዳንቺ ያለ አላገኝም የአንቺን መዓዛ ወደደ፤ ደምግባትሽን ወደደ፤ የሚወደውን ልጁን ወደ አንቺ ሰደደ” እንዲል፡፡ ንፁሐ ባሕርይ እግዚአብሔር ለማደሪያነት /ለተዋሕዶ/ እመቤታችንን መረጠ እርሷም ፍፅምት ናት የአዳም መርገም ያልወደቀባት /ጥንተ አብሶ/ የሌለባት ጠቢቡ ሰሎሞን በመኀል.4፥7 ላይ እንደተናገረ እንዲህ ብሎ “ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውር የለብሽም፡፡” እንዲል እንኳን የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቀርቶ ወዳጆቹ ቅዱሳን እንኳን አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ሲያደርጉ ከፍፁምነት ማዕረግ ይደርሳሉ ይህንንም ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክርላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ኖኅ በትውልዱ ጻድቅ ፍፁምም ሰው ነበር  ዘፍ.6፥9፡፡ ኢዮብም ፍጹምና ቅን እግዚአበሔርንም የሚፈራ ከክፋትም የራቀ ነበር ኢዮብ 1፥1፡፡ ይላል፡፡ የኖኅን እና የኢዮብን አምላክ የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍፅምትነቷ አያጠራጥርም፡፡ የድንግል ማርያም ጸጋ በረክት ይደርብን፡፡

 

ሐ. ማርያም ማለት የሕያዋን እናት ማለት ነው፡፡ ዘፍ.3፥20 ላይ “አዳምም ለሚስቱ ሔዋን” ብሎ ስም አወጣ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና፡፡ ይላል በእርግጥ ሔዋን ለሕያዋን ሁሉ ማለትም ለፍጥረት ሁሉ እናት ናት ግን ፍጥረትን ሁሉ አስጐድታለች ማለትም አትብሉ ተብሎ ከእግዚአብሔር የታዘዘውን ዕፀ በለስን በልታ ለባሏ ለአዳም በማብላቷ በሰው ልጆች ላይ የሞት ሞት እንዲመጣ /እንዲፈርድባቸው/ ምክንያት ሁናለች ከእርሷ ምክንያተ ስህተትነት የተነሣ የገነት ደጃፎች ተዘጉ በምትገለባበጥ የኪሩብ ሰይፍ እንድትጠበቅ ሆነ፡፡ ዘፍ.3፥24 በዚህ የተነሣ በሰው ልጆች ላይ 5500 ዘመን ሞት ሰለጠነ፡፡ አዳም ግን “ሔዋንን” የሕያዎን ሁሉ እናት ብሎ በትንቢት የተናገረላት ሔዋንን ሳይሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ “በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኀወ ለነ” ይላል ትርጉሙም “ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ ዳግመኛ ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን” ማለት ነው፡፡ ሔዋን ሕያዋንን ሁሉ አስጐዳች ዳግማዊት ሔዋን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ ለሕያዋን ሁሉ እናት ሆና ፍጥረቱን ሁሉ ለማዳን ምክንያት ሆነች፡፡

 

ሕያዋን የሚባሉት ጥምቀተ ክርስትና ያላቸውን ወልድ ዋሕድ ብለው በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የሚያምኑትን ክርስቲያኖችን ነው፡፡ እነዚህ ሕያዋን  ናቸው፡፡ ጌታ በቅዱስ ወንጌሉ “በወልድ ያመነ የዘለዓለም ሕይወት አለው ያላመነ ግን አሁን ተፈርዶበታል፡፡” እንዲል ዮሐ.3፥37 ደግሞም ሰው ሰው ተብሎ በሕይወት ለመኖር ከእናት ከአባቱ መወለድ ግድ እንዲሆንበት ክርስቲያንም ክርስቲያን ይባል ዘንድ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት መወለድ አለበት ዮሐ.3፥5፡፡ የእነዚህ እናታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ አንድም ሕያዋን የሚላቸው ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃቸውን የነፍስ ሥራ ሠርተው በጽድቅ የተሸለሙ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ናቸው የእነዚህ እናታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናትና ስማን “ማርያም” አሉት፡፡

 

መ. ማርያም ማለት ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች የከበረች ደግ ፍጥረት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሚታየውንና የማይታየውን ብዙ ፍጥረት ፈጥሯል ከእነዚህ ፍጥረታት መካከል ግን ሰው እና መላእክት ክብሩን እንዲወርሱ ስሙን እንዲቀድሱ ለይቶ ፈጥሮአቸዋል፡፡ ከሰው መላእክት በቅድስና ለእግዚአብሔር የቀረቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መላእክት መካከል ስድስት ክንፍ ያላቸው ብዙ ዐይኖች ያሏቸው የእግዚአብሔርን ዙፋን የሚሸከሙ እግዚአብሔርም በዘፈቀደ ለወዳጆቹ ሲገለጽ የሚታይባቸው ክብር ያላቸው ናቸው፡፡ በፈጣሪያቸው ፊት ግን ሲታዩ ትእምርተ ፍርሐት አላቸው ከዙፋኑ የሚወጣው እሳት እንዳያቃጥላቸው በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን ይሸፍናሉ፤ ገጽህን ማየት አይቻለንም ሲሉ፤ በሁለት ክንፋቸው ከዳርቻ እስከ ዓለም ዳርቻ ይወጣሉ ይወርዳሉ ባህርይህን ተመራምሮ መድረስ አይቻልም ሲሉ፡፡ እንዲህ ባለ ፍርሐት ፈጣሪያቸውን “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ፍጹም ምሉዕ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ” እያሉ ያመሰግናሉ፡፡ ራዕ.4፣ ኢሳ.6 እነዚህ ከፍጡራን ሁሉ የከበሩ ለእግዚአብሔርም የቀረቡ ናቸው ከእነዚህ ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትበልጣለች፡፡ ምክንያቱም እነርሱ እንዲህ ከሚንቀጠቀጡለት ከሦስቱ ቅዱስ አንዱን ቅዱስ ወልደ እግዚአብሔርን ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን በማሕፀኗ የተሸከመች አዝላ የተሰደደች በማስተማር ዘመኑ ያልተለየች እስከ እግረ መስቀል ድረስ የነበረች የአምላክ እናት ናትና ስለዚህም ቅዱስ ኤፍሬም ሲናገር “ይእቲ ተዓቢ እም ኪሩቤል ወትፈደፍድ እም ሱራፌል እስመ ኮነት ታቦተ ለአሐዱ ዘእም ቅድስት ሥላሴ” ብሏል በእውነትም ከኪሩቤል እና ከሱራፌል ትበልጣለች ከቅድስት ሥላሴ አንዱን ወልደ እግዚአብሔርን በሕቱም ድንግልና ፀንሳ በሕቱም ድንግልና ወልዳዋለችና ይህ ጸጋ ለእመቤታችን እንጂ ከፍጡራን መካከል ለሌላ ለማንም አልተሰጠምና ከነገደ መላእክት ከደቂቀ አዳም በክብር የሚመስላት በጸጋ የሚተካከላት የለም፤ ከፍጡራን በላይ ያሰኛታል፡፡ “ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ….. ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ ነው፡፡ የልዑል እግዚአብሔርም ልጅ ይባላል፡፡” ሉቃ.1፥28፣ ሉቃ.1፥35 እንዲል፡፡

 

ሠ. ማርያም ማለት መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው /መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታስገባ/ ማለት ነው፡፡ የቀደመው ፍጥረት የታደሰባት ወደ ቀደመ ርስቱ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ምክንያተ ድሂን የሆነችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ዛሬም ያለው ፍጥረት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት የድንግል ማርያም ምልጃ ያስፈልገዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን መርቶ መንግሥተ ሰማያት የምታስገባ የመሆኗን ነገር በምሳሌ እንዲህ ስትል ታስተምራለች፡፡ በዘፀ.ም.32 እና 34 ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ሙሴ በደብረ ሲና 40 መዓልት 40 ሌሊት ከጾመ ከጸለየ በኋላ እግዚአብሔር ተቀብሎ ከተራራው ሲወርድ እስራኤል ጣዖት አቁመው ሲሰግዱ ተመለከተ በዚህ ጊዜ ፍቅረ እግዚአብሔር ቢያቃጥለው በፅላቱ ጣዖቱን መታው ፅላቱ ተሰበረ ጣዖቱ ደቀቀ፡፡ ወደ እግዚአብሔር ሲያመለክት ከማይነቅዝ እንጨት ሠርቶ ወደ ተራራው እንዲወጣ በዚያም እንደ ቀድሞው እንዲጾም እንዲጸልይ እግዚአብሔር አዘዘው እርሱም እንደታዘዘው አደረገ እግዚአብሔርም በተሰወረች ጣት ትዕዛዛቱን ጻፈበት ለሙሴም ሰጠው ሙሴም ይህንን ይዞ ከተራራው ሲወርድ ብርሃን ተሳለበት እስራኤል በዚች ፅላት እየተመሩ የዮርዳኖስን ባህር ከፈሉ ኢያሱ.3፥14-17 የኢያሪኮን ቅፅር ናዱ /አፈረሱ/ ኢያ.6፥8 ምድረ ርስት ከነዓን ገብተው ርስት ተካፈሉ፡፡ በዚህ ምሳሌ የቀደመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሙሴ የተሰጠው የእንቁ ፅላት የአዳም የፅላቱ መገኛ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ ለአዳምም እናትና አባት መገኛ የሚሆን የለውም ወድቆ መሰበሩ ሕግ ትዕዛዝ በመተላለፉ ከፈጣሪው መለየቱን ያመለክታል፡፡ ፅላቱ እንደተሰበረ ይቅር እንዳላለ አዳምም እንደወጣ ይቅር አላለም በንስሓው ተቀብሎታልና፡፡ ሁለተኛይቱ ፅላት እመቤታችን ሙሴ ሠርቶ መውሰዱ እመቤታችን በዘር መገኘቷን ከቅድስት ሐና ከቅዱስ ኢያቄም መወለዷን ያመለክታል፡፡ ከማይነቅዝ እንጨት መሥራቱ እመቤታችን በሐልዮ /በማሰብ/ በነቢብ /በመናገር/ በገቢር /መሥራት/ ኀጢአት እንዳልፈጸመች ንፅናናዋን ቅድስናዋን ያመለክታል፡፡ በፅላቱ ላይ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ በማሕፀነ ድንግል የተቀረጸው የአብ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ዮሐ.1፥1 “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነው” ዮሐ.1፥14 የቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” እንዳለ፡፡ በዚያች ፅላት እስራኤል ባህር እንደተከፈለላቸው፣ ቅፅር እንደተናደላቸው ተመርተው ርስት እንዲወርሱ ጥንተ ጠላታትን ዲያብሎስ ተሸንፎ በእመቤታችን በተሰጣት ቃል ኪዳን አማላጅነት ከገቡ መውጣት ካገኙ ማጣት የሌለባት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ እድል አገኘን፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ከላይ የተጠቀሰውን አልን እንጂ ስለ እመቤታችንስ የተነገረው ብዙ ነው፡፡ የድንግል ማርያም ጣዕሟ በአንደበታችን ፍቅሯ በልቡናችን ይደርብን በአማላጅነቷ ለርሥተ መንግሥተ ሰማያት ታብቃን አሜን፡፡