abune petros statute

የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ለጊዜው ከቦታው ይነሣል

ኅዳር 15 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ እንዲያስችል በሚዘረጋው የቀላል ባቡር መሥመር ዝርጋታ ምክንያት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት እንደሚነሣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

abune petros statute

አቶ አበበ ምሕረቱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮምኒኬሽን አገልግሎት ክፍል ሓላፊ የሐውልቱ መነሣት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጹ “በቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ምክንያት መንገዱ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ጀምሮ ወደ አውቶቡስ ተራ የሚወስደው መንገድ አትክልት ተራ ድረስ ባቡሩ በዋሻ ውስጥ ነው የሚያልፈው፡፡ በተጨማሪም የባቡሩ መስመር  ከምኒልክ አደባባይ ወደ ሽሮ ሜዳ ይዘረጋል፡፡ እንደሁም ከአውቶቡስ ተራ ወደ ቅድስት ልደታ ለማርያም የሚታጠፈው መስመር መነሻም ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ከማዘጋጃ ቤት አጥር ጀምሮ ወደ ትግበራ የተገባበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ሥራው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ሲደርስ ስዊድን አገር የሚገኘውና ከፍተኛ ልምድ ያለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ሥራውን በበላይነት የሚቆጣጠረው ሲሆን በሚያስመጣቸው ባለሙያዎች አማካይነት በክብርና በጥንቃቄ ሐውልቱን አንሥቶ የዋሻው ግንባታ እንደተጠናቀቀ አንዲትም ሣ/ሜትር ሳይዛነፍ እንደነበረ በቦታው ላይ በክብር እንዲያስቀምጥ ይደረጋል፡፡ ሐውልቱ የሀገር ቅርስና ሀብት ነው፤ ለዚህም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ይሠራል፡፡” ብለዋል፡፡

 

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ብቻውን የሚያከናውነው ሳይሆን የአዲስ አበባ የጽዳትና ውበት ኤጀንሲ፤ የአዲስ አበባ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፤ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮዎች፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን እንደሚከናወን የገለጹት የኮርፖሬሽኑ የኮምኒኬሽን አገልግሎት ክፍል ሓላፊው  በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ወደ ትግበራ እንደተገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

 

“ሐውልቱ ተነሥቶ የት ነው የሚቆየው?” በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም “ሐውልቱ በክብር ከተነሣ በኋላ ባለሙያዎቹ በሚያቀርቡት ጥናት መሠረት ባለ ድርሻ አካላት ተወያይተው በሚዘጋጀው አስተማማኝና ምቹ ሥፍራ ላይ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም በክብር ወደ ቦታው ይመለሳል” ብለዋል ፡፡

 

የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልት በተመለከተም ”አሁን ባለው ዲዛይን መሠረት ሐውልቱን ስለማይነካው አይነሣም” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

“ይህንን ጉዳይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሳውቃችኋል?” ብለናቸውም “ፕሮጀክቱ የሁላችንም ነው፡፡ የሀገር ነው፡፡ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለተባሉት አካላት ሁሉ አሳውቀናል፡፡” በማለት የመለሱ ሲሆን ወደፊትም ተቀራርበው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

 

“ሌላ ዲዛይን ለመሥራት ለምን አልተሞከረም?” ላልናቸው ሲመልሱም “ዲዛይኑ ማእከላዊውን መንገድ ይዞ ነው የተሠራው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ይከናወናል፡፡”በማለት መልሰዋል፡፡

 

በመጨረሻም “ሐውልቱ ከተነሣ በኋላ ወደ ቦታው ለመመለሱ ሓላፊነቱን ማነው የሚወስደው?” ብለን ለጠየቅናቸው  “መንግሥት የህዝብን ችግር ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ሁሉም ሀላፊነቱን ወስዶ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ባለ ድርሻ አካላቱም የመንግሥትን ሥራ የሚያስፈጽሙ በመሆናቸው ሓላፊነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሓላፊነት አለበት” ብለዋል፡፡