በእኛ ዘመን ምንጮቻችን እንዳይነጥፉ

ኅዳር  17 ቀን 2005 ዓ.ም.


የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት መሠረት የሆኑት፤ የአባቶች ካህናት፣ ሊቃውንት መምህራን፣ ጳጳሳት የአገልጋዮቿ መፍለቂያ፤ ለዘመናት የማይነጥፉ ምንጮች ሆነው የኖሩት አብነት ትምህርት ቤቶቻችን፤ በዚህ ዘመንና ትውልድ ህልውናቸውን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ፈተና እንደተጋረጠባቸው የዐደባባይ ምስጢር ከሆነ ቆይቷል፡፡

 

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት እንዲሁም ቅን አሳቢ እውነተኛ ልጆቿ ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የተግባራዊ መፍትሔው አካል በመሆን ሲንቀሳቀሱም ይታያል፡፡

 

እንዲህም ሆኖ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እየተደራረበ መጥቶ በወቅቱ መሠረታዊ ለውጥና የተሻለ እድገት የሚያስገኝ መፍትሔ ባለመሰጠቱ የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን ፈተና ከፍቷል /ተባብሷል/፡፡

 

የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱ ጊዜና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ከመንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶች ጋር በማገናዘብ ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን አለመደረጉ፤ በተቀላጠፈና ወጥ በሆነ መንገድ ተደራጅቶ አለመሰጠቱ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት የመማሪያ ክፍሎች፣ የትምህርቱ መርጃ መሣሪያዎች፣ መጻሕፍት ወዘተ በፍጹም አለመሟላታቸው፤ የሊቃውንት መምህራኑ የኑሮ ችግርና በቂ መተዳደሪያ ድጋፍ አለማግኘት፤ የደቀ መዛሙርቱ ለረኃብና ለዕርዛት መዳረግ፤ መጠለያ ማጣት፤ የጤና ክብካቤና ትምህርት የሚያገኙበትና በዝቅተኛ ደረጃም ቢሆን የሕክምና አገልግሎት አለመኖር፤ በአንጻሩ ደግሞ ይህንን ሁሉ ችግርና መከራ ተቋቁመው ለዓመታት ደክመው ከሊቃውንት መምህራን አባቶቻቸው የዕውቀት ማዕድ የቀሰሙትን ዕውቀትና ሙያ ለቤተ ክርስቱያኒቱ አገልግሎት የሚያውሉበት የሥራ ዋስትና ማጣታቸው ከሌሎችም ውጫዊ ተግዳሮቶች ጋር ሲደመር ለመማር ማስተማሩ ትልቅ ፈተና ስለሆነ ወዘተ…. አፋጣኝ ተግባራዊ መፍትሔ የሚፈልግ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ሕልውናና ቀጣይነት ላይ የተደቀነ ገሐድ አደጋም ስጋትም ነው፡፡

 

ሁለንተናዊ ፈተናዎቹን በሚፈታ መልኩ መሠረታዊ መፍትሔ በአፋጣኝ ባይታይም፤ ይህንን ችግር በመቅረፍ የአብነት ትምህርት ቤቶቻችንን ከተደቀነባቸው አደጋ ለመታደግ ተስፋ ሰጪ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

 

ባለፈው የጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር የተወሰነው የዐሥር ሚሊዮን ብር በጀት ለችግሩ የተሰጠውን ትኩረት የሚያመለክት፤ ለአስተማማኝ ቀጣይነቱም የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቅ ነው፡፡

 

ይህንን በድርሻው ለማጠናከር በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አማካኝነት፤ “የጥንቱ ከሐዲሱ ጋር በደጃችሁ አለ” በሚል መሪ ቃል ኅዳር 2 ቀን 2005 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ይፋ የሆነው፤ “አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የነጻ ትምህርትና ሥልጠና ዕድል” የአብነት ትምህርቱን ዘመኑን በዋጀ መልኩ በትውልዱ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያስችል መርሐ ግብር ነው፡፡

 

እንዲህ ዓይነቶቹ ተጠቃሽ የመፍትሔ እርምጃዎች ለቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቀጣይነት ዋስትና ሰጪ ጥረቶች ናቸው፡፡ አፈጻጸማቸውን በተመለከተም የተቀናጀ አሠራር፤ የቅርብ ክትትልና ቁርጠኛ አገልግሎት ይፈልጋሉ፡፡ ችግሩ እየከፋ ከመምጣቱ አኳያም ቀዳሚ ትኩረትና አፋጣኝ የተግባር ክንውን እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው፡፡

 

አብነት ትምህርት ቤቶች ወቅቱና ትውልዱን እንዲሁም አካባቢያዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ከዘመናዊው ትምህርት ጋር ተቀናጅተው የሚያድጉበትና የሚቀጥሉበትን መፍትሔ መፈለግና በተግባር ማረጋገጥ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡

 

በተለይም በገጠሩ አካባቢ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታና ለአብነት ትምህርቱ ያለው አመለከካከት እየተለወጠ መምጣቱን ተከትሎ ለመምህራኑና ለተማሪዎቹ የሚያደርገው ድጋፍ መቅረት ዐቢይ ችግር ነው፡፡ ይህንን ችግር ተረድቶ መፍትሔ የሚሆኑ ተተኪ አሠራሮችን መቀየስና በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ደቀመዛሙርቱ የነገይቷን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስፋፋት ተስፋ አድርገው፤ ለዓመታት በችግርና መከራ ውስጥ እያለፉ በአብነት ትምህርቱ የቀሰሙትን ዕውቀትና ሙያ ይዘው ከተመረቁ በኋላ፤ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተመድበው መተዳደሪያ አግኝተው ቤተ ክርስቲያንንም የሚያገለግሉበት አስተማማኝ የሥራ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ዓለም አቀፋዊውንና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን የሚገነዘቡበት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አጠቃላይ ለውጦችን በማስተዋል በቀላሉ ተረድተው የሚያዘጋጁበትና በነገ አገልግሎታቸው የትውልድ መሪ የምእመናን አለኝታ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችሏቸውን ተጨማሪ ትምህርቶች የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸትና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

 

የአብነት ት/ቤቶች ባልተስፋፉባቸው አህጉረ ስብከት የገጠርና ጠረፋማ አካባቢዎችም፤ የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡና በሚገባ የተደራጁ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ በየአካባቢው ቋንቋ ሊያስተምሩና ሊያገለግሉ የሚችሉ መምህራነ ወንጌልና አገልጋይ ካህናትን ማውጣት (ማፍራት) ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባራት አንዱ ነው፡፡

 

አለበለዚያ አገልጋይ ካህናትና መምህራነ ወንጌል በማጣት ከዕለት ወደ ዕለት የሚዘጉት በየገጠሩና በየበረሐው እንዲሁም በየጠረፉ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን እቅፍ እየወጡ በሌሎች የሚነጠቁት ምእመናንም ቁጥር የዚያኑ ያህል እየጨመረ እነሱን ለመታደግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

 

ተተኪ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እያነሱ፣ በየገዳማቱ የሚያገለግሉ እውነተኛ መነኰሳት እየቀነሱ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በሁለንተናዊ መንፈሳዊ አገልግሎቷ እየተዳከመች፤ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የሚኖራት ተሳትፎ እየጠበበ፤ እስተዳደራዊ መዋቅሯና አሠራሯ ብቃት እያነሰው፤ ምእመናኗም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ በዕለት ተዕለት ኑሮአቸውና ማኅበራዊ ግንኙነታቸው የሚያበረታቸው፣ የሚመክራቸው፣ የሚከታተላቸው፣ የሚያጸናቸውና የሚያመላክታቸው እያጡ በዘመኑ ሥልጣኔ የባሕል ወረርሽኝ እየተዋጡ፣ ለማንነት ጥያቄያቸው ምላሽ እያጡ፣ ለሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ቀውስ እየተዳረጉ ይመጣሉ፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሚያስከትለውን የከፋ ችግር ከወዲሁ ለመገንዘብ ከሁላችንም የሚሰወር እንዳል ሆነ ይታወቃል፡፡

 

ስለዚህ ዘርፈ ብዙ ለሆነው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት መሠረት የሆኑት፤ የሊቃውንቱ፣ የጳጳሳቱ፣ የአገልጋይ ካህናቱ፣ የመምህ ራነ ወንጌሉ ሁሉ መፍለቂያ ምንጮች አብነት ትምህርት ቤቶቻችን በእኛ ዘመንና ትውልድ ሳይነጥፉ እንዲቀጥሉ በተጠናና ችግር ፈቺ በሆነ መንገድ ጥረት የሚያደርጉትን አካላት በሚቻለን ሁሉ በማገዝ ከሁላችንም ተጨባጭነት ያለው ተሳትፎ ይጠበቅብናል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር