የብፁዕ አቡነ ኢሬኔጅ ዜና ዕረፍት

ዲያቆን አበበ እሸቴ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኢሬኔጅ የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

ከጥቅምት ፳፭፤፳፻፲፫ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ መታመማቸው ከታወቀ በኋላ በሰርቢያ ቢልግሬድ ካራቡርና የወታደሮች የሕክምና ማእከል ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየታቸው ይታወቃል።

ብፁዕነታቸው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ነሐሴ ፳፰ ፲፱፻፴ ዓ.ም በሰርቢያ ቪዶካ የተወለዱ ሲሆን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በ፲፱፶፱ ዓ.ም ወደ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት በመግባት ከቢልግሬድ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ተመርቀው በራብቪካ ገዳም በምንኩስና ሕይወት እየኖሩ በነበረበት ጊዜ ሐምሌ ፲፬ ፲፱፸፬ ዓ.ም የማራቪካ ኤጲስቆጶስ ሆነው ተሾሙ።

ከፕትርክናቸው በፊት የኒስና የፔክ ሊቀ ጳጳስና የቢልግሬድ ሜትሮጶሊታን ሆነው እየሠሩም ሳለ በ፳፻፲ ዓ.ም ከፓትርያርክ ጳውሎስ ዕረፍት በኋላ የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ መሾማቸው ይታወሳል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኢሬኔጅ ፵፭ኛው የቤተክርቲያኗ ፓትርያርክ ሲሆኑ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ቤተክርስቲያኗን በማገልገል ላይ እያሉ በኮሮና ቫይረስ ታመው ክትትል ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፲፩ ፳፻፲፫ ዓ.ም ሕይወታቸው ማለፉን ኦርቶዶክስ ታይምስና ባስሊካ ኒውስ ኤጀንስ የሰርቢያ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ቩቺክን ዋቢ በማድረግ ዘግበዋል።