የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል

በዝግጅት ክፍሉ

ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በንጉሥ ናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት እስራኤላውያንን በባቢሎናውያን ቅኝ ግዛት ሥር በወደቁበት ጊዜ ከአይሁድ ወገን የሆኑ አዛርያ፣ አናንያ እና ሚሳኤል የተባሉ ሦስት ሕፃናትም ተማርከው በባርነት ተወሰዱ፡፡ ንጉሡም መልካቸው ያመረ፣ የንጉሣዊና የመሳፍንት ልጆች የሆኑትን መርጦ ሥነ ጥበብ፣ የመንግሥት አስተዳደርና የባቢሎናውያን ቋንቋዎችን እንዲሠለጥኑ ለማድረግ በቤተ መንግሥቱ አስቀመጦ ይቀልባቸው ጀመር፡፡ ሦስቱ ሕፃናት ግን እርሱን በመንቀፍ የንጉሡ አገልጋይ ጥራጥሬና ውኃ ብቻ እንዲሰጣቸው በማሰማን ለፈጣሪያቸው ታምነው ለዐሥር ቀናት ቆዩ፤ በኋላም ሲታዩ ጮማ ከሚበሉትና ጠጅ ከሚጠቱት ይልቅ ያምሩ ነበር፡፡ (መዝገበ ታሪክ ገጽ ፻፯)

ከዚህ በኋላም ወጣት ምርኮኖቹ በሙሉ ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር ፊት ቀርበው ዕውቀታቸው በተለካበት ጊዜ ሦስቱ ሕፃናት ጥበባቸውና ማስተዋላቸው ከሌሎቹ እጅጉን በልጦ ተገኘ፡፡ በዚህም ንጉሡ በዚህ ነገር በመደነቅ በሦስት አውራጃዎች ላይ ሾማቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ባቢሎናውያን በሕፃናቱ መመረጥና መሾም ከመቅናታቸው የተነሣ ከንጉሡ ጋር ቀንተው ለማጣላት፣ ንጉሡ ወዳጅና ጠላቱን ይለዩ ዘንድ ራሱን የሚመስል ምስል ሠርቶ እንዲያቆም መከሩት፡፡ እርሱም  ምክራቸውን ተቀብሎ ‹‹ቁመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነ ወርቅ ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው፡፡ መኳንንትንና ሹሞችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዢዎችንም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ፥ ንጉሥ ናቡከደነፆርም ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ፡፡›› (መዝገበ ታሪክ ገጽ ፻፯-፻፰፣ዳን. ፫፥፩-፪)

አሕዛብ በሙሉም ንጉሡ ለሠራው ምስል ምረቃ ተገኙ፤ ዐዋጅ ነጋሪውም እንዲህ በማለት ተናገረ፤ ‹‹ሕዝቡምና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ! ንጉሥ ይላችኋል፥ የመለከትና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በስማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ስገዱ፤ ወድቆም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል፡፡›› እነርሱም ንጉሡ እንዳዘዘው ማድረግ ጀመሩ፡፡ (ዳን. ፫፥፬-፮)

ሆኖም ግን ሦስቱ ሕፃናት የንጉሥ ናቡከደነፆርን ትእዛዝ እንዳልተቀበሉ ሕዝቡ በሰማ ጊዜ ንጉሡ ጋር ሄደው ከሰሷቸው፡፡ እንዲህም አሉት፤ ‹‹ንጉሥ ሆይ፥… በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሾምካቸው፥ ለአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዛትህን እምቢ ያሉ፥ አምላክህን ያላመለኩ፥ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ አዛርያ፣ አናንያ እና ሚሳኤል የተባሉት ሰዎች አሉ›› ብለው ነገሩት፡፡ (ዳን. ፫፥፱-፲፪)

ንጉሡም ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ ሦስቱን ሕፃናት ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ፤ ካሉበትም ተጠርተውም  ወደ እርሱ ቀረቡ፡፡ እርሱም ስለምን የእርሱን አምላክ የቀረቡትንና እንደቀሩና ላቆመው ምስል ያልሰገዱበትን ምክንያት ጠየቃቸው፡፡ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ ወድቀው  ላሠራው ምስል ቢሰግዱ መልካም እንደሆነ፤ ባይሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ እንደሚጣሉ ነገራቸው፡፡  እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ ‹‹ናቡከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፥ ከሚነድደው ከእሳት እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ፥ ላቆምከውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ›› አሉት፡፡ (ዳን.፫፥፲፮-፲፰)

ንጉሥ ናቡከደነፆርም እጅጉን ተቆጣ፤ የእቶኑን እሳት ይነድድ ከነበረው ሰባት እጥፍ የሚያቃጥል እንዲሆን ካደረገ በኋላ ሦስቱ ሕፃናትን በዚያ የእሳት ነበልባል ውስጥ አምላካቸው እግዚአብሔርን ከእሳቱ ያወጣቸውም ዘንድ ጸለዩ፤ ወዲያውኑም የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል እሳቱ ወደ ሚነድበት ምድጃ ወርዶ እሳቱን በበትረ መስቀል መታው፡፡ ነበልባሉንም እንደ ቀዝቃዛ ነፋስ አደረገው፤ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልም እሳቱ ምንም ሳይነካቸው የራስ ጠጉራቸውን እንኳን ሳይለበልባቸው ዳኑ፤ በእሳቱ ጉድጓድ ውስጥም ያለፍርሃት እየተመለሱ ‹‹የአባቶቻችን ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን፤ ስሙ የተመሰገነ ነው፤ ለዘለዓለም የከበረ ነው›› እያሉ አመሰገኑት፡፡ (ዳን.፫፥፲፱-፳፫)

ንጉሥ ናቡከደነፆርም የእነርሱን መዳን አይቶና ሲያመሰግኑም ሰምቶ ተደነቀ፤ አማካሪዎቹንም ሦስቱ ሕፃናት ታስረው በእሳት ከተጣሉ በኋላ እንዴት ሊፈቱ እንደቻሉ በመገረም ጠየቃቸው፤ ከአማካሪዎቹ አንዱ ‹‹እኔ የተፈቱ በእሳትም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ፤ ምንም የነካቸው የለም፤ የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል›› አላቸው፡፡ ወደ ምድጃውም ቀርቦ ሦስቱ ሕፃናትን ይወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ እነርሱም ከእሳቱ መካከል ወጡ፡፡ በዚያ የተሰበሰቡት ሁሉም ሰውነታቸውም ጠጉራቸው እንዳልተነካ አዩ፡፡ (ዳን.፫፥፳፭-፳፯)

ንጉሡም በፊታቸው ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ለሕዝቡም ከእግዚአብሔር በስተቀርም ሌላ አማልክት እንዳያመልኩ ለጣዖታትም እንዳይሰግዱ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ እንዲያውም አናንያ፣ አዛርያንና ሚሳኤልንም ያዳናቸውን አምላክ የስድብን ነገር የሚናገር እንደሚቀጣም አስታወቀ፤ ሦስቱ ሕፃናትን ደግሞ አይሁድን ሁሉ አስገዛላቸው፡፡ (ዳን.፫፥፳፰-፴)

ይህ ድንቅ ተአምር ያደረገው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በዕለቱ ታኅሣሥ ፲፱ ዓመታዊ በዓሉ በመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡

አናንያ፣ አዛርያንና ሚሳኤልንም ከእሳት ያወጣቸው አምላክ አሁን ካለንበት ችግር፣ መከራ እና ሥቃይ ያወጣን እንዲሁም ከዘለዓለማዊ እሳት ይታደገን ዘንድ እኛም አማላጅነቱ ተረዳኢነቱ ያስፈልገናልና እንማጸነው፤ በእርሱም ስም እንመጽውት፤ በጎ ምግባርንም አብዝተን እንፈጽም፡፡

ከሃይማኖት ርቀን የምንገኝና ባዕድ አምልኮት የምንፈጽም ሰዎች ደግሞ ለግዑዝ ነገር መገዛት አቁመን ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ እግዚአብሔር በንስሓ እንመለስ፤ ቸርነቱን ምሕረቱን እንዲያበዛልን ለእርሱም ተገዝተን እንድንኖር ያበቃን ዘንድም የእርሱ ፈቃድ ይሁንልን፤ እንማጸነው፤ አሜን፡፡