001paulos

የሰዋስወ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርትን አስመረቀ

ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

001paulosበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በብሉያት እና በሐዲሳት ትርጓሜ፤ እንዲሁም በቀንና በማታ በነገረ መለኮት ትምህርት በዲፕሎማ ያሰለጠናቸውን 218 ደቀመዛሙርት ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አደራሽ አስመረቀ፡፡

ተመራቂ ደቀመዛሙርቱ ለአምስት ዓመታት ኮሌጁ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ትምህርት የተከታተሉ ከብሉያት ትርጓሜ አንድ፤ ከሐዲሳት ትርጓሜ 16፤ በነገረ መለኮት ትምህርት በቀን 21፤ በማታው 180 ደቀመዛሙርት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እጅ የዲፕሎማ ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

002paulosብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምእዳን፡- የደከማችሁበት ሁሉ ፍሬ እንዲያፈራ ሌሎች የእናንተን ዕድል ያላገኙ ወገኖቻችሁን ለማስተማር ተዘጋጅታችኋልና እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ በአእምሮና በዕውቀት ጎልምሳችሁ በየአካባበቢው ያሉትን ወገኖቻችንን ለማስተማርና ለማጽናት ፤ ከመናፍቃን ንጥቂያ ለመጠበቅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት ሰጥታችኋለች፡፡ በተለያዩ የመናፍቃን እንቅስቃሴ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን እየወጡ ወደ ሌሎች እየኮበለሉ ይገኛሉ፡፡ የኮበለሉትን ለመመለስ ፤ያሉትንም ለማጽናት ቤተ ክርስቲያን ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለች፡፡ የተሰጣችሁን ሓለፊነት እንድትወጡም አደራ እንላለን ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት መመረቃችሁ መልካም ነው፤ ነገር ግን ለእምነታችሁ ታማኞች ሆናችሁ የተጣለባችሁን አደራ ወደመጣችሁበት ሀገረ ስብከት በመሄድ ሓላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል፡፡ ወደ ወረዳ ስንልካቸው ወደ ሀገረ ስብከት እየሄዱ፤ ከሀገረ ስብከት ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስንልካቸው ደግሞ ወደ ውጭ ሀገር እየኮበለሉ ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ምድር የተዘራባትን ታበቅላለች፤ ፍሬዋንም ትሰጣለች፤ እናንተም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የወንጌል አርበኛ አድርጋ በምታሰማራችሁ ቦታ ሁሉ በታማኝነት ምእመናንን ወንጌል እያስተማራችሁ በእምነታቸው እንዲጸኑ፤ መናፍቃን እንዳይሰለጥኑባቸው ልትመክቱ ያስፈልጋል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ በተመራቂ ደቀመዛሙርት ያሬዳዊ ወረብ፤ እንዲሁም ቅኔ የቀረበ ሲሆን በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ደቀመዛሙርት ኮሌጁ ያዘጋጀውን ሽልማት ከቅዱስነታቸው እጅ ተቀብለዋል፡፡