‹የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው›› (መዝ. ፵፭፥፯)

     መምህር ሶምሶን ወርቁ         

ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር በረድኤት ከሕዝቡ ጋር እንደሆነ፤ በፍጻሜው ሰው ሆኖ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ሲናገር ‹‹የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው›› አለ፡፡ እግዚአብሔር አብ በነቢያት አድሮ ሰው ሆኖ እንደሚወለድ ብሎ ትንቢት አናገረ፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነስቶ ከእኛ ጋር አንድ ባሕርይ ሆነ ሲል ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረውም ሆነ፡፡ አስቀድሞ በረድኤት ከቀደሙ አባቶቻችን ጋር የነበረ እግዚአብሔር በሥጋ እንደሚገለጥ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው የትንቢት ቃልም ተፈጸመ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ አስቀድማ በአምልኮተ እግዚአብሔር በሕገ ኦሪት ጸንታ የቆየች የመሲሕ ክርስቶስ መወለድን የነቢያትን መጻሕፍት ይዛ እየጠበቀች የነበረች ስለነበረ ትንቢቱ ሲፈጸም ፈጥና ወንጌልን ተቀበለች፡፡ ከዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ክርስትና ከሁለት ሺ ዓመት በላይ አስቆጠረ፤ ይሁን እንጂ ያለፉት ሁለት ሺ ዓመታት ያለፈተና ነገር ሁሉ ምቹ ሆኖ እኛ እስካለንበት ዘመን ደረስን ማለት አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያናችንን ህልውና በእጅጉ ተፈታትነው የነበሩትን የዮዲት ጉዲት፤ የግራኝ መሐመድንና የጣሊያን ወረራን ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ይህን ሁሉ ፈተና በእግዚአብሔር ቸርነት በሕዝበ ክርስቲያኑ ጽናት ተሻግራ ከዚህ ዘመን ደርሳለች፡፡

ዛሬም ቢሆን ትናንት በዮዲት እና በግራኝ አድሮ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥል ምእመናንን ለስደት ለመከራ ለሞት ያደርስ የነበረ ሰይጣን ዲያብሎስ ዛሬም በአፅራረ ቤተክርስቲያን አድሮ እየተዋጋን ይገኛል፡፡ መከራው ፈተናው እንደየዘመኑ የሚለያይ ቢሆንም  ለቤተክርስቲያናችን አዲስ አይደለምና መንፈሳዊ ብርታት ከእኛ ኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተለየ በመንፈስ ያልጠነከሩ ምእመናን በክርስቲያን ወገኖቻቸው ላይ እየተፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ግፍና መከራ እየተመለከቱ እግዚአብሔር በእውነት አለን? ካለስ ይህን አይመለከትምን? በእውነት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውን? ከእኛ ጋር ቢሆንማ ይህ ሁሉ ችግር ባልደረሰ ነበር ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ አንዳንዶች እግዚአብሔር የተዋቸው፤ ጸሎታቸው የማይሰማ እየመሰላቸው ወደ ቀቢጸ ተስፋ ደርሰው በእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ ይታደጉናል ብለው በሚያስቧቸው ምድራውያን ላይ ተስፋቸውን ሲጥሉ ይታያል፡፡ ነገር ግን ትናንት ከአባቶቻችን ከአብርሃም፣ ከይስሐቅ እና ከያዕቆብ ጋር የነበረ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ያወጣ፣ የኤርትራን ባሕር ከፍሎ በደረቅ ያሻገረ፣ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ፣ ጠላቶቻቸውን እና ታላላቅ ነገሥታትን የመታ የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፡፡

፩.ስለምን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዳልሆነ እናስባለን?

ዛሬ በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ባለው አሰቃቂ ግድያ፣ ስደት፣ መከራ ውስጥ እያለፉ ያሉ ወገኖቻችን በእውነት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውን? ብለው ቢያስቡ መጽናናትን እንቢ ብለው መፍረድ ግብዝነት ነው፡፡ ‹‹ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች›› (ኤር. ፴፩፥፲፭)፡፡ ጻድቁ ኢዮብም በሥጋ እየተቀበለ ከነበረው መከራ ጽናት የተነሣ የተወለደበትን ቀን ረግሟል፡፡ ‹‹ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ›› (ኢዮ. ፫፥፩)፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያስተምረን ሊባርከን ወዶ እኛ በመከራ ውስጥ እንድናልፍ ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው ጽድቁ ይመሰከር ዘንድ የተፈተነውን ኢዮብን እግዚአብሔርም ከፊተኛው ኑሮ ይልቅ ኋለኛውን ኑሮ አብዝቶ ባረከለት፡፡ (ኢዮ. ፵፪፥፲፪)

ሀ. እየኖርን ያለንበትን ዓለም አለመረዳት

ዓለም እኛ ክርስቲያኖች ስለሆንን አበባ ታቅፋ ዘንባባ ይዛ አትቀበለንም፡፡ ዘንበባ ይዛ የተቀበለችውን ንጉሧን ክርስቶስን ቸንክራ ሰቅላለች፡፡ እኛም በስሙ ክርስቲያኖች የተጠራን ጌታዋን በሰቀለች ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፤ የምንቀበለው መከራ የቱንም ያህል ቢበረታ ልንጽናና ልንጸና ይገባል፤ የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነውና፡፡ አስቀድሞ ጌታ በመዋዕለ ሥጋዌው ያስተማረን ይህን ነው፡፡ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› (ዮሐ. ፲፮፥፴፫)፡፡ ስለዚህ እየኖርንባት ያለችው ዓለም የበዛባት ብትሆንም ነገር ግን የተሸነፈች መሆ‘ን ልንረዳ ይገባል፡፡ ተኩላ የሠለጠነባት፣ ትላንት ሐዋርያት ወንጌልን ሊሰብኩና ለአገልግሎት በተላኩባት መከራ ያጸናችባቸው ዓለም ናት፡፡ ‹‹እነሆ እኔ እንደ በጎች በተኵላ መካከል እልካችኋለሁ፤ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ፡፡ ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል÷ በምኩራባቸውም ይገርፏችኋልና . . .›› (ማቴ. ፲፥፲፮)  ትናንት ጌታዋን የሰቀለች ዓለም በተከተሉት ሐዋርያቱ እና በስሙ በጠራን በክርስቲያኖች ላይ መከራ የምታጸና ዓለም ናት፡፡ ስለዚህ በመከራ ውስጥ ብንሆንም የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ስለሆነ ልንጸና ልንጽናና ይገባል፡፡ ከምንቀበለው መከራ ይልቅ የምናገኘውን ክብር ማሰብ ያጽናናል፡፡ ‹‹ለእኛ ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ስቃይ ምንም እንደሆነ አስባለሁ›› ሲል በጽኑ መከራ ውስጥ ተፈትኖ ያለፈው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያበረታናል፡፡ (ሮሜ ፰፥፲፰)

ለ. ከእምነት ይልቅ በማየት መመላለስ

‹‹እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፤ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት››  ዕብ. ፲፩፥፩) የምንቀበለው መከራ የቱንም ያህል ቢበዛ ወደ ቀቢጸ ተስፋ የሚያደርሰን ሳይሆን ተስፋ የምናደርገውን ነገር የሚያስረግጥ ሳናየው በአመነው እግዚአብሔር ላይ ያለን መታመን ሊጨምር ይገባል፡፡ ‹‹ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው›› እንዲል (ዮሐ. ፳፥፳፱)፡፡ ነገር ግን እምነታችን ሲጎድል በማየት ስንመለስ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዳልሆነ ሆኖ ይሰማናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲናገር ‹‹ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለን፡፡ . . . እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን በእምነት እንጂ በማየት አንመሳሰልምና››
ይላል (፪ቆሮ. ፭፥፩)፡፡

፪.እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ እንዴት እንረዳ?

ምንም እንኳ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰን በጎ ማንነትን ገንዘብ ያላደረግን ብንሆንም እግዚአብሔር ግን ከእኛ ጋር ነው፡፡ የእኛ አምላክ ፈጥሮ የሚተው ሳይሆን ፈጥሮ በመግቦት፣ በጠብቆትና በረድኤት ከእኛ የማይለይ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ረድኤት በዘመኑ የተመለከተ ክቡር ዳዊት ሲናገር ‹‹እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው›› (መዝ. ፻፵፬፥፲፰)፡፡ ትናንት ከዳዊት ጋር የነበረ አምላክ ዛሬም በእውነትና በእምነት ከጠራነው ከእኛ ጋር ነው፡፡ ጥያቄው በእርግጥና በእውነት ሆነን ጠርተነዋል ወይ የሚል ይሆናል? ዛሬ በንጹሐን ክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ እርሱ ይመለከታል፡፡ ‹‹እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ በዐይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም፡፡›› (ዕብ. ፬፥፲፫)፡፡ በእርሱ ፊት እንኳን የፍጥረት ሁሉ አክሊል የተባልን የሰው ልጆች በዳግም ልደት የከበርን ክርስቲያኖች ቀርቶ ለአንክሮ ለተዘክሮ የተፈጠሩ የእንስሳትና የአራዊቱ ነገር እንኳ የተሰወረ አይደለም፡፡

እኛ በሃይማኖት ጸንተን እንጠብቅ እንጂ ከእኛ ጋር የሆነ አምላክ በጊዜው ይፈርዳል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የእነርሱን ፍርድ ይፈርድላቸዋልና የቀሙአቸውንም ሰዎች ሕይወት ይቀማልና፡፡›› (ምሳ. ፳፪፥፳፫) ለጊዜው በክርስቲያኖች ላይ ስልጣን ያላቸው የሚመስላቸው የንጹሓንን ሕይወት የሚቀሙ ሕይወታቸው ይቀማል፡፡ ‹‹ኀጢአተኛን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዛፍም ረዝሞ አየሁት፡፡ ብመለስ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁት፤ በቦታውም አላገኘሁትም፡፡›› (መዝ. ፴፮፥፴፭) ለጊዜው አፅራረ ቤተክርስቲያን ከፍ ከፍ ያሉ ቢመስላቸውም ነገ አናያቸውም፡፡ ዛሬ በወገኖቻችን ላይ የሚፈጸመው ግፍ ከባድ ቢሆንም ፍጻሜው መልካም ነው፡፡ ‹‹የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል›› (መክ፯፥፰) ይህን በዮሴፍ ሕይወት እናያለን የገዛ ወንድሞቹ ዮሴፍን ለባርነት ሲሸጡት እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር፤ በባርነት በጲጢፋራ ቤት እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር፤ በእስር ቤት በተጣለ ጊዜ እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ በባዕድ ሀገር ሲከብር እግዚብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚለይበት ጊዜ የለም፡፡ ዛሬ በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ መከራና ሞት የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ መጀመሪያ መሆኑን አምነን ተረድተን ትንሣኤዋን ልንጠባበቅ ይገባል፡፡

ስለዚህ ከመከራ ጽናት የተነሣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዳልሆነ የምናስበው አስቀድመን እየኖርንባት ያለችውን ዓለም ጠባይ አለማወቃችን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግዝፈት በሚታዩ ነገሮች ላይ እምነት ጥለን በእምነት ከመመላለስ ይልቅ የማይተኛ የማያንቀላፋ አምላካችን እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር መሆኑን አምነን ልንቀበል ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር