‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› (ዮሐ.፲፬፥፮)

መምህር ገብረእግዚአብሔር ኪደ

በወልድ ውሉድ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ክርስቲያኖች ከተጠመቅንበት ጊዜ አንሥቶ የምንጓዝበት የድኅነት መንገድ መድኀነ ዓለም ነው፡፡ ይህም ጉዞ መንገዱና መዳረሻው የት እንደ ሆነ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ቶማስ እንዲህ ሲል ነገረው፤ ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› (ዮሐ.፲፬፥፮)፡፡ መንገድ የሚመስል የሐሰት መንገድ፣ መዳረሻ የሚመስል የውሸት መንገድ፣ እሳተ ገሃነም የሚያደርስ ሰፊ መዳረሻም በመኖሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› አለ፡፡ ወደ ባሕርይ አባቱ ወደ አብ፣ ወደ ባሕርይ ሕይወቱ ወደ መንፈስ ቅዱስ እንደዚሁም ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርሰው መንገድ እርሱ እንደሆነ አስተማረን፤ መሄጃው መንገዱ እና አብነት መምህሩም እርሱ ራሱ ነውና፡፡

እኛም ክርስቲያኖች በእኛ ዘንድ ባደረው መንፈስ ቅዱስ ጉዞውን እንጓዝ ዘንድ ዘወትር በማይነገር ምሥጢሩ መድኅነ ዓለም ይረዳናል፡፡ አንድ ሰው ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ስለሚሔድበት መንገድ ጠባይና ስለ መዳረሻው ሀገር ማወቅ አለበት፡፡ የሚሔድበትን ሀገር ካወቀ ‹‹የእገሌ ሀገር በየት በኩል ነው? ወደዚያ የሚወስደው መንገዱስ የቱ ነው?›› ብሎ እየጠየቀ ይሔዳል፤ የሚሔድበትን ሀገር ካላወቀ ግን የመንገዱን ጠባይ ብቻ ሳይሆን መንገዱን ራሱ ማወቅ አይቻለውም፡፡

ስለዚህም ይህ እውነተኛው መንገድ ክርስቲያኖች ዕለት ዕለት ሊጓዙበት የሚገባ ሐሰት የሌለበት የመዳኛው መንገድ ይህ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ እንደሌለው በበረት እንደ ተወለደ፤ ሰዎች ለሥጋችን ማደሪያ ሊያሳጡን ይችላሉ፡፡ ጌታችንም ወደ ግብፅ እንደ ተሰደደ፤ እኛንም ሊገድሉን ሽተው ከተወለድንበት ሀገር ሊያሳድዱን ይችላሉ (ማቴ.፪፥፲፫)፡፡ እርሱም ከተጠመቀ በኋላ በገዳመ ቆሮንቶስ ከዲያብሎስ እንደ ተፈተነ፤ በወልድ ውሉድ በክርስቶስ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን ስለ ተሰኘን ዲያብሎስ የእርሱ አለመሆናችንን ቆጭቶት እኛን ለመጣል ብሎ በተለያየ መንገድ ሊፈትነን ይችላል (ማቴ.፬፥፫)፡፡ ከሀገራቸው እንዲሄድላቸው እንደ ለመኑት፤ እኛንም የክርስቶስ በመሆናችን ከሀገራቸው እንድንወጣላቸው ግድ ሊሉን ይችላሉ (ማቴ.፰፥፴፬)፡፡ ጌታችን ክርስቶስን ‹‹ጋኔን አለበት›› (ሎቱ ስብሐት) እንዳሉት እኛንም የተለያየ ስም እየሰጡ ሊሰድቡን ይችላሉ (ዮሐ.፲፥፳)፡፡ ጌታችን ክርስቶስን በቅንዓት ተነሣሥተው ‹‹ይሰቀል ይሰቀል›› እንዳሉት፤ እኛንም እንደዚሁ በተለያየ መንገድ አመካኝተው ግርግር አንሥተው መነሻውም እኛ እንደ ሆንን ዋሽተው ‹‹ይወገሩ፣ ይቀጥቀጡ›› ብለው ሊፈርዱብን ይችላሉ (ማቴ.፳፯፥፳፪-፳፫)፡፡

ጌታችን ክርስቶስን ስፍር ቊጥር የሌለውን ግርፋት ገርፈው መከራ አድርሰው በመስቀል ላይ ዕራቁቱን እንደ ሰቀሉት፤ እኛንም የክርስቶስ በመሆናችን ቊጥር የሌለው መከራ አድርሰው ሊገድሉን ይችላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን መንገዳችንን ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ‹‹ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጁ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነው…›› ብሎ እርሱ ራሱ ነግሮናልና ልንጠራጠር አይገባንም (ማቴ.፯፥፲፬)፡፡ መንገዳችንን ብቻ ሳይሆን መዳረሻችንም ልንጠራጠር አይገባንም፡፡ የዚህ አብነቱ፣ የዚህ መምህሩ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣና እንዳረገ እኛም በእርሱ መንገድነት ስንሄድ መዳረሻችን እንደ እርሱ በክብር መነሣት ነውና ልንጠራጠር አይገባንም፡፡

ልዑለ ቃል ኢሳይያስ እንዳለ ይህ መንገድ ‹‹ንጹሕ መንገድ›› ነውና ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ይህ መንገድ ‹‹የተቀደሰ መንገድ›› ይባላልና ልንጠራጠር አይገባም፡፡ በዚህ መንገድ ንጹሐን ያልሆኑ አያልፉበትምና ልንጠራጠር አይገባም፡፡ በዚህ መንገድ የሚሄዱት ድኅነታቸውን የሚፈጽሙ ተጓዦች ናቸው፤ ይህም መንገድ ወደ ዘለዓለም ደስታ የሚያደርስ ነውና ልንጠራጠር አይገባም (ኢሳ.፴፭፥፰-፲)፡፡

ይህ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት ምንኛ ድንቅ ነው፡- በሁሉም ረገድ ራሳችንን እናበርታ፡፡ የሀብት ማጣትም ቢሆን፣ ሞት ራሱም ቢሆን ሃይማኖታችንን ካልቀማን ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ደስተኞቹ እኛ ነን፡፡ ጌታችን ክርስቶስም ይህን በማስመልከት እንዲህ ብሎ አዝዞናል፡- ‹‹እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ›› (ማቴ.፲፥፲፮)፡፡ እባብ ራሱን (ጭንቅላቱን) ለማዳን ሲል ሌላው ሰውነቱን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ሁሉ አንተም እንዲህ አድርግ፡፡ ሃይማኖትህን ለመጠበቅ ስትል ሀብትህን፣ ሰውነትህን፣ የዚህ ዓለም ሕይወትህን ወይም ያለህን ሁሉ እንኳን መስጠት ካለብህ ስጥ፤ ይህን በማድረግህም በፍጹም አትዘን! አንተ ሃይማኖትህን ይዘህ ወደ ወዲያኛው ዓለም ስትሔድ እግዚአብሔር ደግሞ ሁሉንም ነገር እጅግ ውብ አድርጎ ይመልስልሃልና፤ ሰውነትህን በታላቅ ክብር ያስነሣልሃልና፤ ከሀብት ከንብረት በላይ የሆኑ በጎ በጎ ነገሮችን ይሰጥሃልና››፡፡

ይልቅስ ተወዳጆች ሆይ! የእግዚአብሔርን ጥበብ እያደነቅን እንጓዝ፡፡ እርሱስ ምንድንነው ያላችሁኝ እንደ ሆነ፤ አዳም በመሳሳቱ ምክንያት መከራና ሞት ወደ ሕይወቱ ዘልቀው ገቡ፡፡ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርም እነዚህን ሁሉ በመከራና በሞት አራቀልን፡፡ መከራችንን ያራቀው ስለ እኛ በተቀበለው መከራ ነው፤ ሞታችንን ያራቀው ስለ እኛ በሞተው ሞት ነው፡፡ ምን ይደንቅ? ምንስ ይረቅ? ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በውሸትና ኦርቶዶክሳውያን ከመሆናችን የተነሣ የሚደርሱብን ከሆነ በሥጋ የምንቀበለው መከራ ለነፍሳችን ድኀነት የሚሆን ነው፡፡ በሥጋችን ብንሞት የዘለዓለም ሞታችንን የምናርቅበት ክቡር ሞት ነው፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው ‹‹የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን››፡፡ (፪ኛ ቆሮ.፬፥፲)

ትራጃን የተባለው ንጉሥ ‹‹የተሰቀለውን ክርስቶስን እንደ ተሸከመና በውስጡ እንዳለ አረጋግጦአል፡፡ ስለዚህ ለሕዝቡ መቀጣጫ እንዲሆን በወታደሮች ታስሮ ወደ ታላቅዋ ከተማ ወደ ሮም ሔዶ ለተራቡ አንበሶች ይሰጥ፡፡ ሕዝቡን ለማስደሰትና ለማርካት ሲባል ይህ እንዲሆን አዘናል›› በማለት በቅዱስ አግናጥዎስ ላይ በፈረደ ጊዜ ሊቀ ጳጳሱ ይህን ሰምቶ እጅግ ነበር የተደሰተው፡፡ እንዲያውም ተንበርክኮ፤ ‹‹አምላክ ሆይ! የፍቅርህን ብዛት ለግሰኸኛልና ስለ ሰጠኸኝ ክብር አመሰግንሃለሁ፡፡ ሐዋርያህ እንደ ሆነው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በብረት ሰንሰለት እንድታሰር ፈቅደህልኛልና አመሰግንሃለሁ›› ብሎ ነበር ያስሩት ዘንድ ያመጡለትን የብረት ሰንሰለት የሳማቸው፤ መንገዱ የጽድቅ መንገድ ነውና፡፡ (ቅዱስ አግናጥዎስ)

ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር፣ ጌትነት፣ ኃይል የባሕርይ ገንዘቡ የሚሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ በአባቱ ቤት ወዳለው ብዙ መኖሪያ እንደርስ ዘንድ የጽድቅ መንገዱን ይምራን፤ አሜን፡፡