debre_Tsege.jpg

የመነኮሳት አባቶች የጋራ መኖሪያ ቤት ተመረቀ

በደረጀ ትዕዛዙ
 
debre_Tsege.jpgበ ሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ቅድስት ማርያም ገዳም የተሠራው የአረጋውያን አባቶች መነኮሳት የጋራ መኖሪያ ቤትና መጦሪያ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡መንፈሳዊ ዕውቀት ሀብታቸውን ሲያካፍሉ የኖሩ አባቶችን ለመንከባከብ የተደረገው ጥረት የሚያስመሰግን መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ተናገሩ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በገዳሙ ተገኝተው የመነኮሳቱን መኖሪያ ሕንፃ መርቀዋል፡፡

 

በምእመናን፣ በበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም በገዳሙ ትብብር ተሠርቶ ጥቅምት 21 ቀን 2003 ዓ. ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና ሌሎችም ብፁአን አባቶች በተገኙበት ለምረቃ የበቃው ይኸው የጋራ መኖሪያ ቤትና መጦሪያ ከአራት መቶ ሰባ ሺሕ ብር (400,000) በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን ሃያ (20) አረጋውያን አባቶች መነኮሳትን ለመንከባከብ ያስችላል፡፡

መጦሪያ ቤቱን ባርከው የከፈቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትርያርክ ርዕሰ ሊቀ ጳጳስ ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዘዳንት እንደተናገሩት፤ «መንሳዊ ዕውቀታቸውን ሲያካፍሉ የኖሩ አባቶች ሲደክሙ ማረፊያና መንከባከቢያ ስፍራ መዘጋጀቱ ተገቢ እና ትውልዱ ሊከተለው የሚገባ ተግባር ነው፡፡» ብለዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሕፃናት ማሳደጊያ፣ የአረጋውያን መጦሪያና የጎልማሶች መማሪያ በየሀገረ ስብከቱ እንዲቋቋም የታዘዘ መሆኑን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፤ ሊቃነ ጳጳሳት ከመንፈሳዊ ልጆቻቸው ጋር በመሆን ይህንኑ ለማከናወን እየጣሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለአረጋውያኑ አስቦ ኮሚቴው የድርሻውን ለመወጣት የሠራው በጎ ሥራ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ በበኩላቸው፤ የደቀ መዛሙርት መገኛ በሆነው በዚህ ስፍራ አባቶች መነኮሳትን አስቦ ይህን በጎ ተግባር መፈጸም ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትደግፈው የተባረከ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አረጋውያኑ በገዳሙ ለረጅም ዘመን መንፈሳዊ አገልግሎት ሲፈጽሙ የነበሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተደረገላቸው ድጋፍ የጸሎት ተግባራቸውን ለመቀጠል የሚያስችላቸው በመሆኑ ኮሚቴው ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡

የገዳሙ አበምኔት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ መስፍን አስተባባሪ ኮሚቴውን በመወከል ባቀረቡት ሪፖርት፤ በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድና መመሪያ መሠረት ሚያዝያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም የተቋቋመው ኮሚቴ ዋነኛ ዓላማው የአረጋውያን አባቶች መነኮሳት መኖሪያ ቤት ማሠራት፣የዕለት ምግባቸውን ማቅረብ እና አጠቃላይ ጤንነታቸውን መንከባከብ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ኮሚቴው ተግባሩን በአግባቡ እንደተወጣ የገለጡት አበምኔቱ አረጋውያን አባቶች ቀደም ሲል ያጋጠማቸውን ምግብ የማጣት ችግር ከማቃለል ጎን ለጎን አባቶችን የሚከባከብና ንጽሕናቸውን በመጠበቅ የሚያገለግል ሰው በመመደብ ችግራቸውን ለመፍታት ተችሏል ብለዋል፡፡ በዚህ ተግባርም አሁን በገዳሙ የሚገኙ አገልጋይ መነኮሳት አባቶች የበለጠ ተስፋ አግኝተው መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙ እንዳበረታታቸው መገንዘብ እንደተቻለም አስረድተዋል፡፡

የአረጋውያኑ መጦሪያ ከመኖሪያ ክፍላቸው የመመገቢያ፣ የማብሰያ፣የመታጠቢያ የመፀዳጃ እና አዳራሽን ያካተተ መሆኑን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡አረጋውያኑ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ክፍል ያላቸው ሲሆን አልጋ፣ ፍራሽ፣አንሶላ፣ ብርድልብስ፣ ጋቢ፣ የሌሊት ልብስ እንዲሁም ለመነኮሳት የሚሆን አልባሳት እንደተሟሉላቸው ተገልጧል፡፡

የገዳሙ አበምኔት አረጋውያኑን ለመደገፍ በተደረገው ጥረት ድጋፋቸውን ላደረጉ ለሀገረ ስብከቱ እና በጎ አድራጊ ምእመናን በልዑል እግዚአብሔር ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ወደፊትም አረጋውያኑን በገንዘብ ለመደገፍ ለሚሹ የደ/ቅ/ደብረ/ጽጌ ቅ/ማሪያም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 0173036575400 ቢልኩ እንደ ሚደርስ ተናግረዋል፡፡

ወደ አረጋውያኑ መጦሪያ የገቡ አንዳንድ መነኮሳት አባቶች በሰጡት አስተያየት በጸሎትና በምስጋና ቀሪ ዕድሜያቸውን እንዲያሳልፉ የተመቸ ቦታ ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል፡፡

የ85 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ አባ ወልደ ትንሳኤ በሰጡት አስተያየት፤በገዳሙ ለሠላሳ ሦስት ዓመታት በቅዳሴ መምህርነት ሲያገለግሉ መኖራቸውን ጠቅሰው ዛሬ በደከማቸው ጊዜ ደጋፊ ማግኘታቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ ሌሎች አባቶችም በተሰጣቸው ክብር እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ፣ለሕዝቡና ለሀገሪቱ ሰላም በመጸለይ እነደሚተጉ ተናግረዋል፡፡

ገዳሙ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በ1938ዓ.ም ከተመሠረተ ጀምሮ በርካታ  ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ማፍራቱ ይታወቃል፡፡