«በአዳም ምክንያት ሁላችን እንደምንሞት፣ እንዲሁም በክርስቶስ በኲርነት ሁላችን እንነሣለን፡፡» 1ኛ ቆሮ. 15፥22

                            ክፍል አራት

በጸጋ እግዚአብሔር አምላኩ የከበረ ይህ ሐዋርያው ጳውሎስ ትምህርቱን የበለጠ ተቀባይነት ያለው ለማድረግ  ብርሃነ እግዚአብሔር ኦሪትን ለሐዲሱ ምስክር እያደረገ ያስተማምናል፡፡ስለሆነም «ነሥአ መሬተ ወገብሮ ለእጓለ እመሕያው ወነፍሐ ላዕሌሁ መንፈሰ ሕይወት፤እግዚአብሔር አዳምን ከምድር ዐፈርን ወስዶ ፈጠረው፡፡ የሕይወትንም እስትንፋስ አሳደረበት፡፡»ብሎ መጽሐፍ እንደተናገረ በዚች ነፍስ ሕይወትነት የሚኖር ሥጋ አስቀድሞ መፈጠሩን ይገልጽና፤ከትንሳኤ ዘጉባኤ በኋላ ግን መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሆኖት የሚኖር ሥጋ እንደሚገኝ /እንደሚነሳ/ ለአጽንዖተ ነገር ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ዘፍ 2÷7

ከዚህም አንጻር «በነፍስ ሕያው ሆኖ የሚኖር ቀዳማዊ አዳም አስቀድሞ ተገኝቶአል፡፡ በመለኮታዊ ሕይወት ሕያው ሆኖ የሚኖረው ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ ከአምስት ሽሕ አምስት መቶ ዘመን በኋላ በአዳም ባሕርይ ተገኝቶአል፡፡» ብሎ ቅደም ተከተሉን ከአሳየ በኋላ በትንሳኤ ዘጉባኤ የሚነሳ የመጀመሪያው ሰው የአዳም ዘር ሁሉ መሬታዊ እንደሆነ እንደ ሰማያዊው የባሕርይ አምላክ ክርስቶስም ሰማያዊ እንደሚሆን ያረጋግጣል፡፡በትንሳኤ ዘጉባኤ የሰው ልጅ ሁሉ የሚያገኘውን የተፈጥሮ መዓርግ መሬታዊ አዳም መምሰልን በስሕተቱ፣ በኀጢአትና በሞት ሀብቱ፣ ገንዘቡ እንደ አደረገ ሁሉ፤ ሰማያዊ ክርስቶስ መምሰልንም በዘለዓለም ሕይወትና በጸና ቅድስና ሀብቱ ገንዘቡ ያደርጋል፡፡ እያለ በሙታን ትንሳኤ ጥርጥር ያገኘባቸው የቆሮንቶስ ምእመናን ደቀ መዛሙርቱን ልባቸውን በተስፋ ሕይወት ይመላዋል፡፡ምክንያቱም ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ሥርየተ ኀጢአትን ያገኘ ክርስቲያን ክርስቶስን የሚመስልበት ምስጢር ትንሳኤ ዘጉባኤ ነውና ይህም መንግሥተ እግዚአብሔርን ሀገረ ሕይወትን ለመውረስ በክብርና በቃለ ሕይወት ተጠርቶ የሚቆሙበት ዐደባባይ ዳግም ልደት ነው፡፡ፊል 3÷20-22 ፣እርሱን የሕይወት ባለቤት ክርስቶስን የመምሰል ታላቁ ቁም ነገርና የማያልቅ ጥቅም በእርግጥም ይህ እንደሆነ ከሐዋርያው መልእክተ ቃል እነሆ እንረዳለን፡፡ ይህን ለመረዳትም የዕውቀትና የማስተዋል ባለቤቱ እርሱ መድኃኒታችን ስለሆነ ፈቃዱን በተሰበረ ልቡና ዘወትር መጠየቅ ታላቅ ብልኅነት ነው፡፡

እነሆ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንደበተ ርቱዕ ጥዑመ ልሳን ሆኖ በትምህርተ ወንጌል ለደከመላቸው ወገኖች በቁጥር 50ኛ መልእክቱ «ወንድሞቻችን ይህ ሥጋዊ ደማዊ ሰው መንግሥተ ሰማያትን አይወርስምና ይህን አውቄ እነግራችኋለሁ፡፡»በማለት ይህ ሟች፣ ጠፊ ኃላፊ፣ ፈራሽ፣ በስባሽ ሥጋ በመቃብር ታድሶ ካተነሳ ሕያው ማሕየዊ መንፈስ ቅዱስን ገንዘቡ ሀብቱ እንዳያደርግ ያውቁ ዘንድ ሳይታክት ያስገነዝባቸዋል፡፡ ሞት ርስተ አበው ሆኖ ለሁሉ የሚደርሰው ይህ ኃላፊ ጠፊ ሥጋና ደም ተለውጦ የማይጠፋ ሕያው ሆኖ ለትንሳኤ ዘጉባኤ እስኪደርስ ነው ስለሆነም የሞትን ኃይል ኀጢአትን እንጂ ሞትን ሳንፈራ ትንሳኤ ሙታንን በጽኑ ተስፋ መጠበቅ ይገባናል፡፡ቅዱስ ጳውሎስ የትንሳኤን ሁኔታ ሲያስረዳ «ናሁ ኅቡአ ነገረ እነግርክሙ ፤ እነሆ ስውር ረቂቅ ሽሽግ አሁን የማይታወቅ ነገርን እነግራችኋላሁ፤የሰው ልጆች ሁላችንም ሞተን በስብሰን ተልከስክሰን የምንቀር አይደለም፡፡» «ወባሕቱ ኲልነ ንትዌለጥ በምዕር ከመ ቅጽበተ ዐይን በደኀሪ ንፍሐተ ቀርን፤በኋለኛው የዐዋጅ ቃል እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጠነን ከዚህ ተፈጥሮአችን ወደ አዲስነት እንለወጣለን፡፡» ብሎ ከአስታወሰ በኋላ የሦስተኛ ደረጃ ዐዋጅ በተነገረ ጊዜ ሙታን ከቁጥራቸው ሳይጐድሉ፤ አንዲት አካል ሳይጐድላቸው እንደሚነሡ ገልጦ ያስረዳል፡፡ ይህ ሓላፊ ጠፊ ሥጋችን የማይጠፋ የማያልፍ ሆኖ በመለወጥ ማለት ሕያው መንፈስ ቅዱስን ገንዘቡ፣ ሀብቱ በማድረግ ለዘለዓለም ሕይወት ይነሳል ማለት ነው፡፡ይህ ጸጋና በረከት ለሰው የተጠበቀው ጥንቱን ለሕይወት በፈጠረው ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው ግን ከሕያውነት ኑሮው ወደ ሞት ጐራ ገብቶ ስለነበር በጥንተ ተፈጥሮ ታድሎት የነበረው በሕይወት መኖር ይመለስለት ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ ስሙ፣ በተለየ አካሉ፣ በተለየ ግብርና ኩነቱ /አካኋኑ ኹኔታው/ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ክሶ፣ ሙቶና ተቀብሮ በመነሳት እነሆ የዘለዓለም ሕይወትን በትንሳኤ ዘጉባኤ ያድለዋል፡፡

ትምህርቱን አጠናክሮ ለመፈጸም በተገለጠው ምዕ.በቁ. 54 ላይ «ወአመ ለብሰ ዝንቱ መዋቲ ዘኢይመውት፤ ይህ ሟች የሆነ ሥጋ ከትንሳኤ በኋላ ተለውጦ የተነሳ የማይሞት የሆነውን ሥጋ በለበሰ ጊዜ» ከአለ በኋላ እነሆ! ሞት በመሸነፍ ባሕር ጠለቀ ሰጠመ ተብሎ በልዑለ ቃል ነቢይ የተነገረው ቃል ይፈጸማል፣ይደርሳል፡፡ ይህም ሞት ሆይ ድል መንሳትህ ወዴት አለ? መቃብርስ ብትሆን ሰውን ይዘህ ማስቀረትህ ወዴት ነው? አለ የሞትም ኀይሉ ብርታቱ ኀጢአት ሲሆን፣ የኀጢአትም አበረታች ትእዛዛተ ኦሪት ናቸው፡፡ አለ፡፡ ኀጢአት፣ ኀጢአትነቱ የታወቀው በሕገ ኦሪት ደጉ ከክፋው፣ ክፉውም ከደጉ ተለይቶ በመደንገጉ፣ በመገለጡ መሆኑን ሲያመለክት ነው፡፡ ምንጊዜም ሕግ ሥርዐት መውጣቱ በተላላፊው ወገን ላይ የጥፋት ነጥብን አስቆጥሮ ፍርድን ሊያስከትል፣ ከፍርድ በኋላም ቅጣትን ለማምጣት እንደሆነ ይህች ሕግ ልኩንና ተጨባጭ ማሰረጃን አፍሳ በነሲብ ስለምትሰጠን ለልቡናችን ይደምንብናል ማለት አይቻልም፡፡ዕውቅ ነው፡፡ ኢሳ 25÷8፣ ሆሴ 13÷14፣ሮሜ 13÷19 እንዲህ ስለተደረገለን ፣ እንዲህም ስለሚደረግልን «ወለእግዚአብሔር አኮቴት ዘወሀበነ ንማዕ በእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከሰው ምክንያት ይኸው እንግዲህ በርኅርኅት ሕገ ወንጌል ኦሪትን፣ በጽድቅ በእውነተኛ ንስሐ ኀጢአትን፣በትንሳኤ ሞትን ድል እንነሳ ዘንድ ድል ማድረጉን የሰጠን ሁሉን ያዥ ሁሉን ገዥ እግዚአብሔር አምላክ ይክበር ይመስገን፡፡»በማለት የምግበ መላእክት ስብሐተ እግዚአብሔር ፍጹም ተሳታፊነቱን አንጸባርቆ ገለጠው፡፡በመልእክቱ ማጠቃለይም «እርስ በርሳችሁ የምትዋደዱ እግዚአብሔርን የምትወዱ እርሱም የሚወዳችሁ ወንድሞቻችን ሆይ! ብርቱዎች ሁኑ፤ በማናቸውም ሥራ ሁሉ ዝግጁዎች ሁኑ»ብሎ ሲያበቃ ከላይ እንደታተተው፣እንደተዘረዘረው ከሃይማኖታቸው እንዳይናወጡ፣ እግዚአብሔርን ለማገልገል፣ ሁልጊዜ ከሕጋዊው ሥራ ላይ የትሩፋት ሥራን አብዝተው እንዲሠሩ የትንሳኤ ሙታን ደገኛ የክብር የዋጋ የጽድቅ ማግኛውን ምስጢር ገልጦ ያስረዳቸዋል፡፡»ይልቁንም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመናቸው የተነሳ የተቀበሉት መከራ ሁሉ ከገለጠላቸውና ከአረጋገጠ በኋላ በሃይማኖታቸው መሠረትነት የጽድቅ መልካም ሥራን አብዝተው እንዲሠሩና ለክብር ትንሳኤ እንዲበቁ እንዲዘጋጁም በፈሊጥ ከልቡ ይመክራቸዋል፣ያስተምራቸዋል፤ ያንጻቸዋል፡፡ 2ኛ ዜና መዋ 15÷7 ፣2ኛ ጴጥ 1÷5፡፡ለባስያነ ኀይለ እግዚአብሔር /የእግዚአብሔር ኀይሉን እንደሸማ የተጐናጸፋችሁ/ ክርስቲያኖች ሆይ! አክሊለ መዋዕ የድል አክሊል ሀብተ መንፈስ ቅዱስን የተቀዳጀው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሰዎች አንጻር እንዳስገነዘበን «በአዳም በደል ምክንያት ሁላችን እንደምንሞት፣ እንዲሁም በክርስቶስ ካሳና በኩርነት ሁላችንም እንነሳለን፡፡»በሚል ርእስ «ርእሱ ለአእምሮ፤ የዕውቀት መገኛዋ»የሆነ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በማይመጠን ቸርነቱ በገለጠልን መጠን የምስጢረ ትንሳኤን እሙንነት ይኸው አብራርተን አቅርበናል፡፡ ተስፋው እንደሚፈጸም አምኖ ለመጠባበቅ በርትቶ በማስተዋል ደጋግሞ ማንበቡ ግን የእናንተ ፈንታ ይሆናል፡፡በመሆኑም የሙታን ትንሳኤ መነሳት ወይም አነሳሥ ለተለየ አዲስ ሕይወት ነው፡፡ በዓለመ ሥጋ ምንም ምን አይመስለውም፡፡ይህንም ራሱ ባለቤቱ መድኀኒታችን በዘመነ ሥጋዌው «ወአመሰ የሐይው ምውታን ኢያወስቡ፣ወኢይትዋሰቡ፣ አላ ከመ መላእክተ እግዚአብሔር በሰማያት እሙንቱ፣ ሙታንስ በሚነሡበት ጊዜ አያገቡም፤ አይጋቡም፤ እነርሱ በሰማያት እንደ እግዚአብሔር መላእክት ሆነው ይኖራሉ እንጂ፡፡»በማለት በሕያው ቃሉ የሰጠው ትምህርት በግልጥ ያስረዳናል፡፡ በጌታችን መዋዕለ ሥጋዌ የነበሩ የእምነት መሪዎች፤ በዘመናችንም ብጤዎቻቸው «ሙታን ከተነሡ በኋላ ለዘለዓለም አግብተው እንደሚኖሩ በመስበክ እያስጐመጁ ለያዙት ሃይማኖት ማስፋፊያ አድርገውት ይገኛል፡፡ ይህን አጉልና ከንቱ ሽንገላ ለይቶ በማወቅ ወደ ዕውነት መመለስ፣ ጸንቶ መኖርም በመንፈስ ቅዱስ መቃኘት ነው፡፡ 2ኛ ቆሮ 11÷13-16 ኤፌ 5÷6 ከትንሳኤ ዘጉባኤ በኋላ መብላት መጠጣት የመሳሰለው ሰብአዊ ግብር የለም ጌታችን ከትንሳኤው በኋላ በቅዱሳን ሐዋርያት ፊት የበላው ምግብ አስፈልጐት አይደለም በምትሐት ነው ብለው እንዳይጠራጠሩና ትንሳኤውን እንዲያምኑ ማስረጃ ይሆናቸው ዘንድ ነው፡፡ሉቃ 24÷14-44

መላልሰን እንዳስገነዘብነው ትንሳኤ ዘጉባኤ የክብር የሚሆነው ከዳግም ዘለዓለማዊ ሞት የዳኑ እንደሆነ ብቻ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ይህም ዳግም ሞት የሰው ከእግዚአብሔር መለየት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመጽሐፈ አበው «ሞታ ለነፍስ ርኂቅ እም እግዚአብሔር ፤ የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር መለየቷ ነው፡፡» እንደተባለው ነው፡፡

በአስተዋይ ልቡና ሊተኮርበት የሚገባው ምን ጊዜም የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር የባሕርይ ጐዳናው ምሕረትና ቸርነት ብቻ እንደ ሆነ ከምእመናን ንጹሕ ልብ ሊደበቅ አይገባውም፡፡መዝ 24÷10 የክብር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ትንሳኤውን ለመላው ዓለም አብርቶ የገለጠው የሰው ሁሉ ትንሳኤ ያለጥርጥር የታወቀ የተረዳ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ግበ.ሐ. 26÷23

ከላይ በመልእክቱ ማእከል እንደተገለጸው በሰው ሁሉ አባት በአዳም በደል የሰው ልጅ በሙሉ ሞተ፡፡ በእርሱ በባሕርይ አምላክ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ካሰ እነሆ! መላው የሰው ልጅ ከሞት ከመርገም ዳነ፡፡ የጌታችን ካሳ የራሱ አለማመን ከሚገድበው በስተቀር ማንንም ከማን አይለይም፡፡ዮሐ 3÷36፤ 5÷24 ሮሜ 5÷12-19 በጌታችን ምስጢረ ሥጋዌና ነገረ አድኅኖት አምኖ መጠመቅ ከእርሱ ጋር ተቀብሮ የመነሳት ምስጢር ነው፡፡የትንሳኤ ሙታንም ምልክት ይሆናል፡፡መድኃኒታችንን አምነው ለተቀበሉት ዋጋቸው የሆነ ልጅነትን ይሰጣቸዋል፡፡ በልጅነታቸውም እርሱ እንደተነሳበት ባለ ሥልጣኑ ትንሳኤ ዘለክብርን ያስነሳቸዋል፡፡ በትንሳኤያቸውም የዘለዓለም መንግሥቱ ሀገረ ሕይወትን ያወርሳቸዋል፡፡ ዮሐ. 1÷13፣ ሮሜ 1÷5፡፡

ይህን የትንሳኤ ሙታን ተስፋ ለሰው ሁሉ ተግቶ ያለፍርሃት መመስከር ክርስቲያናዊ ግዳጅ ነውና አምነን በማሳመኑ ሥራ ልንበረታ ይገባናል፡፡ሲራ 4÷20-29፣ 1ኛ ተሰ 4÷18

በገነት በመንግሥተ ሰማያት የማይሰለች ተድላ ደስታ እንጂ ሐዘንና መከራ የለም፡፡ኢሳ 49÷10

ይህን ታላቅ ምስጢር ዐውቀን በሕያው ቃሉ መመራት በእጅጉ ይገባናል፡፡ይህንም በልቡናችን፣ ከመምህራነ ወንጌል፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ተምረን ተመራምረን አምነን ለትንሳኤ ዘለክብር እንድንበቃ በቸርነቱ ይርዳን፡፡