የሀገር አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ በመካሔድ ላይ ነው

ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሀገር አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት 3ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ተጀምሯል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት፤ በኮተቤ ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያን ልዑካን አማካይነት በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን፤ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ የሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ ቀጥሏል፡፡

ብፁዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምእዳን “ነብዩ ሕዝቅኤል ወጣቶችን ሰብስቦ ልጆቼ ሆይ እግዚአብሔርን ታገለግሉት፤ በፊቱም ትቆሙ ዘንድ መርጧችኋልና ችላ አትበሉ እንዳለው ከእናንተ ወጣቶች ብዙ ይጠበቃል፡፡ አባቶቻችን ነብያት፤ ሐዋርያት፤ ሊቃውንት ከራሳቸው በፊት እግዚአሔርን አስቀድመዋል፡፡ እኛም የእነሱን መንገድ ልንከተል ይገባናል፡፡ ዛሬ ከእግዚአብሔር ይልቅ ገንዘብን በማስቀደም ብዙ ነገሮች ሲሰሩ እንመለከታለን፡፡ እናንተ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ዘመኑን ዋጁ፤ በሃይማኖት ቁሙ፡፡ከፊታችን ብዙ ሥራ ይጠበቅብናልና መቀራረብ፤ መተራረም፤ መወያየት ያስፈልገናል” ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ የስልጤ፤ ጉራጌና ሃዲያ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ሲያስተላልፉም “አባቶቻችን የዚህች ጥንታዊት፤ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፤ ቀኖና፤ ሥርዓትና ትውፊት በሚገባ ጠብቀው ዘመን ተሸጋሪ የሆነ ወርቃማ ታሪክ ሰርተው ክርስትናን እስከነ ሙሉ ክብሩ በአግባቡ አስረክበውናል፡፡ እናንተም የአባቶቻችሁን ፈለግ ተከትላችሁ እየተመካከራችሁና እየተናበባችሁ መመሪያውንና ሕጉን አክብራችሁ በመንቀሳቀስ አሁን ካለው መልካም አገልግሎታችሁ የተሻለ ታሪክ እንድትሰሩ አደራ እንላችኋለን” በማለት ጉባኤው ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ውይይት እንደሚካሔድ እምነታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይነትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የ2006 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ በመምህር እንቁባሕርይ ተከስተ አማካይነት ለጉባኤው ቀርቧል፡፡
በቀረበው ሪፖርት በ2006 ዓ.ም. የተከናወኑ አበይት ክንውኖችን በመዳሰስ ያጋጠሙ ችግሮች፤ ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱ መፍትሔዎችም ተብራርተዋል፡፡ በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት መሠረት ከተሳታዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ለጥያቆዎቹም ከመምሪያው ሓላፊ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

ከስዓት በኋላ ቀጥሎ በዋለው ጉባኤም በሰንበት ትምህርት ቤቶች የአንድነት ጉባኤ ውስጠ ደንብና ሀገራዊ አደረጃጀት፤ አፈጻጸምና ፈተናዎቹን አስመልከቶ በመምህር ሙሴ ኃይሉ በማደራጃ መምሪያው ምክትል ኃላፊ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችም ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በየአኅጉረ ስብከት የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ አበይት ተግባራትና ያጋጠሙ ችግሮች አስመልክቶም የቡድን ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአንድነት ጠቅላላ ጉባኤው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፤ ከ50 አኅጉረ ስብከት የተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሓላፊዎች፤ ከመላው ሀገሪቱ የተወከሉ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ተቀዳሚና ምክትል ሰብሳቢዎች፤የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሊቃነ መናብርት ተገኝተዋል፡፡ ጉባኤው በነገው እለትም ቀጥሎ ይውላል፤ ውሳኔዎችንም ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡