የማቴዎስ ወንጌል

ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓ.ም

ካለፈው የቀጠለ

  • ይሁዳ የእግዚአብሔር አብ

  • ኤራስ ዓዶሎማዊ የቅዱስ ገብርኤል

  • በግ የእግዚአብሔር ወልድ

ቀለበት፡- የሃይማኖት፤ ባርኔጣ፡- የአክሊለ ሦክ፤ በትር የመስቀል ትዕማር የቤተ አይሁድ፡፡ ትዕማር መያዣ ይዛ ቀረች እንጂ ዋጋዋን እንዳላገኘች ቤተ አይሁድም ትንቢቱን ተስፋውን ሰምተው ቀሩ እንጂ በክርስቶስ አላመኑምና፡፡

ፋሬስ የኦሪት ዛራ የወንጌል ምሳሌ፡፡ ዛራ አስቀድሞ እጁን እንዳወጣ፡፡ ወንጌልም በመልከ ጼዴቅ ታይታ ጠፍታለችና፡፡ ፋሬስ እሱን ወደኋላ ስቦ እንደተወለደ በመካከል ኦሪት ተሠርታለች፡፡ ዛራ በኋላ እንደተወለደ ወንጌል ኋላ ተመሥርታለችና፡፡

“ሰልሞንም ከራኬብ ቦኤዝን ወለደ”

ራኬብ ያላት ረዓብ ዘማን ነው /ኢሳ.6፥1-27/፡፡ ያለውን ተመልከት በዚህ ቦታ በተገለጸው ታሪክ ላይ ያሉት ሁሉ ኋላ ሊሆን ላለው ምሳሌ ናቸው፡፡

  • ኢያሱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ

  • ኢያሪኮ የምእመናን

  • አሕዛብ የአጋንንት ምሳሌ

ኢያሱ አሕዛብን አጥፍቶ ኢያሪኮን እጅ እንዳደረገ፡፡ ጌታም አጋንንትን ድል ነስቶ ምዕመናንን ገንዘብ ለማድረጉ ምሳሌ፡፡

“ቦኤዝም ከሩት ኢዮቤድን ወለደ”

ትዕማር፣ ራኬብ፣ ሩት እነዚህ ሦስት ሴቶች የተነሡበት ምክንያት ተስፋ ከተሰጣቸው ከእስራአል ወገን ሳይሆን ትንቢት ካልተነገረላቸው ከአሕዛብ ወገን ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም የጌታ ልደት ከእስራኤል ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ወንጌላዊው ማቴዎስ ለወገኖቹ ለዕብራውያን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት የተነገረለት ሱባዔ የተቆጠረለት መሲሕ እርሱ መሆኑን ለማስረዳት የጌታን የዘር ሐረግ በመተንተን ወንጌሉን መጀመሩን ባለፈው እትማችን ተገልጿል፡፡ ከዚያ የሚቀጥለው እነሆ፡-

በጌታችን የትውልድ ቁጥር ውስጥ ከአሕዛብ ወገን የነበሩ ሴቶች የመጠቀሳቸው ምክንያት ባለፈው የተገለጸ ሲሆን ዕብራዊትዋ ቤርሳቤህ /የኦርዮ ሚስት/ ለምን ተነሳች? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ አይሁድ ክርስቶስ በዳዊት ከበረ ይላሉና፡፡ ዳዊት በክርስቶስ ከበረ እንጂ እሱማ ኦርዮንን አስገድሎ ሚስቱን የቀማ አልነበረምን ለማለት እንዲመቸው ነው ሲሉ መተርጉማን ተርጉመውልናል /ወንጌል አንድምታ/፡፡

ጌታ የተወለደው ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆኖ ሳለ ወንጌላዊው ለዮሴፍ የተወለደ ይመስል ቆጥሮ ቆጥሮ ዮሴፍ ላይ ማቆሙ ለምንድር ነው?

በዕብራውያን ሥርዓት የትውልድ ሐረግ የሚቆጠረው በወንድ በኩል እንጂ በሴት አይቆጠርም በዚሁም ላይ አይሁድ ጌታን የዳዊት ልጅ እያሉ ይጠሩት የነበረው በአንዳር በአሳዳጊው በዮሴፍ በኩል ነበርና ዓላማውም የዳዊት ወገን መሆኑን መግለጽ በመሆኑ በዮሴፍ በኩል ቆጠረ፡፡ ዳሩ ግን ጌታ ከእመቤታችን በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱ የታወቀ ነው፡፡ ማቴ.1፥34-36፣ ኢሳ.7፥14፡፡

ዮሴፍና እመቤታችን ዘመዳሞች መሆናቸውን ወንጌላዊው በእጅ አዙር ገልጿል፡፡ አልአዛር በወንጌሉ እንደተገለጸው ማታንን ብቻ ሳይሆን የወለደው ቅስራንም ነው፡፡ ማታን ያዕቆብን ሲወለድ፡፡ ቅስራ ደግሞ ኢያቄምን ወለደ፡፡ ያዕቆብ ቅዱስ ዮሴፍን /የእመቤታችንን ጠባቂ/ ወለደ፡፡ ኢያቄም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን፡፡ ዝምድናቸው በጣም የቀረበ /ሦስት ቤት/ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ሁለቱም የዳዊት ወገን ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ክርስቲያኖች ጌታን የዳዊት ልጅ የምንለው በአንጻር በዮሴፍ ሳይሆን በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡

ዮሴፍ የእመቤታችን እጮኛ ተብሎ መጠራቱ እንዴት ነው? እመቤታችን ለዮሴፍ በእጮኝነት ስም መሰጠትዋ ስለብዙ ምክንያት ነው፡፡ ከእነዚህም ጥቂቶቹ፡-

ሴት ልጅ ናት ጠባቂ ያስፈልጋታልና በእጮኛ ስም እንዲጠብቃት ነው፡፡ እንዲሁም ዮሴፍ ምክንያት ባይሆን እመቤታችን ጌታን በግብረ መንፈስ ቅዱስ በፀነሰችበት ጊዜ መከራ ላይ በወደቀች ነበር፡፡ ስለዚህ ምክንያት ሆኖ ከመደብደብ ከመንገላታት እንዲያድናት ነው፡፡

ክርስቶስ ያለ ወንድ ዘር መወለዱን ዐይተው እናቱ ቅዱስት ድንግል ማርያምን ከሰማይ የመጣች ኃይል አርያማዊት ናት እንጂ የአዳም ዘር ሰው አይደለችም፡፡ ክርስቶስም ከመልአክ የተገኘ መልአክ ነው የሚሉ መናፍቃን እንደሚነሱ ያውቃልና ከመላእክት ወገን ብትሆንማ ኖሮ እንዴት ለማረጋገጥ ለዮሴፍ ታጨች ለማለትና የአዳም ዘር መሆንዋን ለማረጋገጥ፡፡

በመከራዋ በስደትዋ ጊዜ እንዲያገለግላት እንዲላላክላት ነው፡፡

የእግዚአብሔር ጥበብ ድንግል ማርያም በውጭ የዮሴፍ እጮኛ እንድትባል ማድረጉ ከላይ ስለተጠቀሱት ምክንያቶች ነው እንጂ ዘር ለማስገኘት ሔዋን ለአዳም ረዳት ሁና እንደተሰጠችው ዮሴፍ ልጅ ለማስገኘት ረዳት እንዲሆናት አይደለም፡፡ አያይዞም ወንጌላዊው ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን ሲገልጽ፡፡ “እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች” ብሏል፡፡

ጌታም ልደቱን ያለወንድ ዘር ያደረገበት ምክንያት ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን ለማስረዳት ነው፡፡ የመጀመሪያው ልደት በኋላኛው ልደት ታውቋልና፡፡ ቀዳማዊ አዳም ከኅቱም ምድር እንደተገኘ ሁሉ ሁለተኛው አዳም ጌታም ከኅቱም ማኅፀን ተገኝቷል፡፡ እመቤታችን እናትም ድንግልም ስትባል መኖሯ አምላክ ወሰብእ /ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው/ ሲባል ለመኖሩ ምሳሌ ነውና፡፡ ለትውልድ ማኅተመ ድንግልናዋ አለመለወጡ ሰው ሲሆን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ ምሳሌ ናትና፡፡

“የበኲር ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” ሲል ምን ማለቱ ነው?

የበኲር ልጅ ለመባል የግዴታ ተከታይ ሊኖረው አይገባም፡፡ አንድ ብቻ ቢሆንም በኲር ይባላል፡፡ ከእርሱ በፊት የተወለደ የለምና፡፡ ዘጸ13፡1-2፡፡ የጌታ በኲር መባል የመጀመሪያም የመጨረሻም ብቸኛ ልጅዋ ስለሆነ ሲሆን ከድንግል የተወለደውም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ የአብ ልጁ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ዕብ.1፡6፡፡

በሌላም በኩል ከፍጥረታት በፊት ያለና የነበረ፡፡ ፈጣሬ ኲሉ ዓለም መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡ ይህንንም የቤተ ክርስቲያን የንጋት ኮከብ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጾታል “….. ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኲር ነው ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፡፡” ቆላ.1፡17፡፡

“እስከ” የሚለውን ቃል አገባብ በተለያየ ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደገባ በሚከተሉት ምሳሌዎች እንመልከት፡፡

  1. “የሳኦል ልጅ ሜልኮል አስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለችም” 2ሳሙ.6፡23፡፡ አባባሉ ከሞተች በኋላ ልጅ ወለደች የሚል ይመስላል፡፡ ዳሩ ግን ሰው ከሞተ በኋላ ሊወልድ ስለማይችል ትክክለኛው ትርጉም ሳትወልድ መሞትዋን ለመግለጽ የተጠቀሰ መሆኑን ይገነዘቧል፡፡

  2.  “ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ” ሮሜ.5፡7፡፡ የሞት ንግሥና ከሙሴ በኋላ አለመቅረቱ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ አነጋገሩ መቀጠሉን የሚገልጽ ነው እስከ ጌታ ሞት ድረስ፡፡

  3. “እግዚአብሔር ጌታዬን ጠላቶችህን ለእግርህ መረጋገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው” መዝ.110፡1፡፡ ጠላቶቹን ካሸነፈ በኋላ በቀኝ መቀመጡ ቀረን ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታ በመስቀሉ ላይ ዲያብሎስን ድል ካደረገ በኋላ /ቆላ.2፡14ና 15/ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ሆኖ ያየው መሆኑን ተናግሮአል፡፡ የሐዋ ሥራ 7፡55፡፡ የእስከ አገባብ በዚህ ላይ ፍጻሜ የሌለው ሆኖ እናገኛለን፡፡

  4. “እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ማቴ.28፡20፡፡ ከዓለም ፍጻሜ በኋላ ከእናንተ እለያለሁ ማለቱ አይደለም፡፡ ከላይ በተገለጸው መሠረት “እስከ” የሚለው ቃል ፍጻሜ ላለው ነገር እንደሚገባ ሁሉ ፍጻሜ ለሌለው ነገርም ይገባል፡፡ ስለሆነም ወንጌላዊው ማቴዎስ “እስከትወልድ ድረስ አላወቃትም” በማለት ዮሴፍ ጌታን ከወለደች በኋላ በሴትና በወንድ ግብር ፍጹም አላወቃትም ማለቱ ነው፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 3ኛ ዓመት ቁጥር 1 ታኅሥሥ 1988 ዓ.ም.