ዘርና ቦዝ አንቀጽ

መምህር በትረማርያም አበባው
ሚያዚያ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! በዓለ ትንሣኤን በሰላም እንዳሳለፋችሁ ተስፋ እናደርጋለን፤ መልካም!

ታስታውሱ እንደሆነ ባለፈው የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን ‹ንዑስ አንቀጽና ቅጽሎች› በሚል ርእስ አስተምረናችኋል። በዚያም መሠረት ትምህርቱን በተረዳችሁበት መጠን እንድትሠሩትም የሰጠናችሁ መልመጃ ነበር። ስለዚህም በዚህ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ላቀረብንላችሁ የመልመጃ ጥያቄዎች ምላሻቸውን እንዲሁም ስለ ‹ዘርና ቦዝ አንቀጽ› አቅርበንላችኋል፤ በጥሞና ተከታተሉን!

የመልመጃ ጥያቄዎች
፩) ለሚከተሉት ቃላት ሣልስ ውስጠ ዘ አውጡ!
ሀ) ጸሐፈ-ጻፈ
ለ) ሠዐለ-ሣለ
ሐ) ኖለወ-ጠበቀ

፪) ለሚከተሉት ቃላት ንዑስ አንቀጽ አውጡ1
ሀ) አርመመ-ዝም አለ
ለ) ነጸረ-አየ
ሐ) አእመረ-አወቀ

፫) ለሚከተሉት ቃላት ሳድስ ውስጠ ዘ አውጡ!
ሀ) ሠምረ-ወደደ
ለ) ከብረ-ከበረ
ሐ) አፍቀረ-ወደደ
መ) ፈጠረ-ፈጠረ

፬) ለሚከተሉት ቃላት ባዕድ ቅጽል አውጡ!
ሀ) ወደሰ-አመሰገነ
ለ) ናዘዘ-አረጋጋ

፭) ለሚከተሉት ቃላት መድበል አውጡ!
ሀ) ጸሐፈ
ለ) ኖመ
ሐ) መርሐ

የጥያቄዎች መልሶች

፩) ሀ) ጽሓፊ- ለወንድ
ጸሓፍያን-ለብዙ ወንዶች
ጸሓፊት-ለሴት
ጸሓፍያት-ለብዙ ሴቶች

ለ) ሠዓሊ-ለወንድ
ሠዓልያን-ለብዙ ወንዶች
ሠዓሊት-ለሴት
ሠዓልያት-ለብዙ ሴቶች

ሐ) ኖላዊ-ለወንድ
ኖላውያን-ለብዙ ወንዶች
ኖላዊት-ለሴት
ኖላውያት-ለብዙ ሴቶች

፪) ሀ) አርምሞ/አርምሞት
ለ) ነጽሮ/ነጽሮት
ሐ) አእምሮ/አእምሮት

፫) ሀ) ሥሙር-ለወንድ
ሥሙራን-ለብዙ ወንዶች
ሥምርት-ለሴት
ሥሙራት-ለብዙ ሴቶች

ለ) ክቡር-ለወንድ
ክቡራን-ለብዙ ወንዶች
ክብርት-ለሴት
ክቡራት-ለብዙ ሴቶች

ሐ) ፍቁር-ለወንድ
ፍቁራን-ለብዙ ወንዶች
ፍቅርት-ለሴት
ፍቁራት-ለብዙ ሴቶች

መ) ፍጡር-ለወንድ
ፍጡራን-ለብዙ ወንዶች
ፍጥርት-ለሴት
ፍጡራት–ለብዙ ሴቶች

፬) ሀ) መወድስ፣መስተወድስ፣መስተዋድስ
መወድሳን፣መስተወድሳን፣መስተዋድሳን
መወድስት፣መስተወድስት፣መስተዋድስት
መወድሳት፣መስተወድሳት፣ መስተዋድሳት

ለ) መናዝዝ፣መስተናዝዝ
መናዝዛን፣መስተናዝዛን
መናዝዝት፣መስተናዝዝት
መናዝዛት፣መስተናዝዛት

፭) ሀ) ጸሐፍት
ለ) ነወምት
ሐ) መራሕት

ዘር

ከግሥ የሚወጡ ብዙ ዓይነት ስሞች አሉ። እነዚህም ዘር ይባላሉ። ባዕድ ዘር፣ ጥሬ ዘር፣ ምዕላድ፣ ሳቢዘር፣ ዘመድ ዘር፣ ባዕድ ከምዕላድ፣ ጥሬ ምዕላድ፣ ባዕድ ጥሬ ዘር እና ጉልት ናቸው። እያንዳንዳቸውን ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

ዘመድ ዘር

ከግሡ ሆህያት ምንም ሳይጨምር መድረሻው ሳድስ ሆኖ የሚወጣ ዘር ዘመድ ዘር ይባላል። ካሉት ኆኅያት ሊቀንስም ላይቀንስም ይችላል። ለምሳሌ ደምፀ፤ተሰማ ከሚለው ድምፅ የሚል ዘመድ ዘር ይወጣል። የመጨረሻ ፊደሉ ‹ፅ› ሳድስ መሆኑን ልብ ይበሉ። በዚህ ጊዜ የቀነሰው ሆሄ የለም። አንቀልቀለ፤ተነዋወጠ ከሚለው የግእዝ ቃል ደግሞ ‹ቃል› የሚል ዘመድ ዘር ይወጣል። በዚህ ጊዜ ከግሡ ከነበሩ ሆሄያት አራቱ ተቀንሰዋል። በአጭሩ ዘመድ ዘር ከግሡ ምንም ባዕድ ሳይጨምር መጨረሻውን ሳድስ አድርጎ የሚወጣ ነው። ተጨማሪ ምሳሌዎች፦

ግሡ/አማርኛ…የወጣው ዘመድ ዘር
ነሰረ/በረረ…………………ንስር
ፈለከ/ፈጠረ………………ፈለክ
ለበወ/ልብ አደረገ………..ልብ
አንፀብረቀ/አብረቀረቀ……ነፀብራቅ
ሔሰ/ነቀፈ…………………ሒስ
መጽወተ/ሰጠ……………..ምጽዋት
ጾመ/ጾመ…………………..ጾም
ሐለበ/አለበ…………..ሐሊብ/ወተት

ጥሬ ዘር

ጥሬ ዘርም ልክ እንደ ዘመድ ዘር ሁሉ ከግሡ ሆሄያት ላይ ምንም ምን ሳይጨምር መድረሻውን ‹ራብዕ፣ ኃምስ፣ እና ሳብዕ› አድርጎ የሚወጣ ነው። ለምሳሌ ቀደሰ አመሰገነ ከሚለው የግእዝ ቃል ‹ቅዳሴ› የሚል ጥሬ ዘር ይወጣል። የመጨረሻ ፊደሉ ‹ሴ› ኃምስ መሆኑ ልብ ይሏል። ጥሬ ዘርም በሆህያቱ ላይ የሚጨመር ምንም ባዕድ ፊደል የለም እንበል እንጂ ከነበሩት ሆሄያት ግን ሊቀንስ ይችላል። ለምሳሌ ‹ተሠገወ፤ሰው ሆነ› ከሚለው የግእዝ ቃል ሥጋ፣ ሥጋዌ የሚሉ ጥሬ ዘሮች ይወጣሉ። በዚህ ጊዜ ከነበረው ሆሄ ‹ተ› እንደተቀነሰ አስተውል። ተጨማሪ ምሳሌዎች፦

ግሡ/አማርኛ……የወጣው ጥሬ ዘር
ተቀጸለ/ተቀዳጀ………….ቀጸላ
አደመ/አማረ……………..ዕድሜ
ዘመረ/አመሰገነ………….ዝማሬ
ቀነየ/ገዛ………………….ቅኔ
ደመነ/ጋረደ………………ደመና
ማሰነ/ጠፋ……………….ሙስና
ተንሥአ/ተነሣ…………….ትንሣኤ
ከብረ/ከበረ………………ከበሮ

ሳቢ ዘር

ከግሡ መድረሻ ‹ት› ፊደልን የሚጨምር ሆኖ የግሡን መድረሻ ግእዝ አድርጎ ሌላውን ‹ሳድስ› አድርጎ የሚወጣ ዘር ነው። ለምሳሌ ‹ሐይወ፤ኖረ፣ዳነ› ከሚለው የግእዝ ቃል ‹ሕይወት› የሚል ሳቢ ዘር ይወጣል። አስተውሉ! የግሡ መድረሻ ሆሄ ‹ወ› ባለበት ‹ግእዝ› ሲሆን ሌሎቹ ግን ማለትም ‹ሐ› እና ‹ይ› ሳድስ ሆነው ‹ሕ›፣ ‹ይ› መሆናቸውን አስተውሉ! በመድረሻው ላይም ‹ት› ፊደል ተጨምሯል። ተጨማሪ የሳቢ ዘር ምሳሌዎች፦

ግሡ/አማርኛ…….የወጣው ሳቢ ዘር
ፈርሀ/ፈራ………………ፍርሀት
ሰቀለ/ሰቀለ…………….ስቅለት
ጸልመ/ጨለመ…………ጽልመት
ፈለሰ/ተሰደደ…………..ፍልሰት
ፈጠረ/ፈጠረ…………..ፍጥረት
ሐብረ/አንድ ሆነ………….ኅብረት
አምነ/አመነ…………….እምነት
ሰገደ/ሰገደ……………..ስግደት

በሳቢ ዘር የቆመ ቤቶች በተለየ መነሻቸውን ካዕብ ያደርጉና ‹ት› ፊደልን ይጨምራሉ። ይሄውም ቆመ ለሚለው ሳቢ ዘሩ ‹ቁመት› ይላል። የሤመ ቤቶች ደግሞ መነሻቸውን ‹ሣልስ› አድርገው ‹ት› ፊደልን ጨምረው ይወጣሉ። ሢመት ይላል። መነሻቸው ‹ወ› የሆኑ ግሦች ሳቢ ዘራቸው ሲወጣ ‹ወ› ይጎረዳል። ለምሳሌ ‹ወለደ ወለደ› ከሚለው የግእዝ ቃል ልደት የሚል ሳቢዘር ይወጣል እንጂ ውልደት አይልም።

ባዕድ ዘር

ከግሡ መነሻ ባዕድ ቀለማትን ‹መ፣ ተ፣ አ› ን ከግእዝ እስከ ሳብዓቸው እየጨመረ የሚወጣ ሲሆን መድረሻው ግን ሳድስ ነው። ለምሳሌ ‹ቀደሰ፣ አመሰገነ› ከሚለው የግእዝ ቃል መቅደስ የሚል ባዕድ ዘር ይወጣል። መቅደስ ባዕድ ፊደል ‹መ› ን ጨምሮ መድረሻው ‹ስ› ደግሞ ሳድስ መሆኑን አስተውል። ተጨማሪ ምሳሌዎች፦

ግሡ/አማርኛ….የወጣው ባዕድ ዘር
ቀበረ/ቀበረ……………..መቃብር
አመረ/አመለከተ………..ተአምር
ዘመረ/አመሰገነ………..መዝሙር
አዕረፈ/አረፈ…………..ምዕራፍ
ከለለ/ጋረደ……………..አክሊል
ቆመ/ቆመ………………ተቅዋም
ገብረ/ሠራ………………ተግባር
መሰለ/መሰለ……………አምሳል

ምዕላድ

ምዕላድ ደግሞ ከግሡ መድረሻ ላይ ባዕድ ፊደል የሚጨምር እና መድረሻውን ሳድስ አድርጎ የሚወጣ ነው። ለምሳሌ ቆረበ=ቆረበ ከሚለው የግእዝ ቃል ቁርባን የሚል ምዕላድ ይወጣል። አስተውል ‹ን› የሚለው ፊደል ባዕድ ሆኖ ከግሡ መድረሻ ላይ ተጨምሯል። ተጨማሪ ምሳሌዎች፦

ግሡ/አማርኛ……የወጣው ምዕላድ
ተየውሃ/የዋህ ሆነ………..የውሃት
በርሀ/በራ…………………ብርሃን
ሠርዐ/ሠራ………………..ሥርዓት
ኀበሰ/ጋገረ………………..ኅብስት
ረድአ/ረዳ………………….ረድኤት
ተሠልጠ/ሰለጠነ………….ሥልጣን
ተነበየ/ተናገረ……………..ትንቢት
መዐደ/መከረ………………ምዕዳን

ባዕድ ከምዕላድ

በግሡ መነሻ እና መድረሻ ላይ ባዕድ ጨምሮ የሚወጣ ባዕድ ከምዕላድ ይባላል። ለምሳሌ ቀሠፈ=ገረፈ ከሚለው የግእዝ ቃል መቅሠፍት የሚል ባዕድ ከምዕላድ ይወጣል። አስተውል ከመነሻው ‹መ› ን ከመድረሻው ‹ት› ን ጨምሯል። ተጨማሪ ምሳሌዎች
ግሡ/አማርኛ……..ባዕድ ከምዕላዱ
መሀረ/አስተማረ……….ትምህርት
አንጦልዐ/ጋረደ………..መንጦላዕት
ዐደወ/ተሻገረ………….ማዕዶት
ሦዐ/ሠዋ………………መሥዋዕት
ሰፈረ/ለካ………………መስፈርት

ጥሬ ምዕላድ

ከግሡ መድረሻ ባዕድ ጨምሮ የተጨመረው ባዕድ ‹ራብዕ፣ ኃምስ ወይም ሳብዕ› ከሆነ ጥሬ ምዕላድ ይባላል። ለምሳሌ ተትሕተ=ዝቅ ዝቅ አለ ከሚለው የግዕዝ ቃል “ትሕትና” የሚል ጥሬ ምዕላድ ይወጣል። ‹ና› ባዕድ ሆና ራብዕ ስለሆነች ጥሬ ምዕላድ ይባላል። ተጨማሪ ምሳሌዎች፦

ግሡ/አማርኛ……….ጥሬ ምዕላዱ
ኀለየ/አሰበ…………………ኅሊና
ነጽሐ/ንጹሕ ሆነ…………..ንጽሕና
ለበወ/አስተዋለ……………ልቡና
ተሰብአ/ሰው ሆነ………….ሰብእና
ሀለወ/ኖረ………………….ህልውና

ባዕድ ጥሬ ዘር

ከግሡ መነሻ ባዕድ ፊደል ይጨምርና መድረሻ ፊደሉ ‹ራብዕ፣ ኃምስ ወይም ሳብዕ› ከሆኑ ባዕድ ጥሬ ዘር ይባላል። ለምሳሌ ‹ሰንቀወ፣መታ› ከሚለው የግዕዝ ቃል ‹መሰንቆ› የሚል ባዕድ ጥሬ ይወጣል። ባዕድ ያሰኘው ‹መ› ፊደልን በመጨመሩ ሲሆን ጥሬ ያሰኘው ደግሞ መድረሻው ‹ቆ› ሳብዕ በመሆኑ ነው። ሰፈነ ገዛ ከሚለው ግሥ ምስፍና የሚል ባዕድ ጥሬ ዘር ይወጣል።

ጉልት ውስጠዘ

የግሡን መድረሻ ካዕብ ካደረገ ጉልት ይባላል። ለምሳሌ ‹አከለ፤በቃ› ከሚለው የግዕዝ ቃል ‹ኵሉ› የሚል ጉልት ይወጣል። ‹አሐደ፤አንድ አደረገ› ከሚለው የግእዝ ቃል አሐዱ የሚል ጉልት ይወጣል ማለት ነው።

ቦዝ አንቀጽ

ቸልታ የሚሆን አንቀጽ ነው። ይኸውም በዐሥሩ መራሕያን ይዘረዘራል። ለምሳሌ ቀደሰ የሚለውን ቃል መሠረት አድርገን በዐሥሩም መራሕያን ቦዝ አንቀጽ ስናወጣ እንደሚከተለው ነው።
መራሒ…..ቦዝ አንቀጽ……ትርጉሙ
ውእቱ ……..ቀዲሶ……..አመስግኖ
ውእቶሙ….ቀዲሶሙ…አመስግነው
ይእቲ………ቀዲሳ……..አመስግና
ውእቶን…….ቀዲሶን…..አመስግነው
አንተ……….ቀዲሰከ….አመስግነህ
አንትሙ..ቀዲሰክሙ.አመስግናችሁ
አንቲ…….ቀዲሰኪ……አመስግነሽ
አንትን…..ቀዲሰክን…አመስግናችሁ
አነ……….ቀዲስየ………አመስግኜ
ንሕነ……..ቀዲሰነ……..አመስግነን

እያለ በአምስቱ አዕማድም መዝለቅ ይችላል።

የመልመጃ ጥያቄዎች

የሚከተሉትን ቃላት ዘራቸውን እየለያችሁ አውጡ! በቅንፍ ያለው መነሻ ግሡ ነው።
፩) ርደት (ወረደ)
፪) ተውኔት (ተዋነየ)
፫) ትውፊት (አወፈየ)
፬) ብኵርና (ተበኵረ)
፭) ኵፋሌ (ከፈለ)
፮) ተግሣፅ (ገሠፀ)
፯) ልሳን (ለሰነ)
፰) ላዕሉ (ተልዕለ)
፱) ቴሮጋ (ረግዐ)
፲) ሃይማኖት (ሃይመነ)

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።