ዘመነ ክረምት

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የቀናት፣ የወራት እንዲሁም የዓመታት መገለጫዎች የሆኑት ወቅቶች በዘመናት ዑደት በመፈራረቅ በሚከሰቱበት የተፈጥሮ ሂደት ውስጥ ከሰዎች ሕይወት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ በብዙ መልኩም ተምሳሌትነታቸው የተገለጸ ነው፡፡ የሰው ልጅ በአበባ ይወለዳል፤ በንፋስ ያድጋል፤ በፀሐይ ይበስላል፤ በውኃ ታጥቦ ይወሰዳል፤ ይህም ምሳሌው በእግዚአብሔር ፍቃድ እንደምንወለድ፣ በክርስቲያናዊ ሕይወትም መከራና ሥቃይ እንደምንቀበል፣ እንድምንጸድቅና በሞት ወደ ዘለዓለም ዕረፍት እንደምንገባ ነው፡፡

አሁን ያለንበት ወቅት ዘመነ ክረምት ከሞት በኃላ ሕይወት እንዳለ ሁሉ ከድካም በኋላ ዕረፍት እንዳለ የምናረጋግጥበት ወቅት ነው፤ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላጋትና ጠል ጎልተው የሚታዩበት እና ፍሬዎች የሚታዩበት ዘመነ መስቀል ይገለጥበታል።

ዘመነ ክረምት ተምሳሌነቱ ከድካምና ከሥራ በኋላ ውጤት ስለምናይበት፣ ፍርድ ስለምንቀበልበት፣ እርጅናችን በግልጥ ስለሚታይበት፣ የተራቡ ስለሚጠግቡበት፣ ድሆች ስለሚደሰቱበት፣ የዕረፍት ጊዜያችንን በግልጽ ስለምናይበት እና ስለምንጓጓበት ጊዜ ነው።

ይህም  የዝናብ፣ የአዝርእት፣ የአረም ጊዜ እንዲሁም ዕፅዋትና አትክልት በቅለውና ለምልመው የሚያድጉበትና ምድር በአረንጓዴና በልምላሜ የምታሸበርቃበት ወቅት መሆኑ ምሳሌያዊ ነው፤ ገበሬ ያልደከመባቸውና ዘር ያልቀደማቸው በዕለተ ማክሰኞ የተፈጠሩ እነዚህ ፍጥረታትም ለደማዊውም ለነፍሳውያንም ምግበ ሥጋ ይሆኑ ዘንድ ነው ተፈጥረዋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ አዝርዕት በስብሰው እንደሚበቅሉ ሁሉ የሰው ልጅም ከሞት በኋላ እንደሚነሣ፤ ሲነሣም እግዚአብሔር እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን እንደሚከፍለው አስረድቷል፤ የሰው ልጅ ሞቱንና ትንሣኤውን በማሰብ ከኃጢአት መለየት እንደሚገባውም አስተምሮናል። (፩ቆሮ.፲፭፥፴፫-፶፩)

ቅዱስ ያዕቆብም በመልእክቱ ‹‹ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበር፤ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ፤ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች፤ ወንድሞች ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት እንዲሁም ቢመልሰው ኃጢአተኛም ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን የኃጢአቱን መብዛት እንዲሸፍን ይወቅ›› በማለት ተናግሯል። (ያዕ.፭፥፲፯)

ኤልያስ ከሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናብን እንዳይዘንብ እንዳደረገ ሁሉ እንዲሁም እንዲዘንብ አድርጓል። ይህን አምላካዊ ጥበብ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ (፻፵፮፥፰) ላይ ‹‹ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል፤ ሣርን በተራሮች ላይ ልምላሜውንም ለሰዎች ግዛት ያበቅላል›› ሲል ገልጾታል፡፡

በመልካም ግብር በቱሩፋት ጸንተው የሚኖሩ ምእመናን ዝናብ ባለው ደመና ይመሰላሉ። ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር በስመ ክርስትና ብቻ የምንኖር ምእመናን ደግሞ ዝናብ በሌለው ደመና እንመሰላለን። ሐዋርያው ይሁዳም በመልእክቱ ውኃ የሌላቸው ደመናዎችን ‹‹በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፣ ፍሬ የማያፈሩ፣ ሁለት ጊዜ የሞቱ፣ ከነሥራቸው የተነቀሉ፣ በበጋ የደረቁ ዛፎች፣ የገዛ ነውራቸው አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፣ ድቅድቅ ያለ ጨለማ፣ ለዘለዓለም የተጠበቀላቸው፣ የሚንከራተቱ ከዋክብቶች ናቸው›› ብሏቸዋል። (ይሁዳ ፩፥፲፪)

ሐዋርያውም ዝናብ ያለው ደመና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነው፤ እርሷ ንጹሑን የሕይወት ውኃ (ዝናብን) ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታለችና። ‹‹አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ አስተርኤኪ ለነማየ ዝናም፤ የዝናብ ውኃን ያስገነሽልን እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ›› ብሎ ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊው በረቡዕ ውዳሴ ማርያም እንዳስተማረን እርሷ እውነተኛ የሕይወት ምንጫችን ስለሆነች የእውነት ደመናችን ናት።

ሆኖም እንደ ክርስትና የሚያጋጥሙን ፈተናዎች በዝናብ ይመሰላሉ፤ ይህንንም ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል አስተምሮናል፡፡ ‹‹ቃሉን ሰምቶ በሥራ ላይ የሚያውል ክርስቲያን ቤቱን በዐለት ላይ የመሠረተ ብልህ ሰውን ይመስላል›› ብሏልና። (ማቴ.፯፥፳፬-፳፯) እንዲሁም ቤቱ በጎርፍ ቢገፋ አይናወጥምና። ቃሉን ሰምቶ የማይተገብር ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ግን ቤቱ በዝናብ፣ በጎርፍና በነፋስ ተገፍቶ የከፋ አወዳደቅ እንደሚወድቅ ተነግሮናል።

ሃይማኖቱን በበጎ ኅሊና ያልያዘ ክርስቲያን ግን ፈተና ባጋጠመው ጊዜ በቀላሉ እንደሚክድና ለአጋንትም እጁን እንደሚሰጥ አስረድቶናል። ዝናብ ሲጥል የወንዞች ሙላትና ማዕበል ቤት እንደሚያፈርስ ንብረትም እንደሚያወድም በክርስቲያናዊ ሕይወት የሚያሰጥም ፈተናም የእምነት መዛል፣ በመከራ መያዝ፣ በኑሮ መቸገር፣ መውጣትና መውረድ ማብዛት ያጋጥሙናል።

ዝናብ ለጊዜው እንደሚያስበርድና ልብስ እንደሚያስለብስ ሁሉ ፈተናም እስኪያልፍ ድረስ ያሰንፋል፤ ያስጨንቃል፤ እንዲሁም ያዝላል። ነገር ግን ዝናብም ጎርፍም ማዕበልም ጊዜያቸው ሲደርስ ጸጥ እንደሚሉ ሁሉ ምድራዊ ፈተናም ከታገሡት የሚያልፍ የሕይወት ክስተት መሆኑን አውቀን በጾምና በጾሎት እንበርታ!

ይቆየን!