ዐራቱ የእግዚአብሔር ሠራዊት

መምህር ዐቢይ ሙሉቀን

ጥር ፳፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላክ በፍጥረቱ ሁሉ እንደሚመሰገን ‹‹ይባርክዎ ኵሉ ፍጥረት ለእግዚአብሔር፤ ፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል›› በማለት ሠለስቱ ደቂቅ በጸሎታቸው መሥክረዋል።

ከበረሐውያን አንደበት በተሰኘው መጽሐፍ (በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የተዘጋጀ፤ገጽ ፹፮) ላይ ከአበው አንዱ እግዚአብሔር በግዛቱ እንደሚመሰገን እንዲህ ሲል ይገልጻል፤ ‹‹በእግዚአብሔር ዘንድ ዐራት ሠራዊት አየሁ፡፡ ሰባቱ ነጎድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም ሰባቱ ነጎድጓድ የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው አትጻፈውም የሚል ድምጽ ሰማሁ›፤ መጀመሪያው በደዌው ሆኖ እግዚአብሔርን የሚያመሰግን በሽተኛ (ድውይ ዘበአኰቴት) ነው። ሁለተኛው ሰዎችን (እንግዶችን) ደስ እያለው በፍቅር የሚቀበልና የሚያሳርፋቸው ነው። ሦስተኛው በገዳም የሚኖርና ከሰው ጋር የማይነጋገር (ዝጉሐዊ) ነው። አራተኛው ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ለመምህሩ የሚታዘዝና የሚላላክ ረድእ ነው። በዚህ ረድእ በአንገቱ ላይ የወርቅ ባዝግና ተሸልሞ መንበሩም ከሁሉም በላይ ሆኖ አየሁት። ይህን ለሚያሳየኝ ይህ ታናሽ እንዴት ከሁሉ በለጠ? ብየ ጠየቅሁት። እርሱም እነዚህ መልካም የሠሩት በራሳቸው ፈቃድ ነው። ይህ ግን የራሱን ፈቃድ ለእግዚአብሔርና ለመምህሩ የተወ ነው። ስለዚህም ከፍ ያለ ክብርና መንበር ተሰጠው አለኝ። ይህ አባት እንደተጻፈው ለአንዱ ተገልጦ ለሌላው የማይገለጥ አለና ያ አባት የተገለጠለትን ተናገረ እንጂ የእግዚአብሔር ሠራዊት በቁጥር የሚገደብ ሆኖ አይደለም። ስለዚህም እርሱ በተገለጠለት ምሥጢር በእኛም አረዳድ ዐራቱን የእግዚአብሔር ሠራዊት እንመለከታለን፡፡ (ራእ.፲፡፬)

ከዐራቱ ሠራዊት የመጀመሪያው ድውይ ዘበአኮቴት ነው። ይኸውም በሕመም እያለ እግዚአብሔርን የሚያመሰግን አንድ ሠራዊት ነው። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑን አበው መነኰሳት እና እማት መነኰሳይያት ናቸው። ሕመማቸው ዋጋ እንደሚያሰጣቸው ስለሚያውቁ በሕመም ያመሰግኑታል። ከዓለም ተገልለው ለብዙ ዘመናት ብቻቸውን በብሕትውና የሚኖሩ አንድ አባት ነበሩ። አንድ ሰውም ሊጠይቃቸው ሄደና ‹‹አባ ከዚህ በኋላ ደክመዋል፤ በዚህ ገንዘብ የሚያስፈልግዎትን ሁሉ አድርጉ›› ብሎ ገንዘብ ይሰጣቸዋል። እሳቸውም ‹‹እስከዛሬ ሲመግበኝ የኖረ እግዚአብሔርን አንተ በአንድ ጊዜ ልታሳዝንብኝ ነውን? በል ይዘህ ሂድ›› ብለውታል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም  ‹‹ስለዚህ በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልክተኛ ተሰጠኝ፣ ይኸውም እንዳልታበይ ነው›› ብሎ ተናግሯል፡፡ በፈተናዎቹ እና ሕመሙ ሁሉ ላይ ትዕግሥትና የነበረውን ጻድቁን ኢዮብን ማንሳት ይቻላል። (፪ቆሮ.፲፪፡፯)

ሁለተኛው እንግዶችን ደስ እያለው በፍቅር የሚቀበል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። ሐዋርያው ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንደሚነግረን እንግዶችን መቀበል ለክርስቲያኖች የተገባ ነው። ‹‹የወንድማማቾች መዋደድ ይኑር፤ እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ተቀብለዋልና።›› አብርሃም እንግዳ በመቀበል ልማዱ አጋእዝተ ዓለም ሥላሴን ተቀብሏል፤ ሎጥ እንግዳ በመቀበል ልማዱ መላእክትን ተቀብሏል። ሞልቶ ከተረፈው ላይ መሥጠት ላያስደንቅ ይችላል ‹‹ድሀን መጽውት ባለጠጋን ጹም›› ማለት ከባድ ነውና። አባቶቻችን ግን  ካላቸው ላይ ቀንሰው ብቻ ሳይሆን ሳይኖራቸው እንኳን እንግዶችን ተቀብለው ያስተናግዱ ነበር። ይህን በማድረጋቸውም ያገኙት በረከትም ላቅ ያለ ነው። በበረሐ የሚኖር አንድ አባት እንግዶች ሊጠይቁት መጡ። ደስ ብሎትም ተቀበላቸው። የሚበላም አቀረበና ተመገቡ፣የመመገቢያ ሰዓት አልደረሰም ነበርና እንግዶች ጠየቁት ‹‹አባ ሰዓት ሳይደርስ አስበላንህ አትቀየምም?›› አሉት፤ እርሱም ‹‹የማዝንስ የራሴን ፈቃድ ሳደርግ ነው፤ አሁን ግን ያደረግሁት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ነውና እጅግም ደስ ይለኛል፤ይልቁንም በእናንተ ክርስቶስን ተቀብዬዋለሁና›› አላቸው። (ዕብ ፲፫፡፩)

ሦስተኛም በገዳም የሚኖር እና ከሰው ጋር የማይገናኝ የእግዚአብሔርን አገልጋይ ነው። በገዳም መኖር ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ የማስገዛት እና ንጽሕናን ጠብቆ የመኖር ትልቅ የተጋድሎ ሕይወት ነው። ሰው ማኅበራዊ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን ከሌሎች ጋር ተግባብቶ መኖር መኖር ይፈልጋል። እግዚአብሔርም የፈጠረውን ፍጥረት ስለሚውቀው ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምለ አጋር እንፍጠርለት ያለው፤ ሊቃውንቱ ይህን በትርጓሜ ሲያስረዱ ጌታ እግዚአብሔር አምላካችን ዕለተ ዓርብ አዳምን ፈጠረ፤ በዕለተ ቀዳሚትም ዐረፈ። ከዕለተ እሑድ ጀምሮ እንስሳቱን እንዲታዘዙት ወደ አዳም ይልካቸው ነበር፤ ሁሉን እንዲገዛ ሥልጣን ሰጥቶት ነበርና፤ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደእርሱ ሲቀርቡ ባያቸውም ጊዜ ሔዋንን እስከሚያገኝበት ጊዜ ብቻውን ነበርና ‹‹አምላኬ እኔን ብቻ ነው በብቸኝነት የፈጠርከኝ›› እያለ ያዝን ነበር። ብቸኝነት ከባድ መሆኑን ከዚህ እንረዳለን። ‹‹ይሄንን ብቸኝነት እታገለዋለሁ፤ ከሰው በመለየት የሚመጣውን ፈተና እጋፈጣለሁ›› ብሎ መኖር ታላቅ የእግዚአብሔር አገልግሎት ነው። ስለዚህ ሰው መሆንህን ለድካምህ እንደ ምክንያት አታቅርብ ሰው ሆነው ሳለ እንደ መላእክት መኖር የቻሉ አሉና። (ዘፍ ፪፡፲፰)

ዐራተኛውና የበለጠ ክብር ያገኘው ለእግዚአብሔር ብሎ ለመምህሩ የሚታዘዝና የሚላላክ ረድእ ነው። ይህንን በራሱ ላይ  ወርቅ ተሸልሞ መንበሩም ከእነዚህ ከሦስቱም ሠራዊቶች ከፍያለ ልዩ ጸጋ ተሰጥቶታል።  ይህ የሆነበት ምክንያትም እነዚያ ሦስቱ እጅግ የሚደንቅ መልካም ሥራ ቢሠሩ እንኳን ለራሳቸው ፈቃድ ነው። ይሄ ግን ለእግዚአብሔር ብሎ የራሱን ፈቃድ ለመምህሩ አሳልፎ ሰጥቷልና ነው። ‹‹መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል›› ተብሎ በመጽሐፍ እንደተነገረ መታዘዝ ትልቅ ጸጋ አለው፤ ከሁሉ በላይ ክብር ያሰጣልና ከሰው ተለይቶ ከሚኖረው ባሕታዊ፣ እንግዶችን በፍቅር ከሚቀበለው ደግ ሰው እንዲሁም ደዌውን በጸጋ ከተቀበለው ሰው ይልቅ ለዚህ ለታዛዡ የበለጠ ጸጋ ተሠጠው። እነ ዮሐንስ ሐፂርም የደረቀውን እንጨት ለማለምለም የቻት በመታዘዛቸው ነው።(፩ሳሙ.፲፭፥፳፪)

መታዘዝ ከሰነፍ መሥዋዕት ይበልጣል የሚለውን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ፈጽመን፣ታዛዥ የነበሩት ቅዱሳን ያገኙትን በረከት ለማግኘት ያብቃን!