ዐሥሩ ማዕረጋት

ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የምድርን መከራ፣ ችግርና ሥቃይ አልፎ በእምነት ጽናትና በመልካም ምግባር ለሚኖር ሰው የቅድስና ሕይወት እጅግ ጣፋጭ ናት፡፡ በጠቧቧ መንገድ በእውነት በመጓዝ ፍቅር፣ ሰላምንና የመንፈስ እርካታን በማጣጣም ጥዑመ ነፍሰ ምግብን እየተመገበ የመንፈስን ፍሬ ለመብላት በሚያበቃው በክርስትና ሕይወትም ይኖራል፡፡ መስቀልን የጦር መሣሪያ ወንጌልን ጋሻ መከታ አድርጎ ጠላት ዲያብሎስን ድል የነሣ እንደ እነ አቡነ ተክለሃይማኖት ዓይነት ጻድቅ ደግሞ በቅድስና ማዕረግ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይጓዛል፡፡

በርግጥም በቅድስና ሕይወት ሁሉም ተመሳሳይ ችሎታና ትጋት ሊኖረው አይችልም፤ እግዚአብሔር በሰጠው መክሊት ግን አትርፎ በከበረ ሞት ወደ ፈጣሪው መሄድ ይቻለው ዘንድ የአምላካች ቅዱስ ፈቃድ ነው፡፡ ሰው በመንፈሳዊ ብርታት ፈታናውን ሁሉ ማለፍ ከቻለ ለተለያዩ ክብር እንደሚበቃ ቅዱሳት መጻሕፍት ምሥክሮች ናቸው፡፡ ቅዱሳን በገድልና በትሩፋት ብዛት የሚያገኟቸው ዐሥር ማዕረጋት አሉ፡፡ ጽማዌ፣ ልባዌ፣ ጣዕመ ዝማሬ፣ አንብዕ (አንብዐ ንስሓ)፣ ኩነኔ፣ ፍቅር፣ ሑሰት፣ ንጻሬ መላእክት፣ ተሰጥሞ እና ከዊነ እሳት የሚል ስያሜም አላቸው፡፡ የንጽሐ ሥጋ፣ የንጽሐ ነፍስና የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት በመባል ደግሞ በሦስት ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡

. የንጽሐ ሥጋ ማዓረጋት

፩. መዓርገ ጽማዌ

ጽማዌ የቃሉ ትርጓሜ ድንቁርና ማለት ነው፤ ይህም መስማት የተሣነው ሰው ማንኛውንም ድምፅ እንደማይሰማና የልቡን ሐሳብ ብቻ እንደሚያዳምጥ ሁሉ በቅድስና ሕይወት በዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ ቅዱሳንም ማስተዋልን፣ ትዕግሥትን፣ ትሕትናን እና የራስ ሚዛንን ገንዘብ በማድረግ በዓለም ላይ ያለ ምንም ምን ነገር እንደማይሰሙ የሚያመለክት ነው፡፡ በእዝነ ልቡናቸው ግን የእግዚአብሔርን ቃል ያዳምጣሉ፤ በዓይነ ልቡናቸው ደግሞ ግሩማን አራዊትን፣ ከሥጋዋ የተለየች ነፍስንና አጋንንትን ለመለየት ይችላሉ፤ ቅዱሳንም መላእክትንም ለተልእኮ ሲመላለሱ ማየት ይቻላቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ስማቸውንም ሆነ ተግባራቸውን ለይተው ማወቅ አይቻላቸውም፤ በዚህም የተነሣ ጽሙም ተብለው ይጠራሉ፡፡

በዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን ከሰው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነትም ሆነ ንግግር የላቸውም፤ መግቦታቸው መንፈሳዊ ምግብ እንጂ እንደ ተራው ሰው ዘርተው፣ አጭደው፣ ለቅመውና አብስለው አይበሉም፤ ዘወትርም ጾምና ጸሎት ላይ ናቸው፡፡

፪. መዓርገ ልባዌ

የዚህ ማዕረግ ቅዱሳን እንደ ቃሉ ፍቺ ልብ የሚያደርጉ፣ አስተዋይ የሆኑና ዕውቀትና ገንዘብ ያደረጉ ናቸው፡፡ በእነዚህም ጠባያት አንደበታቸውን ለንግግር ከማስቀደም ይልቅ እዝናቸውን ሌሎችን ለማዳመጥ፣ በከንቱ ውዳሴ ለማስተማር ከመቸኮል ይልቅ ለመማር የሚሹ፣ መጽሐፍትን፣ ትንቢትና ተግሣጽንና መመርመርን የሚያበዙ ናቸው፡፡

ቅዱሳኑ ኅሊናቸውንም በኃጢአት ፍላጻ የሚመታቸውን ጾር ለማሸነፍ መስቀል ተክሎ በስግደት ይተጋሉ፡፡ በዚህም ጊዜ በውስጣቸው አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መውረዱን፣ መከራ መቀበሉን፣ መታመም፣ መሰቀሉንና መሞቱን እያሰቡ በኀዘንን በልቅሶ ይሰግዳሉ፡፡ ልባቸውን በፍቅረ እግዚአብሔር፣ አንደበታቸውን በመንፈሳዊ ሕይወት በመስበርና ዓላማን በገጸ መስቀል በመትከል ይተጋሉ፡፡

፫. መዓርገ ጣዕመ ዝማሬ

ቅዱሳን በዚህ ማዕረግ ደረጃ ላይ ምሥጢራትን በሙሉ መረዳት ይቻላቸዋል፤ በጸሎታቸው የሚያሏቸውን የእያንዳንዱን ቃላት ትርጓሜ ያውቃሉ፤ ዝማሬያቸውም እንደ መላእክት ሆኖላቸውም ቀን ከሌሊት አምላካቸው እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡

. የንጽሐ ነፍስ ማዓረጋት

የንጽሐ ነፍስ ማዕርግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን ሥጋቸውን ረስተው ከነፍስ ኃጢአት ይለያሉ፡፡ በብሕትውና ስለሚኖሩ የእግዚአብሔር ጸጋ ያድርባቸዋል፡፡ ተራው ሰው ማየት የማይቻለውን የልዑል ብርሃንን ምሥጢርም ያያሉ፡፡ ሆኖም በተለያዩ ፈተናና ጾር ስለሚፈተኑ ያለመጠራጠር ሳይናወጹ በእምነትና በሃይማኖት ጽናት የፈተናውን ጊዜ ካለፉት ክብራቸው አይለያቸውም፡፡ እነዚህም  በንጽሐ ነፍስ ማዕርግ ላይ ያሉ ቅዱሳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ፷ (ስድሣ) ፍሬ ባፈራው ዘር የተመሰሉ ናቸው፡፡ (ማቴ.፲፫፥፩-፱)

፩. መዓርገ አንብዕ

ከዚህ ማዕረግ ቅዱሳን ሲደርሱ እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ  ያለውን ፍቅር፣ ለድኅነታችንም የከፈለውን መሥዋዕትነት፣ መከራ መስቀልና መቃብር በማሰብ በሚሰጣቸው ሀብተ እንባ አብዝተው ያለቅሳሉ፡፡ እንዲሁም የአዳም ዘር ገሃነመ እሳት እና ዘለዓለማዊ ሞት መኖሩን ሳያገናዝቡ ለወደፊትም ርስተ መንግሥተ ሰማያት እንደተዛጀላቸው ባለማወቅ በፈቃደ ሥጋ መኖራቸውን እያሰቡ ያነባሉ፡፡

በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም እንደተገለጸው ‹‹ሰዎች ለዚህ ዓለም ድሎት ብለው የሚያለቅሱት ልቅሶ ፊትን ያንጣጣል፤ ዓይንን ያመልጣል፡፡ የቅዱሳን ልቅሶ ግን ፊትን ያበራል፤ ኃጢአትን ያስወግዳል፡፡ እርጥብ እንጨት ከእሳት ጋር በተያያዘ ጊዜ እንጨቱ ከነበልባለ እሳት ሲዋሐድ እንጨቱ እርጥብነቱን ትቶ ውኃውን በአረፋ መልክ እያስወገድ ይነዳል፡፡ ቅዱሳንም በግብር (በሥራ) ከመለኮት ጋር ሲዋሐዱ የዚህ ዓለም ምስቅልቅል ሥራ በሰማያዊ የረጋ ሕይወት ተለውጦ አሠራራቸው፣ አካሄዳቸው ፍጹም ሕይወታቸው መልአካዊ ይሆናል፡፡››

፪. መዓርገ ኵነኔ

ኵነኔ ቃሉ እንደሚያመለክተው ሥጋዊ ፈቃድ ለነፍስ ፈቃድ የሚገዛበት ማዕረግ ነው፤ ቅዱሳኑ በዚህ ደረጃ የነፍስ ፈቃዳቸው የሥጋ ፈቃዳቸውን ያስገዛሉ፡፡ ስለዚህም የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድን ብቻ የሚፈጽሙበት ማዕርግ ኵነኔ (አገዛዝ፣ ግዛት) ነው፡፡

፫. መዓርገ ፍቅር

ቅዱሳን እዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ሀብተ ፍቅር ስለሚሰጣቸው ፍቅረ እግዚአብሔር ፍቅር ቢጽ ሲኖራቸው ሁሉንም ደግሞ መውደድ ይቻላቸዋል፡፡ ሰዎችን ሁሉ በዘር፣ በጎሳ፣ በብሔር፣ በጾታ፣ በሀብት እንዲሁም በመሳሰሉት ሳይለዩ ሁሉንም እኩል የመውደድ ብቃት ይኖራቸዋል፡፡ እንደ ሊቃውንቱ አገላለጽ በእነርሱ ዘንድ ‹‹አማኒ፣ መናፍቅ፣ ኃጥእ፣ ጻድቅ፣ ዘመድ፣ ባዕድ፣ ታላቅ፣ ታናሽ፣ መሐይም፣ መምህር፣ በማለት ሳይለዩ ሁሉንም በመውደድ የመፍቀሬ ሰብእ እግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ያስመሠክራሉ፡፡››

፬. መዓርገ ሑሰት

ሑሰት የቃሉ ትርጓሜ ‹‹እንደ እግር ፀሐይ (የፀሐይ ብርሃን) ካሰቡበት ሁሉ መገኘት እና በሌላ ቦታ የሚሠራውን በአንድ ቦታ ሆኖ ማየት መቻል›› ማለት ነው፡፡ በዚህም ብቃት ቅዱሳን ባሉበት ቦታ ሆነው ሁሉን ማየትና መረዳት ይችላሉ፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ማንኛውም ኩነትን ማወቅ ይቻላቸዋል፡፡ እዚህ ደረጃ ሲደርሱ መንፈስ ቅዱስ ስለሚዋሐዳቸው ረቅቃን ይሆናሉ፡፡ ሊቃውንቱም ‹‹በሥጋ ግዙፋን ቢሆኑም ጠፈር ደፈር ሳይከለክላቸው በመስተዋት ብርሃን እንደሚያልፍ ማለፍ ይችላሉ›› በማለት ይገልጹታል፡፡

. የንጽሐ ልቡና ማዓረጋት

ንጽሐ ልቡና ማዕረግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን ዓይናቸው እንደማንኛውም ሰው ቢመለከትም እንዲሁም የሰውነት ሙቃት ቢኖራቸውም ነፍሳቸው ከሥጋቸው በመለየት ወደ የመላእክት ዓለም የሚሄዱበት ደረጃ ነው፡፡ በዚያም ሳሉ ከመላእክት ጋር አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ጥዑም በሆነ ዝማሬ እያመሰገኑ በተመስጦና በሐሴት ከቆዩ በኋላ ወደ ምድር ይመለሳሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም እነዚህን ቅዱሳን ፻ (መቶ) ፍሬ በሚያፈራው ዘር መስሏቸዋል፡፡ (ማቴ.፲፫፥፩-፱)

፩. መዓርገ ንጻሬ መላእክት

ንጻሬ መላእክት መላእክትን የማየት ብቃት ወይም ደረጃ ነው፡፡ ቅዱሳን በዚህ ጊዜ ማዕረግ በዚህ ዓለም ላይ ሆነው ለተልእኮ የሚላኩትን መላእክት ማንነት ማወቅና ወደ ላይ ሲወጡና ወደ ታች ሲወርዱ መመልክት ይችላሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ተእልኳቸውን መረዳትና እነርሱንም ማነገጋር ይችላሉ፡፡

ይህም ብቻም አይደለም፤ እነዚህ ቅዱሳን ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለይታ ወደ ሰማይ በመሄድ የመላእክትን ዓለም መመልከት፣ ዝማሬያቸውን መስማት፣ እንደ እነርሱም ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ ማመስገን ይችላሉ፡፡

፪. መዓርገ ተሰጥሞ

ተሰጥሞ በባሕር ውስጥ እንደሚሰጥሙ ዓሣዎች እዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ ቅዱሳንም ኅሊናቸው ጸጥ የሚልበት እንዲሁም ልዑል፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ በሚሆን ብርሃን የሚሰጥሙበት ደረጃ ነው፡፡ የብርሃን ውቅያኖስ ውስጥ እንደሚወኙ እና እንደሚንሳፈፉ ማለት ነው፤  ሊቃውንቱ ይህን ሲያመሳጥሩት ‹‹ይሄ የብርሃን ውቅያኖስ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው፡፡ በዚያ ብርሃን ልቦናቸው ይታጠባል፤ ፍጹም ሆነው የልብ ንጽሕና ላይ ይደርሳሉ፡፡

፫. መዓርገ ከዊነ እሳት

ከዊነ እሳት ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ ተብሎም ይጠራል፡፡ የመጀመሪው መጠሪያውም እንደሚያመለክተው እሳትን የመሆን ማዕረግ እንዲሁም የመጨረሻ የብቃት ደረጃ ነው፡፡ ይህም ማለት ቅዱሳን በዚህ ደረጃ እሳት ይሆናሉ፡፡ ሊቃውንቱም ይህን ‹‹ሰውነታቸው በብርሃን ይከበባል፤ ከእግር እስከ ራሳቸው ድረስ እሳት ይመስላሉ፡፡ ንጽሐ ልቡና ስለተሰጣቸው ቅድስት ሥላሴን የማየት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፤ በተዋሕዶ ከመላእክት ጋር ሆነው፣ ረቀው እግዚአብሔርን ማመስገን ይቻላቸዋል፡፡ የለበሱትን ሥጋ ለብቻቸው ለይተው ማየት፤ በአካለ ነፍስ ሰማየ ሰማያትን መጐብኝት፤ ገነት ውስጥ መግባት ይችላሉ›› በማለት ያብራራሉ፡፡ ዐሥሩ ማዕረጋት የዐሠርቱ ትእዛዛትና የዐሥሩ ብፁዓን ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ስለዚህም ትእዛዛቱን ጠብቀን እንደ ቅዱሳኑ በንጹሕ ልቡና በቅድስና ሕይወትና ኖረን  ጌታችን፣ ‹‹ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና›› እንዳለው አምላክችን እያገለገልን መኖር ያስፈልገናል፡፡ (ማቴ. ፭፥፰)

የቅዱሳን በረከት አይለየን፤ አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!