ሙሻ ዘር

መምህር በትረማርያም አበባው

 ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ‹‹እርባ ቅምር›› በሚል ርእስ የሁለተኛውን ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበን ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ስለ ‹‹ሙሻ ዘር›› እናስተምራችኋለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!

የሚከተሉትን የግእዝ ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ።

፩) ሰክረ ወይነ።

፪) ክርስቶስ መጽአ መላእክተ።

፫) አምላክ ተሰቅለ ሰብአ።

፬) ለይኩን ብርሃን።

፭) ወረደ ባቢሎን

የጥያቄዎች መልሶች

፩) በወይን ሰከረ።

፪) ክርስቶስ ከመላእክት ጋር መጣ።

፫) አምላክ ለሰው ብሎ ተሰቀለ።

፬) ብርሃን ይሁን።

፭) ወደባቢሎን ወረደ።

ሙሻ ዘር

ሙሻ ዘር የሚባል ተናባቢ ቃል ነው። አንድም ሙሻዘር ማለት ማያያዣ ማጣበቂያ ማለት ነው። አንድ ቃል ተናቦ አገባብ ሲያወጣ ሙሻ ዘር ይባላል። ሙሻ ዘር የሚሆኑ ቀለማት ፲፩ ናቸው። እነዚህም ቀዳማይ አንቀጽ፣ ካልዓይ አንቀጽ፣ ሣልሳይ አንቀጽ፣ ዘንድ አንቀጽ፣ ቦዝ አንቀጽ፣ ሣልስ ቅጽል፣ ሳድስ ቅጽል፣ ባዕድ ቅጽል፣ መድበል፣ ሳቢ ዘር እና ንዑስ አንቀጽ ናቸው። ከእነዚህም አምስቱ ማለትም ቀዳማይ፣ ካልዓይ፣ ሣልሳይ፣ ዘንድ፣ ቦዝ፣ ዘርዝረው ሳይናበቡ ስድስቱ ግን ማለትም ንዑስ አንቀጽ፣ ሳቢ ዘር፣ ሣልስ ቅጽል፣ ሳድስ ቅጽል፣ ባዕድ ቅጽል እና መድበል እየተናበቡ ዘጠኝ አገባባትን ያመጣሉ። እነዚህም:- በይነ/ እንበይነ/ በእንተ/ ህየንተ/ ፍዳ/ ተውላጠ/ አስበ/ ዕሴተ/ ቤዛ/ ዓይነ ስለአንድ፣ ለ፣ በ፣ እም፣ ከመ፣ ምስለ፣ ኀበ፣ እስከ፣ እንበለ እና ግእዝ ናቸው። እያንዳንዳቸው እንዴት እንደሚወጡ ቀጥለን እንመለከታለን። ቀዳማይ፣ ካልዓይ፣ ሣልሳይ ሲቀሩ ውእቱ ከሁሉም ይመረምራል።

ለ፣በይነ (ለ፣ስለ) ሲወጡ:-

ንዑስ አንቀጽ:- ለዘካርያስ አብ መዊተ ዮሐንስ ወልድ ሲል ትርጉሙ ለልጅ ዮሐንስ መሞት ለዘካርያስ አባት ይገባል ይላል። ወይም ደግሞ ስለ ልጅ ዮሐንስ መሞት ለዘካርያስ አባት ይገባል ይላል።

ሳቢ ዘር:– ለአምላክ ኦርዮ ሙተተ ሔዋን ቤርሳቤህ ይላል። ትርጉሙ ለቤርሳቤሕ ሔዋን መሞት ለአምላክ ኦርዮ ይገባል። ወይም ስለ ቤርሳቤሕ ሔዋን መሞት ለኦርዮ አምላክ ይገባል ይላል።

ሣልስ ቅጽል:- ነስሐ ዳዊት መስፍን ቀታሌ ቤርሳቤሕ መርዓት ኦርዮንሀ ብእሴ ይላል። ትርጉሙ ኦርዮን ሰውየን ስለ/ለ ሙሽራ ቤርሳቤሕ የገደለ ዳዊት ተጸጸተ ይላል።

() ሲወጣ

ንዑስ አንቀጽ:– ለአምላክ ተሰቅሎተ መስቀል ይላል። ትርጉሙ በመስቀል መሰቀል ለአምላክ ይገባል ማለት ነው።

ሳቢ ዘር:- ለይሁዳ ስቅለተ መስቀል አምላከ ይላል። ትርጉሙ አምላክን በመስቀል ማሰቀል ለይሁዳ ይገባል ማለት ነው።

ሣልስ ቅጽል:- ተክዕወ ወይነ አማኑኤል ደም ተቀዳሔ መስቀል ጽዋዕ ይላል። ትርጉሙ በመስቀል ጽዋዕ የተቀዳ የአማኑኤል ወይን ደም ፈሰሰ ማለት ነው።

እም () ሲወጣ

ንዑስ አንቀጽ:– ለአማኑኤል ወይን ተቀድሖተ ድንግል ቀሡት ይላል። ትርጉሙ ከድንግል እንስራ መቀዳት ለአማኑኤል ወይን ይገባል።

ሳቢ ዘር:-ለያዕቆብ ወልድ ልደተ ማርያም ርብቃ ይላል። ትርጉሙ ከማርያም ርብቃ መወለድ ለወልድ ያዕቆብ ይገባል ይላል።

ሣልስ ቅጽል:- ያስተፌሥሕ ልበ ደመ ኢየሱስ ወይን ተቀዳሔ ገቦ ቀሡት ይላል። ትርጉሙ ከእንስራ ጎን የተቀዳ የኢየሱስ ደም ወይን ልብን ያስደስታል ማለት ነው።

ከመ፣ምስለ (እንደ፣ ጋር) ሲወጡ

ንዑስ አንቀጽ:- ለይሁዳ ገብር አቅትሎተ ፈያት አምላከ አይሁደ ይላል። ትርጉሙ አይሁድን አምላክን እንደ ሽፍታ ማስገደል ለይሁዳ ባርያ ይገባል። ለአሳሔል ገብር ተራውጾተ ፈረስ ብሎ ከፈረስ ጋር መሯሯጥ ለአሳሔል ባርያ ይገባል ይላል።

ሳቢ ዘር:- ለአማኑኤል ገብር ሙተተ ፈያት ኃያላን ይላል። ትርጉሙ እንደ ኃያላን ሽፍቶች መሞት ለአማኑኤል አገልጋይ ይገባል ይላል፤ ወይም ከኃያላን ሽፍቶች ጋር መሞት ለአማኑኤል አገልጋይ ይገባል ይላል።

ሣልስ ቅጽል:- ይረውጽ ገብርኤል ላእክ ተፈናዌ ሚካኤል ወልድ ይላል። ትርጉሙ ከሚካኤል ልጅ ጋር የተላከ ገብርኤል ተማሪ ይሮጣል። የኀዝን ይሁዳ አርጤክስስ ሰቃሌ ፈያት ኃያላን ሐማሀ ወልደ ይላል። ትርጉሙ ወልድ ሐማን እንደ ኃያላን ሽፍቶች የሰቀለ አርጤክስስ ይሁዳ ያዝናል።

ኀበ፣እስከ (ወደ፣ እስከ) ሲወጡ

ንዑስ አንቀጽ:- ለገብርኤል ላእክ ተፈንዎ ድንግል ንግሥት ይላል። ትርጉሙ ወደ ድንግል ንግሥት መላክ ለገብርኤል ተማሪ ይገባል ማለት ነው። ለንጉሥ አብ አስተፋንዎተ ድንግል ንግሥት ገብርኤልሀ መሢሐ ምስለ መለኮት መስፍን ይላል። ትርጉሙ ከመለኮት መስፍን ጋር መሢሕ ገብርኤልን ወደ/እስከ ድንግል ንግሥት ማላላክ ለገብርኤል ተማሪ ይገባል ማለት ነው።

ሳቢ ዘር:-ለገብርኤል ላእክ ብጽሐተ ድንግል ንግሥት ይላል። ወደ/እስከ ድንግል ንግሥት መድረስ ለገብርኤል ተማሪ ይገባል።

ሣልስ ቅጽል:- ክቡር ውእቱ ዳዊት ገብርኤል በጻሔ ድንግል ቤርሳቤሕ ይላል። ትርጉሙ ወደ/እስከ ቤርሳቤሕ ድንግል የደረሰ ገብርኤል ዳዊት ክቡር ነው ማለት ነው።

እንበለ (ያለ በቀር) ሲወጣ

ንዑስ አንቀጽ:- ለአማኑኤል አቤል ተቀትሎተ ኃጢአት ሰይፍ ይላል። ትርጉሙ ያለ ኃጢአት ሰይፍ መገደል ለአማኑኤል አቤል ይገባል ማለት ነው።

ሳቢዘር:- ለአማኑኤል ዳዊት ንግሠተ ሐዋርያት እስራኤል በመስቀል ኬብሮን ይላል። ትርጉሙ በመስቀል ኬብሮን ያለ እስራኤል ሐዋርያት መንገሥ ለአማኑኤል ዳዊት ይገባል።

ሣልስ ቅጽል:- ክቡር ውእቱ አማኑኤል ዳዊት ተቃታሌ ኃጢአት ሰይፍ ምስለ ጎልያድ መልአከ ሞት ይላል። ትርጉሙ ከጎልያድ መልአከ ሞት ጋር ያለ ሰይፍ ኃጢአት የሚገዳደል ዳዊት አማኑኤል ክቡር ነው ይላል።

ተሳቢ (ግእዝ) ሲያወጣ

ንዑስ አንቀጽ:- ሠምረ ይሁዳ ሄሮድስ አስተቃትሎ አማኑኤል ዮሐንስ ምስለ አይሁድ ሐራሁ ይላል። ትርጉሙ ከአይሁድ ጭፍሮቹ ጋራ አማኑኤል ዮሐንስን ማገዳደል ሄሮድስ ይሁዳ ወደደ።

ሳቢ ዘር:- ለንግሥት ድንግል ቅድሐተ ድንጋሌ ወይን በቢረሌሃ ልቡና ይላል። ትርጉሙ በልቡና ዋናጫዋ ድንግልና ወይንን መቅዳት ለንግሥት ድንግል ይገባል ይላል።

ሣልስ ቅጽል:- ክብርት ድንግል ለባሲተ ንጽሕ ጸምር ይላል። ትርጉሙ ንጽሕና ግምጃን የለበሰች ድንግል ክብርት ናት ማለት ነው።

እስከዚህ ድረስ ዘመድ ሙሻዘር፣ ዘመድ ቅጽል፣ ዘመድ ዝርዝር ይባላል። ከዚህ ቀጥለን የምንመለከተው ደግሞ ባዕድ ሙሻዘር፣ ባዕድ ቅጽል፣ ባዕድ ዝርዝር ይባላል። ይህም አገባቡን ከእነ ዝርዝሩ አውጥቶ ዝርዝሩን ወደ ኋላ ይዘረዝራል።

 “ለ፣በይነ ሲዘረዝር

ንዑስ አንቀጽ:- ለአዳም መዊተ አምላክ ይላል። ትርጉሙ ለእርሱ/ ስለእርሱ የአምላክ መሞት ለአዳም ይገባል ማለት ነው ይላል።                    –

ሳቢ ዘር:- ለአዳም አብ ልደተ አማኑኤል ወልድ ይላል። ትርጉሙ ለእርሱ/ስለእርሱ የአማኑኤል ልጅ መወለድ ለአዳም አባት ይገባል።

ሣልስ ቅጽል:- ድኅነ አዳም መዋቴ እግዚእ ይላል። ትርጉሙ ለእርሱ/ስለእርሱ ጌታ የሞተለት አዳም ዳነ ማለት ነው።

ሲዘረዝር

ንዑስ አንቀጽ:- ለመስቀል ተሰቅሎ አምላክ ይላል። ትርጉሙ በእርሱ የአምላክ መሰቀል ለመስቀል ይገባል።

ሳቢ ዘር:- ለመስቀል ዓረፍት ስቅለተ አማኑኤል ወልታ ይላል። ትርጉሙ በእርሱ የአማኑኤል ጋሻ መሰቀል ለመስቀል ግድግዳ ይገባል ማለት ነው።

ሣልስ ቅጽል:- ሠናይት ርስት ተጻባኢተ ናቡቴ ልሂቅ ምስለ አክአብ ዘመድ ይላል። ትርጉሙ በእርሷ ከዘመድ አክአብ ጋር ሽማግሌ ናቡቴ የተጠላላባት ርስት ያማረች ናት ይላል።

እም ሲዘረዝር

ንዑስ አንቀጽ:- ለቤት ወፂአ ነጋዲ ይላል። ትርጉሙ ከእርሱ የነጋዴ መውጣት ለቤት ይገባል።

ሳቢ ዘር:- ለድንግል ጽርሕ ፀአተ አማኑኤል ንጉሥ ይላል። ትርጉሙ ከእርሷ የአማኑኤል ንጉሥ መውጣት ለድንግል አዳራሽ ይገባል።                  –

ሣልስ ቅጽል:-ሚ ይርኅቅ ሰማይ መቅደስ አምጻኤ ገብርኤል ካህን ታቦተ ብሥራት እስከ ማርያም ባሕረ ጥምቀት ይላል። ትርጉሙ ከእርሱ እስከማርያም ባሕረ ጥምቀት የምሥራች ታቦትን ካህን ገብርኤል ያመጣበት መቅደስ ሰማይ ምንኛ ይርቃል!።

ከመ፣ምስለ ሲዘረዝር

ንዑስ አንቀጽ:- ለፈያት ተሰቅሎ አምላክ ይላል። ትርጉሙ እንደነሱ የአምላክ መሰቀል ለፈያት ይገባል ወይም ከእነርሱ ጋር የአምላክ መሰቀል ለፈያት ይገባል ይላል።

ሳቢ ዘር:- ለፈያት መጣብሕ ስቅለተ አማኑኤል ወልታ ይላል።

ሣልስ ቅጽል:- ከብረ ኢዮአብ አስተቃታሌ ዳዊት አሳሔልሀ ምስለ አቤኔር ይላል። ትርጉሙ ከእርሱ ጋራ/እንደ እርሱ ከአቤኔር ጋራ አሳሔልን ዳዊት ያገዳደለለት ኢዮአብ ከበረ።

ኀበ፣እስከ ሲዘረዝር

ንዑስ አንቀጽ:- ለባቢሎን ወሪደ ንስር ይላል። ትርጉሙ ወደ እርሱ/እስከ እርሱ የንስር መውረድ ለባቢሎን ይገባል ይላል።

ሳቢ ዘር:- ለድንግል ንግሥት ሑረተ አማኑኤል ንጉሥ ይላል። ትርጉሙ ወደእርሷ/እስከእርሷ የንጉሥ አማኑኤል መሄድ ለድንግል ንግሥት ይገባል።

ሣልስ ቅጽል:- እምነ ይእቲ ድንግል ተፈናዊተ ገብርኤል እምነ ሰማይ ይላል። ትርጉሙ ወደእርሷ/እስከእርሷ ከሰማይ ገብርኤል የተላከላት ድንግል እናታችን ናት ይላል።

እንበለ ሲዘረዝር

ንዑስ አንቀጽ:- ለእስራኤል ተናግሦ ዳዊት ምስለ ሳኦል ይላል። ትርጉሙ ያለ እርሱ ከሳኦል ጋር የዳዊት መናገሥ ለእስራኤል ይገባል ማለት ነው።

ሳቢዘር:- ለእስራኤል ንግሠተ ሳሙኤል ዳዊትሀ ይላል። ትርጉሙ ያለ እነርሱ ዳዊትን የሳሙኤል ማንገሥ ለእስራኤል ይገባል::

ሣልስ ቅጽል:- ክቡራን እስራኤል አንጋሥያነ ሳሙኤል ዳዊትሀ ይላል ትርጉሙ ያለ እነርሱ ዳዊትን ሳሙኤል ያነገሠላቸው እስራኤል ክቡራን ናቸው ይላል።

እንበለ ከተሳቢ/ግእዝ ጋር ሲወጣ

ንዑስ አንቀጽ:- ለይሁዳ ሰቂለ አምላክ ይላል። ትርጉሙ ያለ እርሱ አምላክን መስቀል ለይሁዳ ይገባል።

ሳቢ ዘር:- ለይሁዳ ስቅለተ አምላክ ይላል። ትርጉም ያለ እርሱ አምላክን መስቀል ለይሁዳ ይገባል።

ሣልስ ቅጽል:- ነስሐ ይሁዳ አስቃሌ አይሁድ አምላከ ይላል ትርጉሙ ያለ እርሱ አምላክን አይሁድን ያሰቀለ ይሁዳ ተጸጸተ።

ስምንቱን አገባባት ዘጠነኛው እንበለ ይበዘብዛቸዋል። ለምሳሌ ለአዳም ኢተሰቅሎ አምላክ ቢል ያለ እርሱ የአምላክ አለመሰቀል ለአዳም ይገባል ማለት ነው። በዚህ ጊዜ በይኔሁ፣ ሎቱ እንደተበዘበዙ አስተውሉ! እንዲህ እያለ እንበለ ስምንቱንም አገባቦች ይበዘብዛቸዋል ማለት ነው። በሳድስ ቅጽል፣ በባዕድ ቅጽል፣ እንዲሁም በመድበልም ከላይ ያየናቸውን መስሎ ይወጣል።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!