ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ ብሔራዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሕግና በሥራዓት የምትመራ፣ የሀገራችን ሕዝቦች ሁሉ የመልካም ሥነ ምግባር ባለቤቶች በመሆን የመከባበርና የመደማመጥ ባህል በሀገራችን እንዲዳብር ዘርና ቀለም፣ ቋንቋ ሳትለይ ሁሉንም ያስተማረች፣ የሥነ ምግባርና የባህል መሠረት መሆኗ የማይካድ ሀቅ ነው።

ቤተ ክርስቲያናችን ፈተናዎች በሚገጥሟት ጊዜ ሁሉ በትዕግሥትና በጥበብ፣ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የመፍታት ልምድና ተሞክሮ ያላት ተቋም ስትሆን ሕዝበ ክርስቲያኑም አባቶቹ የሚሉትን የሚያዳምጥ ከጠብና ግርግር ራሱን በማራቅ ጸሎትና ትዕግስትን የሚያስቀድም በዚሁ መንገድ ብቻ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት የሚወጣ መንፈሰ ጠንካራና ሃይማኖተ ጽኑዕ ሕዝብ ነው።
በአሁኑ ወቅት ሃይማኖቷን፣ ክብርና ልዕልናዋን በሚፈታተን ደረጃ የገጠማት ችግርም በሕግና በሕግ አግባብ ብቻ የሚፈታ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዩን የሀገራችንን ሕግጋት መሠረት በማድረግ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ ሕጋዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ችግሩን ባልተገባ መንገድ መፍታት እንደሚቻል በማመን ከቤተ ክርስቲያናችን አሠራርና ዓላማ ውጪ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚዘዋወሩ መልዕክቶች ምስክር ናቸው። ይህ አይነቱ ድርጊት ከቤተክርስቲያን ታላቅነትና ታጋሽነት ይልቁንም ከምታራምደው መንፈሳዊ አስተምህሮ ጋር የሚጋጭ ተግባር በመሆኑ በእንደዚህ ዓይየቱ ተግባር ላይ መሰማራት ቀርቶ ማሰቡ እንኳን ተገቢነት የለውም።

ስለህነም በተለይም ወጣት የቤተክርስቲያን ልጆቻችን ሁሉ ቤተክርስቲያን በተቋም ደረጃ የምታከናውነውን በህጋዊ መንገድ መብቷን የማስከበር ተግባር ከመደገፍ፣ ከመጸለይና ከአባቶች የሚተላለፉ መልዕክቶችን ብቻ ተቀብሎ ተግባራዊ ከማድረግ ወጪ በማንኛውም አይነት መልኩ ሁከትና ብጥብጥን ከሚፈጥሩ ተግባራት ፍጹም በመራቅ ሕግ አክባሪና ለሕግ ተገዢ በሥነ-ምግባር የታነጻችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ልጆች መሆናችሁን በተግባር ማሳየት ይኖርባችኋል።

በሚቀጠሉት ጥቂት ቀናትና ወራት የሚከበሩ በዓላት ማለትም በታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም የሚከበረውን የቅዱስ ገብርኤል በዓል፤ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም የሚከበረውን የልደት በዓልና ጥር ከጥር ፲- ፲፪ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም የሚከበሩት የከተራ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት አከባበር ዙሪያ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በአንድነትና በኅብረት፣ በለሰላምና በስምምነት ራሳችሁን እንደ ሰላም አስከባሪ በማቁጠር፣ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበርና በጋራ በመስራት ለበዓላቶቻችን በሰላም መከበር ዘብ በመቆም ኦርቶዶክሳዊ የልጅነት ድርሻችን ልትወጡ እንደሚገባ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችሁ መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ