ሥርዓተ አምልኮ

ክፍል አንድ

ታኅሣሥ ፲፩፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ሥርዓት  “ሠርዐ” ሠራ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ደንብ፣ አሠራር፣ መርሐ ግብር ማለት ነው። በሃይማኖት ውስጥ የሚፈጸም የመንፈሳዊ አገልግሎትና አሠራር እንዲሁም ክርስቲያናዊ ሥርዓትን ያመለክታል።

 ሥርዓተ አምልኮት

የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮት ለአምላካችን እግዚአብሔር የሚቀርብ ሥርዓት ነው፡፡ ይህም ሥርዓተ ጸሎትን፣ ሥርዓተ ጾምን፣ ሥርዓተ ምጽዋት፣ ሥርዓተ ስግደትን፣ ሥርዓተ በዓላትን፣ ሥዕላትን፣ መስቀልንና ንዋያተ ቅድሳትን ያካትታል፡፡

፩. ሥርዓተ ጸሎት

ጸሎት ቃሉ ግእዝ ሲሆን “ጸለየ፣ ለመነ” ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ የቃሉ ትርጉምም ልመና እንዲሁም ምስጋናም ነው፡፡ ለምሳሌ “ይትቀደስ ስምከ” /ስምህ ይቀደስ/ ስንል ምስጋና ነው፡፡ “ሲሳየነ ዘለለዕለትነ ሀበነ ዮም” (የዕለት ምግባችንን ዛሬ ስጠን) ስንል ደግሞ ልመና ነው፡፡ እንዲሁም ጸሎት ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገርበት ነው፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፬)

ሀ. ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት

ነቢዩ ዳዊት “ስለ ጽድቅህ ፍርድ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለው” ብሎ እንደተናገረ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሰባት የጸሎት ጊዜያት አሉ፡፡ (መዝ.፻፲፰-፻፷፬)

ጸሎተ ነግህ

ነቢዩ ዳዊት “አምላኬ አምላኬ በማለዳ ወደ አንተ እገሰግሳለሁ” በማለት እንደተናገረው ሌሊቱ አልፎ ቀኑ ሲተካ ከጥዋቱ በዐሥራ ሁለት ሰዓት የምንጸልየው የጸሎት ዓይነት ነው፡፡ (መዝ.፷፪÷፲፩)

በነግህ የምንጸልየው፡-

፩. በዚህ የጸሎት ጊዜም ሌሊቱን በሰላም ስላደረሰን አምላካችን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ ዕለቱንም ከክፋት እንዲሠውረን፣ ከፈተና እንዲያወጣን እና በሰላም እንዲያውለን እንጸልያለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን የፈጠረው በነግህ በመሆኑ ያንን ታሳቢ በማድረግ  እንጸልያለን፡፡

፪. ቅዱሳን መላእክትም ለተልእኮ ሲፋጠኑ የሚገናኙበት ሰዓት በመሆኑ የእነርሱን አማላጅነትና ተራዳኢነት በመታመን እንዲሁም የሌሊቱ ጠባቂ መልአክ ተልእኮውን ጨርሶ በቀን በሚጠብቀን መልአክ የሚተካበት እንደመሆኑ ሁለቱ ጠባቂ መላእክት የሚገናኙበት ሰዓት በማሰብ በዚህም ሰዓት እንጸልያለን፡፡

፫. ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች በደል በጲላጦስ ዐደባባይ የቆመበት ሰዓት በመሆኑም እንጸልያለን።

ጸሎተ ሠለስት

ይህ የጸሎት ሰዓት በሦስት ሰዓት የሚጸለይ ነው፡፡

በሦስት ሰዓት የምንጸልየው፡-

፩. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቅዱስ ገብርኤልን ብሥራት የሰማችበት በመሆኑ

፪. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሲል በጲላጦስ አደባባይ የተገረፈበት ሰዓት ስለሆነ

፫. ነቢዩ ዳንኤል ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ መልሶና የቤቱን መስኮት ከፍቶ የጸለየበት ሰዓት በመሆኑ

፬. ለአባቶቻችን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት /በኢየሩሳሌም ጸንተው በመቆየታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይህንን ታላቅ ጸጋ የተቀበሉበት /ሰዓት ነው፡፡

ቀትር

የቀትር ሰዓት የሚጸለየው በዕለተ እኩሌታ (በስድስት ሰዓት) ላይ ነው፡፡ በዚህ ሰዓትም የምንጸልየው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡፡

፩. አዳም በጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ተታሎ ዕፀ በለስን  በመብላቱ ከክብሩ የተዋረደበት ስለሆነ ያን በማስታወስ እንጸልያለን፡፡

፪. አዳም ዕፀ በለስን በልቶ የሞት ፍርድ ስለተፈረደበት ኃጢአተ በደሉን ሊያጠፋለት ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ ዐደባባይ የተሰቀለበት በመሆኑ

፫. ቀትር የቀን እኩሌታ በመሆኑ የፀሐይ ሙቀት የሚያይልበትና የሰው ልጅ ለድካም የሚዳረግበት በመሆኑ አጋንንት ስለሚበረቱበት በቀትር ሰዓት እንጸልያለን፡፡

ተሰዓተ ሰዓት

በዚህ የጸሎት ጊዜ (በዘጠኝ ሰዓት ላይ) ዐራተኛውን ጸሎት እናደርሳለን። ጸሎት የምናደርግበት ምክንያቶችም የሚከተሉት ናቸው፡፡

፩. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መከራ ሥቃይን ተቀብሎ ቅዱስ ሥጋውን ከቅድስት ነፍሱ የለየበት ሰዓት ነው።

፪. ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን በጎም ሆነ ክፉ ሥራ ወደ ፈጣሪ የሚያሳርጉበት ነው፡፡

፫. በዚህ ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ እና ሞት አያሰብን ቅዱሳን መላእክት ከፈጣሪያቸው እንዲያስታርቁን እየለመንንና እየተማጸንን እንጸልያለን፡፡

ጸሎተ ሠርክ

የሠርክ ጸሎት ጊዜ በዐሥራ አንድ ሰዓት የሚጸለይ ጸሎት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይላል፡፡ “ጸሎቴን እንደ ዕጣን በፊትህ ተቀበልልኝ እጅ መንሳቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን” (መዝ.፻፵÷፪)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ከለየ በኋላ ወደ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነው፡፡ (ማቴ.፳፯÷፶፯)

ጸሎተ ንዋም

ንዋም መኝታ ማለት ነው፤ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ዕለቱን በሰላም አሳልፈን ለሌሊቱ ዕረፍት የምንዘጋጅበት በመሆኑ በሰላም ላዋለን ፈጣሪ በሰላም እንዲያሳድረን ከሌሊት አጋንንትና ከቅዠት እንዲጠብቀን እየተማጸንን እንጸልያለን፡፡

በዚህ ጊዜም የምንጸለየው፡-

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ ዛሙርቱን በጌቴሴማኒ ጸሎት ስላስተማራቸው እርሱ ስለጸሎት ማስተማሩን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ 

መንፈቀ ሌሊት (እኩለ ሌሊት)

ቅዱስ ዳዊት ‘’መንፈቀ ሌሊት እትነሣእ ከመ እግነይ ለከ በእንተ ኵነኔ ጽድቅከ፤ ስለ ጽድቅህ ፍርድ በእኩለ ሌሊት አመሰግነህ ዘንድ እነሳለሁ” በማለት ይህ ሰዓት ከእግዚአብሔር ጋራ የሚነጋገርበት እንደሆነ ገልጿል፡፡ (መዝ.፻፲፰፥፷፪)

በመንፈቀ ሌሊት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ዋሻ የተወለደበት በመሆኑ እንዲሁም ሞትን ድል አድርጎ በታላቅ ኃይልም የተነሣበት ሰዓት በሌሊት ያንን ታሳቢ በማድረግ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ለፍርድ ሚመጣበትም ሰዓት  በመሆኑ ለከፈልንን መሥዋዕት እያመሰገንን ምሕረትን ድኅነትን እንድናገኝ ተስፋ በማድረግ በመንፈቀ ሌሊት እንጸልያለን፡፡

ለ. ሥርዓተ ቅዳሴ

ቅዳሴ ምሥጋና ማለት ነው፤ ይኸውም ለፈጣሪያችን እግዚአብሔር የምናቀርበው ምስጋና ነው፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ ወይም የቅዳሴ ሥርዓት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጸሎት ሁሉ በላይ የሆነ፡፡ ለአምላካችን እግዚአብሔር የምናቀርበው ምስጋና ከሰማያውያን መላእክት የተጀመረ ነው፡፡

ቅዳሴንም የጀመሩትም ሰማያውያን መላእክት ናቸው፤ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባታችን ለአዳም ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል የገባለት አምላካዊ የተስፋ ቃል ሲፈጸም ቤተ ልሔም በምትባል የዳዊት ከተማ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ” ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ እያሉ እንዳመሰገኑ በሉቃስ ወንጌል ላይ ተጽፎ እናገኛለን። (ሉቃ.፪፥፲፬)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ለደቀ መዛሙርቱ ኅብስቱን አንሥቶ ባርኮ ፈትቶ  “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው፤ ጽዋውንም ይዞ አክብሮ አመስግኖ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” በማለት የቅዱስ ቁርባንን ሥርዓት በሠጠን መሠረትም ቅዱስ ቁርባን በቅዳሴ ሥርዓት ውስጥ ይፈጸማል፡፡ (ማቴ. ፳፮፣ ፳፮፥፳፱  ማር፥ ፲፬፣ ፳፪፥፳፭)

የቅዳሴ ሥርዓት አገልግሎት በሚፈጸምበት ቦታ ቅዱሳን መላእክት እንደ ቅጠል ረግፈው፣ እንደ ሻሽ ተነጥፈው የሚያከብሩት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ኅብስቱን በጻሕል፣ ወይኑን በጽዋ በማቅረብ ኅብስቱ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር፤ ወይኑ ደመ ወልደ እግዚአብሔር የሚሆንበት ነው።

ቅዱሳን ሐዋርያት ይህንን ሥርዓት ተረክበው ለትውልድ ትውልድ በማስተላለፋቸው ሥርዓቱ ሳይቋረጥ በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ይፈጻማል፡፡

በቅዳሴ ሥርዓት ወቅትም ለዕለቱ በተመደቡ ካህናትና ምእመናን በአንድነት በመሆን ለአምላካችን ምስጋና እናቀርባለን፤ ለበደላችን ይቅርታና ምሕረት እንጠይቃለን፤ ለኃጢአት ሥርየትን እናገኛለን፤ ሥጋ ወደሙ የበቃንም ቅዱስ ቁርባንን እንቀበላለን፡፡ በዚያም የዘለዓለም ሕይወትን እናገኛለን።

ይቆየን!