“ኦሪትና ነቢያት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ጸኑ” (ማቴ.፳፪፥፵)

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው በዚህ ኀይለ ቃል ፍቅር የሁሉም ነገር ማሰሪያና መደምደሚያ መሆኑን  ፡፡ ሰው የሕግ ሁሉ ማሰሪያ የሆነውን እርሱም ፍቅርን ገንዘብ ሊያደርግ እንደሚገባ ያስረዳበት አማናዊ ትምህርት በመሆኑም ሁሉም ሊያውቀውና ሊረዳው እንዲሁም በተግባር ሊፈጽመው የሚገባ ነው፡፡

ምእመናን የእውነተኛ ፍቅርን ምንነት ተረድተው ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዲገልጹት ይጠበቃል፡፡

የፍቅርን ምንነት፣ የፍቅር አይነትን፣ ፍቅርን ገንዘብ እንድናደርግ የሚያስችሉን እና ፍቅርን ገንዘብ እንዳናደርግ ምክንያት የሚመስሉን ግን ያልሆኑ እክሎች የሰው ልጅ ሊረዳቸው የሚገባቸው ነገሮች ናቸው።

የፍቅር ምንነት፡- ፍቅርን በአንድ ቃል ወይም ዐረፍተ ነገር መግለጽ እጅግ አስቸጋሪ ነው፣ ፍቅር ራሱ እግዚአብሔር ነውና። እግዚአብሔርን ደግሞ በመግቦቱ፣ በአባታዊ ቸርነቱ፣ በአምላካዊ ጥበቃው እናውቃዋለን እንጂ በቃላትና በዐረፍተ ነገር ደረጃ እንዲህ ነው ብለን መግለጽ የምንችለው አይደለም። ያም ሆነ ይህ ፍቅር የሕግ ሁሉ የበላይ እንደሆነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት መሠረት አድርገው ሐዋርያት እንዲሁም ሊቃውንት አምልተውና አስፍተው አስረድተዋል። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት በተረጎመበት ከገቢረ ተአምራት “ሙት ከማስነሣት፣ ሕሙም ከመፈወስ፣ ከዕውቀት፣ በመላእክት ቋንቋ ከመናገር፣ ከምጽዋት፣ ሥጋንም ለመሥዋዕት አሳልፎ ከመስጠት ፍቅር ይበልጣል፡፡ ገቢረ ተአምራት ለሁሉ አልተሰጠም፤ ዕውቀትም ለሁሉ አልተሰጠም፤ ፍቅርን ግን መያዝ የሚችለው ሁሉ፣ የታደለውም ለሁሉ ስለሆነ ከሁሉ የሚበልጥ ሕግ ነው” በማለት ያስረዳል፡፡

ከላይ ሊቁ የዘረዘራቸው ልዩ ልዩ ጸጋዎች ናቸው፣ በአንዴ ግን ለሁሉም አልተሰጡም። የመፈወስ ጸጋ ያለው የመስበክ ጸጋ ላይኖረው ይችላል፤ የመስበክ ጸጋ ያለው ደግሞ በተመሳሳይ ተአምር የማድረግ ጸጋ  ላይኖረው ይችላል፤ ተአምር የማድረግ ጸጋ  ያለው እንዲሁ የመስበክ ጸጋ ላይኖረው ይችላል። ለእያንዳንዳቸው የራሳቸው ጸጋ አላቸው። ፍቅር ግን ለሁሉም ስለታደለ ሁሉም ያገኘዋል በማለት ሊቁ ያስረዳን በዚህ መልክ ነው። በመሆኑም በተሰጠው ጸጋ ፍቅርን ገንዘብ አድርጎ መኖር ይቻላልና ሁሉም ሰው ገንዘብ እንዲያደርገው ይጠበቃል።

የፍቅር ዓይነቶች፡-  ፍቅር በዋናነት ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ተብሎ ይከፈላል።

ፍቅረ እግዚአብሔር፡- እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ፍቅር እና ሰው ለእግዚአብሔር ሊኖረው የሚገባው ፍቅር ማለት ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ፍቅር ሲባል “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዷልና” (ዮሐ.፫፥፲፮) የተባለው ነው። ይህ ፍቅር ምንም ምሳሌ ሊገኝለት አይችልም።

ምድራዊ አባት ልጁን ምን ቢወደው ርስቱንና ጉልቱን ያወርሰዋል እንጂ ሕይወቱን አሳልፎ አይሰጠውም። ሰማያዊው አባታችን እግዚአብሔር ግን አስቀድሞ ሰውን በአርአያውና በአምሳያው ፈጠረው። ንጹሕና ቅዱስ ሁኖ ስሙን ቀድሶ ክብሩን ወርሶ እንዲኖር እጅግ በሚደንቅና በፍጹም ፍቅር ፈጠረው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ “ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን፣ ንጹሐንና ያለነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን። በኢየሱስ ክርስቶስም እንደውድ ፈቃዱ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነ” (ኤፌ.፩፥፬-፭) በማለት የእግዚአብሔርን ፍጹም ፍቅር ያስረዳል። እንዲህም የፈጠረው ሰው ትእዛዙን ቢያፈርስና ቢያምጽበት ደግሞ ራሱ  ክሶ ሕይወቱን አሳልፎ፣ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ አድኖታል። ስለዚህ እንዲህ ያለው ፍቅር መቼም ቢሆን ምሳሌ አይገኝለትም።

ሰው ለእግዚአብሔር ሊኖረው የሚገባው ፍቅር ሲባል ደግሞ “አምላክህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስ በፍጹም ኃይልህ ውደደው፣ ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህቺ ናት” (ማቴ.፳፪፥፴፯) የሚለው ነው። ሰው ከራሱም በላይ ከምንም በላይ እግዚአብሔርን ሊወድ ይገባል። ሰው እግዚአብሔርን ሲወድ ሌላ አምላክ አያመልክም፤ ትእዛዙን ያከብራል፤ እንደ ሕጉ ይኖራል። በቅዱስ ወንጌልም “ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ.፲፬፥፲፭) በማለት መድኅነ ዓለም በአጽንዖት ያስተማረው ትምህርት ይህ ነው።

ፍቅረ እግዚአብሔር የመጀመሪያይቱና ታላቂቱ ሕግ እንደሆነች የተመሰከረላት በራሱ በባለቤቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ ከምንም በላይ ሊያስቀድመው የሚገባው ነገር ቢኖር ይህን ሕግ ነው። እግዚአብሔር ሳንወደው ነው የወደደን፣ እኛ ግን የምንጠየቀው ሳንወደው የወደደንን እግዚአብሔርን እንድንወድ ነው። እኛ እየከሰስነው እውነተኛ ፍርድ ፈርዶ ነጻ ያወጣንን፣ እየሰደብነው ያከበረንን፣ እያሳደድነው የርስቱ ወራሾች ያደረገንን አምላክ በፍጹም ሰውነታችን ልንወደው የግድ ይላል።

ፍቅረ ቢጽ፡- ሁለተኛው ሕግ የተባለው ፍቅረ ቢጽ ሰው ለባልንጀራው ሊኖረው የሚገባው ፍቅር ነው። “የምትመስላት ሁለተኛይቱም ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የምትለው ናት” (ማቴ.፳፪፥፴፰) እንዲል። ከዋለበት እየዋለ፣ ካደረበት እያደረ የቃሉን ትምህርት የጠገበው፣ የእጁን ተአምራት የተመለከተውና እስከ መስቀል ድረስ ያልተለየው እንዲሁም ፍቁረ እግዚእ የተባለው ሐዋርያ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ የሚል ወንድሙን የሚጠላ ሐሰተኛ ነው፡፡ የሚያየውን ወንድሙን የማይወድ ግን የማያየውን እግዚአብሔርን እንዴት ሊወድ ይችላል” (፩ኛ ዮሐ.፬፥፳) በማለት ሁለቱ የማይለያዩ እንደሆነ አንድ ሰው የእግዚአብሔር ወዳጅ ለመሆኑ ማረጋገጫው ባልንጀራውን ሲወድ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ሐዋርያው ከፍቅረ እግዚአብሔር ፍቅረ ቢጽን ማስበለጡ ሳይሆን የፍቅረ እግዚአብሔር መገለጫው በዓይነ ሥጋ የሚያየውን ባልንጀራውን ሲወድ ስለሆነ ነው፡፡ እግዚአብሔርን መውደዱ የሚታወቅ እግዚአብሔር በአርአያው የፈጠረውን ሰው ሲወድ ስለሆነም ነው፡፡

በዚህ ባለንበት ዘመን እውነተኛ ማንነታችን ይልቁንም ክርስትናችን የሚለካበት ዘመን  ነው። በዚህ ጊዜ ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ አድርገን ይህን የመከራ ወቅት ካላለፍን በዕለተ ምጽአት በአምላካችን ፊት ስንቆም የሚቀርቡትን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ መመለስ አንችልም። ደግሞም ከእውነት በተሰበረ ልብ እና በቀና መንፈስ ልናደርገው እንጂ እንደ ሕግ አዋቂው “የግብር ይውጣ፣ ባልንጀራየ ማነው?” እያልን በሕግና በፎርሙላ ስንጨነቅ መዋል የለብንም። መልካም የማድረግ ቅንነቱና ሐሳቡ ካለን ባልንጀሮቻችን ሁሌም ከእኛው ጋር ናቸው። በቅዱስ ወንጌልም “ድሆችንስ ዘወትር ታገኟቸዋላችሁ፤ በወደዳችሁም ጊዜ በጎ ታደርጉላቸዋላችሁ” (ማቴ.፳፮፥፲፩) ተብሎ እንደተጻፈ መልካም ማድረግ ከወደድን ሁሌም ከእኛ ጋር ናቸው። በዚህ ጊዜ ግን በተለየ መልኩ ልንደግፋቸውና ልንደርስላቸው ይገባል።

ፍቅርን ገንዘብ አድርገን እንድንኖር የሚያደርጉን ነገሮች

እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር መረዳት፡- እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር በአርአያውና በአምሳሉ ከመፍጠር ጀምሮ ራሱን አሳልፎ እስከ መስጠት ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር በሥራ የተገለጠ ነው። የማያልፍ፣ የማይጠፋ፣ ጊዜ የማይሽረው ፍጹም የሆነ ፍቅር ነው። ስለዚህ ይህን  ፍቅሩን ስንረዳ እኛም በፍጹም ፍቅር እንድንኖር ያስችለናል።

ወዶን ምን እንዳደረገልን መረዳት፡- እግዚአብሔር እኛን ወድዶ ያደረገልን ነገር  በቃላት ተገልጾ አያልቅም። አስቀድሞ በአርአያውና በምሳሌው መፍጠሩ፣ የፍጥረታት ሁሉ ገዢ ማድረጉ፣ በኋላም በበደላችን ምክንያት እንደወጣን እንድንቀር አለመውደዱና ከውድቀታችን ማንሣቱ ጥቂቶቹ ናቸው።  ያም ብቻ ሳይሆን እኛን ያነሣበት ወይም ያዳነበት መንገድ ፍጹም ፍቅሩን እንድንረዳው ያደርገናል። ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዜማው “አኮ በወርቅ ኃላፊ ዘተሣየጠነ አላ በደሙ ቤዘወነ ወለደነ በጥምቀቱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ ኃላፊ በሆነው በወርቅ በብር የገዛን አይደለም፣ በደሙ ዋጀን እንጂ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በጥምቀቱ ዳግመኛ ወለደን እንጂ” በማለት እንደገለጸው የደም ዋጋ የተከፈለልን ልጆቹ ነን።

ሰው ወርቅ ብር የሰጠውን እጅግ ይወደዋል። ወርቅ ብር ከፍሎ የገዛውን ገንዘብም እጅግ አብዝቶ ይወደዋል፤ ይንከባከበዋልም፡። የእኛ አባት መድኃኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በወርቅ በብር ሳይሆን ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ ነው ገንዘብ ያደረገን። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ሲያስረዳ “ከአባታችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ። ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ” (፩.ጴጥ.፩፥፲፰-፲፱) በማለት በመንፈስ ቅዱስ ለወለዳቸው ልጆቹ በላከው መልእክቱ ጽፎላቸው እናገኛለን። ስለዚህ ይህን ውለታ ማሰብ እንዲህ ያለ ዋጋ የከፈለልንን አምላክ ፍጹም ፍቅሩን ገንዘብ አድርገን እንድንኖር ያደርገናል።

የሚያስገኘውን በረከት መገንዘብ፡- ይህን የሕግ ሁሉ ማሠሪያ የተባለውን ፍቅር ገንዘብ አድርገን ብንኖር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ባስተማረው መጽሐፈ ኪዳን ተመዝግቦ እንደምናገኘው  “ዘዐይን ኢርእየ ወእዝን ኢሰመዐ ውስተ ልበ ሰብእ ዘኢተኀለየ ዘአስተዳለወ እግዚአብሔር ለእለ ያፈቅርዎ፤ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ በሰው ልቡና ያልታሰበውን እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውን”  መንግሥተ ሰማያት እንወርሳለን።

በዕለተ ምጽአትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በተገለጠ ጊዜ ለወዳጆቹ “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ፣ ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼም አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳም ሆኜ ተቀብላችሁኛልና። ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜም ጎብኝታችሁኛልና፤ ታስሬም ወደእኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና” (ማቴ.፳፭፥፴፬-፴፮) በማለት ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ብቁ ለመሆን፣ የአባቴ ቡሩካን ለመባል የሚያበቃቸው፣ ወደ ዘለዓለማዊው ርስት ግቡ የሚያስብላቸው ይህ አይነት ደግነታቸውና በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ገንዘብ አድርገውት የሚኖሩት ፍቅር ነው።

በመሆኑም ማንም ሰው በፍቅር ሲኖር ያሰበውን ያገኛል፣ የጀመረውን ይጨርሳል፣ የወደደውን ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ፍቅር ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ  ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖር ሰው በፍቅርና በሰላም ይኖራል፡፡ የሕግ ሁሉ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ገንዘብ ያደረገ ሰው የእግዚአብሔር ወዳጅ ነው፣ የሰው ልጅም ሁሉ ወዳጅ ነው፣ ኃጥእ፣ መናፍቅ፣ አማኒ ወይም ጻድቅ ሳይለይ ሁሉንም በእኩል ዐይን ይወዳል፡፡

ፍቅርን ገንዘብ አድርገን እንዳንኖር የሚገድቡ እክሎች ፡- ሰዎች በዚህ ዓለም ሲኖሩ በርካታ ችግሮች ይገጥሟቸዋል። መልካም ነገር ሠርተው በፍቅር ጸንተው እንዳይኖሩ በርካታ መሰናክሎች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ምክንያት የሚሆኑት ከሰዎች ድክመት እንጂ በእርግጥም በፍቅር ጸንተው እንዳይኖሩ ምክንያት አይደሉም። ይህን አስመልክቶ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለእኛ ብሎ በመስቀል ላይ ከዋለው ሥጋውን ከቆረሰው ደሙን ካፈሰሰው አምላክ ከክርስቶስ ፍቅር አይለዩኝም ብሎ ከጠቀሳቸው መከራ፣ ኀዘን፣ ረኀብ፣ ስደት ጥቂቶችን እንመልከት።

መከራ፡- መከራ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚደርስ ሥቃይ፣ ፈተና፣ ችግር ወዘተ ሊባል ይችላል፡፡ ይህ መከራ በብዙ መንገድ ይከሰታል፡፡ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ መከራ አለ፤ ለክብር የሚመጣ መከራ አለ፤ ይህም በመፈተናችን እግዚአብሔር ከመከራ ስለሚያወጣን የበለጠ ክብር የምናገኝበት ነው፡፡ ለትምህርት የሚመጣ መከራ አለ፤ ይህ ማለት በምንሠራው ሥራ ተመክተን የትዕቢት መንፈስ እንዳይታገለን አቅማችንን እናውቅ እንረዳ ዘንድ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቸርነት እንረዳ ዘንድ የሚመጣ መከራ አለ፤ እነርሱም፡፡

ኀዘን፡- ሰው መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ፍላጎት ያለው ፍጡር ነውና ፍላጎቱ አልሟላልህ ሲለው በተለያየ መንገድ ያዝናል፡፡ በቤተክርስቲያናች አስተምህሮ የሚገባ ኃዘን እና የማይገባ ኀዘን ተብሎ በሁለት ይከፈላል፤ የሁለቱንም ምንነት ከምሳሌ ጋር እንየው፡፡

የማይገባ ሐዘን፡- “እናት፣ አባት፣  እህት፣ ወንድም፣አክስት ጎት ወዘተ ሞተብኝ፣ ርስት ጉልት ሔደብኝ” ብሎ ማዘን አይገባም፡፡ እንደ እናት እንደ አባት አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ፣ እንደ እህት እንደ ወንድም መላእክት እንደ አክስት እንደአጎት ቅዱሳን አሉንና፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስትምር “እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ በሰማይ የምትኖር አባታችን ብላችሁ ጸልዩ” (ማቴ.፮፥፱) ብሎ ያስተማረን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለገላትያ ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ “እንኪያስ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፤ ልጆች ከሆናችሁ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡” (ገላ.፬፥፯) በማለት አስተምሯል፡፡

 እንግዲህ በሐዲስ ኪዳን እናት አባት ሞተብኝ ብለን እንዳናለቅስ እግዚአብሔር ራሱ ልጆቼ ናችሁ ብሎናል፡፡ ርስት ጉልት ሄደብን ብለን እንዳናዝንም “የእግዘአብሔር ልጆች ናችሁና የእግዚአብሔርን መንግሥት ትወርሳላችሁ” ተብለናል፡፡ ስለዚህም በዚህ ጉዳይ ማዘን አይገባም ብላ ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች፡፡ ሐዋርያው አሁንም ለኤፌሶን ሰዎች የላከውን እንጥቀስ፤ “ከእንግዲህ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም” (ኤፌ.፪፥፲፱) በማለት ለምን መጨነቅ እንዳለብን ለምን ደግሞ መጨነቅ እንደሌለብን ያስረዳል፡፡ እኛ እንደ እንስሳት በዚህ ዓለም ኖረን፤ ፈርሰን፤ በስብሰን የምንቀር ሰዎች እንዳይደለን የሰማያዊ ርስት ባለቤቶች እንደሆንን አስተማረን፡፡ ስለዚህ ለምድራዊው ርስት ጉልት ማዘን የማይገባ ኃዘን ነው፤ የሚገባ ኀዘን የተባለውን ደግሞ እንደሚከተለው ነው፡፡

የሚገባ ኃዘን፡- ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን፤ ግፍዐ ሰማዕታትን፤ የባልንጀራንም ኃጢአት እያሰቡ ማዘን ይገባል፡የስሙ ትርጓሜ “ፍሥሓ ወሐሴት” የተባለውና የጌታ ወዳጅ የሆነው ወንጌላዊው ዮሐንስ ከዕለተ ዐርብ በኋላ የኖረው እንደስሙ ሳይሆን የዕለተ ዐርቡን የጌታ ሥቃይ እየታወሰው በኀዘን ነበር፡፡ ፊቱ ሳይፈታ የኀዘን እንጂ የደስታ ስሜት ሳይታሰበው የኖረ ሐዋርያ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ማንም የእኔ ሊሆን የሚወድ መስቀሉን ይሸከም በኋላዬም ይከተለኝ” ብሎ እንዳስተማረ ይህን አብነት አድርገው ሰማዕታት ደረታቸውን ለጦር፤ እግራቸውን ለጠጠር፤ አንገታቸውን ለስለት፤ ሰውነታቸውን ለእሳት ሲገብሩ ኖረዋል፤ በጽኑዕ መከራቸውም አምላካቸውን መስለውታል፡፡ ታዲያ ይህን የሰማዕታትን መከራና ግፍ እያሰቡ ማዘን የሚገባ ኀዘን ይባላል፡፡ እንዲሁም የባልጀራን ኀዘን እያሰቡ “እባክህን እግዚአብሔር ሆይ ገሃነመ እሳትን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ባይረዳ ነውና እንዲረዳ አድርገው” እያሉ ስለ ሰዎች ኃጢአት ማዘን ወደ ንስሓ እንዲመለሱ ማልቀስ  የሚገባ ኀዘን ይባላል፡፡

የሚገባ ኃዘን ወደ ክርስቶስ ፍቅር የሚያደርሰን እንጂ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ስላልሆነ ልናስብበት እንደሚገባ አስረድቶናል፡፡ ጌታችን ክርስቶስም እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና፡፡” (ማቴ.፭፥፬) የማይገባውን ኀዘን ሳይሆን የሚገባውን ኀዘን ማዘን የሚያስመሰግን፣ በኋለኛው ዘመን የማታልፈውን መንግሥተ ሰማያት ወርሰንና ዘለዓለማዊ ደስታን ተጎናጽፈን የምንኖርበት አንደሆነ አስተማረን፡፡

ፍቅርን ገንዘብ እንዳናደርግ እንቅፋት የሚሆኑን ነገሮች

ፍርሃት፡- ፍርሃት ማንም ሰው በሕይወቱ እንዲደርስበት የማይፈልገው፣ በሕይወቱም ውስጥም እንዲከሰት የማይመኘው ነገር ነው፤ የማይፈልገውን ነገር ይደርስብኛል፣ ይመጣብኛል፣ ያጠፋኛል… ብሎ የሚጨነቀውና ውስጡ ላይ የሚፈጠረው መልካም ያልሆነ ስሜት ነው።

በእርግጥ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የሚገባ ፍርሀት አለ፤ እንዲያውም የጥበብ መጀመሪያ የተባለውም እግዚአብሔርን መፍራት ነው። ይሁን እንጂ ይህ እግዚአብሔርን መፍራት አግባብነት ያለው ሲሆን በሥጋዊው ሕይወቱም ሆነ በመንፈሳዊው ሕይወቱ እጠፋለሁ፣ እቀጣለሁ ብሎ የማይገባ ፍርሀት ግን የሚመከር አይደለም።

ወቅቱ እጅግ አስቸጋሪና ከባድ ነው። በሽታውም ቢሆን በጥበብ ለማይረዳው ሁሉ ሰውን ከሰው የሚለያይና ሀገርኛ የሆነውን የእርስ በእርስ መተሳሰብና መረዳዳት የሚያስረሳ ከነጭራሹም የሚያጠፋ ነው። ነገር ግን በቅዱስ ወንጌል “እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ” (ማቴ.፲፥፲፮) ተብሏልና በጥበብ እርስ በእርስ ተሳስበን ይህን ክፉ ዘመን ማለፍ ይኖርብናል።

ጥበበኛ መሆን ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው” (ምሳ.፩፥፯) የሚለውን መመልከት ይቻላል። በእርግጥ ሰው በሥጋዊና በመንፈሳዊ ፍላጎት መካከል ያለ አንዳንድ ጊዜ ሥጋዊ ፍላጎቱ የሚያይልበት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎቱ የሚጎላበት ፍጥረት ነው። በዚህም እግዚአብሔርን ፈርቶና አክብሮ፣ በሃይማኖት ጽንቶ በምግባር ቀንቶ ይኖራል። በሥጋዊ ፍላጎቱ ደግሞ ለሥጋዊ ምኞትና ፈቃዱ ይወጣል፤ ይወርዳል።

ምእመናን መፍራት ያለባቸውን ነገር ፈርተው፤ መፍራት ከሌለባቸው ነገር ደግሞ ተጠብቀው፤ ነገር ግን ከአላስፈላጊ ፍርሀት ወጥተው፤ ፍቅርን ገንዘብ አድርገው በዚህ ክፉ ወቅት የድርሻቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል። ፍርሀትን አግባብነት ያለውና አግባብነት የሌለው ብለን እንደተረጎምነው ሁሉ የሚገባው ፍርሀት እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው። ይህም በሃይማኖት ጸንቶ፣ በጎ ምግባር ሠርቶ እና በክርስትና ሕይወት በመኖር የሚገኝም ነው።

ነገር ግን በዘመኑ እንደተከሰተው ዓይነት በሽታ መጣ እንጠፋለን፣ ጠላት መጣ እንሰደዳለን፣ እንሞታለን ወዘተ ብሎ ክርስትናው የማያስተምረውን ተገቢ ያልሆነ ፍርሀት የሚመነጨው ግን ሰማያዊው ርስት ዘለዓለማዊ ሕይወት እንዳለ ካለማመን፣ ሕይወትን በምድር ብቻ ወስኖ ከማሰብና ከመረዳት የሚመጣ ነው።

ይህ ሲባል መጠንቀቅ አያስፈልግም ማለት አይደለም። መጠንቀቅና መፍራት የተለያዩ ናቸውና የሁለቱን ልዩነት በጥልቀት መረዳትም ያስፈልጋል።

ምእመናን መፍራት ያለባቸውን እግዚአብሔርን እየፈሩ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እያከበሩና በቤተ ክርስቲያን አባቶችም የሚተላለፋ ምክሮችን መስማት መልካም ነው። ምክርን በአግባቡ እየሰሙ ሕይወታቸውን ማትረፍ ደግሞ ፈቃደ እግዚአብሔር ሁኖ የሚመጣ ነገርም ካለ በጸጋ መቀበል ይኖርባቸዋል።

መጠራጠር፡- ፍቅርን ገንዘብ እንዳናደርግ ከሚያደርጉን ምክንያቶች መካከል ሁለተኛ ደግሞ መጠራጠር (አለማመን) ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ባለመረዳት እና ፍቅርን ገንዘብ አድርጎ በመኖር የሚገኘውን ዋጋም አምኖ አለመቀበል መጠራጠር ነው። ያም ሆነ ይህ አለማመን ከብዙ ነገር ያስቀራል። ኖኅ የጥፋት ውኃ ይመጣል ብሎ ሲሰብካቸው ያላመኑት በጥፋት ውኃ ሰጠሙ። ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በዓለም ላይ ተመላልሶ ቢያስተምራቸው አላምን ብለው በርካታ ሰዎች ጠፍተዋል።

በዘመኑ የተከሰተው በሽታ የሚያደርሰውን ጉዳት ባለመረዳትና የሚጠበቀውን ጥንቃቄ ባለመውሰድ እንዲሁም መልካም ነገሮችን ማድረግ እንደሚገባ አለመገንዘብና አለማመን እንዲሁ ሊጎዳ ይችላል። መቼም ከሰው ወደሰው ይተላለፋል የተባለው በሸታ ያለምንም መብል እና መጠጥ ብቻቸውን ወድቀው ያሉትን የጎዳና ላይ ኖዋሪዎች የበለጠ ያጠቃ ነበረ። ከበሽታው ይልቅ ግን ረኀቡ የሚያጠፋቸው በርካታ ሰዎች ባሉባት ሀገር ተቀምጠን እንዲሁ ባልሰማ ጆሮ ማለፍ ኋላ የባሰ ዋጋም ሊያስከፍል ይችላልና ምን ላድርግ ማለት ያስፈልጋል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስጦታዎች ሁሉ ለሁሉም እንዳልተሰጡ ካስረዳ በኋላ ለሁሉም የተሰጠው ስጦታ ያለው ፍቅርን ነው። (በ፩ኛ ቆሮ.፲፪፥፳፰-፴፩)  ጸጋም የተለያየ እንደሆነ እና ለሁሉም ተአምራት ማድረግ፣ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር እንዲሁም መተርጎም ወዘተ እንደማይቻል ያስረዳል። ነገር ግን ለምትበልጠው ጸጋ ትጉ፤ የምትሻለዋንም መንገድ ፈልጉ በማለትም ያስተምራል። በ፩ኛ ቆሮ.፲፫፥፩ ጀምረን ስናነብ ደግሞ ከሁሉ የምትበልጠዋ መንገድ ፍቅር እንደሆነች እንማራለን። ስለዚህ ለዓለም ሁሉ ሥጋት ከሆነው በሽታ ጠብቆ መንግሥቱን ያወርሰን ዘንድ ፍቅርን ገንዘብ አድርገን፣ የተቸገሩትን እየረዳን፣ በሃይማኖታችን ጸንተን፣ እርስ በእርሳችን ተሳስበን ልንኖር ይገባል። እግዚአብሔር በቸርነቱ የመጣብንን ቸነፈር ይመልስልን። እኛም የሕግ ሁሉ ማሠሪያ የተባለውን ፍቅርን ገንዘብ አድርገን የስሙ ቀዳሾች የመንግሥቱ ወራሾች እንዲያደርገን እግዚአብሔር ይፍቀድልን፤ አሜን።