“በመካከላችንም ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን፤ በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛም ወደ ገነት መለሰው” (ቅዱስ ኤፍሬም)

ዲያቆን ዐቢያ ሙሉቀን

አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ለማመስገን አጅግ አብዝቶ ይለምን የነበረ፤ በእመቤታችን ጥሪም “አመስግነኝ” የተባለ ታላቅ  ሰው ነበር፡፡ በድርሰቱ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ጥምቀትን፣ ምሥጢረ ቊርባንን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን፣ በአጠቃላይ ሃይማኖትን ከምግባር፣ ነገረ ድኅነትን ከነገረ ቅዱሳን ጋር አስማምቶ የደረሰና ያስተማረ ታላቅ አባት ነው፡፡ በአባቶች የተመሰለውን ምሳሌና በነቢያት የተነገረውን ትንቢት አመሥጥሮና አራቅቆ የተረጎመ ሊቅም ነው፡፡ በመሆኑ ነገረ ድኅነትን በተናገረበት ምስጋናው “በመካከላችን ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን፤በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው”የሚለውን ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ ቊጥር ፭)

የሰው ልጅ በኃጢአት ቁራኛነት ታስሮ በሚኖርበት ምድር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ፤ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶ በመልዕልተ መሰቀል ተሰቅሎ በሦስተኛው ቀን በመነሣት ነፃ አወጣው፡፡ ዳግመኛም ወደ ገነት መለሰው፤ የሰው ዘር በሙሉም ሰላምን አገኘ፡፡

ሰላም ረቂቅ ከመሆኑ የተነሣ በስሜት የሚገለጽ እንጂ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ጥንት ለሰው ልጅ ድኀነት ተስፋ የሰጠው፣ ቃል የገባው፣ በአበው ምሳሌ ያስመሰለው፣ በነቢያት ትንቢት ያናገረው ጊዜው በደረሰም ጊዜ በድንግልና ተጸንሶ፣ በድንግልና ተወልዶ፣ በግእዘ ሕፃናት ያደገው ተርቦ፣ ተጠምቶ፣ ታሞ፣ በምልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ በመስቀሉ ድኅነታችንን ሊያውጅልን፣ በሞቱ ሞታችንን ሊያጠፋልን፣ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ሊያበሥረን ነውና፤ በመስቀል ተሰቀለ፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን መሠረት በማድረግ “ወገብረ ሰላመ ማእከሌለነ፤ በመካከላችን ሰላምን አደረገ” ካለ በኋላ ሰላምን ያደረገበትን መንገድና ኃይል ሲናገርም “በመስቀሉ ወበትንሣኤሁ ቅድስት” በማለት ያስረዳል፡፡

መስቀል በብሉይ ኪዳን የወንጀለኛ መቅጫ፣ የኃጢአተኞች ማጋለጫ ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም  መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለት መንገድ ተጠቅሞበታል፡፡

ይህም በመጀመሪያ በብሉይ ኪዳን ይገለገሉበት እንደነበረው ወንጀለኛው ዲያብሎስን ቀጣበት፤ ኃጢአተኛው ዲያብሎስን አጋልጦ በአደባባይ ኃይሉን ሻረበት፤ ግዛቱን ነጠቀበት፡፡

ቀጥሎም የተጣሉትን አስታረቀበት፤ የተለያዩትን ሰበሰበበት፤ የወደቁትን አነሣበት፤ ሰላም ላጡት ሰላምን አደለበት፡፡

እርሱ በመልዕልተ መስቀል ተነግሮ የማያልቅ መከራን ተቀብሎ በእርሱ መከራ የእኛን ኃጢአት አስወገደልን፤ ሰላምንም አደለን፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቆሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን” (ኢሳ.፶፫፥፭) በማለት አስቀድሞ በመንፈስ ትንቢት የተናገረውን ይፈጸም ዘንድ እውነተኛው ሰላማችን በእርሱ መከራ የሚታወጅ ስለነበር በመስቀል ላይ ዋለ፤ ስለ እኛ ቆሰለ፤ ስለእኛም ታመመ፤ እንዲሁም እርሱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ ሞተ፤ ሆኖም ግን በመለኮቱ ለዘለዓለም ሞት ሽረት የሌለበት ሕያው አምላክ ነውና በእኛና በአባቶቻችን ላይ ለዘመናት የነገሠብንን ሞት በሞቱ ሽሮ ሰላምን አወጀልን፤ ከሞት ባርነትም ነፃ አወጣን፡፡

አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬምም “ዘዚአነ ሞተ ነሥአ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወሀበነ፤ የእኛን ሞት ለእርሱ ወስዶ የእርሱን ሕይወት ለእኛ አደለን” (ውዳሴ ማርያም) በማለት ነገረን፡፡ የበደለው መካስ ሲኖርበት የተበደለው ካሰ፤ የቀማ መመለስ ሲኖርበት የተቀማው አብዝቶ እንዲሰጥ ፍርድ በማያውቁት የአይሁድ ሸንጎ  ዘንድ ተፈረደበት፡፡

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስይስ ምእመናን በላከው መልእክቱ “በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደም ሰላምን አደረገ፤ በምድርና በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና” (ቈላ.፩፥፲፱) በማለት እንደገለጸው ሰማያውያን መላእክትን ከምድራውያን ሰዎች፣ ሰውን ከእግዚአብሔር፣ ነፍስን ከሥጋ ጋር አስታረቀና ሰላም አደረገ፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “መርሕ በፍኖት ሞገሶሙ ለጻድቃን ዝንቱ ውእቱ መስቀል ለአዳም ዘአግብኦ ውስተ ገነተ ወለፈያታዊ ኀረዮ በቅጽበት መድኃኒት ዕፀ ሕይወት ዝንቱ ውእቱ መስቀል፤ በመንገድ መሪ፣ የጻድቃን ሞገሳቸው ይህ መስቀል ነው፡፡ አዳምን ወደ ገነት ያስገባው ፈያተዊውንም በቅጽበት ለደኅንነት የጠቀሰው የጠራው መድኃኒት ዕፀ ሕይወት ይህ መስቀል ነው” ብሏል፡፡ ( መጽሐፈ ድጓ)

ከላይ ሊቁ የተናገረውን ኃይለ ቃል ስንመለከት የተነሣንበትን መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ አምልቶና አስፍቶ የሚያስረዳ ነውና እጅግ የጠለቀ ምሥጢርን እናገኝበታለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃዱ ሁኖ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ባለው መሠረት ከልጅ ልጁ ተወልዶ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ አዳምን ወደ ገነት መለሰው፡፡ ፈያታዊ ዘየማንንም በቅጽበት ወደ ንስሓ መልሶ የገነት ወራሽ አደረገው፡፡ ስለዚህ ነው “መድኃኒት ዕፀ ሕይወት ዝንቱ ውእቱ መስቀል፤ መድኃኒት ዕፀ ሕይወት ይህ መስቀል ነው” የተባለው፤ መድኃኒቱ የተዘጋጀበት መሣሪያ ነውና፡፡ የሰው ልጅ ያጣውን ሰላም ያገኘው በመስቀሉ ላይ እንደሆነ ሊቃውንትም ያስረዱሉ፡፡

ቅዱስ ያሬድ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን ያደረገው በመስቀሉና በትንሣኤው መሆኑን ሲናገር “ወገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ” ቅዱስ ያሬድ ደግሞ “ወበትንሣኤሁ ቅድስት አግበአ ለብእሲ ዳመ ውስተ ገነት፣ ለልዩ በሆነች ትንሣኤውም የሰውን ልጅ ዳግም ወደ ገነት መለሰው” ብሏል፡፡ በዚህ መሠረት ትንሣኤውን ቅድስት ወይም የተለየች ብሎ ገልጿታል፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የተለየ የሚያደርገው በገዛ ሥልጣኑ እንደሌሎች ሙታን አስነሽ ሳያስፈልገው በመነሣቱ ነው፡፡ ለጊዜው የተነሡ ሌሎች ዳግም ሞት አለባቸው፤ ትንሣኤ ዘጉባኤንም ይጠብቃሉ፤ እርሱ ግን ይህ ሁሉ የለበትምና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የተለየችና ቅድስት ተብላለች፡፡

ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ቅድስት ነፍሱ ከክብርት ሥጋው ከተለየችበት ጊዜ ጀምሮ በእርሱ ሞት ሰላማቸውን አጥተው ለነበሩት ለእነ ማርያም መግደላዊት፣ ለቅዱስ ጴጥሮስና ለቅዱስ ዮሐንስ ትንሣኤውን ገልጦ የተጨነቁትን በማረጋጋት ሰላምን አደረገ፡፡

እንዲሁ ይህቺ ቅድስትና ልዩ የሆነች ትንሣኤው ለአንድ ለሁለት ብቻ ተገልጣ የምትቀር አይደለችምና ለሐዋርያትም ገለጣት፡፡ ለሐዋርያት “እረኛውን እመታለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ”(ማቴ.፳፮፥፴፩) ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይደርስ፣ ይፈጽም ዘንድ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ሲይዙት ተበትነው ነበር፡፡ ጌታችንን “እስከሞት ድረስ አልለይህም” ያለው የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ እንኳን ዶሮ ሳይጮኽ  ሦስት ጊዜ ክዷል፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፴፫)

በመሆኑም ከሞቱ ከትሣኤው በኋላ “ክርስቶስን ያገኘ ያገኘናል፤ በክርስቶስ ላይ የደረሰ ይደርስብናል” ብለው ተሰብስበው ሳሉ በተዘጋው በር ገብቶ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፡፡ እነርሱም ከፍርሃታቸው የተነሣ ደንግጠው የሚሉትን አጥተው ነበር፤ እርሱ ግን የዘለዓለም አባት የተባለ ነውና “አይዟችሁ! መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም፤ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” በማለት ሰላማቸው ፍጹም እንዲሆን በድጋሚ አረጋጋቸው፡፡(ዮሐ.፳፥፲፱)

መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጀመሪያ ጊዜ ትንሣኤውን በገለጠበት ዕለት ከሐዋርያት አንዱ ቶማስ አልነበረምና ለእርሱም እንዳይቀርበት ሁሉም ባሉበት ዳግመኛ ተገኝቶ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ እንዲሁ ሰላሙ ዓለም እንደሚሰጣቸው አይደለምና ፍጹም የሆነውን ሰላም እንዲሁ አደላቸው፡፡ ሐዋርያው ቶማስ ሥልጣነ ክህነት የሚሰጠው፣ ምእመናንን የሚያጠምቅ፣ ሥጋ መለኮተን፣ ደመ መለኮትን ለምእመናን የሚያድል ነውና እምነቱ ፍጹም እንዲሆን “ና እይ” ተባለ፤ እየተጠራጠረ ሥጋ መለኮትን ደመ መለኮትን ማደል ስለሌለበት “እመን እንጂ አትጠራጠር” ተባለ፡፡ ይህም ዛሬም ሥጋ መለኮትን ደመ መለኮትን ለምእመናን የሚያድሉ ካህናት ከማንም በበለጠ ሁኔታ ጽኑእ እምነት እንዲኖራቸው ለማጠየቅ ነው፡፡(ዮሐ.፳፥፳፮-፳፱)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ “ሰላሜን እተውላችኋለሁ፤ የአባቴን ሰላም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም” ብሏቸው ነበር፡፡ ይህን ፍጹም ሰላም ሊያረጋግጥላቸው በተጨነቁበት እና መረጋጋት ባልቻሉበት ወቅት በተዘጋ በር ገብቶ ሰላሙን አደላቸው፡፡(ዮሐ.፲፬፥፳፯)

ይህንና የትንሣኤውን ነገር አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አርጋኖን በተባለ ድርስቱ ሲገልጽ “አነክርኬ ተኬንዎቱ ለወልደ አብ ዘኢያርኀወ ሠለስተ አናቅጸ አንቀጸ ሥጋ ድንግልናዌ በልደቱ፣ ወአንቀጸ መቃብር በትንሣኤሁ፣ ወአንቀጸ ኃዋኅው ዘአርዳኢሁ፤ ሦስት በሮችን ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት የወጣበትን የአብን ልጅ ጥበብ ሳስብ እጅግ አደንቃለሁ፤ አንዱ አንቀጸ ድንግልናዋን ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት የወጣበት ነው፤ ሁለተኛው በትንሣኤው መቃብር ሳይከፈትለት በሕቱም መቃብር መነሣቱ ነው፡፡ ሦስተኛው ደቀ መዛሙርቱ ፈርተው በዝግ ቤት ሳሉ በሩ ሳይከፈት ገብቶ የወጣበት ነው” በማለት ያስረዳል፡፡ ይህ ምሥጢር ሰላሙን ተነጥቆ የነበረው የሰው ልጅ ሰላሙን የታደለበት ነውና እጅግ ታላቅ ነው፡፡

በመሆኑም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም “ወገብረ ሰላመ ማእከሌነ በመስቀሉ ወበትንሣኤሁ ቅድስት በመስቀሉና ቅድስት በምትሆን ትንሣኤው ሰላምን አደረገ”፤ በማለት አስረዳን፡፡ ሊቁ ይቀጥልና ከሰላሙ በኋላ የታደልነውን እውነተኛ ስጦታ ሲገልጽ “አግብኦ ለብእሲ ዳግመ ውስተ ገነት፤ ዳግመኛም አዳምን ወደ ገነት አስገባው” በማለት ነፃነቱ የተመለሰለት ሰው ርስቱን ይወርስ ዘንድ ይገባዋልና ከድኅነት ከእርቅ እና ከሰላም በኋላ የሚያጣው ሀብት ንብረት መኖር የለበትምና ዳግመኛ ወደ ገነት አስገባው በማለት ያስረዳል፡፡

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በመስቀሉ ሞታችንን አራቀለን፤ በልዩ ትንሣኤውም ትንሣኤያችንን አወጀልን፤ እርሱ ሞቶ እኛን ከሞት አዳነን፤ ከእንግዲህ በኋላ በትንሣኤ ዘጉባኤ ስንነሣ አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱሳን ባለሟሎቹ ጋር በቀኙ ለመቆም ያበቃን ዘንድ ዛሬ በትንሣኤ ልቡና ተነሥተን ቅዱስ ሥጋውን እየበላን ክቡር ደሙን እየጠጣን በቤቱ ፀንተን እንድንኖር የእርሱ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡