‹‹እግዚአብሔር ከእኛ በላይ ለእኛ ያውቃል›› (ሮሜ ፷፥፳፯)

መምህር ምትኩ አበራ

የካቲት ፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ሰዎች በሕይወት ዘመናችን ውስጥ በሁለት ነገሮች ታጥረን እንጸልያለን፤ እንሠራለን፤ እንኖራለን፡፡ ሁለቱ ነገሮችም እኛ የምንፈልጋቸውና የሚያስፈልጉን ናቸው፡፡ እነርሱንም ይዘን ከእግዚአብሔር ፊት በመቆም የሚያስፈልገንን ነገር እንጠይቀዋለን፡፡ ነገር ግን የፈለግነውን ወይም የጠየቅነውን ሁሉ ሳይሆን የሚያስፈልገንን አምላካችን ለእኛ ያደርግልናል፤ ወይም ይሰጠናል፡፡

እግዚአብሔር ሁሉንም መስጠት፤ የፈለግነውን፣ የጠየቅነውን፣ ያሰብነውን ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡ ይህ የባሕርዩው ነው፤ ሆኖም ግን ለልጆቹ የሚሰጠው የጠየቅነውን ሳይሆን የሚያስገልንን ብቻ ነው፡፡ እርሱ ከእኛ በላይ ለእኛ የሚያስፈልገንን ያውቃልና፡፡ (ሮሜ ፷፥፳፯)

አብዛኛውን ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ግጭት እንፈጥራለን፤ እናኮርፋለን፤ እንጠራጠራለን፤ ጸሎታችንንም እንደማይሰማን በማሰብ በሌሎች ሰዎች ጸሎት መታስብን እንመርጣለን፤ ይህም ተስፋ የመቁረጥ ውጤት ነው፡፡

በምድራዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚያስፈልጉን ነገሮች በዘመናት ተለዋዋጭ የሆኑና እንደ ዕድገታችን የሚወሰኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፴፰ ቁጥር ጫማ ያደርግ የነበረ ሰው ሁሌ ተመሳሳይ ጫማ ሊያደርግ አይችልም፤ ምክንያቱም ዕድሜው በጨመረ ቁጥር የእግሩ መጠን እያደገ ስለሚሄድ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩም በተፈጥሮም ሆነ በዕውቀት እየተቀየርን ስንሄድ ስጦታውም በዚያው ልክ ይሆናል፡፡ በዕለተ ሰኞ የሚያስፈልገንን ማክሰኞ አይሰጠንም፡፡ በዚህ ምክንያት ግን ግጭቶች ይፈጠራሉ፡፡

እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ እናንሣ፤ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም አባ ይትባረክ የተባሉ ታላቅ አባት ነበሩ፡፡ እርሳቸውም እግዚአብሔርን ስለ ሁለት ነገር እንዲያመሰግኑት ይናገሩ ነበር፡፡ ‹‹የመጀመሪያው የለመንኩት ሁሉ ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ፤ ሁለተኛው የለምኩትን ሁሉ ስላልሰጠኝ እና ስለከለከለኝም አመሰግነዋለሁ፡፡ የለመኑትን ስለሰተጦት ማመስግን ደንብ ነው፤ ግን የለመኑትን ስላልሰጦት ለምን ያመሰግኑታል? ተብዬ ብጠየቅ የከለከለኝ ስለማይጠቅመኝና ስለማያስፈልገኝ እንጂ ነፍጎኝ ወይም ሰስቶ አይደለም፤ይሄን አምናለሁ፡፡››

የእግዚአብሔር ሥራ ድንቅ ነው፤ የሚያስፈልገንን ነገር በጊዜው ይሰጠናል፤ በዘወትር የኪዳን ጸሎት ላይ አንድ ቃል አለ፤ ‹‹የምትለውን ሰውነት ቸል የማይል፣ ከኅሊና አስቀድሞ ሁሉን የሚያውቅ፣ የሚደረገውን ሐሳብ ከመደረጉ አስቀድሞ የሚያውቅ እና የሚመረምር ሳንለምነው የምንሻውን ዐውቆ የሚሰጥ፣ ሳንጠራጠር የምንለምነውን የሚሰማን እግዚአብሔር ነው፡፡››

እግዚአብሔር ሳንጠራጠር የምንለምነውንና የሚያስፈልገንን የሚሰጥ አምላክ ነው፤ ‹‹ለምኑ ይሰጣችኋል›› እንዲል፤ እናት ልጇ ጡት እየጠባ እሳት ቢመለከት ስለሚያብለጨልጭ ብቻ ጡቷን ትቶ እሳቱን መያዝ ይፈልጋል፡፡ እናት ግን የፈለገውን ቢያደርግ እንደሚቃጠል ስለምታውቅ እሳቱን እንዳይዝ ትከለክለዋለች፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደ ደግ እናት ነው፡፡ ሕፃኑ ጡት መጥባት ትቶ በሚያለቅስበት ጊዜ ወይም ከእናቱ እቅፍ ወርዶ እየተንፈራፈር እሳቱን እንድትሰጠው ቢለምናት ሳትሰጠው ስትቀር ጎረቤቶች ይሰበሰባሉ፡፡ እናትንም በሚጠይቋት ጊዜ ከልክላው እንደሆነ ስትነግራቸው ከእርሷ ጋር በመስማማት ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ እንጂ ‹‹ታዲያ ስጪዋ፤  ቢበዛ መቃጠል ነው፤ ከዚያም ይታከማል››  አይሉም፡፡ (ማቴ.፯፥፯)

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን ሲያስረዱ እናት የእግዚአብሔር ተምሳሌት ናት፤ የሕፃኑ ምሳሌ እኛ ስንሆን ጎረቤቶቹ ደግሞ መላእክት ናቸው፡፡ እኛ የሚያስፈልገንን ትተን የምንፈልገውን ልንይዝ ስንል እንድንተው በሚነግረን ሰዓት እንነጫነጫለን፡፡ ያን ጊዜ ምን እንደሆንን ለማወቅ አማላጆቻችን መላእክት ይመጣሉ፤ እሳቱን ለመያዝ እንደፈልግን ሲያውቁ ዝም ብለው ይመለሳሉ እንጂ እንዲሰጥን አያማልዱንም፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ የጠየቅነውን ሁሉ መስጠት ይችላል፤ ነገር ግን እርሱ ከእኛ በላይ ስለሚያውቅ የሚያስፈልገንን ብቻ ያደርግልናል፡፡ በአካል፣ በአእምሮ፣ በዕውቀት፣ በቦታ እንዲሁም በጊዜም የተወሰኑ ስጦታዎችን ይሰጠናል፡፡ የመንፈሳዊ ዕድገት ደረጃችን የሚወስናቸው ስጦታዎችን በየጊዜው ይለግሰናል፡፡ እነዚህን ስጦታ ለማግኘት ግን ሁለት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው፤ የመጀመሪያው ሳንጠራጠር መለመን ወይም መጸለይ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደሚሰማን በሙሉ ልባችን በማመን መጸለይ ይጠበቅብናል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጸሎት ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ስለዚህ እላችኋለሁ! የጸለያችሁትን የለመናችሁትን ሁሉ እንዳገኝችሁት እመኑ፤›› ጸልየን እስክንቀበል መጠበቅ ሳይሆን እንዳገኘነው ማመን እንደሚገባ ከዚህ ኃይለ ቃል እንረዳለን፡፡ (ማር.፲፩፥፳፬)

ሁለተኛው ደግሞ የምንሻውን ሳይሆን የሚያሻንን ወይም የምንፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልገንን ዐውቀን ስንጠይቀው ወይም ስንለምነው የሚሰጠን መሆኑ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ወጣቶች ስለማያስጨንቅ ነገር በማስብ የማያስፈልጋውን ነገር ይጠይቃሉ፤ ለምሳሌ የዘጠነኛ ክፍል ሆነው ስለሚያገቡት ሚስት ይጨነቃሉ፤ ግን ስለእርሱ የመጨነቂያ ጊዜ ባለመሆኑ የማያስፈልጋቸውን ነገር አምላክ ሊመምኑ ይችላሉ፤ ስለዚህ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አያገኝም፡፡

በማቴዎስ ወንጌል ‹‹ሳትለምኑት የሰማይ አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል፤›› እንደተባለው እርሱ የፈቀደውን እንዲያደርግልንና የፈቀደልንን ሕይወት እንዲሰጠን መለመን የተሻለ ነው፡፡ በዘወትር ጸሎታችን ላይ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ›› ብለን የምንጸልየው ሁል ጊዜ የዕለት እንጀራችንን እንዲሰጠን እንድለምነው ጌታችን ኢየሱስ አስተምሮናል፡፡ (የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፲፩፥፪-፬፣ማቴ.፮፥፰) መግቦቱ አያቋርጥም የተባለውም ስለዚህ ነው፤ በአቅማችን፣ በዕድሜያችን፣ በዕውቀታችን፣ በኑሮአቻን ልክ ይሰጠናል፡፡

ለዚህ ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት፤ ‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ።›› ይህ መልእክት ለእስራኤል ሕዝብ የተነገረው ለፈተና ነው፤ አምላክ ሰዎችን የሚፈትነው ለበጎ ነውና፡፡(ዘፀ.፲፮፥፬)

ከዚያም ‹‹እንዲህም ይሆናል በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን አለው።›› ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ ‹‹እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይልቀም በድኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ጎሞር ውሰዱ።›› ሙሴም፦ ማንም ከእርሱ አንዳች ለነገ አያስቀር አላቸው። ነገር ግን ሙሴን አልሰሙትም፤›› የሕዝቡ ትኩረት የሚስፈልጋቸው ሳይሆን የሚፈልጉት ላይ ብቻ ስለነበረ ‹‹አንዳንድ ሰዎችም ከእርሱ ለነገ አስቀሩ፥ እርሱም ተላ፤ ሸተተም፤ ሙሴም ተቈጣቸው።›› (ዘፀ.፲፮፥፭፣፲፮-፳) የብዙ ሰዎች ሕይወት እንደዚህ የሚሆንብት አጋጣሚ አለ፡፡ ስለዚህ የዕለት ጉርሻችንን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን፣ ዕድሜያችንን፣ ጊዜያችንን፣ ሰውነታችንን ላላማባከን መጠንቀቅና መጣር አለብን፡፡

ሁለተኛው ምሳሌ የአባ ዳንኤል ታሪክ ነው፡፡  ቅዱስ ዕውነተኛ ንጹሕ ፍጹም ነው፤ ይህም ቅዱስ ስሙ አውሎጊስ የሚባለውን ሰው አየው፤ ይህም አውሎጊስ የወፍጮ ድንጋይ እየወቀረ ለግርሽ እየሸጠ ሁል ጊዜ በመጠኑ እየተመገበ ድኆችንና ጦም አዳሪዎችን ይመግባቸዋል የተረፈውንም ፍርፋሪ ለውሾች ይጥላል፤ ለነገ ብሎ ምንም አያሳድርም።

አባ ዳንኤልም ይህን መልካም ሥራውን አይቶ በርሱ ደስ አለው፤ እጅግም አማረው፤ ለአውሎጊስም የዚህን ዓለም ብልጽግና እንዲሰጠውና ለድኆች የሚመጸውተው እንዲጨመርለት ወደ እግዚአብሔር ለመነ።

ለአውሎጊስም ዋስ ሆነው የሚወቅረውንም ደንጊያ ሲፈነቅል በሸክላ ዕቃ የተደፈነ ወርቅን አገኘ፤ ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ ሒዶ የንጉሥ የሠራዊት አለቃ ሆኖ ተሾመበት የሚሠራውንም የቀደመ በጎ ሥራውን ተወ። አባ ዳንኤልም ስለርሱ ሰምቶ ወደርሱ በሔደ ጊዜ የንጉሥ ሠራዊት አለቃ ሆኖ በፈረስ ላይም ተቀምጦ ብዙ ሠራዊት አጅቦት እርሱም በትዕቢት ተመልቶ የቀድሞ በጎ ሥራውንና ለድኃ መመጽወቱንም ትቶ አገኘው።

አባ ዳንኤልም አይቶ አዘነ፤ ስለእርሱ በመለመኑም ተጸጸተ። ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ እንደ መጣ አባ ዳንኤልንም እንዲሰቅሉት ሲያዝ የአውሎጊስንም ነፍስ ከእርሱ እንዲሹ በእርሱ ምክንያት ጠፍቷልና የከበረች ድንግል እመቤታችን ማርያምም የክብር ባለቤት ጌታችንን ልጅዋ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ አባ ዳንኤል እንደ ለመነችው፤ በሌሊት ራእይ አባ ዳንኤል ራሱ አየ።

በነቃም ጊዜ ደነገጠ፤ አውሎጊስንም ወደ ቀድሞ ሥራው ይመልሰው ዘንድ በጸሎትና በምሕላ በመትጋት ወደ እግዚአብሔር እየለመነ ግብር ገባ ሱባኤ ያዘ።

ከዚህ በኋላም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለት፤ በፍጥረቱ ላይ በሚያደርገው በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ለመግባት በመድፈሩ ገሠጸው። በዚያንም ወቅት አውሎጊስን የሾመው ንጉሥ ሞተ ሌላ ንጉሥም ነገሠ፤ በአውሎጊስም ላይ ተነሥቶ ገንዘቡን ሁሉ ወረሰ። ደግሞም ሊገድለው ፈለገው፤ አውሎጊስም ነፍሱን ለማዳን ከንጉሡ ሸሽቶ ወደ ሀገሩ ደረሰ፤ እንደ ቀድሞውም ደንጊያ ይወቅር ጀመረ፤ አባ ዳንኤልም ወደርሱ ተመልሶ ስለርሱ ያየውን ሁሉ ስለ ርሱም እንደሰቀሉትና ነፍሱንም ከእርሱ እንደፈለጉ ነገረው። በዚህ በአባ ዳንኤልም የትንቢት መንፈስ አድሮበት ነበር፤ ከእርሱም ብዙዎች ታላላቅ ታአምራት ተገለጡ። (መጽሐፈ ስንክሳር ግንቦት ፰)

ስለዚህም እግዚአብሔር የሚያስፈልግንን ስንጠይቅ ብቻ እንደሚሰማን ልንረዳና በዚያም መሠረት ጸሎታችንን ወይም ልመናችንን ልናደርግ ይገባል፡፡ አምላካችንም እንደሚሰማን ማወቅም ያስፈልጋል፡፡