የነነዌ ጾም

የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ነነዌ የሜሶፖታምያ ከተሞች ከሆኑት መካከል አንዷ ናት፡፡ ከሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ ፫፻፶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደ ነበረች በታረክ ይነገራል፡፡ በ፵፻ (ዐራት ሺህ)  ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በናምሩድ በኩል ከተቆረቆረችም በኋላ በ፲፻፬፻ (አንድ ሺህ ዐራት መቶ) ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የአሦራውያን ዋና ከተማ ሆናለች፡፡ (ዘፍ.፲፥፲፩፣፪ነገ.፲፱፥፴፮)

በከተማዋም ታዋቂ የነበረ አስታሮት የተባለ የጣዖት ቤተ ነበረ፡፡ በዚህች ከተማ የሚኖሩት ሰዎች የሚሠሩት ክፋትና ኃጢአት እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ጽዋው ሞልቶ መጥፊያቸው ስለ ደረሰ ለፍጥረቱ ርኅራኄ ያለው እግዚአብሔር ግን ንስሓ ይገቡ ዘንድ ነቢዩ ዮናስን ልኮላቸዋል፡፡ ይህ ነቢይ ከአሕዛብ ወደ አሕዛብ ወደ ንስሓ ይጠራቸው ዘንድ ነበር የተላከ ነው፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ወደዚያች ከተማ እንዲሄድ በእግዚአብሔር ቢታዘዝም ወደ ተርሴስ ሲኮበልል እንመለከተዋለን፡፡

ቅዱስ ጄሮም ነቢዩ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲናገር፡- ‹‹ዮናስ አሕዛብን ከመጥላቱ የተነሣ ሳይሆን መዳን ከእስራኤል እየራቀ መሆኑን በትንቢት መነጽር ሲመለከት ወደ ነነዌ አልሄድም አለ፡፡›› ይኸውም ሙሴ ይህን ሕዝብ ከምታጠፋው እኔን ከሕይወት መጽሐፍህ ደምስሰኝ ያለው ዓይነት ነበር፡፡ (ዘፀ.፴፪፥፴፩-፴፪) ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ስለ እነርሱ እርሱ ቢረገም እንደሚመርጥ እንደሰማነው›› ብሏል፡፡ (ሮሜ ፱፥፫)

በእርግጥም በዘመነ ሐዲስ አሕዛብ በክርስቶስ አምነው ሲጠመቁ እስራኤል ግን መጻሕፍትን ብቻ ይዘው ቀርተዋል፤ እስራኤል ነቢያትን ብቻ ይዘው ሲቀሩ አሕዛብ ግን የነቢያቱን የትንቢት ፍጻሜ ይዘዋል፡፡ (ማቴ.፲፪፥፵፪)

ልብና ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ አምላክ ግን ዮናስ ላለመታዘዝ ብሎ እንዳላደረገው ስላወቀ በልዩ ጥበቡ ሲወስደው እናያለን፡፡ አስቀድሞ ታላቅ ነፋስን በመርከቢቱ ላይ አመጣ፤ ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ቀጥሎም ዓሣው በየብስ እንዲተፋው አደረገ፡፡ ዮናስ ወደዚያች ከተማ ከደረሰ በኋላ ግን ምንም እንኳን የሦስት ቀን መንገድ ዙሮ መስበክ ቢጠበቅበትም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም፤ ‹‹በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች›› አለ።

የነነዌም ሰዎችም እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። አዋጅም አስነገረ፥ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፥ እንዲህም አለ፡- ‹‹ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም፤ ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?›› (ዮና.፫፥፰-፱)

እግዚአብሔር አምላክም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም። በእርግጥም እግዚአብሔርን የሚፈራ ልቡና የትምህርት ጋጋታ አያስፈልገውም፤ የቀናት ብዛት አያስፈልገውም፡፡ እኛ ክርስቲያኖችም ይህን በማዘከር ‹‹ንስሓ ብንገባ እንደ ነነዌ ሰዎች ከተቃጣው ማንኛውም መቅሠፍት እንድናለን›› በማለት በየዓመቱ ከዓብይ ጾም መግቢያ ሁለት ሳምንት አስቀድማ ካለችው ሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ ‹‹ጾመ ነነዌ›› በማለት እንጾማታለን፡፡ ዘንድሮም ዓብይ ጾም የካቲት ፳፩ ስለሚገባ የፊታችን ሰኞ የካቲት ሰባት እስከ ረቡዕ የካቲት ዘጠኝ እንጾማለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ጾማችንን ይቀበለን፤ አሜን!!

ምንጭ፤ ሉማሜ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን