‹‹እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱ ከሆነ ግን እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ›› (ገላ.፭፥፲፭)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እርስ በርሳችሁ የምትነካሱ ከሆነ ግን፥ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ›› ብሎ በገላትያ ምእመናን በኩል እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሡ ክርስቲያኖች የሚሰማም ቢሆን ለዓለም ሁሉ በፍቅርና መገለጫው በሆነው መተሳሰብ አንድ እንዲሆኑ አስተምሯል፤ ይህ ባይሆን ግን መጠፋፋት እንደሚመጣ በኃይለ ቃሉ አስጠንቅቋል፡፡ (ገላ.፭፥፲፭)

በዓለም እንዲሁም በቅዱሳት መጻሕፍት ታሪክ የሕዝብ መጠፋፋት አያሌ ጊዜያት ተከስቶዋል፡፡ የመጠፋፋቱ መንሥኤም ልዩነቶች ሳይሆኑ ልዩነቶችን ዓለም የተቀበለበትና የተረዳበት መንገድ ነው፡፡ የቋንቋ፣ የባህልና የሐሳብ ልዩነቶች በአግባቡ ከተያዙ ጌጦች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንጻሩም ልዩነቶችን መሠረት አድርገን የምናበጃቸው መደቦችና የምንፈጥራቸው አሉታዊ አስተሳሰቦች መለያየትን ወልደው መጥፊያዎቻችን ሊሆኑ  ይችላሉ፡፡ ልዩነቶች የዕውቀት ምንጮች መለያየት ደግሞ የጥፋት ሁሉ መነሻ ነውና፡፡ በወንጌል እንደተነገረን እርስ በእርሱ የሚለያይ ሕዝብም ሆነ መንግሥት ጸንቶ አይቆምም፤ ይጠፋልም፡፡ በመሆኑም እንደ ባለ አእምሮ በማስተዋል መለያየትን እንድናስወግድ፣ መለያየትንም የሚፈጥሩትን ሰዎች ደግሞ እንድንጠነቀቅ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በተማጽኖም ጭምር አስተምረውናል፤ መክረውናልም፡፡ (ገላ.፭፥፲፭ማቴ. ፲፪፥፳፭፣ ሮሜ. ፲፮፥፲፯)

መለያየት ሥር የሰደደ የሥጋ ምኞትና ፈቃድ ውጤት ነው፡፡ ሰይጣን እርስ በእርሱ ባይለያይም ሰዎች ግን ተስማምተው በአንድነት እንዳይኖሩ እንቅፋት ይሆናል፤ በመካከላችንም ልዩነትን ያበዛል፡፡ በሀገራችን መለያየቱ ሥር ሰድዶ እርስ በርስ ወደ መገዳደል ደረጃ መድረሱ ምን ያህል መንፈሰ ቅዱስ እንደራቀንና ክፉ በሆነ የሥጋና የሰይጣን መንፈስ እንደተከበብን ያሳየናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ አንድነትን የምታስተምርና የምትደግፍ በመሆኗ መለያየትን እጅግ አድርጋ ታወግዛለች፡፡ ልጆችዋም የቋንቋ፣ የሰውነት ቆዳ ቀለም እንዲሁም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ቢኖራቸው እንኳን ልዩነቶቹን አገናዝበው መኖር እንደሚገባቸው በጽኑዕ ታስተምራለች፡፡ (ገላ. ፭፥፲፱)

ከዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል የመጡ ቅዱሳን ሐዋርያት ለወንጌል ዓላማ በአንድነትና በመተባበር ለመቆም አልተቸገሩም፡፡ የነገድ ልዩነታቸው መለያየትን አላነገሠባቸውም፡፡ አንዲት ቤተክርስቲያን በለኮሰችው የወንጌል ችቦ ሕዝብና አሕዛብን አንድ አድርጋለች፡፡ የሎሌና ጌታ መደብን ሳይቀር በወንጌል መዶሻነት አፍርሳ የአንድነትን መደላደል ፈጥራለች፡፡ ይኸውም ከክርስቶስ የተሰጣት ተልዕኮዋና የቆመችለት የወንጌል ዓላማ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በባሕርይዋ ኩላዊት በመሆኗ ዓለም ዓቀፋዊት ናት፡፡ ስለ ዘመኗ ሲነገር እንኳን ዕድሜዋ የሚቆጠረው ከዓለመ መላእክት ነው፡፡ ከዓለመ መላእክት የምትቆጠር ቤተ ክርስቲያንን የመለያየት መራኮቻ ማድረግ ጠባይዋን አለማወቅ ነው፡፡ እጅግ ሰፊ የተራቀቀና ምጡቅ የሆነ የነገረ መለኮት ትንታኔ የሚሰጥበት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚያስተምረንም የሰዎችን ከቅዱሳን መላእክት ጋር በምስጋናና መንፈሳዊ ሐሴት በተሞላበት ቅዳሴ በአንድነት መቆምን ነው፡፡ በጌታችን ልደት ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳን መላእክትም ጋር ሳይቀር አንድ እንደሆነች በታወቀ ነገር ተገልጧልና፡፡ (ሉቃ. ፪፥፲-፲፮፣ የሐዋ. ፲፥፴፬-፴፭፣ ፲፥፵፭፣ የሐዋ. ፲፩፥፩፣ ገላ. ፫፥፳፰፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ. ፳፮)

የመጠላላትና የመነካከስ መሠረት መለያየት ነው፡፡ መገዳደልና መጠፋፋት ደግሞ የመለያየት ዋና ባሕርያት ናቸው፡፡ መለያየት ካለ ልማትና ዕድገት በምንም መንገድ ሊኖሩ አይችሉም፡፡ እንኳን ልማትና ዕድገት በሰላም ውሎ ማደርም የሚታሰብ አይደለም፡፡ መለያየት ካልጠፋ  በሐሳብ የመበልጸጋችን ምክንያት ሊሆን የሚችለው የቋንቋ ልዩነታችን እንኳን ጥላቻን ይወልዳል፤ አንዳችን የሌላችንን ቋንቋ በሰማን ቁጥርም ውስጣችን በጥላቻ ይሞላል፡፡

ዓለም አንድ መንደር ለመገንባት የሚያደርገውን ሩጫ ባፋጠነበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በችግሮቻችን የተነሣ መለያየታችን እየባሰ በመሆኑ ሥቃያችን፣ ሞታችን፣ ስደታችንና መከራችን እየበዛ ነው፡፡ የመለያየቱ ጡዘት ሞትን እንጂ ሕይወትን፣ ማጣትን እንጂ ማግኘትን፣ ውርደትን እንጂ ክብርን አላመጣልንም፡፡ በመለያየት የዓለም ጅራት እንጂ ራስ አልሆንም፡፡ መለያየት ኋላ ቀርነትን እንጂ በረከትን ይዞልን አልመጣም፡፡ በመገዳደል ጠላትን ማሸነፍ   ወይንም ድል ማድረግ አይቻልም፡፡ በመጻሕፍት እንደተማርነው ገድለው የወረሱ በጊዜ ሂደት ውስጥ ተገድለው ተወርሰዋል፡፡ ቆም ብለን ማስተዋል እስካልቻልን ድረስ ወደ ፊትም ይህ እውነት ይቀጥላል፤ አይቆምም፡፡

መነካከሳችን ለምን?

ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሣሡ አንቂ ንግግሮች፣ ጽሑፎችና ዲስኩሮች

አብዛኛዎቹ ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሰዎች በየመገናኛ ብዙኃኑ የሚናገሯቸው ንግግሮች፣ የሚጽፏቸው ጽሑፎችና በጉዳዮች ላይ የሚሰነዝሯቸው ሐሳቦች ከመተባበር ይልቅ የሚያገፋፉ፤ ከማሰባሰብ ይልቅ የሚበታትኑ፤ ከሰላም ይልቅ የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ‹‹ተነሥ! በለው! ቁረጠው! ፍለጠው›› የሚሉ መልእክቶችን ያዘሉ ናቸው፡፡ ያለውም ሆነ መጪው ትውልድ የሚጠቀምበት በአንድነት ተባብሮ የምጣኔ ሀብት ድኅነቱን የሚያሸንፍበት፣ የአስተሳሰብ መዛነፉን የሚያስተካክልበት፣ እንደ ቀደመ አኗኗሩ  በብዝኃነት ውስጥ ልዩነቶቹን አገነዛዝቦ በሰላም የሚኖርበትን ገንቢና ጠቃሚ ሐሳብ ከማመንጨት ይልቅ የሆነውን አባብሰው ያልሆነን ነገር አጋንነውና ፈጥረው በመጻፍ በመናገር ትውልዱን ለዚህ መነካከስና መበላላት አብቅተውታል፡፡ ‹‹ምላስም እሳት ነው፡፡ እነሆ፥ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ  ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት፤ ሥጋችንንን ትበላዋለች፤ ውስጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች፤ ከገሃነም ይልቅ ታቃጥላለች›› የሚለውን የቅዱስ ያዕቆብ መልእክትም ከማናቸውም ጊዜ በላይ እንድናጤነው አድርጎናል፡፡ (ያዕ. ፫፥፮)

በቅዱስ ያዕቆብ ቃል መሠረት ከአንደበት በማናቸውም ሁኔታ የሚወጡ አሳዳፊ አቃጣይና የዓመፅ ንግግሮች ሰሚዎቹ ካልተጠነቀቁበት ራሳቸውንም ጭምር ወዳልተረዱትና ኑሯቸውንም ወደሚያመሰቃቅል ሁኔታ ይወስዳቸዋል፡፡ ክፉ ሐሳቦችን ለሚያመነጩ ሰዎች እንደ መልካም መደላደል የሆናቸውም የብዙኃኑ አድማጭ ጆሮና ልብ አመዛዛኝ አለመሆኑ ነው፡፡ የሚነገሩ ንግግሮችን የሚጻፉ ጽሑፎችና የሚሰጡ አስተያየቶችን ለምን እንዴት ብሎ የሚጠይቅ ማግኘት ዛሬ አስቸጋሪ ሆኖዋል፡፡ ምክንያታዊነትና ማመዛዘን ርቀውናል፡፡ ከምናደንቃቸውና በሰብእናቸው ከተማረክንባቸው ሰዎች የሚወጡ ሐሳቦችን እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ አድርገን ስለምንቆጥር ግደሉ ካሉን እንገድላለን፤ አጥፉ ካሉን እናጠፋለን፤ አፍርሱ ካሉን እናፈርሳለን ‹‹ትዳራችሁን በትኑ›› ካሉን ሳናቅማማ እንበትናለን፡፡ ገድሎ መገደል፣ ጠፍቶ መጥፋት፣ አፍርሶ መፍረስ፣ በትኖ መበታተን እንደነበረና እንዳለ ማስተዋል ግን አልቻልንም፤ ‹‹ሰው የሚዘራውን ያጭዳልና›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች የሚያደርጉት አንቂ ንግግር እርስ በእርሳችን እንድንተናነቅ አደረገን እንጂ ተቀራርበን እንድንነጋገር፣ የሀሳብ ልዩነቶቻችንን ከተቻለ አንድ ልናደርጋቸው፣ ካልቻልንም አገነዝበናቸው እንድንጓዝ አላደረገንም፡፡ እንደ ሐሳብ መሪና አንቂ ሕዝብን ለልማት፣ ለዕድገት፣ ለመተሳሰብና ለመሳሰሉት ገንቢ ዕሤቶች ሊያስተባብሩ የሚችሉ ሀሳቦችን አመንጭቶ ወደ ሕዝብ ማድረስ እግዚአብሔርም የሚወደው፣ ሰውም የሚጠቀምበት ሀገርም የሚያድግበት ነበር፡፡ (ገላ.፮፥፯)

ነገር ግን በሀገራችን እየሆነ ያለው የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የማኅበረሰብ አንቂዎች ሳይፈጠሩ ተከባብሮ፣ ልዩነቶቹን አገናዝቦ፣ የወገኑን ሞት በዕድር፣  የምጣኔ ሀብት ችግሩን በዕቁብ አሰባስቦ ሲያሸንፍ የነበረ ሕዝብ አንቂዎቹ ሲበዙ መከባበሩ፣ መዋደዱ፣ መጠያየቁና በሐዘንና በደስታ ጊዜ አብሮነቱ ቀረ፡፡ በአንድነት በመሆን ራሱንና ሀገሩንም ከጠላቶቹ ንክሻ ሲከላከል የነበረ ሕዝብ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦችን ባነገቡ ግለሰቦችና ቡድኖች እርስ በእርሱ መነካከስ አበዛ፡፡ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ወደማስተዋል ካልመጣና በ አንቂዎች የሚነገሩ ነገሮችን መመርመር ካልቻለ መበላላቱ ይቀጥላል፡፡ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል›› ተብሎ እንደተነገረው  ታዋቂ የተባሉ ግለሰቦችና ቡድኖችም ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ በመሆናቸው ንግግሮቻቸውን አደብ እስካላስያዙት ድረስ የእግዚአብሔር ቁጣ በእነርሱ ላይ ይበረታል፡፡ በሥጋም በነፍስም ጥፋትን ያመጣባቸዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል እንደተናገረው ከአንደበታችን በሚወጣ ቃል እንጸድቃለን፤ እንኮነናለንም፡፡ ዛሬ ለምንናገረው ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን የሚጠይቀን አምላክ አለና፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስም  ‹‹ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው!›› ተብሎ ተጽፎዋል፡፡ (ሆሴ. ፬፥፲፬፣ ማቴ. ፲፪፥፴፮፣ ኢሳ. ፲፥፩)

ቂም የወለደው በቀል

መበቀል በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ላይ ልቀመጥ ማለት ነው፡፡ ዘጠና ከመቶ በላይ የሆነው ሕዝብ አማኝ ነው በሚባልበት ሀገር ‹‹አትበቀል፤ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንድራስህ ውደድ›› እንዲሁም ‹‹ወንድሞቻችን፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ቁጣን አሳልፏት፤ እኔ እበቀላለሁ፤ እኔ ብድራቱን እከፍላለሁ ይላል እግዚአብሔር›› የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ተረስቷል፡፡ በሆነውም ባልሆነውም ነገር እየተነሣን በቂም ሰክረን እንበቀላለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔርን እንበድላለን፤ እናሳዝናለንም፡፡ የሰዎችንም ኑሮ እናቃውሳለን፡፡ ትናንት ላይ ቆመን በመቅረታችን ምክንያት ዛሬ የምናጠፋው ወገን ጊዜውን ጠብቆና ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርለት የእኛ የሆነውን ያጠፋል፤ ይበቀላልም፡፡ በበቀል ስሜት ሆነን ደሙን አፍስሰን ኑሮውን ያቃወስንበት ማኅበረሰብ እርሱም በተራው እንዲሁ ያደርግብናል፡፡ እንዲሁ በበቀልና በቂም ምክንያት ተራ በተራ እንደተገዳደልን ምጽአት ሊደርስ ይችላል፡፡ (ዘሌ. ፲፱፥፲፰፣ ሮሜ ፲፪፥፲፱)

በቀደመው ታሪክ አባቶቻችን በመተባበር ቆመው ያሸነፏቸውና በመጡበት የመለሷቸው የውጭ ኃይሎች በፈጠሩልን የገዳይ ተገዳይ፣ የአሳዳጅ ተሳዳጅ፣ የጨቋኝ ተጨቋኝ፣ የመጤ ነዋሪ ትርክትና ድርሰት ታውረን እርስ በርሳችን መነካከስ ከያዝን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አንዳችን የሌላችን ጋሻ እንዳልነበርንና በአንድነት ቆመን ወራሪ ጠላትን እንዳልመከትን በተፈጠረልንና በተራገበልን የፈጠራ ድርሰትና ትርክት በሥጋት መተያየት ጀመርን፡፡ እንደ አማኝ ‹‹እኔ እበቀላለሁ፤ እኔ ብድራቱን እከፍላለሁ›› ብሎ የተናገረውን የአምላካችንን ቃል ብንሰማ በልባችን ብናኖረውም ችግሮች ከነበሩ እንኳን በክፋት ሳይሆን በበጎ አስተሳሰብና ምግባር ብንፈታቸውና ከትናንትና ማንነታችን ጋር ብንታረቅ ኖሮ የቂማችን ቋጠሮ ለወለደው በቀልና መበላላት ባልበቃን ነበር፡፡

በቀል ካለ ደም ማፍሰስ፣ መገዳደል፣ መፈነቃቀል፣ የሥርዓተ ማኅበር ቀውስ፣ ኋላ መቅረት ይኖራሉ፡፡ በሰነድና በሌሎች ማስረጃዎች የተረጋገጠ፣ በስማ በለው ያልተነገረ ግፍ፣ በሂሮሺማ ናጋሳኪ ዜጎቿ ላይ የተፈጸመባት ጃፓንና ግፍ ሠሪዋ ሀገር አሜሪካ ያን ጥፋት ያስከተለ ቂምና በቀል የሚወልድ ክስተት ትተው ዛሬ በመተባበር ቆመው መሥራት እንዴት ጀመሩ? ጃፓን እንዴት ሠለጠነች? የትናቱን የተፈጸመባትን ግፍ ደጋግማ በመተረክ ዜጓችንም ለበቀል በማነሣሣት ይሆን? ከዘጠና ከመቶ በላይ ኢ አማንያን የሞሉባት ሀገር የጃፓን ሕዝቦች የተደረገባቸውን ክፉ ነገር ትተው ወደ ሥልጣኔ ማማ ሲገሰግሱ ዘጠና ከመቶ በላይ አማኝ የበዛባት ሀገር ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተደረገብን የምንለውን አወዛጋቢ ትርክት እንድናመነዥግ፣ ራሳችን ላይ ፈርደን በቂምና በበቀል እየኖርን የቁልቁለቱን ሩጫ ተያያዝነው፡፡ ይህ የቁልቁለት ሩጫችንም ይኽው ሲያናክሰን ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ የጎረቤታችን የሩዋንዳ ሕዝቦች እንኳን በዘመናችን በውጭ ኃይሎች በተጠመደላቸው ወጥመድ ገብተውና እርስ በርሳቸው ተፋጅተው ከጊዜያት በኋላ ያ ወጥመድ ያደረገባቸውን ተገንዝበው፣ ቂምና በቀላቸውን ትተው፣ የትናንት የታሪክ ጠባሳቸውን አክመው ዛሬ ከደረሱበት የሰላምና መከባበር ኑሮ ይኖራሉ፡፡ እኛ ደግሞ እነርሱ ወደ ተነካከሱበትና ወደ ተላለቁበት ሜዳ ወረድን፡፡ ስለ ግጭት አፈታት መንገዶች የሚተነትኑ አዋቂዎች የበዙባት ሀገር ኢትዮጵያ ወደ እርስ በእርስ ግጭት የምታመራበት መንገዶችን በሚጠርጉላት አዋቂዎች ተናጠች፡፡ በቀልን እያወገዝን የምንበቀል ምስኪኖች!! ቂም ይወገድ! በቀል ይጥፋ! የሚሉ ቀና ሰዎችን ‹‹ስለ ፖለቲካ አትናገሩ›› እያሉ የሚያሸማቅቁ ፖለቲከኞች የበዙባት ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም አንድነቷን አጥታለችና ልንጸልይላት ይገባል!!

የውጭ ኃይሎች ደባ                 

ሰፊውን የኢትዮጵያ ታሪክን በከፊልም ቢሆን ስንመለከት በተለይ ደም ያፋሰሱ ሕዝቡን እርስ በእርስ ያነካከሱና ያገዳደሉ አካላትን ስንመለከት ሁላችንንም ሊያግባባን የሚችል ሐሳብ ዋና ጠላቶቻችን የውጭ ሀገር ባለሥልጣናት መሆናቸውን ነው፡፡ እነርሱ ሠራዊት አስከትለው ዘምተውብን፣ የነከሱን፣ የወጉንና የዘረፉን ጊዜ እንዳለ ዛሬ ጥንታውያን ቅርሶችን ያከማቹባቸው ቤተ መዛግብቶቻቸውና በተለያዩ ጊዜያት ዳግም የመለሱልን ቅርሶች ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህን ክስተት ያስተናገዱ አድዋና ማይጨው፣ ፍቼና አዲስ አበባ፣ ሐረርና ካራማራ ከተሞቻችንም ምስክርነት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ አልሳካ ሲላቸው አንዴ በቋንቋ ልዩነታችን ሌላ ጊዜ ደግሞ የሃይማኖትና የእምነት ልዩነታችንን በዚህም ባይሆን በዚህ ያላችሁት ከምንትስ ነገድ የመጣችሁ ናችሁ ከዚያ ያላችሁት ደግሞ ከእንቶኔ ነገድ የመጣችሁ ናችሁ የሚል የማለያያ እሾህና መርዝ እየጋቱን አናክሰውናል፡፡ የውጭ ኃይሎች ትልቁ ሕመማቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ማጠንከር እንደሆነ ታሪክ ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በጦር ሜዳ ያለ አንዳች ዘመናዊ መሣርያ ትጥቅና ስንቅ እንዲሁም የጦር አካዳሚ ትምህርት በአንድነት ሆኖ ያሸነፋቸውን ሕዝብ በአሉባልታና በበሬ ወለደ እንዲሁም በተጋነኑ የታሪክ ጥፋቶች መለያየት አንግሠው አናከሱት፡፡ የወንጌል መልእክተኛ በመምሰል በሚሽነሪነት ስያሜ፣ በመሬት በወንዞችና ሕዝቦች ጥናት ሽፋን፣ በእርዳታና የድጋፍ ጭምብል፣ በአማካሪነት ስምና በመሳሰሉት እየገቡ አመሱን፡፡ ተራ የወንድማማቾች ጠብን አድማሱን ያሰፋ ጦርነት አድርገው ነገሩን ጻፉልን፤ በልብ ወለድ ድርሰት ሳይቀር አስመስለው ‹‹አንዳችሁ አንዳችሁን አጥፍታችኋል›› ብለው ነገሩን፡፡ እኛም ሳንመረምር የእነርሱን ነገር ሰምተን ተናከስን፡፡ በዚህም በእግዚአብሔር አማኞች ናቸው የምንባል እኛ ‹‹ሁሉን ፈትኑ (መርምሩ) መልካሙንም ያዙ›› ተብሎ የተነገረንን ቃል ቸል ብለን ባልመረመርነውና ባልደረስንበት ነገር መጠፋፋትን ፋሽን አድርገን ያዝን፤ የእነርሱ እኛን የማጠፋፋታቸው ትልቁ ምክንያት ቂምና በቀል ነው፡፡ (፩ ተሰ. ፭፥፳፩)

ትናንት በአንድነት የቆሙ ኢትዮጵውያን የመስፋፋት ሕልማቸውን አጨናግፈውባቸዋል፡፡ ረግጠው ይገዟቸው የነበሩ ሌሎች ሀገራትንም እንዲነሡባቸውና ‹‹እምቢ ለነፃነቴ›› ብለው የቅኝ ገዥነት መንፈሳቸውን እንዲታገሉአቸው ምክንያት ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን እነርሱን ማሸነፍ የዓለምን አስተሳሰብ ርዕዮትና ነጮች የተመረጡ ዘሮች ሲሆኑ ጥቁሮች ደግሞ የነጮች ሸክሞች ናቸው የሚለውን በወንጌል ስም ይሸቃቅጡ የነበሩ የታሪክ ትውስታዎች የእነ ዮሐንስ ካልቪንና ዥዊንግልን እኩይ ፀረ ሰብእ አመለካከት ገልብጧል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ላይ ቂም ስለያዙ መጀመሪያ የአድዋ ድል በተበሠረ በዐርባኛው ዓመት (፲፱፻፳፰ ዓ.ም) ላይ ዳግም ለቅኝ ግዛት ወረራ መጡ፡፡ ዛሬ እኛ እንደተለያየን ያልተለያዩ አባቶቻችንና እናቶቻችንም በአምስት ዓመት ትግል ወደ መጣበት መለሱት፡፡ ከዚህ በኋላ የማለያየቱ ስልት ተቀየረ፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማሸነፋችን ምሥጢር የሆኑ ዕሤቶቻችንን መናድና ዕውቀታችንንና ጉልበታችንን ‹‹ነፃ የውጭ ሀገር ቪዛ›› እየሰጡ ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችንን በ ‹‹ኢንቨስትመት›› ስም በዘበዙት፡፡ ‹‹የተበዘበዘና የተዘረፈ ሕዝብ›› እንዲል፡፡ (ኢሳ. ፵፪፥፳፪)

የግእዝ ቋንቋችንን እኛ እንድናጣጥለው አድርገው እነርሱ በየዩኒቨርስቲዎቻቸው ያጠኑት እስከ ዶክትሬት ዲግሪም ድረስ ይደርሱበት ጀመር፡፡ ለኛ ክፉ ትርክትን እየጋቱ የመለያየትን አጀንዳ እየሰጡና እያናከሱን፤ እነርሱ ግን ሒሳቡን፣ ምድረ-ጽፉን (ጂኦግራፊን)፣ ሥነ ጽሑፉን፣ ሥነ ከዋክብቱን፣ ሥነ እንስሳቱን (ዙኦሎጂ)፣ ሥነ ዕፅዋቱን (ቡታኒ) በኛው አባቶች ለኛ የተጻፈውን ጥበብ ከእኛው ቀድተው ለእነርሱ ወስድው ዞረው ደግሞ ተመጽዋች አደረጉን፡፡ እኛ ግን ዛሬም አሁንም በመለያየት አልጋ ላይ ተኝተን እንጫረሳለን፡፡

እናም ልንነቃ ይገባል፤ ሕዝብ ለሕዝብ አጫርሰውና የሀገራችንን አንጡራዊ ሀብት ተጠቅመው ምድራዊ ሕይወታቸውን በሀብትና በጉልበት ለማበልጸግ የሚዳክሩ ጠላቶቻችን ድል እንነሳቸው ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችንን ጋሻ መከታ ልናደርግ ይገባል፤ ወደ ቀደመ ማንነታችን እንመለስ! ኢትዮጵያ ሀገራችን ሀገረ እግዚአብሔር በመሆኗ አምላካችን እኛን ከጠላት ወገን ለይቶ ከታሰበብን ክፋትና ከሚደርስብን ጥቃት እንዲጠብቀንና ከችግር መከራ እንዲታደገን ከሁሉም አስቀድሞ ቃሉን መጠበቅና ለሕጉ መገዛት አለብን፤ ፈጣሪያችንን የሚያሳዝን ሥራ እየሠራን ግን በችግር ጊዜ ብቻ ወደ እርሱ መጮህ ዋጋ የለውም፤ ነገር ግን ከልብ ተጸጽተን እርሱን መማፀን አለብን፡፡ በንስሓ ወደ እርሱ እንመለስ፤ እርሱም እጁን ዘርግቶ ይቀበለናልና፤ ክፋትን፣ ቂም በቀልና ጥላቻን ከውስጣችን አስወግደን በመተዛዘንና በአንድነት እንኑር!

እግዚአብሔር አምላክ ለሀገራችን ሰላም፣ ለእኛም ፍቅርና አንድነትን ያድለን፤ አሜን፡፡