መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፬ኛው ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤
• ብፁዕ በአቡነ ያሬድ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
• ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሲዳም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፡-

የምሕረት አባት፣ የሰላም አለቃ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ለዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ስላደረሰንና በስሙ ልንወያይም ስላበቃን ክብርና ምስጋና ሁሉን ለሚችል ለኃያሉ አምላካችን ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡

‹‹ወተጸመዱ ለጸሎት ኩሎ ጊዜ በእንተ ኩሎሙ ቅዱሳን፡- ስለ ቅዱሳን ሁሉ ዘወትር ለጸሎት የተጠመዳችሁት ሁኑ›› (ኤፌ. ፮፥፲፰)

ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኘን የቤተ ክርስቲያናችንና የሃይማኖታችን ቁልፍ፣ የግንኙነት መሣሪያ ጸሎት እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በሁሉም ያለና የሚገኝ ምሉእ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉንም ያውቃል፤ ያያልም፤ ነገሮች ከመሆናቸው ወይም ከመታሰባቸው በፊት ሳይቀር ድንበርና ወሰን በሌለው እውቀቱ ያውቃል፡፡

ይሁንና ቢያውቅም ለፍጡራን ሁሉ በተለይም አእምሮና ለብዎ ላላቸው መላእክትና ሰዎች የተሰጣቸውን ብሩህ አእምሮ ተጠቅመው የሚበጃቸውን በራሳቸው እንዲመርጡና እንዲወስኑ ፍጹም ነጻነትን አጎናጽአቸዋል፡፡ ሰዎችም ሆኑ መላእክት ይህንን ነጻነት ተጠቅመው ያለ ምንም ተፅዕኖ ሲወስኑ በውሳኔአቸው ላይ እግዚአብሔር ተፅዕኖ አያደርግም፡፡

ውሳኔአቸውን ተከትሎ በሚመጣው ውጤት ግን ይጠያቃል፤ ዳኝነትም ይሰጣል፡፡ የመላእክትም ሆነ የሰዎች ውድቀት ሊከሰት የቻለው በዚህ ነጻ ምርጫና ውሳኔ እንደሆነ ቤተ ክርሰቲያን የምታስተምረን እውነት ነው፤ ዛሬም በዓለም እየሆነ ያለው ይኸው እውነት ነው፡፡
ሰው የከፋ ኃጢአትን ለመፈጸም ሲሮጥ ምክርና ትምህርት ከመስጠት ባለፈ እግዚአብሔር በነገሩ ጣልቃ ገብቶ ሲያስቆም አናይም፡፡ ‹‹አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ፤ ደይ እዴከ ኀበ ዘፈቀድከ፤ እሳትንና ውኃን አቅርቤልሃለሁ፤ እጅህን ወደ ፈለከው ክተት›› የሚለውም ይህንን እውነታ ያመለክታል፡፡

ከዚህ አንጻር ሰው መከራዎችንና ፈተናዎችን እያሰበና እየጎተተ የሚያመጣቸው በራሱ ነጻ ምርጫና ውሳኔ እንጂ በሌላ ተፅዕኖ እንዳይደለ እናስተውላለን፡፡ የርኩሳን መናፍስት ተፅዕኖ እንዳለ የምናይበት ጊዜ ቢኖር እንኳ መግቢያቸው የሰው ነጻ ዝንባሌ እንደሆነ በአዳምና በሔዋን ያየነው እውነት ነው፡፡

ከዚህ ሌላ ደግሞ ሰዎች በሌሎች ምክንያቶች ሲፈተኑና መከራ ላይ ሲወድቁ የምናየው እውነት ነው፤ ከዚህም አኳያ በቃየን ምክንያት አቤል ሕይወቱን ሲያጣ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ሰዎች በኃጢአት ምክንያት ከወደቁ በኋላ በራሳቸው ምርጫና ውሳኔ ወይም በሌላ ወገን ግፊት ፈተና ላይ ሲወድቁ እናያለን፡፡
• ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

የምንኖርባት ዓለመ ሰብእ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ምን ጊዜም ከመከራና ከፈተና ተለይታ አታውቅም፡፡ ይህ የማይቀር ነገር መሆኑን የሚያውቅ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን መርሕ ቢኖር፤ ‹‹ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፤ ማለትም ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ›› የሚለው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችንን ተከትሎ ዘወትር ስለ ቅዱሳን እንድንጸልይ አስትምሮናል፡፡

ከዚህ አንጻር ከመከራና ከፈተና ለመዳን የተሰጠን የመዳኛ ስልት ተግቶ መጸለይ ነው፤ ስንጸልይም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለቅዱሳን ሁሉ ተግተን ዘወትር መጸለይ እንዳለብን ተነግሮናል፤ ኃላፊነትም አለብን፡፡

ቤተ ክርስቲያንም በደመ ክርስቶስ አንጽታ ስለ ቀደሰቻቸው ምእመናን ልጆቿ ዘወትር ስትጸልይ የምንትኖረውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ስለሆኑ ምእመናን ብቻ ሳይሆን ስለ ዓለሙ ሁሉ ማለትም ስለ ሰማዩም፣ ስለ ምድርም፣ ስለ እንስሳቱም፣ በአጠቃላይ ስለ ፍጥረት ሁሉ ትጸልያለች፡፡

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሀገራችን፣ በሕዝባችንና በደመ ክርስቶስ በተቀደሱ ክርስቲያን ልጆቻችን ላይ ከበድ ያለ ፈተና እየተከሰተ ስለሆነ ከምንም በላይ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀን ልንጸልይ፣ ልናለቅስና ልናዝን ይገባናል፡፡

ገዳማትና አድባራት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ወጣቶች፣ ምእመናንና ምእመናት ፈተና ላይ ሲወድቁና መከራ ሲጸናባቸው ቅዱስ ሲኖደስን በቀጥታ የሚመለከተው ስለሆነ የመፍትሔው አካል ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

ይህንን የፈተና ጊዜ አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን በዝምታ የምናልፈው ከሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን ጠባሳ ታሪክ መሆኑ አይቀረም፤ በእግዚአብሔርም ተጠያቂነትን ማስተካከሉ አይቀርም፡፡ ምእመናን ልጆቻችንም በዚህ ጉባኤ ላይ አመኔታ እንዳያጡ በጣም መጠንቀቅ አለብን፡፡

ይህ ጉባኤ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተጎዱ ለሚገኙት ምእመናንና ምእመናት እንደዚሁም በአጠቃላይ ያለ ፍትሕ እየተጉዱ ለሚገኙት ሰዎች መፍትሔ አምጪ አካል ሆኖ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል፡፡

ይህንንም ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠው የጥበቃ ኃላፊነት መሠረት በጸሎት፣ በማስታረቅ፣ በቁሳቁስ ማለትም መጠለያ፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስና መድኃኒት በማቅረብ ሊያከናውነው ይገባል፡፡ ይህ መሰሉ ቅዱስ ተግባር ለቤተ ክርስቲያናችን አዲስ ነገር ሳይሆን ስታደርገው የነበረና አሁንም እያደረገችው የሚገኝ ነው፡፡ የአሁኑ ከሌላው ጊዜ ልዩ የሚያደረግው ነገር ቢኖር የችግሩ ክብደትና ውስብስብነት ማየሉ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሕልም አለ ተብሎ መተኛት እንደማይቀር ሁሉ ክብደቱን አይተን የምንሸሸው ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን የውስጥ ጥቅምን በማየት ምእመናንን ትብብርና እገዛ በመጠየቅ፣ እንደዚሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናትንና ልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር መከራውንና ፈተናውን መቋቋም ይኖርብናል፡፡ ለዚህም የዛሬ ሠላሳ ዓመት ገዳማ የነበረው ዓይነት አሠራር ዘርግተን ብንሠራ ሰውን ከረሃብ እልቂት ማዳን እንችላለን፡፡

ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ዙሪያ በሰፊው መክሮበት ውሳኔ እንዲያሳልፍ በዚህ የመክፈቻ ጉባኤ በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡

በመጨረሻም፡-
ለመንግሥት ሆነ ለሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የምንፈልገው የአደራ መልእክት ቢኖር የሁሉም ነገር መሠረትና የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ሰላምና ሰላም ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም ሲባል አስፈላጊ የሆነ ዋጋ መክፈል እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ነው፡፡
ዋስትና ያለው ሰላም በሀገራችን ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስበው መወያየት፣ መግባባትና ሀገራዊ ስምምነትን መፈጸም ሲችሉ ነው፡፡
ስለሆነም ይህ ለነገ የማይባል፣ የህልውናችን ጥያቄ መልስ መሆኑን አውቀን ሁላችንም በዚህ መልካም ሥራ እንድንተባበር በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ