ነገረ ግሥ ወአገባብ

መምህር በትረማርያም አበባው

ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፉት ክፍሎች ዘመድ የሙሻ ዘርን የመጨረሻውን ክፍል አቅርበንላችኋል። በዚህ የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ደግሞ ስለ ‹‹የነገረ ግሥ ወአገባብ›› ይዘንላችሁ ቀርበናል። በጥሞና ተከታተሉን!

ነገረ ግሥ ወአገባብ ማለት የእያንዳንዱ ግሥ የአገባብ ስልት እና የተለየ አመል(ጠባይ) ያላቸው ግሦች የሚጠናበት አገባብ ክፍል ነው፤ ግሦችንም በቅደም ተከተል እንመለከታለን፡፡

መሣግር:– መሣግር የሚባለው በዝርዝር ጊዜ ካልአይ አንቀጹን የቀተለን ወደ ቀደሰ፣ የቀደሰን ወደ ቀተለ፣ የገብረን ወደ ሰብሐ፣ የሰብሐን ወደ ገብረ፣ የክህለን ወደ ቀደሰ እየለዋወጠ የሚዘረዝር ማለት ነው። መሣግር የሚሆኑ ፊደላት “ሀ፣ ረ፣ አ፣ ወ፣ ዘ” ናቸው።

“ሀ”:- የሰብሐን ወደ ገብረ ሲያሠግር ገንሐ ብሎ ካልአዩ ይገንሕ ይላል። “ሀ” የቀተለን ወደ ቀደሰ ሲያሠግር መሀረ አስተማረ ብሎ ይሜህር ያስተምራል ይላል።

“ረ”:- የቀደሰን ወደ ቀተለ ሲያሠግር ጠፈረ ብሎ ካልአዩ ይጠፍር ይላል።

“አ”:- የክህለን ወደ ቀደሰ ሲያሠግር ርእየ አየ ብሎ ይሬኢ ያያል ይላል።

“ወ”:- የቀተለን ወደ ቀደሰ ሲያሠግር ወጠነ ጀመረ ብሎ ይዌጥን ይጀምራል ይላል።

“ዘ”:- የቀተለን ወደ ቀደሰ ሲያሠግር ነዘረ ብሎ ይኔዝር ይላል። የክህለን ወደ ቀደሰ ሲያሠግር ተዝኅረ ብሎ ይዜኀር ይላል።

ኅርመት:-በቀዳማይ መልተው በካልአይ የሚጎድሉ ግሦች ሁለት ናቸው። እነዚህም ወሀበ እና ክህለ ናቸው። እነዚህም ግሦች ኅርመት ይባላሉ። አወራረዳቸውም ወሀበ-ሰጠ ብሎ ይሁብ-ይሰጣል፣ የሀብ-ይሰጥ ዘንድ፣ የሀብ-ይስጥ ይላል። ክህለ-ቻለ ብሎ ይክል-ይችላል፣ ይክሀል-ይችል ዘንድ፣ ይክሀል-ይቻል ይላል። እነዚህ ግን በአራቱ አዕማድ ሲገቡ ያጎደሉትን ቀለም ያስገኛሉ። ይኽውም ተውህበ ይትወሀብ ይትወሀብ እንደሚለው ነው፡፡

የቆመ ቤቶች ሳድስ ቅጽላቸው በመካከል ሳድስ ” ው”ን አምጥተው ይወጣሉ። ይህም ከሌሎች የተለየ ነው። ለምሳሌ የቀደሰ ሳድስ ቅጽል ቅዱስ ነው። “ዱ” ካዕብ ነው። ቆመ ብሎ ቅውም ሲል ግን “ው” ሳድስ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

‘ኀሠሠን’ የመሰሉ ግሦች በብዙ በካልአይ በዘንድ እና በትእዛዝ አንቀጽ፣ በአንድ ወንድና በአንድ ሴት ዝርዝር ያጎድላል። ለምሳሌ “ነበበ-ተናገረ” ይላል። በብዙ ነበብክሙ-ተናገራችሁ ይላል። በካልአይ “ትነቡ-ትናገራላችሁ” ይላል ማለት ነው። በትእዛዝ አንቀጽ ደግሞ “ንቡ-ተናገሩ” ይላል። ተጨማሪ ምሳሌ “ኀሠሠ” ን ብንመለከት። በብዙ “ኀሠሥክሙ-ፈለጋችሁ” ይልና። በትእዛዝ አንቀጽ “ኅሡ-ፈልጉ” ይላል። ‘ኀሠሡ-ፈለጉ’ ይልና በትእዛዝ “ይኅሡ-ይፈልጉ” ይላል። በአንዲት ሴት ደግሞ በዝርዝር ኀሠሠቶ-ፈለገችው ብሎ በካልአይ አንቀጽ “ተኀሦ-ትፈልገዋለች” ይላል።

የንባብ ተገብሮ የትርጓሜ ገቢር የሚሆኑ ግሦች አራት ናቸው። እነዚህም “ተለቅሐ-ተበደረ፣ ተመጠወ-ተቀበለ፣ ተጸገወ-ተሰጠ፣ ተወክፈ-ተቀበለ” ናቸው። የእነዚህም አድራጊዎቻቸው “ለ”ን ይሻሉ። ሁለቱም ግእዝ ይስባሉ። መጠወ/ጸገወ/ለቅሐ ወርቀ ለነዳይ ይላል።

የንባብ ገቢር የትርጓሜ ተገብሮ የሚሆኑ ግሦች አራት ናቸው እነዚህም ሐመ-ታመመ፣ ደወየ-ታመመ፣ ጸምአ-ተጠማ፣ ርኅበ-ተራበ ናቸው።

የንባብ አስደራጊ የትርጓሜ አድራጊ አለ። ምሳሌ:- አስደራጊ አፍቀረ-ወደደ:አስወደደ፣ አእመረ-አወቀ:አሳወቀ የሚሉት ናቸው።

የንባብ አስደራጊ የትርጓሜ አድራጊ፣ ተደራጊ፣ አስደራጊ አለ። ምሳሌ:- አንቀልቀለ-ተነዋወጠ፣ አነዋወጠ ይላል።

የንባብ አደራራጊ የትርጓሜ አድራጊ፣ አስደራጊ፣ ተደራጊ፣ አደራራጊ አለ። ለምሳሌ አስተርአየ-ታየ፣ አሳየ ይላል።

የንባብ ተደራራጊ የትርጓሜ ተደራጊ አለ። ምሳሌ ተጋብአ-ተሰበሰበ ይላል።

የተገብሮ አመል በንባባቸውም በትርጓሜያቸውም የማይገኝባቸው አራት ናቸው። እነዚህም “ከብረ፣ ነግሠ፣ ሞተ፣ ቆመ” ናቸው። እነዚህም ዘራቸውን ይስባሉ እንጂ ከሌላ ነገር ገብተው አይስቡም። ከብረ ክብረ፣ ነግሠ ንግሠ፣ ቆመ ቆመ፣ ሞተ ሞተ ይላል። ምሥጢራቸው ግን ተደራጊ ነው።

በፍጹም ገቢራቸው በውድ ሁለት በግድ አንድ፣ በተገብሯቸው በውድ አንድ የሚስቡ ግሦች አሉ። እነዚም ላጸየ-ላጨ፣ መተረ-ቆረጠ፣ ረገዘ-ወጋ፣ ሐነቀ-አነቀ፣ ኰርዐ-መታ ናቸው። በውድ ሁለት ሲስቡ ላጸየ ሕፃነ ርእሶ ይላል፤ ትርጉሙ ሕፃኑን ራሱን ላጨ ይላል። አሕዛብ መተርዎ ለዮሐንስ ክሣዶ ይላል፤ ትርጉም አሕዛብ የዮሐንስ አንገቱን ቆረጡት ማለት ነው። አይሁድ ረገዝዎ ለክርስቶስ ገቦሁ ይላል ትርጉሙ አይሁድ የክርስቶስን ጎኑን ወጉት ይላል። ተደራጊዎቻቸው በውድ አንድ ሲስቡ ሕፃን ተላጸየ ርእሶ ይላል ትርጉሙ ሕፃን ራሱን ተላጨ ማለት ነው።

አሥራወ ቀለማት በአሉታ ጊዜ በአስደራጊ በአደራራጊ ከቀዳማይ ይወጣሉ። ሲወጡም ሁለት “አ” ቢገኝ አንዱን፣ አንድ “አ” ቢገኝ ያንኑ ያስለቅቁታል። ከሁለቱ “አ” አንዱን “አ” ሲያስለቅቁ ‘አእመረ-አወቀ’ ለሚለው አሉታው ‘ኢያእመረ-አላወቀም’ ነው። አንዱን ‘አ’ ሲያስለቅቁ “አፍቀረ-ወደደ” ለሚለው አሉታው “ኢያፍቀረ-አልወደደም” የሚለው ነው።

በእርባታ ጊዜ “ተ” ን ውጠው የሚያስቀሩ ቀለማት ስድስት ናቸው እነዚህም “ሰ፣ተ፣ዘ፣ደ፣ጠ፣ጸ” ናቸው። ተሰብሐ-ተመሰገነ ብሎ ይሴባሕ-ይመሰገናል፣ ይሰባሕ-ይመሰገን ዘንድ፣ ይሰባሕ-ይመስገን ይላል። ተጠምቀ-ተጠመቀ ብሎ ይጠመቅ-ይጠመቃል፣ ይጠመቅ-ይጠመቅ ዘንድ፣ ይጠመቅ-ይጠመቅ ይላል። ተደንገለ-ተጠበቀ ብሎ ይደነገል-ይጠበቃል፣ ይደንገል-ይጠበቅ ዘንው፣ ይደንገል-ይጠበቅ ይላል። ተተርአሰ-ተንተራሰ ብሎ ይተረአስ-ይንተራሳል፣ ይተርአስ-ይንተራስ ዘንድ፣ ይተርአስ-ይንተራስ ይላል። ተጸምደ-አገለገለ፣ ይጸመድ-ያገለግላል፣ ይጸመድ-ያገለግል ዘንድ፣ ይጸመድ-ያገልግል ይላል። ተዘምደ-ዘመድ ሆነ፣ ይዘመድ-ዘመድ ይሆናል፣ ይዘመድ-ዘመድ ይሆን ዘንድ፣ ይዘመድ-ዘመድ ይሁን ይላል። ነገር ግን ይህን ሕግ የማይጠብቁ ሁለት ግሦች አሉ እኒህም ተስዐ-ዘጠኝ አደረገ የሚለውና ተስዕዐ-ተገፈፈ የሚሉት ናቸው። አረባባቸውም ተስዐ ብሎ ይቴስዕ፣ ይተስዕ፣ ይተስዕ ይላል። ተሥዕዐ ብሎ ይትሰዐዕ፣ ይትሰዐዕ፣ ይትሰዐዕ ይላል።

ንዑስ አንቀጻቸውና ሳድስ ቅጽላቸው አንድ የሚሆኑ ግሦች አሉ። እኒህን ርኅበ-ተራበ፣ ጸበ-ጠበበ፣ ቀለ-ቀለለ፣ መረ-መረረ፣ ኖኀ-ረዘመ፣ መፀ-ቦካ(ኾመጠጠ) ናቸው። ሲነገሩም ርኅበ ካለው ርኂብ ርኂቦት ይወጣል። ሳድስ ቅጽሉ ርኂብ፣ ርኂባን፣ ረኃብ፣ ረኃባት ይላል። የቀለ ንዑስ አንቀጽ ቀሊል ቀሊሎት ነው። ሳድስ ቅጽሉ ቀሊል፣ ቀሊላን፣ ቀላል፣ ቀላላት ይላል። የጸበ ንዑስ አንቀጽ ጸቢብ ጸቢቦት ነው። ሳድስ ቅጽሉ ጸቢብ፣ ጸቢባን፣ ጸባብ፣ ጸባባት ይላል። የመሪር ንዑስ አንቀጹ መሪር መሪሮት ነው። ሳድስ ቅጽሉ መሪር፣ መሪራን፣ መራር፣ መራራት ይላል። የኖኀ ንዑስ አንቀጽ ነዊኅ ነዊኆት ይላል። ሳድስ ቅጽሉ ነዊኅ፣ ነዊኃን፣ ነዋኅ፣ ነዋኃት ይላል። የመፀ ንዑስ አንቀጽ መፂፅ መፂፆት ነው። ሳድስ ቅጽሉ መፂፅ፣ መፂፃን፣ መፃፅ፣ መፃፃት ይላል። ሌሎችም እኒህን መስለው የሚሄዱ አሉ ለምሳሌ ጸልመ-ጨለመ ንዑስ አንቀጹ ጸሊም ጸሊሞት ነው። ሳድስ ቅጽሉ ጸሊም፣ ጸሊማን፣ ጸላም፣ ጸላማት ይላል። ረሥአ-ረሳ ንዑስ አንቀጹ ረሢእ ረሢኦት ይላል። ሳድስ ቅጽሉ ረሢእ፣ ረሢኣን፣ ረሣእ፣ ረሣኣት ይላል። ጠበ-ብልሀተኛ ሆነ ለሚለው ንዑስ አንቀጹ አንቀጹ ጠቢብ ጠቢቦት ይላል። ሳድስ ቅጽሉ ጠቢብ፣ ጠቢባን፣ ጠባብ፣ ጠባባት ይላል። ከላይ ያየናቸው ከዚህ ያየናቸው በሙሉ ንዑስ አንቀጻቸው ላልቶ ይነበባል። ሳድስ ቅጽላቸው የሴቶች ጠብቆ ይነበባል። ከወንዶችም ጸሊም፣ ጸሊማን እና ነዊኅ፣ ነዊኃን ይጠብቃሉ።

በ”ወ” ለደረሰ ግሥ በ”ተ” ካልተነሳ በራሱ ካልተገሰሰ በመድረሻው ሳድስ ቀለም ከካልዓይ ከአንድ ከትእዛዝ የለውም። ካዕብ ነው እንጂ ሳድስ ቀለም ሲታጣ አርኀወ-ከፈተ፣ ያርኁ-ይከፍታል፣ ያርኁ-ይከፍት ዘንድ፣ ያርኁ- ይክፈት ይላል። በ”ተ” ሲነሳ ግን አለው። ይህም ተኄረወ-ቸር ሆነ፣ ይትኄረው-ቸር ይሆናል፣ ይትኄረው-ቸር ይሆን ዘንድ፣ ይትኄረው-ቸር ይሁን ይላል። በራሱ ሲገሰስ ከወወ-ቅልጥፍጥፍ አለ፣ ይከውው-ቅልጥፍጥፍ ይላል፣ ይክውው-ቅልጥፍጥፍ ይል ዘንድ፣ ይክውው-ቅልጥፍጥፍ ይበል ይላል። የሴቲቱ ሳድስ ቅጽል ግን ሳድሱን አስለቅቆ ካዕብ አድርጎ ይነገራል ሲነገርም ከተሠርገወ ሥርጉት፣ ከደለወ ድሉት ይወጣል።

በ”የ” ለደረሰ ግሥ በ”ተ” ካልተነሳ በራሱ ካልተገሰሰ መድረሻው በካልዓይ ሳድስ የለውም። ሣልስ ነው እንጂ። ሳድስ ሲታጣም ኀለየ-አሰበ፣ ይኄሊ-ያስባል፣ ርእየ-አየ፣ ይሬኢ-ያያል ይላል። በ’ተ’ ሲነሳ ተኀሥየ-ተደሰተ፣ ይትኀሠይ-ይደሰታል ይላል። በራሱ ሲገስስ ጸማሕየየ-ጠወለገ፣ ይጸማሐይይ-ይጠወልጋል፣ ይጸማሕይይ-ይጠወልግ ዘንድ፣ ይጸማሕይይ-ይጠውልግ ይላል። በ”የ” በንዑስ አንቀጹና በቦዙ መካከል ሳድስ ቀለም እንጂ ሣልስ ቀለም አይገኝም ሲነገርም ርእይ ርእዮት-ማየት፣ ጸግይ ጸግዮት-ማበብ ይላል። ርእዮ-አይቶ፣ ጸግዮ-አብቦ ይላል።

በግሱ ሁሉ “ሀ” እና “አ” በመካከል ሲገኙ የሚቀድሟቸውን ቀለማት በቀዳማይ ግእዝ፣ራብዕ፣ሳድስ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ተልዕለ፣ ተልዐለ፣ ተለዐለ፣ ተላዐለ፣ ተላዕለ ብሎ ከፍ ከፍ አለ ይላል። በአምስት መንገድ ይሄዳል። በሁለት መንገድ የሚሄድም አለ። ምሳሌ:-ወዐለ፣ ዋዐለ ብሎ ዋለ ይላል።

ከአራት ቀለም በላይ ያለ ግስ ሁሉ የንዑስ አንቀጹ መካከሉ ሳድስ መድረሻው ሳብዕ ይሆናል። ምሳሌ አንቀልቀለ-ተነዋወጠ ይልና አንቀልቅሎ አንቀልቅሎት-መነዋወጥ ይላል። ሦስትም አራትም ቀለም የሆነ ግሥ በራብዕ፣ በኃምስ፣ በሳብዕ ሲነሳ እንዲሁ ነው። ምሳሌ ሌለየ-ለየ ብሎ ሌልዮ ሌልዮት-መለየት ይላል። ሁለትም ሦስትም ቀለም ለሆነ ግስ የንዑስ አንቀጹ መካከሉ ሣልስ መድረሻው ሳድስ ነው። ምሳሌ ሖረ-ሄደ ብሎ ሐዊር ሐዊሮት መግደል ይላል። ክህለ-ቻለ ብሎ ክሂል ክሂሎት መቻል ይላል።

በውስጥ ማሰሪያ የሚያወጡ አገባባት ፲፪  ናቸው። እኒህም በ፣ ውስተ፣ ለ፣ እስከ፣ ምስለ፣ እም፣ መንገለ፣ ቅድመ፣ ድኅረ፣ ዘ፣ ከመ እና ኀበ ናቸው። በ ሲያስር እግዚአብሔር በሰማይ ብሎ እግዚአብሔር በሰማይ አለ ይላል። “ውስተ” ሲያስር ንጉሥ ውስተ ጽርሑ ብሎ ንጉሥ በአዳራሹ ውስጥ አለ ይላል። እስከ ሲያስር ሄኖክ ወኤልያስ እስከ ይእዜ በገነት ብሎ ሄኖክና ኤልያስ በገነት እስከዛሬ አሉ ይላል። ምስለ ሲያስር ማርያም አመ ወረደት ግብፀ ምስለ ዮሴፍ ወሰሎሜ ብሎ ማርያም ወደ ግብጽ በወረደች ጊዜ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ነበረች። ቅድመና ድኅረ ሲያስሩ አመ ገብኡ ኢሎፍሊ ኢዮአብ ወአቢሳ ቅድመ/ድኅረ ዳዊት ብሎ ኢሎፍላውያን በተመለሱ ጊዜ ኢዮአብና አቢሳ በዳዊት ፊት/ኋላ ነበሩ ይላል። ለ ሲያስር ስብሐት ለአብ ብሎ ለአብ ምስጋና ይገባል ይላል። ዘ ሲያስር አምላክ ዘእማርያም ብሎ አምላክ ከማርያም የተገኘ ነው ይላል። ከመ ሲያስር ሚካኤል ዘከመ አምላኩ ለርኅራኄ ብሎ ሚካኤል ለርኅራኄ እንደ አምላኩ ነው ይላል።

ነባር አናቅጽ እንደ ዐበይት አናቅጽ እየተዘረዘሩ በሙሻ ዘር የሚወጡ አገባባትን ሁሉ ያወጣሉ። ሃይማኖት ቦቱ ለጊዮርጊስ ለእርሱ ለጊዮርጊስ ሃይማኖት አለው ይላል። ሎቱ እንደወጣ አስተውል። እምኔሁ ሲወጣ ሃይማኖት አልቦቱ ለንስጥሮስ ይላል፡፡ ትርጉሙ ከእርሱ ለንስጥሮስ ሃይማኖት የለውም ይላል። እንበለ ሲወጣ ክህደት አልቦቱ ለዲያብሎስ ይላል ትርጉሙ ያለ እርሱ ለዲያብሎስ ክህደት የለውም ማለት ነው። በእንቲኣሁ ሲወጣ አምላክ ቦቱ ለሙሴ በታቦር ይላል ትርጉሙ ስለእርሱ በታቦር ለሙሴ አምላክ አለው ይላል። እስከኔሆሙ ሲወጣ አምላክ ቦቶሙ ለአድማስ ወለናጌብ ይላል ትርጉሙ እስከ እነርሱ ለአድማስና ለናጌብ አምላክ አላቸው ይላል። ምስሌሁ ሲወጣ ዕዝራ ቦቱ ለሄኖክ በገነት ይላል ትርጉሙ ከእርሱ ጋራ በገነት ለሄኖክ ዕዝራ አለው ይላል።

ንዑሳን አናቅጽ ሳቢ ከተሳቢ ዘርፍ ከባለቤት እየተናበቡ ፳፭ አገባባትን ያወጣሉ። አገባባቱም ለ፣ በ፣ በእንተ፣ ምስለ፣ ከመ፣ ኀበ፣ እስከ፣ እም፣ እንበለ፣ ግእዝ፣ ውስተ፣ ማእከለ፣ ላዕለ፣ ታሕተ፣ የማነ፣ ጸጋመ፣ ኀበ፣ መንገለ፣ ወእደ ዘንድ ሲሆኑ፣ መጠነ፣ ጊዜ፣ ለለ፣ በበ፣ ዘዘ፣ ድኅረ፣ ቅድመ እና “ኢ” ሆኖ ሲሆን ናቸው። ዐሥሩን ከሙሻ ዘርፍ አይተናል። ቀሪዎቹን ቀጥለን እናሳያለን። ድኅረ ሲገባ አፍቀረ አማኑኤል ዳዊት ንግሠተ ሐማ ሳኦል ይላል ትርጉሙ ከሐማ ሳኦል በኋላ መንገሥን አማኑኤል ዳዊት ወደደ ይላል። መጠነ ሲገባ አፍቀረ አማኑኤል ሰሎሞን ንግሠተ ሐማ ዳዊት ይላል ትርጉሙ የሐማ ዳዊትን ያህል መንገሥን አማኑኤል ሰሎሞን ወደደ ይላል። ቅድመ ሲገባ ፈተወ ሐማ ሳኦል ንግሠተ አማኑኤል ዳዊት ይላል ትርጉሙ ከአማኑኤል ዳዊት በፊት መንገሥን ሐማ ሳኦል ወደደ ይላል።

ላዕለ ሲገባ ገብረ አማኑኤል ስቅለተ መስቀል ይላል ትርጉሙ በመስቀል ላይ መሰቀልን አማኑኤል ወደደ። ታሕተ ሲገባ አፍቀረ ገብር ንብረተ እግዚኡ ይላል ትርጉሙ ከጌታው በታች መቀመጥን አገልጋይ ወደደ። ማእከለ ሲገባ ሠምረ አብ አማኑኤል ንብረተ ፈያት አበው ይላል ትርጉሙ ከአባቶች ሽፍቶች ጋር መቀመጥን አማኑኤል አባት ወደደ ይላል። በንዑስ አንቀጽም በአምስቱ አእማድ ይህንኑ መስሎ ይሄዳል። ምሳሌ ጸጋመ ሲገባ ለኃጥአን ቀዊመ አምላክ ይላል ትርጉሙ በአምላክ ግራ መቆም ለኃጥኣን ይገባል ማለት ነው። ጊዜ ሲገባ አፍቀረ ጲላጦስ አስተቃትሎተ ቀትር አምላከ ምስለ ፈያት ይላል ትርጉሙ ከሽፍቶች ጋር አምላክን በቀትር ጊዜ ማገዳደልን ጲላጦስ ወደደ ይላል። በሳድስ ቅጽል ሲገባ ምሳሌ የማነ ሲገባ ወልድ ንቡረ አብ ይላል ትርጉሙ በአብ ቀኝ የተቀመጠ ወልድ ማለት ነው። ኢ ሲገባ አምላክ ምውተ ሰብእ ይላል ትርጉሙ ሰው ሆኖ የሞተ አምላክ ማለት ነው።

“እም” በዘንድ ሲወድቅ ሕጸቱ እንጂ ምልአቱ አይስማማውም። ይህም እምይብላዕ ይላል እንጂ እምነ ይብላዕ አይልም። እስከም እንዲሁ ነው።

አገባባት ሁሉ ከዘር፣ ከነባር፣ ከስም፣ ከግብር እየተናበቡ አዋጅ አያፈርሱም።  “እም” ብቻ ያፈርሳል። ሲያፈርስም በሳድስ እየተናበበ ነው። ምሳሌ እምድር ይላል። “ሰ” ቀለም ይለውጣል። ሲለውጥም አነ ያለውን አንሰ ይላል።

አገባብ ሲዘረዝር ራሱን ወደ ሣልስ ወደ ራብዕ ወደ ኀምስ እየመለሰ ይዘረዝራል። “እንተ፣ዘ፣እለ” ራሳቸውን ወደ ሣልስ እየመለሱ ባዕድ ቀለም “ኣ”ን ያመጣሉ። ሲገቡም ዚኣሁ፣ እንቲኣሁ፣ እሊኣሁ ይላል። እንዲህ እያለ በዐሥሩም መራሕያን ይዘረዘራል።

ከመ ከአገባባት ተለይቶ በገቢር አንቀጽ ይሳባል ሲሳብም በዐቢይነቱ ነው። ምሳሌ ተነበዩ ነቢያት ከመ ይመጽእ ክርስቶስ ይላል። ነቢያት ክርስቶስ እንደሚመጣ ተነበዩ (ተናገሩ) ማለት ነው። ተነበዩ ተሳቢ ያስፈልገው ነበር ‘ከመ’ ስላለ ግን ተሳቢ እንደቀረ አስተውል። የሚስቡት አናቅጽ ሰባት ናቸው። እነዚህም ተነበየ፣ ሰበከ፣ አእመረ፣ ጠየቀ፣ ሰምዐ፣ ገብረ እና ለበወ ናቸው።

ከነባር አናቅጽ ለከመ ውእቱን ይዞም ሳይዝም አፍዛዥነት ያላቸው ሳቢዎች አሉት። እኒህም እንጋ፣ እንዳኢ ናቸው። ሲገቡ ‘ከመ’ ባለቤት ይሆናል። ምሳሌ እንጋ/እንዳኢ ከመ ብዕለ ሰብእ እስመ ይሜሕር ነዳየ ወምስኪነ ይላል ትርጉሙ ሰው ባዕለ ጸጋ እንደሆነ እንጃ ለነዳይና ለምስኪን ይመጸውታልና ይላል። በዚህ ጊዜ ባለቤቱ “ከመ” ነው። ሰብእ የማንጸሪያ ባለቤት ነው። “እመ”ም እንደ ከመ ይገባል። ንጉሥ እመቦ በመንበሩ ንቅንት ሎቱ ይላል ትርጉሙ ንጉሥ በወንበሩ ካለ እንታጠቅለት ይላል። ንጉሥ የማንፀሪያ ባለቤት እመ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ነው።

“ወ” በትእዛዝና በትእዛዝ መካከል ገብቶ “ና” ይሆናል። ተንሥእ ወሑር ሲል ተነሥና ሂድ ማለት ነው።

‘ሁ፣ኑ፣እንጋ’ ወይ፣ን ይሆናሉ። “ሁ” እመን ሶበን ይዞ ይነገራል። “ኑ” በስምና በእርባ መካከል ይነገራል። “እንጋ” ሁን ምን ይከተላል። ሲገቡም ዘመጽኡ ሰብአ ሰገል ሶበሁ ተወልደ ክርስቶስ ይላል ትርጉሙ ሰብአ ሰገል የመጡ ክርስቶስ ቢወለድ ነውን? /ነው ወይ? ይላል። ተወልደኑ እንጋ ይላል ትርጉሙ ተወልዶ ይሆንን ይላል።

ዘንድ አንቀጽ ‘ከመ’ን ይዞ ሳይዝም መፍትው፣ ድሎት፣ ጽድቅ፣ ፍትሕ፣ ርትዕ፣ ሥርዐት፣ ኩነት፣ ርቱዕ በማሰሪያነት ሲነገሩ ባለቤት ይሆናል። ምሳሌ መፍትው ከመ ያድኅኖ ለአዳም አምላክ ይላል ትርጉሙ አምላክ አዳምን ያድነው ዘንድ ይገባል ይላል። ያድኅኖ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ነው። አምላክ የዘንድ ባለቤት ነው።

እመ፣ሶበ፣ከመ ባለቤት ይሆናሉ። ከመ ሲገባ ተነግረ በነቢያት ወተሰብከ በሐዋርያት ከመ አንተ በአብ ወአብ ብከ ይላል ትርጉሙ አብ በአንተ አንተም በአብ እንዳለህ በሐዋርያት ተሰበከ በነቢያትም ተነገረ ይላል። ሶበ ሲገባ እምኄሶ ለሰብእ ሶበ ይምሕር/ከመ ይምሕር ነዳየ ወይገብር ሰናየ ይላል ትርጉሙ ለሰው ለነዳያን ቢመጸውት መልካምንም ቢሰራ ይሻለው ነበር ይላል። ኄሶ በእም የታገዘ ማሰሪያ አንቀጽ ነው። እም ደግሞ ማሰሪያ አገዝ ነው።

በመካከል ሆነው የሚቆጥሩ የሚጠቀልሉ “ህ” እና “እ” ናቸው። በዘር በነባር ይቆጥራሉ ይጠቀልላሉ። ልዕልና ትሕትና ሲል ይጠቀልላሉ ይቆጥራሉ። ድርድሮች የወ ሳድስ የየ ራብዕ ከሆኑ ይቆጥራሉ ይጠቀልላሉ። አዕዋም፣ አውያን ይላሉ። አይቴ፣ ባሕታዊ ይቆጥራሉ ይጠቀልላሉ። “አ” በራሱ ሳድስ ተደርድሮ ድርድሩን የረ፣ የነ፣ የደ፣ የጸ ካዕብ የጸ ሳድስ የበ ራብዕ ሲቀበላቸው ይቆጥራሉ ይጠቀልላሉም። አዕጹቅ፣ አዕኑግ፣ አዕጽምት፣ አዕሩግ፣ አዕባን፣ አዕዱግ ይላል።

የሀገር ስም ሰው ሲያመጣ ለሴት ለወንድ ለአንድ ለብዙ ይሆናል። ምሳሌ ወተፈሥሑ ግብፅ በጸአቶሙ ግብፆች (እስራኤላውያን) በመውጣታቸው ተደሰቱ ይላል።

በ’ወ’ የጨረሰ እርባ ሳድስ ቅጽሉ ካዕብ ቀለም የለውም። ፍትው፣ ድልው፣ ውርዝው ይላል።

“ቀ፣ተ፣ደ፣ጠ፣ጸ” ከሴቲቱ ሳድስ ቅጽል ሲደርሱ ቀለማቸውን ያጠብቃሉ። ተ ሲያጠብቅ ምውት፣ ትሕት ይላል። ደ ሲያጠብቅ ዋሕድ፣ ንእድ ይላል። ጠ ሲያጠብቅ ሥልጥ ይላል። ቀ ሲያጠብቅ ጥምቅ፣ መጥምቅ ይላል። ጸ ሲያጠብቅ ሕንጽ፣ ድንግጽ ይላል።

“ዘ” ን የሚበዘብዙ (እንዳያስር የሚያደርጉ) አገባባት ፲፫ ናቸው። እኒህም በ፣ ለ፣ እስከ፣ ምስለ፣ በእንተ፣ እም፣ ውስተ፣ ቅድመ፣ ድኅረ፣ አመ፣ ከመ፣ ኀበ፣ እንበለ ናቸው። በ ሲበዘብዝ በዘፈጠረነ ነአምን ይላል ትርጉሙ በፈጠረን እናምናለን ማለት ነው። ለ ሲበዘብዝ ለዘፈጠረነ ንሰግድ ይላል ትርጉሙ ለፈጠረን እንሰግዳለን ማለት ነው። ምስለ ሲበዘብዝ ተሰቅለ ወልድ ምስለ ዘሰረቁ ፈያት ይላል ትርጉሙ ወልድ ከሰረቁ ሽፍቶች ጋር ተሰቀለ ይላል። በእንተ ሲበዘብዝ ሞተ አምላክ በእንተ ዘበልዐ በለሰ አዳም ይላል ትርጉሙ አዳም በለስን ስለበላ አምላክ ሞተ ይላል። እም ሲበዘብዝ ተንሥአ ወልድ እምዘአተወ መቃብር ይላል ትርጉሙ ወልድ ከገባበት መቃብር ተነሳ ይላል። ውስተ ሲበዘብዝ ኀደረ ንጉሥ ውስተ ዘተሐንጸ ማኅደር ይላል ትርጉሙ ንጉሥ በታነጸ ቤት ውስጥ አደረ ይላል። ቅድመ ሲበዘብዝ ዳዊት ነግሠ ቅድመ ዘወለዶ ሰሎሞን ይላል ትርጉሙ ዳዊት ከወለደው ሰሎሞን በፊት ነገሠ ይላል። ድኅረ ሲበዘብዝ ሰሎሞን ነግሠ ድኅረ ዘወለዶ ዳዊት ይላል ትርጉሙ ሰሎሞን ከወለደው ዳዊት በኋላ ነገሠ። አመ ሲበዘብዝ ዐደው እስራኤል አመ ዘከፈለ ባሕረ ሙሴ ይላል ትርጉሙ እስራኤል ሙሴ ባሕርን በከፈለ ጊዜ ተሻገሩ። ከመ ሲበዘብዝ ተሰቅለ ጴጥሮስ ከመ ዘተሰቅለት ዶርሆ ይላል ትርጉሙ ጴጥሮስ እንደተሰቀለች ዶሮ ተሰቀለ ይላል። ኀበ ሲበዘብዝ ተፈነወ ገብርኤል ኀበ ዘተወልደት እምሐና ድንግል ይላል ትርጉሙ ገብርኤል ከሐና ወደተወለደች ድንግል ተላከ ይላል። እንበለ ሲበዘብዝ ኢነአምን ካልአ እንበለ ዘፈጠሩ ሰማየ ወምድረ ሥላሴ ይላል ትርጉሙ ሰማይና ምድርን ከፈጠረ ሥላሴ በቀር በሌላ አናምንም ይላል።

በልዐ ኅብስቶ ለማዕዱ ለሞሰቡ ለባዕል ይላል። ይህም በ፫ ለ ማለት ነው። ትርጉሙ በልዐ ኅብስተ ማዕደ መሶበ ባዕል ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። በ፫ “ዘ”ም ይቻላል። ይሄውም በልዐ ኅብስተ ዘማዕድ ዘመሶብ ዘባዕል ይላል። ትርጉሙ የሁሉም የባዕለ ጸጋ የመሶብ የማዕድ እንጀራን በላ ማለት ነው።

ውጥን ጨራሽ ቀለማት የሚሆኑ ቀለማት ወ፣ ከመ፣ ሰ፣ መጠነ፣ ዳእሙ ናቸው። ወ ሲገባ በልዐ ኅብስተ ወመዓረ ይላል ትርጉሙ እንጀራ በላ ማርም በላ ማለት ነው። ከመ ሲገባ ዐገቱኒ ከመንህብ መዓረ ይላል ትርጉም ንብ ማርን እንደሚከብ ከበቡኝ ማለት ነው። ሰ ሲገባ አፍቅራ ለማርያም እምከ ወፈድፋደሰ ለእግዚአብሔር ይላል፡፡ ትርጉሙ ድንግል ማርያም እናትህን ውደዳት ይልቁንም እግዚአብሔርን ውደደው ይላል። ርሕቅት ማርያም እም ኃጢአት መጠነ ሰማይ እምድር ይላል፡፡ ትርጉሙ ሰማይ ከምድር የራቀውን ያህል ድንግል ማርያም ከኃጢአት የራቀች ናት። ዳዕሙ ሲገባ መኑ ይትዔረዮ ለተክለሃይማኖት ዳዕሙ ገብረ ሕይወት ይላል፡፡ ትርጉሙ ገብረ ሕይወት ይተካከለዋል እንጂ ተክለ ሃይማኖትን ማን ይተካከለዋል ይላል።

ተደራራቢ አገባባት ስምንት ናቸው። እነዚህም አመ፣ ከመ፣ ድኅረ፣ ኀበ፣ ዘ፣ እስከ፣ እንዘ፣ እመ ናቸው። አመ ሲገባ አመ አመ ሙሴ ተከፍለ ባሕር ዐደው እስራኤል ይላል ትርጉሙ በሙሴ ጊዜ ባሕር በተከፈለ ጊዜ እስራኤል ተሻገሩ ይላል። ከመ ሲገባ ከመ ከመ ሙሴ ከፈለ ባሕረ ኤርትራ ኤዎስጣቴዎስ ከፈለ ባሕረ ኢያሪኮ ነአምን ይላል ትርጉሙ ሙሴ የኤርትራን ባሕር እንደከፈለ ኤዎስጣቴዎስም የኢያሪኮን ባሕር እንደከፈለ እናምናለን ይላል። ኀበ ሲገባ ኀበ ኀበ ማርያም ተፈነወ ገብርኤል ተወልደ አምላክ ይላል ትርጉሙ ወደማርያም ገብርኤል ከተላከ ዘንድ አምላክ ተወለደ ይላል። ድኅረ ሲገባ ድኅረ ድኅረ ሳኦል ነግሠ ዳዊት ተመይጠት ጽዮን ይላል ትርጉሙ ሳኦል ከነገሠ በኋላ ዳዊት ከነገሠ በኋላ ጽዮን ተመለሰች ይላል። ዘ ሲገባ ዘዘፈቀደ  እግዚአብሔር ይገብር ይላል፡፡ ትርጉሙ እግዚአብሔር የወደደውን የሚሰራ ይላል። እንዘ ሲገባ እንዘ እንዘ ይወርድ መቅሰፍት ላዕለ አሕዛብ ይሬእዩ እስራኤል ለምንት ሰቀልዎ ለአምላክ ይላል ትርጉሙ መቅሰፍት በአሕዛብ ላይ እየወረደ እያዩ እስራኤል አምላክን ለምን ሰቀሉት ይላል። እስከ ሲገባ እስከ እስከ እግሩ ይውሕዝ ተቀብዐ ወሬዛ ዕፍረተ ይላል ትርጉሙ እስከ እግሩ እስኪፈስ ወጣት ሽቱን ተቀባ ይላል። እመ ሲገባ ክርስቶስ እመ እመ ይምሕል ይሰቀል ድኅነ አዳም ይላል ትርጉሙ ክርስቶስ ቢምል ቢሰቀል አዳም ዳነ ይላል።

በግእዝ ተነሥቶ ድርድሩ ራብዕ፣ ኃምስ፣ ሳብዕ የሆነ ስም ይነሳል ምሳሌ አቤል፣ ረዓብ፣ አዜብ፣ አሞጽ፣ ሰሎሞን ይላል። በግእዝ በራብዕ ተነሥቶ የመድረሻው ኋላ ሳብዕ የሆነ ስም ይነሣል፡፡ ምሳሌ ሰባልዮስ፣ ባስልዮስ፣ ሰንድሮስ ይላል። በግእዝ በራብዕ ተነሥቶ የመድረሻው አጠገብ ሣልስ ሳብዕ የሆነ ስም አይነሳም ምሳሌ አቡቀለምሲስ፣ ናብሊስ፣ ናቡከደነጾር ይላል። በግእዝ በካዕብ ተነሥቶ ድርድሩ አንድ ካዕብ፣ አንድ ራብዕ፣ አንድ ኃምስ የሆነ ስም ይነሣል፡፡ ምሳሌ ሱቱኤል፣ ዱማቴዎስ፣ ደማቴዎስ፣ ቡኤዝ ይላል። በካዕብ ተነሥቶ ሁለት ደካማ ቀለም ያለበት ስም አይነሳም ምሳሌ ሩፋኤል፣ ዑራኤል፣ ሱራፌል ይላል። በሣልስ ተነሥቶ ድርድሩ ሳብዕ ራብዕ የሆነ ስም ይነሣል፡፡ ምሳሌ ኪራም፣ ሲሞን፣ ቂሮስ፣ ኢሳይያስ፣ ሲድራቅ፣ ቂርቆስ፣ ጢሞቴዎስ ይላል። በሣልስ ተነሥቶ ሁለት ደካማ ቀለም ሲደረደር የመድረሻው ኋላ ሣልስ፣ ኃምስ፣ ሳብዕ የሆነ ስም አይነሳም ምሳሌ ጊዮርጊስ፣ ሚካኤል፣ ጲላጦስ፣ ሊባኖስ ይላል።

በራብዕ ተነሥቶ ድርድሩ ካዕብ፣ ራብዕ፣ ኃምስ፣ ሳብዕ የሆነ ስም ይነሳል ናባል፣ ናጌብ፣ ባሮክ፣ ባሦር፣ ሳሙኤል ይላል። በኃምስ ተነሥቶ ድርድሩ ካዕብ፣ ራብዕ፣ ኃምስ፣ ሳድስ፣ ሳብዕ የሆነ ስም ይነሳል ምሳሌ  ኔባል፣ ሤሬቅ፣ ሴኬም፣ ሴዴቅያስ፣ ቄርሎስ፣ ሄኖክ ይላል። በኃምስ በሣልስ ተነስቶ ድርድሩ ሦስት ደካማ ቀለም ያለው ስም አይነሳም ምሳሌ ሄሮድስ፣ ኢያቄም ይላል። በግእዝ በራብዕ በሳድስ ተነስቶ ድርድሩ ራብዕ ኃምስ ሳድስ ሳብዕ የሆነ ስም ይነሣል፡፡ ምሳሌ ግያዝ፣ ብርያል፣ ብልዮስ፣ ግዮን፣ ገብርኤል፣ አቤሴሎም፣ እለእስክንድሮስ ይላል። በሳድስ ተነሥቶ በመካከሉ ሦስት ደካማ ሲሆን አይነሳም ምሳሌ እግዚአብሔር፣ እስጢፋኖስ ይላል። ፍጹም ሳድስ የሆነ ስም አይነሳም ምሳሌ እስክንድር፣ ግብጽ፣ ቅምር ይላል። በሳብዕ ተነሥቶ ድርድሩ ራብዕ ኃምስ ሳብዕ የሆነ ስም ይነሳል ምሳሌ ቶማስ፣ ሮቤል፣ ሶፎር፣ ኮቦር ይላል። ሁለት ቀለም የሆነ ስም አይነሳም ምሳሌ ሴም፣ ካም፣ ኖብ፣ ኖኅ ይላል። ደካማ ቀለማት የሚባሉት ካዕብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ኃምስ፣ ሳብዕ ናቸው።

የሚበዳደሩ ቀለማት ስምንት ናቸው እነዚህም ኈ፣ ቈ፣ ኰ፣ ጐ፣ ኀ፣ ቀ፣ ከ፣ ገ ናቸው። ለምሳሌ ከ ሲበደር ተኬነወ-ብልሀት ሠራ ብሎ ኵናት ይወጣል። ኰ ሲበደር ለሐኰ-ፈጠረ ብሎ ለሐኮ-ፈጠረው ይላል። ሌሎችም እንዲሁ ነው።

በኃምስ በሣልስ የሚነሡ ዘርና ነባር በአመል ሲረቡ ሣልሱን ኃምሱን ሳድስ ያለ አመል ሲረቡ ግእዝ እያደረጉ የየን ራብዕ ያመጣሉ። በአመል ቤዝ-ኮከብ ብሎ አብያዝ-ኮከቦች ይላል። ቢጽ-ባልንጀራ ብሎ አብያጽ ባልንጀራዎች ይሆናል። ያለ አመል ቴፈን-ወይፈን ብሎ ተያፍን-ወይፈኖች ይላል። ሌሊት-ሌሊት ብሎ ሲበዛ ለያልይ ይላል። “የ” በራሱ ግስ ከሴቲቱ ውስጠዘ ሲታጣ ሳድሱን በሣልስ ይጎርዳል። ይሄውም ተርእየት፣ ተሴሰየት፣ ውዕየት ፣ ተላጸየት ካለው ግሥ ሉጺት፣ ርኢት፣ ሲሲት፣ ውዒት ይወጣል።

በቀተለ ቤት በወ ተነስቶ በማናቸውም ሲደርስ መስም ቅጽሉ ይጠብቃል መነሻው አይፈርስም። መወልድ መወርድ ማለቱን ያሳያል።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።