ነቢዩ ሳሙኤል

ሰኔ ፯ ቀን፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም

ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ወገን ከሆኑት ከአባቱ ሕልቅና እና ከእናቱ ሐና የተወለደው  ሳሙኤል የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ተጽፏል፤ ‹‹ሕልቅናና ሐናም ማልደው ተነሥተው ለእግዚአብሔር ሰግደው ሄዱ፤ወደ ቤታችውም ወደ አርማቴም ደረሱ፤ ሕልቅናም ሚስቱን ሐናን ዐወቃት፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤ ፀነሰችም፡፡ የመውለጃዋም ወራት በደረሰ ጊዜ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርስዋም ‹‹ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለምኜዋለሁ›› ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው፡፡›› (፩ሳሙ.፩፥፲፱-፳) በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተጻፈው ደግሞ ‹‹ሐና መካን ነበረች፤ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር እያለቀሰች አዘውትራ ስለማለደች ይህን የተባረከ ልጅ ሰጣት::››  (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፰)

ሐናም ልጇን ለሦስት ዓመት በቤተ ውስጥ ካሳደገቸው በኋላ ስእለቷን አስታውሳ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ የእግዚአብሔር አገልጋይ ይሆን ዘንድ ሰጠችው፤ ሕፃኑም በቤተ መቅደስ ካህኑ ዔሊን ማገልገል ጀመረ፡፡ ብላቴናም በሆነ ጊዜ የበፍታኤፉድ (በጥሩ ለስላሳ ልብስ ከተልባ እግር ተፈትሎ የሚሠራ) ታጥቆ አገልግሎቱን ይፈጽማል፡፡ እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፤ እርሷም በየዓመቱ መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ሕልቅና ጋር እየወሰደች ታቀርብለት ነበር፡፡ ካህኑ ዔሊም ባልና ሚስቱን ባረካቸው፤ ለሕልቅናም ‹‹ለእግዚአብሔር ስለ አገባኸው ስጦታ ፈንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ›› አለው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ሰጣቸው፡፡ ብላቴናው ሳሙኤልም በእግዚአብሔር ፊት አደገ፡፡ (፩ሳሙ.፪፥፲፰-፳፩)

የካህኑ ዔሊ ልጆች ግን እግዚአብሔርን የማያውቁና የሚበድሉ ክፉዎች ነበሩ፡፡ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት አያቀርቡም፡፡ በዚያም ወቅት ቃለ እግዚአብሔርም ሆነ ራእይም ለሕዝቡ አይገለጥም ነበር፡፡ ካህኑ ዔሊም አርጅቶውና ዐይኖቹም መፍዘዝ ጀምረው ነበር፤ በአንድ ሌሊትም እርሱ በመኝታው ተኝቶ ሳለ ሳሙኤል በቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦት አጠገብ ተኝቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ‹‹ሳሙኤል ሳሙኤል›› ብሎ ጠራው፤ እርሱም ‹‹እነሆ አለሁ›› ብሎ ዔሊ ወደ ተኛበት ሄደ፡፡ ‹‹ስለጠራኸኝ እነሆ እኔ መጣሁ›› አለው፡፡ ዔሊም ‹‹አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ›› አለው፤ ሄዶም ተኛ፡፡ እግዚአብሔርም ዳግመኛ ሳሙኤልን ‹‹ሳሙኤል ሳሙኤል›› ብሎ ጠራው፤ ሳሙኤልም ተነሥቶ ዔሊ ወደተኛበት በመሄድ ‹‹ስለጠራኸኝ እነሆ እኔ መጣሁ›› አለው። ዔሊም መልሶ ‹‹አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ››  አለው፤ ከዚህ አስቀድሞ ሳሙኤል እግዚአብሔርን በራእይ ስለማያውቀው እና ቃለ እግዚአብሔርም ስላልተገለጠለት የጠራው ማን እንደሆነ አላወቀም ነበር፡፡

ለሦስተኛ ጊዜም እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ በመሄድ ‹‹ስለጠራኸኝ እነሆ እኔ መጣሁ›› አለው፡፡ በዚህም ጊዜ ዔሊ ሳሙኤልን የጠራው እግዚአብሔር እንደሆነ አሰበ፡፡ ለሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ ‹‹ልጄ ተመልሰህ ተኛ፥ የሚጠራህ ካለም እኔ ባሪያህ እሰማለሁና ጌታዬ ተናገር በለው›› አለው፡፡ ሳሙኤል ወደ መኝታው ሄዶ ተኛ፤ እግዚአብሔርም መጥቶ እንደቀድሞ በፊቱ ቆሞ ጠራው፤ ሳሙኤልም ካህኑ ዔሊ እንደነገረው ‹‹እኔ ባሪያህ እሰማለሁና ጌታዬ ተናገር›› በማለት መለሰ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ ‹‹የሰማው ሁሉ ሁለቱን የሚያስይዝ እነሆ እኔ በእስራኤል ላይ የተናገርኩት ቃሌን አደርጋለሁ፡፡ በዚያችም ቀን በዔሊና በወገኑ ላይ የተናገርኩትን ሁሉ አጸናለሁ፤ እጀምራለሁ፤ እፈጽማለሁም፡፡ ልጆቹ  የእግዚአብሔርን ቃል አቃልለዋልና እርሱም አልገሠጻቸውምና በልጆቹ ኃጢአት እኔ ወገኑን ለዘለዓለም እንደምበቀለው ነገርሁት፡፡ ስለዚህም ነገር በዕጣንም ቢሆን በመሥዋዕትም ቢሆን የዔሊ የወገኑ     ኃጢአት እስከ ዘለዓለም ድረስ እንዳይሠረይ ራሴ እንዲህ ብዬ ማልሁ፡፡›› (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፰)

በማግሥቱም ሳሙኤል ያየውን ራእይ ለዔሊ መንገር ፈራ፤ ሆኖም ግን ዔሊ እግዚአብሔር ለሳሙኤል የነገረውን ነገር ሳይደብቅ እንዲነግረው አጥብቆ ጠየቀው፤ ‹‹ከእኔ አትሸሽግ፤ ከነገረህና ከሰማኸው ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፤ እንዲህም ይጨምርብህ›› ብሎ ገዘተው፤ ሳሙኤልም ራእዩን በሙሉ ነገረው፤ ዔሊም ‹‹እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ›› ብሎ ተናገረ፡፡ የእግዚአብሔርም ቃል በዔሊና በወገኖቹ ላይ ተፈጸመ፡፡ ሳሙኤልም በሚያድግበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር፤ ይገለጥለትማል፤ ሳሙኤልም ከምድር ዳርቻ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ በሕዝቡ ነቢይ እንደሆነ ታመነ፡፡ (፩ሳሙ.፫፥፲፭-፳፩)

ከዚህም በኋላ ዔሊ በ ፺፰ ዓመቱ ሞተ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን የቂስ ልጅ ሳኦልን ቀብቶ እንዲነግሠው ባዘዘውም ጊዜ የዘይቱን ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፤ ሳመውም፤ እንዲህም አለው፥ ‹‹በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ትነግሥ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል፤ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፤ በዙሪያው ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ፡፡ እግዚአብሔርም በርስቱ ላይ ትነግሥ ዘንድ እንደ ቀባህ ምልክቱ ይህ ነው፡፡››  (፩ሳሙ.፲፥፩) ሕዝበ እስራኤልም በነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት መሠረት ንጉሣቸው ሳኦልን ተቀበሉት፡፡ ንጉሡም በእግዚአብሔር ኃይል ጠላቶቹ አሞናውያንን ድል አደረገ፡፡

ሆኖም ግን ሳኦል የልዑልን ትእዛዛ መተላለፍ ጀመረ፤ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ለሳሙኤል እንዲህ አለው፤ ‹‹ሳኦል እኔን ከመከተል ተመልሷልና ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነግሥኩት ተጸጸትሁ፤›› (፩ሳሙ.፲፭፥፲-፲፩) ሳሙኤልም እጅጉን አዘነ፤ ወደ እግዚአብሔርም አብዝቶ ጮኸ፤ ስለዚህም ለእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ ሳሙኤል የዕሴይ ልጅ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ እግዚአብሔር ባዘዘው መሰረት ቀብቶ አነገሠው፡፡ ዳዊትም በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስና ክብር አግኝቶ ‹‹እንደ ልቡ የሆነ ሰው›› ተባለ። በዘመነ መንግሥቱም ኃያል ንጉሥ በመሆን ጠላቶቹን በሙሉ ድል ይነሣ ነበር፡፡ (፩ሳሙ.፲፫፥፲፬)

ነቢዩ ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እየፈጸመ ኖረ። በሕይወት ዘመኑ በሙሉም የእስራኤልን ሕዝብ መርቷል፤ ሳሙኤልም ባረጀ ጊዜ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ ‹‹የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ ንጉሥ አንግሸላችኋላሁ፡፡ አሁንም እነሆ ንጉሥ በፊታችሁ ይሄዳል። እኔም አርጅቻለሁ፤ እንግዲህም አርፋለሁ፡፡›› (፩ሳሙ.፲፪፥፩) ነቢዩ ሳሙኤልም በሰኔ ፱ ቀን ሞተ፤ ሕዝበ እስራኤልም ተሰብስበው አልቅሰው በአርማቴምም በቤቱ ቀበሩት፡፡ (፩ሳሙ.፳፭፥፩)

እግዚአብሔር አምላክ ነቢዩ ሳሙኤል ጸሎት ይማረን፤ አሜን!