ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወቅዱስ ጳውሎስ

ከምንባባት ዐውድ  

ሐምሌ ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

የቅዱሳን ሐዋርያት ታሪክ ገድልና ሥራ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሙሉ አልሰፈረም። አርባዕቱ ወንጌላት ሐዋርያት እንዴት እንደተጠሩና እስከ ዕርገት ድረስ የነበራቸውን ሁኔታ ሲጽፉ፤ ወንጌላዊው ሉቃስ ደግሞ የሐዋርያትን ታሪክ እስከ ፷ መጀመሪያ ያለውን ጽፏል።

ከዚህ በመለስ ያለውን የሐዋርያት ታሪክ ለማወቅ ግን ዋናው ምንጩ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ መጻሕፍት ናቸው። የሐዋርያት ደቀመዛሙርት እነ ፓፒያስ፣ ፖሊካርፐስ፣ አግናጥዮስ፣ ቀሌምንጦስ ዘሮም ወዘተ. የአባቶቻቸውን ታሪክ ጽፈው አቆይተውልናል። ከዚህበኋላ ጊዜም  በ፪ኛውና በ፫ኛው መቶ ክፍለ  ዘመን  የተነሱት የቤተ ክርስቲያን  ታሪክ  ጸሐፍት እነ አውሳብዮስ፣ ሩፊኖስ፣ ጄሮም፣ ወዘተ. በትውፊት የተቀበሉትን መዝግበው አልፈዋል።

ቅዱሳን ሐዋርያት ገድላቸው የተጻፈላቸው፣ በዓላቸው የተከበረላቸው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ናቸው። በቤተ ክርስቲያናችን በሐምሌ ፭ ቀን በታላቅ ድምቀት በዓላቸው ከሚከበረው ሐዋርያት መካከል የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስና የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

፩. ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባሕር ዳር በምትገኘው በቤተሳይዳ ነው። የአባቱ ስም ዮና ይባላል። ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ ያደገው በቅፍርናሆም ከተማ ሲሆን በጐልማሳነቱ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባሕር ዓሳ ማሥገር ጀመረ። ለደቀመዛሙርነት ሲመረጥ ዕድሜው ፶፭ ዓመት እንደነበረ ይነገራ፤ ወደ ጌታችን ያመጣውም ወንድሙ እንድርያስ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ በርናባስና ወንጌላዊው ማርቆስ ቤተ ዘመድ ናቸው። የማርቆስ አባት አርስጦቡሎስና በርናባስ በእናት የሚገናኙ ወንድማማች ናቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ ያገባው የበርናባስና የአርስጦቡሎስን እኅት ስለነበር በጋብቻ ይዛመዳሉ። ቅዱስ ጴጥሮስ ለሐዋርያነት ሲጠራ መተዳደሪያው የነበረውን መረቡንና ታንኳውን እንዲሁም አባቱን እርግፍ አድርጐ ትቶ ጌታውን የተከተለ ሐዋርያ ነው።

የቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያ ስሙን ስምዖን ብላ እናቱ የጠራችው በነገዿ ስም እንደሆነ ይነገራል። በቂሳርያ ከተማ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ማን ትሉኛላችሁ?» ብሎ በጠየቀ ጊዜ «አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» ብሎ ለአይሁድ ሊቃውንት የተሰወረውን ምሥጢረ ተዋሕዶ ገልጦ በመመስከሩ ጌታችን «አንተ ጴጥሮስ ነህ» ብሎታል ይህም በላቲን ቋንቋ ዐለት ማለት ነው፤ በአርማይክ ደግሞ ኬፋ ይባላል።

ቅዱስ ጴጥሮስ ከአዕማድ ወይንም የምሥጢር ሐዋርያት ከእነ ዮሐንስ እና ያዕቆብ ጋር የሚቆጠር ነው። ከሐዋርያት ሁሉ ቀደም ቀደም የማለት ባሕርይ ነበረው። ጌታ በጥብርያዶስ ባሕር ላይ ሌሊት በእግሩ ሲመጣ ቢመለከት ወደ አንተ እመጣ ዘንድ እዘዘኝ በማለት ካስፈቀደ በኋላ ወደ ጌታ ለመምጣት መንገድ ጀምሮ በመሐል ቤት ጥርጣሬ ገባውና መስጠም ስለጀመረ ጌታችን «ያመንክ እንጂ ያላመንክ አትሁን» ብሎ ገስፆ ከመስጠም አድኖታል። (ማቴ ፲፬፥፳፪-፴፫) በቅፍርናሆም ጉባኤ ጌታን ምሥጢረ ቁርባንን ሲያስተምር፣ አይሁድ ስላልገባቸው ወደ ኋላ አፈገፈጉ። ከደቀ መዛሙርቱም «ብዙዎቹ ወደ ኋላ ተመለሱ» በዚህን ጊዜ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁ?» ብሎ ሐዋርያትን ጠየቃቸው። በዚህ ሰዓት «ጌታ ሆይ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም የሕይወት ቃል አለህ። እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክ እናምናለን» በማለት ሐዋርያትን ወክሎ የመለሰ እርሱ ነው። (ዮሐ ፮፥፷፮-፷፰)

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ይወድ ነበር። ፍቅሩ ግን ቅንዓት የተቀላቀለበት በመሆኑ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ የሞቱን ነገር ቀድሞ ሲነግራቸው አይሁንብህ በማለት ተከራክሯል። (ማቴ ፲፮፥፳፫) በኋላም «ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም» ብሎ በራሱ ቅንዓት ተማምኖ ተናግሮ ነበር። ጌታችን «ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ» እያለው እንኳን «ከአንተ ጋር መሞት እንኳን የሚያስፈልገኝ ቢሆን ከቶ አልክድህም» በማለት የተናገረ ሰው ነው። (ማቴ ፳፮፥፴፬)

ቅዱስ ጴጥሮስ አስቀድሞ የተናገረውን ቃል ለመጠበቅ ሞክሮ ነበር። ጌታ ዛሬ «የሰው ልጅ አሳልፎ ይሰጣል» ብሎ አስተምሮአቸው ነበርና መከላከያ ይሆነኛል ብሎ ሠይፍ ደብቆ ይዞ ነበር። የሮም ጭፎሮችም ጌታን ለመያዝ ሲጠጉ የሊቀ ካህናቱን ባርያ (ማልኰስን) በሠይፍ ጆሮውን ቆረጠው። ጌታችን ግን ሞቱ በፍቃዱ ለድኅነተ ዓለም ነውና «ሠይፍህን ወደ ሰገባው» መልስ ሲል ገሠፀው። ቅዱስ ጴጥሮስ የሚታወቅበት ሌላው ትልቁ ነገር ንስሐው ነው። ጌታው የነገረው መድረሱን፣ ቃል የገባለትን አምላኩን መበደሉን እንዳወቀ ከግቢው ወጥቶ አለቀሰ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዕድሜው ታላቅነት በሐዋርያት ዘንድ እንደ አባት ይታይ ስለነበር ጌታ በተለያቸው ጊዜ ሐዋርያቱን ሊመግብ ወደሚያውቀው ሙያ ዓሳ ወደ ማሥገሩ ተሠማራ። ጌታም አስቀድሞ የመረጠው እርሱ ነውና ቢክደው እንኳን  በንስሐ  በመመለሱ  ንስሐውን  መቀበሉን፤  ዛሬም  እንደሚወደው  ይገልጽለትም  ዘንድ  በጥብርያዶስ  ባሕር ተገለጠለት። (ዮሐ ፲፰፥፲)

ሦስት ጊዜ ክዶት ነበርና ቀኖና ሰጠው። አሁን ቅዱስ ጴጥሮስ በራስ መተማመኑ እንዳላዋጣው ዐውቆአልና «ትወደኛለህን?» ተብሎ ሲጠየቅ «አንተ ታውቃለህ» ነበረ መልሱ። የራሱ ዕውቀት የት እንዳደረሰው ያውቃልና ጌታችንም ኅዳጌ በቀል (በቀልን የሚተው) ነውና ዛሬም እንደሚወደው፣ በንስሐ ተመልሶአልና ዛሬም ለእርሱ የሰጠውን ክብር እንደማያጐድልበት ሲነግረው ግልገሎቼን አሠማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጐቼን አሠማራ» በማለት አደራውን አስረከበው። ከዚያም በሞቱ እንደምን አድርጐ እግዚአብሔርን አንደሚያከብረው ነግሮት ወደ ሰማያት ዐረገ። (ዮሐ ፳፩፥፲፭-፲፯)

ቅዱስ ጴጥሮስ በአራቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ በተቀመጡት የሐዋርያት ዝርዝር ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ ይገኛል። ይህም፦ ፩. በሽምግልና አባትነቱ፣ ፪. ጌታ በቂሳርያ በሰጠው ቃል ኪዳን፣ ፫. የሐዋርያት አፈ ጉባዔ ሆኖ ይናገር ስለነበር፣፬. በጥብርያዶስ ባሕር በተሰጠው ቃል መሠረት ነው። በዚህም የተነሣ በይሁዳ ምትክ ሌላ ሐዋርያ እንዲመረጥ ሐሳብ ያቀረበ እርሱ ነበር። በበዓለ ሃምሳም ለደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ለተሰበሰቡት አይሁድ አፈ ጉባዔ ሆኖ ወንጌልን የሰበከ ፫፼ (ሦስት ሺህ) ምእመናንንም አሳምኖ የመጀመሪያዋን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም የመሠረተ እርሱ ነው። (የሐዋ. ፩፥፲፮-፳፫፣ ፪፥፲፬-፴)

አስቀድሞ ፈሪ የነበረውና በሊቀ ካህናት ቀያፋ ግቢ ጌታውን የካደው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ካገኘ በኋላ ግን በአይሁድ ሸንጐ ድውይ ፈወስክ ተብሎ በተከሰሰ ጊዜ በድፍረት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ መሰከረ። የሐዋ ቆርነሌዎስን በማጥመቅ ወንጌልን ለአሕዛብ አስቀድሞ የሰበከው ሐዋርያ ነው። ይህ ሐዋርያ ልዑል እግዚአብሔር ባደለው  ጸጋ ጥላው እንኳን ድውያንን ይፈውስ ነበር። የሐዋ ፭፥፲፭። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፲፭ ላይ በ፶ ዓ.ም. አካባቢ በኢየሩሳሌም በተደረገው የሐዋርያት ሲኖዶስ ከአንጾኪያ ክርስቲያኖች ለቀረበው ጥያቄ የመጀመሪያውን መልስ የሰጠው እርሱ ነበር። ስለ ቅዱስ ጴጥሮስ መልክና ቁመና ጥንታዊያን መዛግብት እንደሚከተለው ያቀርቡታል። «ፊቱ ሰፋ ያለ ሲሆን ሪዛምና መካከለኛ ቁመት የነበረው ራሰ በራ ሰው ነው። በማናቸውም ነገር ፈጣንና ቀልጣፋ ነበር።»

በቤተ  ክርስቲያን  ታሪክ  መሠረት  ቅዱስ  ጴጥሮስ  በፍልስጥኤም፣  በሶርያ፣  በጳንጦን፣  በገላትያ፣  በቀጰዶቅያ፣ በቢታንያ እና በሮሜ ሰብኳል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በሮሜ አንድ ዓመት ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ካስተማረ በኋላ የሮሜ ክርስቲያኖች እየበዙ ከመምጣታቸውም በላይ የክርስትናው ጉዞ እስከ ሮማ ባለሥልጣናት ደረሰ። የኔሮን የቅርብ ባለሥልጣናት የሆኑት የአልቢኖስና የአግሪጳ ሚስቶች ወደ ክርስትናው ገቡ። በዚህን ጊዜ ኔሮን ንጉሠ ሮማ በቅንዓት ተነሣባቸው።

ኔሮን በሮም የነገሠው በ፶፬ ዓ.ም. ነው። በመንግሥቱ መጀመሪያ ደግ ሰው ነበረ። ነገር ግን በነገሠ በዓመቱ የጨካኝነት ዐመሉ ብቅ ማለት ጀመረ እና የአባቱን ልጅ አስገደለ። በ፶፱ ዓ.ም. ደግሞ እናቱን በመርዝ ገደለ። በ፷፫ ዓ.ም. እያስተማረ ያሰደገውን መምህሩን ፣ በ፷፪ ዓ.ም. የልጅነት ሚስቱን አግታሺያን አስገደለ። ከእርስዋ በኋላ ያገባትን ሚስቱንም ፓፒያን በርግጫ ብሎ ገደላት። ኔሮን በ፷፬ ዓ.ም. እርሱ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ተቀምጦ የሮማን ከተማ እሳት ለቀቀባት። የሮም ሕዝብ በደረሰው አደጋ እጅጉን ተቆጣ። ኔሮንም በክርስቲያኖች አመካኘ። በዚህም የተነሣ በሮማ ከተማ ሁለት ዓይነት ወሬ መናፈስ ጀመረ።

የሮማ አማልክት በክርስቲያኖች ሃይማኖት ስለተቆጡ በከተማዋ እሳት አዘነቡባት የሚለው የመጀመሪያው ሲሆን ክርስቲያኖች ሆን ብለው ከተማዋን አቃጥለዋታል የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ወሬ ነበር። የከተማው መጋየት ያበሳጨው የሮማ ሕዝብ፣ ክርስቲያን የሆነውን ሁሉ እያወጣ መግደሉን ተያያዘው። ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ሰዓት በእሥር ነበርና ተሠይፎ ዐረፈ። ይህን የሰሙት የአግቢኖስና የአግሪጳ ሚስቶች (የሮም ባለሟሎች ነበሩ) «ባይሆን አንተ ትረፍልን» ብለው በከተማዋ ግንብ በገመድ አሥረው በቅርጫት በማውረድ ቅፅረ ሮማን ለቅቆ እንዲወጣ አደረጉት።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በኦፒየም ጎዳና ጉዞውን ቀጠለ። ሮማን ለቀቀ። እያዘገመ በሸመገለ ጉልበቱ ሲጓዝ አንድ ቀይ ጐልማሳ ወደ እርሱ ሲመጣ አየ። እየቀረበ ሲመጣ ጌታችን መሆኑን ተረዳ። ወዲያው በፊቱ ተደፋና «ጌታዬ ወዴት እየተጓዝክ ነው?» አለና ጠየቀው። «ዳግም በሮም ልሰቀል» አለው።

በዚህ ሰዓት ቅዱስ ጴጥሮስ አዘነና እንደገና ወደ ሮማ ተመለሰ። የኔሮን ወታደሮች እየፈለጉት ነበር። «እነሆኝ ስቀሉኝ» አለ ቅዱስ ጴጥሮስ። ያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስን ይዘው አሠሩት። ከጥቂት ቀናት በኋላም ሮማውያን የመስቀያውን እንጨት አቀረቡለት። ያን ጊዜ «እኔ እንደ ጌታዬ ልሰቀል አይገባኝም» በማለት ቁልቁል እንዲሰቅሉት ለመነ። ያለውንም አደረጉለት። ሐምሌ ፭ ቀን ፷፯ ዓ.ም. በሰማዕትነት ዐረፈ።

. ሐዋርያው ቅዱስ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዘሩ ከዕብራዊያን፣ ከብንያም ነገድ ሲሆን የተወለደውም በጠርሴስ ከተማ ነው። ጠርሴስ በንግድዋ የታወቀች የኪልቂያ ዋና ከተማ ናት። በከተማዋ እስከ አምስት መቶ ሺህ የሚገመቱ ከየሀገሩ የተሰባሰቡ ሕዝቦች ነበሩባት። ሮማውያን በሥራቸው ለሚተዳደሩት ሕዝቦች ሮማዊ ዜግነትን ይሰጡ ስለነበር፥ የቅዱስ ጳውሎስ አባት በዜግነት ሮማዊ ነበር። ይህም ለቅዱስ ጳውሎስ ተላልፎለታል።

ቅዱስ  ጳውሎስ  በ፲፭  ዓመት  ዕድሜው  ወደ  ትውልድ  ሀገሩ  በመመለስ  በኢየሩሳሌም  ከነበረው  የታወቀው የገማልያል ትምህርት ቤት ገባ። በዚያም የአይሁድን ሕግና ሥርዓት እየተማረ እስከ ፴ ዓመቱ ቆየ። ገማልያል ፈሪሳዊ ስለነበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ተቀብሎታል። በ፴ ዓመቱ የአይሁድ ሸንጎ አካል ሆኖ ተቆጠረ።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ስለነበረ ሁኔታዎቹን ሁሉ ያውቃል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአይሁድ ሸንጎ አባልነት ለሁለት ዓመታት በሠራበት ወቅት ለኦሪታዊ እምነቱ ቀናተኛ ፈሪሳዊ በመሆኑ  ክርስቲያኖችን በማናቸውም አጋጣሚ ይቃወም ነበር። እንዲያውም ሊቀዲያቆናት እስጢፋኖስን በማስተማሩ ምክንያት ተከሶ ለአይሁድ ሸንጎ በቀረበ ጊዜ የተከራከረው እርሱ ነበር። በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ሲያርፍም የወጋሪዎችን ልብስ ይጠብቅ የነበረው እርሱ ነው። ቅዱስ አውግስጢኖስ «በእስጢፋኖስ ጸሎት፣ ቤተ ክርስቲያን የተፋውን ጳውሎስን አገኘች፤» በማለት ተናግሯል።

በ፴፪ ዓመት እድሜው ከኢየሩሳሌም ፪፻፳፫ (ሁለት መቶ ሃያ ሦስት) ኪ.ሜ. ርቀት በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የደማስቆ ከተማ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ሲሰማ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀርቦ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የሚያስችለውን የፈቃድ ደብዳቤ አገኘ። ከዚህም በኋላ ጭሮችን አስከትሎ ወደ ደማስቆ አመራ። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ከተማዋ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ነበር ከሰማይ የወረደው ብርሃን አካባቢውን ያለበሰውና «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?» የሚለውን ድምፅ የሰማው። ሐዋርያው ጳውሎስም «ጌታ ሆይ ማን ነህ?» ብሎ ጠየቀ። «አንተ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ። የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል» ሲል መድኃኒታችን ተናገረው። ያን ጊዜም በወደቀበት ሆኖ እየተንቀጠቀጠ «ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?» ሲል ጠየቀ። ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ወደ ደማስቆ እንዲገባ ተነገረው። (የሐዋ. ፱፥፩)

የሐዋርያው ዓይኖች ለማየት አልቻሉም። እየተመራ ወደ ደማስቆ ገባ። ለሦስት ቀናት ያህልም እህል ሳይቀምስ ቆየ። በዚያች ዕለት እግዚአብሔር አምላክ በደማስቆ ለሚገኘው እና ሐናንያ ለተባለው አባት በራእይ ተገለጠለት። ቅዱስ ጳውሎስም  ያለበትን  አድራሻ  ነገረውና ሄዶ እንዲያጠምቀው  አዘዘው። ሐናንያ አስቀድሞ  የቅዱስ ጳውሎስን  ማንነት ያውቃል። አብዛኞቹ በደማስቆ የሚገኙት የቅዱስ ጳውሎስን ማንነት ያውቃል። አብዛኞቹ በደማስቆ የሚገኙት ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም በስደት የመጡ ናቸው። ያን ስደት ያስነሣው ደግሞ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የደረሰው መከራ ነው። በዚህ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት ደግሞ ዋናው ተዋናይ ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር።

ይህን የሚያውቀው ሐናንያ በቅድሚያ ከእግዚአብሔር ጋር መከራከር ጀምሮ ነበር። እግዚአብሔር አያውቀው ይመስል ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ማስረዳት ጀመረ። በመጨረሻ ግን «ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእሥራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተ ዋለሁና» በማለት እግዚአብሔር ሐናንያን ላከው። ሐናንያ ቅዱስ ጳውሎስን ካጠመቀውና ካስተማረው በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዓረብ ሀገር መሄዱን ራሱ ተናግሮአል። (ገላ ፩፥፲፯)

ለ፫ ዓመታት በዓረቢያ በረሃ ከቆየ በኋላ ወደ ደማስቆ ከተማ ተመለሰ። በዚያም በነበሩ አይሁድ መካከል በፊት ያሳድደው የነበረውን ኢየሱስ ክርስቶስን መስበክ ጀመረ። ከዚያ በፊት በፈሪሳዊነቱና ለአይሁድ ሕግ በነበረው ቅንዓት የሚታወቀው ጳውሎስ ዛሬ ወንጌል ሲሰበክ በማየታቸው አይሁድ ተነሡበት። በዚህም የተነሣ የደማስቆ ክርስቲያኖች በቅርጫት አውርደው ወደ ኢየሩሳሌም ላኩት።

ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የገጠመው ሁለት ችግር ነበር። በቅድሚያ አይሁድ ጳውሎስን እንደሚያውቁት እና እንደለመዱት ሆኖ ስላላገኙት ሊገድሉት ተነሡ። በሌላ በኲል ደግሞ ክርስቲያኖች የቅዱስ ፓውሎስን መመለስ ሊያምኑ አልቻሉም። በመጨረሻ ግን በርናባስ ወደ ሐዋርያት ዘንድ ወስዶ የጳውሎስን መመለስ በመተረክ እንዲያምኑት አደረጋቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም በድፍረት በማስተማሩ አይሁድ ስለተቃወሙት ከተማዋን ትቶ በቂሳርያ በኲል ወደ ትውልድ ሀገሩ ጠርሴስ ተመለሰ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጠርሴስ ከተማ ለዘጠኝ ዓመታት ቆይቷል። ከኢየሩሳሌም ውጭ የአሕዛብ ከተማ በነበረችው በአንጾኪያ የክርስትና ሃይማኖት ተስፋፋ። ከኢየሩሳሌም የተሰደዱት ክርስቲያኖች የአንጾኪያን ሕዝብ ተግተው በማስተማራቸው ዝናው እስከ ኢየሩሳሌም ደረሰ። በዚህም ምክንያት በኢየሩሳሌም የነበሩት አበው በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላኩት። በርናባስ የግሪክ ቋንቋ ችሎታ ያለውን፣ ከማንኛውም ሰው ጋር መግባብ የሚችለውን፣ ደግሞም እግዚአብሔር ለአሕዛብ ሐዋርያ እንዲሆን የመረጠውን ቅዱስ ጳውሎስን ከጠርሴስ በማምጣት በአንጾኪያ ሥራቸውን ጀመሩ። በገላትያ መልእክቱ ምዕራፍ ፪ ላይ ራሱ እንደገለጠው ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ከአንጾኪያ ክርስቲያኖች የሰበሰበውን ርዳታ ይዞ ወጣ። በዚህም በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረውን መለያየት ክርስትና አንድ እንዳደረገው አስመሰክሯል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያው ጉዞ ያደረገው ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ከተመለሰ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ጥሪ በአሕዛብ ሀገር ወንጌልን ለመስበክ ከበርናባስ ጋር ወጡ። በዚህ ጉዞአቸው በጠቅላላ ወደ ፪፼ (ሁለት ሺህ) ኪሎ ሜትር የሚደርስ መንገድ በእግር ተጉዟል። ይህም ጉዞ የተከናወነው በ፵፮ ዓ.ም. አካባቢ ነው። የተሸፈኑትም ሀገሮች ሲሊንውቂያ፣ ቆጵሮስ፣ ስልማን፣ ጳፋ፣ ጰርጌን፣ ገላትያ፣ ጵስድያ፣ ኢቆንዮን፣ ሊቃኦንያ፣ ልስጥራ፣ደርቤን፣ጵንፍልያ፣አታልያና አንጾኪያ ናቸው።

ሁለተኛው ጉዞ የተከናወነው በ፶ ዓ.ም. ገደማ ነው። በመጀመሪያው ጉዞ ማርቆስ አብሮ ተጉዞ ነበር። ነገር ግን ጵንፍልያ ከተማ ሲደርስ እናቱ ስለናፈቀችው መመለስ በመፈለጉ በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም ይዞት መጣ። ስለዚህም በሁለተኛው ጉዞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲላስን ይዞ ወደ ኪልቂያ ሶርያ ሲጓዝ በርናባስ ደግሞ ማርቆስን አስከትሎ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። በዚህ ጉዞው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ግሪክ ደርሶአል። የተጓዘባቸውና ያስተማረባቸው ከተሞችም፦ ደርብያ፣ ልስጥራ፣ፍርግያ፣ ገላትያ፣ ሚስያ፣ጢሮአዳ፣ ሳሞትራቄ፣ ናፑሊ፣ ፊልጵስዩስ፣ ተሰሎንቄ፣  በርያ፣አቴና፣ ቆሮንቶስ፣ አንክራኦስ፣ አፌሶን፣ ቂሳርያ፣ ኢየሩሳሌምና አንጾኪያ ናቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን ያገኘው በዚሁ ጉዞው በልስጥራ ከተማ ነው።

ሦስተኛው ጉዞ የተከናወነው በ፶፬ ዓ.ም. ሲሆን የተሸፈኑትም ሀገሮች የሚከተሉት ነበሩ። ገላትያ፣ ፍርግያ፣ ኤፌሶን፣ መቄዶንያ፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆሮንቶስ፣ ጢሮአዳ፣ አሶን፣ ሚልጢኒን፣ አንጠቀከስዩ፣ ትሮጊሊዩም፣ መስጡ፣ ቆስ፣ ሩድ፣ ጳጥራ፣ ጢሮስ፣ ጵቶልማይስ፣ ቂሳርያ፣ ኢየሩሳሌም ናቸው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ክርስቲያኖች የሰበሰበውን ዕርዳታ ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በመያዝ ሦስተኛውን ጉዞ አጠናቅቆ ኢየሩሳሌም ገባ። ነገር ግን ኢየሩሳሌም የገባበት ጊዜ የፋሲካ በዓል ስለነበር ከልዩ ልዩ ሀገሮች የተሰበሰቡ አይሁድ በከተማዋ ነበሩ። እነዚህ በዝርወት የሚኖሩ አይሁድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን በየሀገራቸው በትምህርቱ የተነሣ ሲቃወሙት የነበሩ ናቸው።

እኒህ አይሁድ ቅዱስ ጳውሎስን በኢየሩሳሌም ሲያዩት ታላቅ ተቃውሞ አነሡበት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ተቃውሞ አነሡበት። ሐዋርያው  ቅዱስ ጳውሎስም  ተቃውሞአቸውን ለመግታት እንደ አይሁድ  ሕግ በቤተ መቅደስ የመንጻት ሥርዓት መፈጸም ጀመረ። ነገር ግን ከኤፌሶን የተከተለውን ጥሮፊሞስን ወደ መቅደስ ያስገባው ስለመሰላቸው ተቃውሞአቸው በረታ። ከተማውንም አወኩት፤ ይህ ቅዱስ ጳውሎስን በ፶፰ ዓ.ም. ለሮም እሥር የዳረገው። ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ ታስሮ ሮም ገባ። በዚያም በቁም እሥር ለሁለት ዓመታት ያህል ወንጌልን ሰበከ። የሁለቱን ዓመት የቁም እሥር እንደጨረሰ ወደ ኔሮን ፍርድ ቤት ቀረበ። ይህም በ፷ዎቹ ዓ.ም. ነው። በፍርድ ቤቱ በተደረገው ምርመራ የሮሜን ሕግ የሚቃወም  ምንም ወንጀል ስላልተገኘበት በነፃ ተለቀቀ፤ ከዚህ በኋላ  ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አራተኛውንና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያልመዘገበውን ጉዞውን ያደረገው። ይህ ጉዞው በመታሠሩ አዝነው ተክዘው የነበሩ ክርስቲያኖችን ለማጽናናት የጀመራቸውን ሥራዎች ፍጻሜ ለማየት የተደረገ ጉዞ ነው። በዚህም ጉዞው ኢየሩሳሌምን፣ ኤፌሶንን፣ ሎዶቅያን፣ መቄዶንያን፣ ቀርጤስን፣ ጢሮአዳን፣ ድልማጥያን፣ እልዋሪቆን፣ ኒቆጵልዮን፣ ብረንዲስን፣ ጎብኝቷል። በዚህ የመጨረሻ የስብከት ጉዞው ለአራት ዓመታት ያህል ቆይቷል።

በመጨረሻ በ፷፬ ዓ.ም. ኔሮን በጥጋቡ የሮማ ከተማ ስትቃጠል ምን እንደምትመስል ማየት እፈልጋለሁ ብሎ አቃጠላት። የሮም ሕዝብ በከተማው መቃጠል በማዘኑና በማመፁ ነገሩን ሁሉ በክርስቲያኖች ላይ አሳበበ። በዚህም የተነሣ ክርስቲያን የተባለ ሁሉ መሰደድ፣ መሠየፍ፣ መታረድ እጣ ፈንታው ሆነ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በኒቆጵልዮን ከተማ ሲያስተምር በ፷፭ ዓ.ም. ተይዞ ወደ ወኅኒ ገባ። ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር በጨለማ ቤት ታሥሮ ከቆየ በኋላ በ፸፬ ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን ተሰይፎ በ፷፯ ዓ.ም. ሐምሌ ፭ ቀን በሰማዕትነት ዐረፈ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ዐስራ አራት መልእክታትን ጽፈዋል። የቅዱሳኑ ሐዋርያት ረድኤትና በረከታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።

ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሐምሌ ፭፤ መጽሐፍ ቅዱስ-ሐዲስ ኪዳን፣ ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ ቁጥር ፩፤ በማኅበረ ቅዱሳን