በዓታ ለማርያም

ታኅሣሥ ፩ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ከተመረጡ የተመረጠች፣ ከተለዩ የተለየች፣ ከተከበሩ የተከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእናቷ ከቅድስት ሐናና ከአባቷ ቅዱስ ኢያቄም በእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ከተወለደችበት ዕለት ግንቦት ፩ ቀን ጀምሮ በወላጆቿ ቤት ለሦስት ዓመት ከኖረች በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ታኅሣሥ ፫ ቀን ‹‹በዓታ ለማርያም›› በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡

ኢያቄምና ሐና የተሳሉትን ስእለታቸው አስታውሰው ወስደው ለቤተ እግዚአብሔር ሲሰጧትም ካህኑ ዘካርያስ ስለምግቧ ተጨነቀ፤ ሕዝቡንም ሰብስቦ ሳለ መልአኩ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ይዞ ከሰማይ ወረደ፤ ዘካርያስ ለእርሱ የመጣ ሀብት መስሎት ታጥቆ እጅ ነሥቶ ቢቆም ወደ ላይ ራቀበት፡፡ ከስምዖን ጀምሮ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎችም በተራ ቢሞክሩ በተመሳሳይ መልኩ ወደ ላይ ራቀባቸው፡፡ ‹‹ምን አልባት ለእንግዶች የመጣ ሀብት እንደሆነ›› ብለው ሐና እና ኢያቄም እንዲቀርቡ አደረጓቸው፤ ነገር ግን ለእነርሱም ራቀባቸው፤ ዘካርያስም ሐናን ‹‹እግዚአብሔር የሚያደርገውን የሚያውቅ የለምና ልጅቷን ትተሸ ወደዚህ ነይ›› አላት፤ በዚያም ጊዜ ቅድስት ማርያም እናቷን ስትከተል መልአኩ ፋኑኤል ወደ እርሷ ቀርቦ አንድ ክንፉን አንጥፎ አንድ ክንፉን ጋርዶ መገባት፤ ከዚያም በክብር ዐረገ፤ ሊቀ ካህናቱና ሕዝቡም ‹‹የምግቧ ነገር ከተያዘልን በቤት እግዚአብሔር ትኑር›› ብለው ወደ ቤተ መቅደስ አስገቧት፡፡

ለ፲፪ ዓመታትም ቅድስት ድንግል ማርያም ሰማያዊ ኅብስትና መጠጥ እየተመገበች በቤተ መቅደስ ኖረች፡፡ በ፲፭ ዓመቷ ግን ለአቅመ ሔዋን በመድረሷ ከቤተ መቅደስ ትውጣልን በማለት አይሁድ በጠላትነት ተነሡባት፡፡ ካህኑ ዘካርያስም ይህን ሰምቶ እመቤታችንን እንዲህ ብሎ ጠየቃት፤ «ኦ ወለተ እስራኤል እፎ ትፈቅዲ ትንበሪ፤ ልጄ እንደምን ሆነሽ ልትኖሪ ትወጂያለሽ?» እርሷም «ከእግዚአብሐር በታች ያለኸኝ አባት አንተ ነህ፤ በዚያውም ላይ እናት አባቴ አደራ ያሉህ አንተን ነው፤ ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ» አለችው፡፡ ካህኑ ዘካርያስም በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ብሎ አዘዘው፤ «ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን በትራቸውን ሰብስበህ በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት ከቤተ መቅደስ አግብተህ ስትጸልይ እደር፤ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት አውጣው፤ ምልክትም አሳይህአለው፡፡» እርሱም እንዳለው አድርጎ በማግሥቱ በትሮቹን አውጥተው ቢያዩ የአረጋዊው ዮሴፍ በትር አብባና አፍርታ ተገኘች፡፡ ከበትሩ ጫፍ ላይ «ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ዕቀባ ለማርያም ፍኅርትከ፤ ዮሴፍ ሆይ፥ እጮኛህ ማርያምን ጠብቃት» የሚል ጽሑፍ አገኙ፤ ርግብም መጥታ በራሱ ላይ ዐረፈች፤ ስለሆነም ዮሴፍ እንዲጠብቃት ተወሰነ፡፡

ከዚህም በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቤተ መቅደስ ወጥታ እስከተሰደደችበት ወራት ድረስ ዮሴፍ ቤት ኖረች፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልመኗ ክብሯ በሁላችን ላይ ይደርብን፤ አሜን፡፡